“ሀሁ” ወይም “ፐፑ”… ታላቁ ደራሲ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን ከዛሬ ሰላሳ ዓመታት በፊት ከካታካምቡው አስፈሪ ዋሻ መሃል አምጦና ወልዶ ለመድረክ ያበቃው ከምርጥ የዘመናችን የመድረክ ተውኔት ሥራዎች መሃከል አንደኛው ነው። “ሀሁ” ወይም “ፐፑ” በሁለት የተለያዩ መንግሥታት ማብቂያና መጀመሪያ፤ በአመሻሽና ንጋት፤ በካታካንቡው ዋሻ በቆሙ ሁለት የፖለቲካ አንበሶች መሃከል ተቀምጦ የጻፈው ቲያትራዊ ተውኔት ነው። ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን ይህን ቲያትራዊ ተውኔት ለመድረክ በ1984ዓ.ም ቢሆንም የጻፈው ግን ቀደም ሲል የደርግ መንግሥት ማብቂያ ደወል ማቃጨል ከጀመረበት ከ1982 ዓ.ም መጨረሻዎቹ ጀምሮ ነበር።
ቲያትሩ “ከእሳት ወይ አበባ” እና “ከሀሁ በስድስት ወር” የቀጠለ ተውኔት ነው። ዛሬ ይህን ጉዳይ ማንሳታችን ጥበበኛውንም ሆነ ይህን ድንቅ ተውኔት በአድናቆት ለማስታወስ ብቻም አይደለም። ይልቁንም በጊዜው በብዙ ጭንቅ አሳር ለመጀመሪያ ጊዜ ከብሔራዊ ቲያትር መድረክ ላይ ወጥቶ ለማደግ ባደገደገበት በዚያው መድረክ ላይ በቆመጥ እንዳይድን እንዳይሽር አድርጎ የመቅጨት ሙከራ ተደርጎበታል። እናም ሸሽቶ ከተደበቀበት ከብዙ ዝምታዎች በኋላ ዛሬ ተመልሶ የብሔራዊ ቲያትርን ደጅ ሲጠና የገጠመው አንድ ጉዳይ አለ። አሁን ጸጋዬ ገብረ መድህን የለም፤ የያኔው አዘጋጅ የነበረው ዓለሙ ገብረአብም እንዲሁ አሁን ከ“ሀሁ ወይም ፐፑ” በስተጀርባ የለም፡፡ አሁን በአዘጋጅነት የቀረበው ሰው ተስፋዬ ሲማ ነው፡፡ ቲያትሩ እትብቱ ወደ ተቀበረበት የብሔራዊ ቲያትር ለመግባት በመሰናዳት ሳለ ሌላ የግምገማና የፍተሻ ኬላ ገጥሞታል፤ ለምን?
“ሀሁ” ወይም “ፐፑ” ሰው ቢሆን ኖሮ ከተወለደባት ጊዜ አንስቶ ያነባው እንባ ዛሬም ድረስ ከዓይኖቹ ላይ ባልደረቀ ነበር። በወጌሻ የማይታሸው የልቡ ስብራትም ሳይጠገን በዓመታት ተሸፍኖ ጠባሳው ሳይሽር ጠቋቁሮ ነጠብጣቦችን እንደያዘ ዛሬ ላይ ደርሷል። “ሀሁ” ወይም “ፐፑ” ቲያትር ብቻ አይደለም። በኢትዮጵያ የመድረክ ሥራዎችም ሆነ በሌላ እስከዛሬም ድረስ ወሰን የሰበረበት ሌላ ድንቅ ታሪክ አለ። ይሄውም በዚህ ቲያትር ዙሪያ የሚያትተው “ምስጢረኛው ባለ ቅኔ” የተሰኘው ከአራት መቶ በላይ ገጾች ያሉት መጽሐፍ ነው። በዚህን ያህል ደረጃ ሂሳዊ ዳሰሳ የተጻፈለት ተውኔት በሀገራችን አንድም የለም።
ታሪኩ በጊዜ ፈረስ አስቀምጦ የኋልዮሽ ያስጋልበናል። የሚያደርሰው እንጂ የማይዋጋው የጊዜ ፈረስ ከ1980ዎቹ ላይ አሳርፎ በፖለቲካ ጦር የተወጋውን ቁስለኛ ቲያትር ከነሰቆቃው ያስመለክተናል። ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን ሥራዎቹ እሳትም አበባም ነበሩ። “እሳት ወይ አበባ” እንዳለው እሳትን መሆን የመረጠ ይመስላል፡፡ በጊዜው በተለያዩ ሥርዓቶች ውስጥ በማን አለብኝ የፖለቲካ ዙፋን ላይ ተቀምጠው ሕዝቡን ቁልቁል ለሚመለከቱ አንዳንድ ባለሥልጣናትና ሹማምንት ሥራዎቹ ከእሳትም የእግር እሳት የነበሩ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ በእነርሱ ግፍ እየተብከነከነ አንጀቱ ለሚያረው ምስኪን ሕዝብ… አንጀት አርስ የተስፋ አበባዎች ነበሩ። ከእነዚህም አንዱ የስቃይ ገፈት ቀማሽ የሆነው “ሀሁ ወይም ፐፑ” የመድረክ ቲያትር ነው። በደርግ መንግሥት የስልጣን መባቻ ላይ የተጻፈው ይህ ቲያትር አብዮቱ በተገረሰሰ በዓመቱ በ1984ዓ.ም እራሱን አስተዋውቆ ወደ ጥበብ መንደር ተቀላቀለ።
በውስጡ የሚገኙት የገጸ ባህሪያቱ ውክልናና የታሪኩ ውልደት አብዛኛዎቹ ከአብዮታዊው የፖለቲካ ማህጸን ውስጥ የተገኙ ናቸው። ከወዲህ ማዶ የደርግ መንግሥት ቀኑ እየጨለመ ሰማይ በላዩ ላይ ለመደፋት ሲያዘቀዘቅ፤ ከወዲያ ማዶ ደግሞ የወያኔ የጦር ሠራዊት መላ ቅጡን ባጣውና ከየአቅጣጫው በተከፋፈተው የደርግ መንግሥት አጥር እየዘለለ ለሕዝቡ ሌላ የንጋት ማብሰሪያ ነጋሪቱን ለመጎሰም በመሰናዳት ላይ ሳለ፤ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን ግን በመሃል ከድልድዩ ስር ቁጭ ብሎ የሚሄደውንም እየመጣ ያለውንም ከመነጽሩ በታች አጮልቆ እየተመለከተ “ሀሁ ወይም ፐፑ”ን በመጻፍ ላይ ተጠምዶ ነበር። እግሬ አውጪኝ ሲል እየፈረጠጠ ያለውን ብቻ ሳይሆን ለመድረስ እግሩ አጥሮ እየገሰገሰ በመምጣት ላይ ያለውንም ደህና አድርጎ ተመልክቶት ነበርና ቲያትሩም በሁለት ሥርዓቶች መሃከል በተፈጠረው ትልቅ ገደል አንድ እግሩ ከወዲያ ማዶ ሌላኛውም ከወዲህ ማዶ እረግጦ በጽናት ቆመ። ቆሞም እንዲህ ሲል አሰበ፤ ‘ሀሁ ብሎ በመጀመር ወይንስ ፐፑ ብሎ በመጠናቀቅ ላይ ይሆን?’ ወሳኙ ጥያቄ ይሄው ነበር። አብዮቱ ተፈረካክሶ በአዲሱ መንግሥት ጅማሮ ውስጥ የታሪክ ፍርስራሽ መሆን ከጀመረ በኋላ የጥያቄውን ምላሽ ለማግኘት እምብዛም ጊዜ አልፈጀም ነበር።
የ”ሀሁ ወይም ፐፑ” የታሪክ ሰንሰለት ጅማሮውን የሚያደርገው እዚህ ጋር ነው። በ1984ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ ወራት አካባቢ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን የቲያትሩን ምናባዊ ቁመና በማጠናቀቅ የቲያትሩ አዘጋጅ ከሆነው ዓለሙ ገብረአብ ጋር በመሆን ለመድረክ ለማብቃት ተሰናዱ። የዚህን ጊዜ ወደ ብሔራዊ ቲያትር ጎራ ማለቱ ግድ ነበር። ቲያትሩ በብሔራዊ ቲያትር መድረክ ላይ እንዲታይ ፈቃድ ካገኘ በኋላ የቲያትር ቤቱ አስተዳደር ሃሳቡን እንደገና ለውጦ፤ ዳግም በኮሚቴ ካልተገመገመ ሲል ያለፈውን ውድቅ አደረገው። በኮሚቴ መገምገም አለበት የሚሉት ሌላ የማይወጣበትን የሳንሱር ቀንበር ለመጫን መሆኑ ነው…ጸጋዬ ግን ሃሳባቸው ምን እንደሆነ አስቀድሞ ገብቶታልና እነርሱን አልፎ በቀጥታ ወደ ባህል ሚኒስቴር በማምራትና ከባለሥልጣናቱ ጋር በመነጋገር ቲያትሩ እንዲታይ ፈቃድ አገኘ።
ነሐሴ 24 ቀን 1984ዓ.ም መሰናክሉን ሁሉ አልፎ ለመጀመሪያ ጊዜ ቲያትሩ ለመድረክ በቃ። በፖለቲካ ብሶት ልቡ የሳሳው የጥበብ ባለሙያና ተመልካቹ ሁሉ ይህን ቲያትር እየተመለከተ በእንባ መራጨት ጀመረ። ብሶት የወለደው እንባ… በሳምንት ለሦስት ቀናት የሚታይ ሲሆን ብሔራዊ ቲያትር ከአፍ እስከ ገደፍ በተመልካች ጎርፍ እየተጥለቀለቀ የማየት እድሉን አጥቶ የሚመለሰውም ብዙ ነበር። በውስጡ የሰላም ናፍቆትና ረሃብ የተሰነቀረበት ምስኪን ሕዝብ ቲያትሩን ሲመለከት ከውስጡ እየገነፈለ እንባ ከዓይኑ መፍሰስ ሆነ። የቲያትሩን እምቅ ሃሳብና የተመልካቹን ሕዝባዊ ስሜት ያጤኑት አዳዲሶቹ ሹማምንት ድባቡ ፈጽሞ ምቾትን አልሰጣቸውም ነበር።
ገና ወደ መድረክ ከመውጣቱ ጀምሮ ዓይናቸውን ጥለውበታል። ጸጋዬ ገብረ መድህን በአንድ ወቅት እንደገለጸው ከሆነ ይህን ቲያትር እንዲያቆም፤ በየጊዜው በስልክ የሚደርሱበት ዛቻና ማስፈራሪያዎችም ጭምር ነበሩበት። “ሀሁ ወይም ፐፑ” ቲያትርን በመድረክ ላይ ለማሳየት ሲወስን፤ አላማው የሀገሪቱን መንሸራተትና የሕዝቡን ጭቆና ማሳየት ብቻ አልነበረም፤ አዲስ የዴሞክራሲና የነጻነት ብርሃን በርቷል የሚለውንም ለማሳየት ጭምር ነበር። ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ አቅጣጫውን ስቶ፤ አዲሱ መንግሥትም እርሱ እንደተመኘው የብርሃን ሳይሆን ሌላ የተጋረደ የጨለማ ሰማይ ከላዩ ላይ ዘረጋበት።
ስለ ቲያትሩ ካወጋን አይቀር ከውስጡ ጥቂት ሃሳቦችን ቦጨቅ ማድረጉ መልካም ነው። የቲያትሩ ጭብጥ በግርድፉ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ ሀገራዊ አንድነትን፣ መተጋገዝን፣ የኢትዮጵያን ከፍታና ሰው የመሆንን ክብር ተደግፎ የሚያዘግም ሲሆን በሌላኛው ጎኑ ደግም የኢትዮጵያን ከከፍታው የመንሸራተትና የፖለቲካውን እድፍ በመንቀስ የከረፋውን እጣቢ ለመድፋት ሲፍጨረጨር እንመለከትበታለን። በዋናነት በሁለት ገጸ ባህሪያት ላይ ትኩረቱን አድርጓል። ለእውነት ሽንጡን ገትሮ በቆመው ታጋይ ነጋና በከተማው ጩልሌ በቢ አራጋው መሃከል፡፡ ብልጣ ብልጡ ከተሜ፤ ጸጉር ከምላሱ የሚነቅል፤ እንደ ምጣድ ላይ ቂጣ በሁለቱም በኩል እየተገለባበጠ በአንደበቱ ቅቤ የሚያነግት ስውር ስለት ነው። ቢሰማ ምንም አያመጣም ብሎ ባሰበው ሰው ፊት እንዳሻው ያሻውን ሁሉ ያወራል። እንዲያውም በደርግ ጊዜ አግበስብሶ የያዛቸው በርካታ ቤቶች በከተማው ውስጥ እንዳሉት በመናገር፤ “አሁንም ቢሆን ገና መላዋን አዲስ አበባ ከተማ አከራይቼ ስንትና ስንት ገንዘብ እሰበስባለሁ” ሲል ሌብነቱን እንደ ጀብዱ ሲያወራም እናደምጠዋለን። ማሸርገድና አፈ ቀላጤነቱ የተካነበትና ጥርሱን የነቀለበት በመሆኑ በታጋይ ነጋ ፊት ሲሆን የለውጡ ደጋፊና ተቆርቋሪ በመምሰል ዓይኑን በጨው አጥቦ ምላሱን ቅቤ ይቀባል። እውነታው ግን ለውጡን የማይደግፍና ፀረ-ኢህዴጋዊ አብዮተኛ መሆኑ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ዳንኬረኛ ሌንሳ፤ ዳንኬረኛ ግደይና ዳንኬረኛ እሙ ይህ እባብ እንዳይተናኮላቸው ይሠጋሉ። “ያን የቀበሌ ሊቀመንበር ታጋይ ነጋ ይሄን ያህል ቤት ከነዋሪዎች ላይ ቀምተህ እንድታስረክበኝ ብሎሃል በለው፡፡ ይህን ትዕዛዝ በፍጥነት ሳይፈጽም ቢቀር ምን ዓይነት ርምጃ ለመውሰድ እንደምንገደድም በደንብ አስረዳው እሺ!?” በማለት ለጀሌዎቹ ትዕዛዙን ሲያስተላልፍ እናደምጠዋለን። ታጋይ ነጋን ጨምሮ ሁሉም እርሱን ለመለወጥና እውነተኛ ማንነት እንዲኖረው ለማድረግ ሲጥሩ የሚያሳዩ ትዕይንቶችንም እንመለከታለን።
“ሀሁ ወይም ፐፑ” ከብሔራዊ ቲያትር ለአንድ ዓመት ያህል ዘለቀ፡፡ ከአንድ ዓመት የመድረክ ቆይታ በኋላ ግን በ1985ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በየትኛውም የቲያትር ቤት ውስጥ እንዳይታይ ታገደ። በዚህ ተስፋ ያልቆረጡት የቲያትር ቡድኑ አባላት ፊታቸውን ወደ ክልል ከተሞች አዞሩ። 1985 በተከለከለበት በዚያው ዓመት ቲያትሩን ለማሳየት ወደ ዲላ ከተማ አቀኑ። ዝግጅታቸውን አጠናቀው የመድረክ ቲያትሩ በመታየት ላይ ነበር። እንደተለመደው ተመልካቹም በስሜት ባህር ላይ ሰጥሟል። ከብዙ ትዕይንቶች በኋላ ከቲያትሩ አጋማሽ ላይ ግን አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ። ማንነታቸው በውል የማይታወቅ ጥቂት የማይባሉ አካላት ከተመልካቹ መሃል ብድግ በማለት ዱላና ቡጢያቸውን እየጨበጡ በፍጥነት ወደመድረኩ አመሩ። ያገኙትን እቃ በሙሉ እየሰባበሩ በቲያትር አባላቱ ላይ የዱላ መአት ማዝነብ ጀመሩ። በቲያትሩ ውስጥ ያልተጻፈና አዘጋጁም የማያውቀው ሌላ አስፈሪ ትዕይንት ታየ። ከመድረኩ የተዘረረው ብዙ ነው። ሁካታና ትርምስ በተሞላበት አዳራሽ ውስጥ ተመልካቹም ነብሱን ለማስመለጥ እግሬ አውጪኝ ሲል መተራመስ ሆነ። የተጎዱት አባላት ወደ ዲላ ሆስፒታል ተወስደው ታክመው መዳን ቻሉ።
በዚህ አልተገቱም ካገገሙ በኋላ እንደገና በሀዋሳ ከተማ ቲያትሩን ለማሳየት ዝግጅታቸውን ቀጠሉ። በሀዋሳው መድረክም በተመሳሳይ ሁኔታ የቲያትሩ ትዕይንት መታየት ጀመረ። ለሰላሳ ደቂቃዎች ያህል ከታየ በኋላ ድንገት ማዕበሉ ተቀሰቀሰ። ልክ ዲላ ላይ እንደነበረው በተመሳሳይ ገቢራዊ ትዕይንት፤ ወንበዴዎቹ ከተመልካቹ መሃል ብቅ ብቅ እያሉ የፊልም ትዕይንት አስመሰሉት። በዚህኛው ዙር፤ ዱላው ለቲያትር አባላቱ ብቻ ሳይሆን ለተመልካቹም ጭምር ሆነ። የወደቀው ወደቀ፤ያመለጠውም አምልጦ ብዙዎቹ ተጎዱ። መልእክቱም “ሀሁ ወይም ፐፑ”ን ያየህ ተቀጣ ነበር።
“ሀሁ ወይም ፐፑ” በኛ ዘመን…በኛ ጊዜ ከሰሞኑ ምን ገጠመው? ዳግም ወደ ብሔራዊ ቲያትር ብቅ ብሎ ነበር። ቲያትሩ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው በመሆኑ ከቲያትር ባለሙያ ይልቅ በሌላ አካል መገምገም አለበት የሚል ነገር ተነስቶበታል። በርግጥ በ2016 ሆነን 1984’ን መድገም ነበረብን ወይ? ጥያቄው ጥያቄ ብቻ ነው። ዛሬያችንን መሸሽ ትላትናችንንም መደበቅ አንችልም። ይህ ቲያትር ካለፈው ትላንት ተምረን ያለንበትን ዛሬን እንድናሳምር ያደርገን ይሆናል እንጂ ስጋትስ አይሆንብንም ነበር። ጉዳዩ እንደተባለው ከሆነ፤ በአሁኑ ሰዓት የምንመለከታትን የኪነ ጥበብ ሥራ የነጻነት ብልጭታ ጭራሹን ድርግም ብላ እንድትጠፋ ማድረግ ይሆናል። አልፈው የሚመጡ ነገሮች እስከሌሉ ድረስ ሙያውን ለባለሙያው መተው አስፈላጊ ነው። “ሀሁ ወይንም ፐፑ” ዛሬም ከመድረክ ላይ ሊያዩት የሚናፍቁ በርካቶች ናቸው። የጥበብ አምባሳደር የሆነው የብሔራዊ ቲያትርም በታሪካዊው ተውኔት ታሪካዊ ዐሻራውን ባማረ መልኩ ማሳረፍ አለበት።
“እኛ የዓለም እዳ ነን። ኒውዮርክና ፓሪስ የተገነቡት እኮ በኛ በአፍሪካውያን አጥንትና ደም ነው…ዘለዓለማችንን ከችግር የማንወጣ አሳዛኝ ተመጽዋች ሆነናል። …እና ዝም ብለን፤ ቁጭ ብለን በረሃብ እንለቅ?…ሳንሰራ ቁጭ ብለን ብቻ?… ሰለጠን ስንል ሰየጠን…ተከባብረን ተቻችለን እናልፈዋለን ወይንስ ሰይጥነን እርስ በርሳችን እንተላለቃለን? ሰዎች ሕልማችሁ ምንድነው?” ይለናል፤ ጸጋዬ በቲያትሩ ውስጥ። ሀሁ ተስፋ ነው። ሀሁ አዲስ ንጋት ነው። ሀሁ የዴሞክራሲ መጀመሪያ ነው። በተቃራኒው ደግሞ ፐፑ ከትላንት በባሰ መሸራተት፤ ከድጡ ወደ ማጡ ቁልቁል የሚያሽቆለቁለን አስፈሪ የካታካንቡ ዋሻ ነው። ሀሁ ወይንስ ፐፑ?
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም