የጋራ ትርክት ለጋራ ሀገር !

ሀገራት እንደየመልክዓ ምድራዊ አቀማመጣቸው፣ እንደተፈጥሯዊ ፀጋቸው፣ እንደትላንት ታሪካቸውና እንደ ኅብረ ብሔራዊነታቸው የየራሳቸው ብሔራዊ ትርክት አላቸው፡፡ የሁሉም ሀገር ምሥረታ ጥንስስ ከትርክት ይጀምራል፡፡ ሀገር በትርክት ይገነባል። በሀገር ታሪክ ውስጥ የነበሩ የተለያዩ የታሪክ ነገረ መንገዶች/ትርክቶች ከአሉታዊዎቹ ይልቅ አዎንታዊዎቹን፣ ከሚያጋጩት ይልቅ የሚያቀራርቡትን መምረጥ ለሀገር መንግሥት ግንባታ ሂደቱ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡

ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ ዓመታት የሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ ካላቸው ሀገራት መካከል ትጠቀሳለች፡፡ በእነዚህ ዘመናት ውስጥም ሕዝቦችዋ አንድ የሚያደርጉ በርካታ ታሪኮች አልፈዋል፡፡ ከዚህ የተነሳም ከሚለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን በርካታ ታሪኮች አሉን፡፡ ይሁንና የግል ጥቅመኞች አንድ የሚያደርጉንን ታሪኮች ከማጉላት ይልቅ ነጠላ ታሪኮችን በመምዘዝ፣ አሉታዊውን ብቻ በማጉላትና የበዳይና ተበዳይ ትርክቶችን በመፍጠር በሕዝቦች መካከል ልዩነቶች እንዲሰፋ፣ አለመተማመንን እንዲነግስ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ አሁንም እየሠሩ ነው።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በብልፅግና አመራሮች ሥልጠና ላይ ጠለቅ ያለ ትንተና አቅርበዋል። እንደ እሳቸው ከሆነ፣ አወንታዊ መስተጋብር ቤተሰብን፣ ሰፈርን፣ ሀገርን፣ አህጉርን ወደ ብልፅግና ይወስዳል፡፡ በተቃራኒው አሉታዊ መስተጋብሮች ዜጎች ሁሉንም ነገር በጥርጣሬ እንዲመለከቱ፣ ግራ እንዲጋቡ፣ ያደርጋል። ይህም እየሰፋ ሲሄድ ጭቅጭቅ፣ አለመግባባት፣ አለመደማመጥ፣ ተፈጥሮ ግጭትና ቀውስ ይፈጠራል፡፡

ለዚህ ዋንኛ ምክንያት ሁሉ ነገር የትርክት ውጤት በመሆኑ ነው፡፡ ትርክት የሁሉ ነገር መነሾ ነው፡፡ ውድም፣ ርካሽም፤ የሚወደድም፣ የሚጠላም በትርክት ነው፡ ፡ ትርክት ወደ ቀናው ወይም ወደ አልቀናው መስተጋብር/መከፋፈፍ እንደሚወስደን ትኩረት ሰጥተው ተናግረዋል። በእርግጥ ሁሉ ነገር የትርክት ውጤት ነው። ጠንካራ የጋራ ሀገራዊ ትርክቶችን መፍጠር የቻሉ ሀገራት በብዙ ተጠቃሚ ሲሆኑ ሀገራቸውን በዓለም አደባባይ ታላቅ ሲያደርጉ ተመልክተናል። በተቃራኒው የሚለያይ/ከፋፋይ ትርክቶች የበዛባቸው ሀገራት ብሔራዊ አንድነታቸው ሳይቀር አደጋ ውስጥ ወድቆ ለማየት ችለናል።

እኛ ኢትዮጵያውያንም ፖለቲከኞች በወለዷቸው መገፋፋት የበዳይና ተበዳይ ንዑስ ትርክት በፈጠረው ቂም ቋጠሮ በብዙ ለመከፋፋል ተገደናል፡፡ በቀደመው ዘመን በነበራት አንድነት በጀግንነት ያስቀለመችው፣ በሥልጣኔ ያሸበረቀ ታሪኳ በግጭቶችና በረሃብ ታሪኮች እንዲጠለሽም ሆኗል። በተለያዩ ወቅቶች ሥልጣን ላይ በነበሩና ለሥልጣን በታገሉ አካላት መካከል በነበረ እሰጣገባ ምክንያት ሀገሪቱ በተለያየ የተቃርኖ ጎራ በተመደቡ የተለያዩ ኃይሎች ስር ውላለች።

እነዚህ ኃይሎች በራሳቸው የታሪክ አረዳድ፣ የየራሳቸውን ንዑስ ትርክትም ፈጥረዋል። ይህም የጨቋኝ ተጨቋኝ ንዑስ ትርክትን ከመፍጠር ባለፈ የጋራ ታሪክ የለንም እስከሚል የተዛባ አረዳድ ድረስ ተጉዟል።

ይህም በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥትና ብሔረ መንግሥት መካከል የተሻለ ትርክት እንዳይፈጠር አድርጓል፡፡ ከዚህም ባለፈ ጠንካራ የጋራ ኢኮኖሚ መገንባት እንዳይቻል ተግዳሮት ሆኗል፣ በሀገሪቱ ያሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባሕል የኢትዮጵያዊነት መገለጫ መሆናቸውን አውቆ በባሕልና እሴት የሚያስተሳስር ጠንካራ ተቋም መገንባት ሳይቻል ቀርቷል፡፡

ታሪክን በታሪክነቱ ከመረዳት ይልቅ ታሪክን የግጭት መንስኤ ቂም መወጣጫ አድርገን የምንወስድ አዝማሚያም ሌላው የጋራ ትርክት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እየተፈታተነው የሚገኝ ሀገራዊ ችግር ነው፡፡ ታሪክ መማሪያ ነው። ከእኛ በፊት የሆነው ታሪክ ለዚህ ትውልድ ዛሬዎች ሆነ ነገዎች የተሻሻሉ መሆን የመማሪያ ምጣድ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ የላቸውም።

በርግጥ ወቅቱ የራሳቸውን ጥቅም ታሳቢ ያደረጉ የሐሰት እና የፈጠራ ትርክቶች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ግለሰቦች የበዙበት ነው። ይህ ደግሞ እንደ ሀገር የጋራ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትርክቶችን ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት ፈተና መሆናቸው የማይቀር ነው፡፡ በተለይም የሐሰት ትርክቶች እያሳደሩት ያለው ጫና እየከበደ መምጣቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው ጽንፍ የረገጠ ብሔርተኝነት ለችግሩ መስፋፋት ላቅ ያለውን ሚና ተጫውቷል። ሀገር ከመገንባት ይልቅ የማፍረስ አቅም ሆኗል። ይህም በሀገሪቱ ዘመናት ያስቆጠረውን አብሮ የመኖር ጠንካራ ባሕል እየሸረሸረው ይገኛል ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንዳሉትም፣ ትርክት ወደቀናው ወይም ወዳልቀናው ሊወስደን ይችላል፡፡ አሁን ላይ እያደገ የመጣው ብሔረሰባዊ ብሔርተኝነት፤ ‹‹የኔ ብቻ ጥሩ›› ትርክት ሀገር ከማፍረስ ውጭ አያሸንፍም። የታሪክ መዛግብት እንደሚያመለክቱት የትም ሀገር አሸንፎ አያውቅም፣ በእኛም ሀገር አያሸንፍም። ንዑሳን ትርክቶች ውጤታቸው ግጭት ነው። የጥፋት ስምሪታቸውም ጥላቻ ዘርቶ ዜጎች በጥርጣሬ እየተያዩ አብሮ የመኖር ባሕላቸው እንዲጠፋ ማድረግ ነው። በንዑሳን ትርክቶች የሚፈጠሩ መስተጋብሮች ጥላቻን እንጂ ፍቅርን አይሰብኩም። መከፋፈልን እንጂ አንድነትን አያሰርፁም፡፡

ይህም በዜጎች መካከል ጥላቻን ጠንስሶ በበላይና በበታች መርዝ ትርክት ጠምቆ ሀገርን በግጭት አቅል ያስታል፡፡ ቂምና በቀል ውስጥ ሆነን የምንቀሳቀስ ከሆነ አዙሪቱ ይቀጥላል፣ መደማማቱ ይብሳል፤ መበቃቀሉ ይጠነክራል። ስለዚህ ይህ የሆነ ቦታና ቀን መቆም እንዲችል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቆም ብሎ ማሰብ ያለበት አሁን ነው። ባለፉት ዓመታት አንዳንድ ፖለቲከኞች ለራሳቸው እንዲመች ታሪክ መፃፍ አሊያም ለተከታዮቻቸው የተዛነፉ እና ከእውነት የራቁ ሀሳቦችን ሲሰብኩና ሲያስተምሩ ነበር፡፡ ይህም የሀገሪቱን ዜጎች አብሮ የመኖር እሴት እየሸረሸረ አልፎም ለግጭት ሲዳርግ ቆይቷል፡፡

ተለዋዋጭ የሆነው የሀገሪቱ የኔ የበላይ ያንተ የበታች የሚል የተሳሳተ እይታን ቀርጾ ለዓመታት ተጉዟል‹፡፡ በዚህም ሀገራዊ የፖለቲካ ባሕሉም የጋራ የሚባል ማንነትና ወደ አንድ የሚያስጠጋ ኅብራዊነትን መፍጠር ሳይችል ቀርቷል፡፡ አለፍም ሲል የፖለቲካ አቋም ልዩነት ለግጭት መንስዔ መሆን ቋሚ መገለጫችን ሆኗል፡፡ በአንድ ወቅት አሜን ተፈሪ የተባለ ሰው በዚህ ጉዳይ ላይ እንደፃፈው፣ የሐሳብ ልዩነቶች በርዕዮተ ዓለም ጎራ ከጫፍ እና ከጫፍ ሆነን ለመጓተት እና ለመዘላለፍ ሲዳርገን አይተናል። የፖለቲካ አቋም ልዩነት ደም ሲያፋስስ ተመልክተናል፡፡ የሐሳብ ልዩነት፤ የልዩነት ጎራ ፈጥሮ፤ የርዕዮተ ዓለም ባንዲራ አስይዞ፤ ይህ ‹‹ወገን›› ያኛው ‹‹ጠላት›› ነው በሚል አስፈርጆ፤ በባላንጣነት ሲያሰላልፈን ቆይቷል፡፡

ይሁንና የሐሳብ ልዩነት፤ የግድ-ሁልጊዜ የግጭት መንስዔ አይሆንም፡፡ የሐሳብ ልዩነት፤ በአንድ መድረክ ተቀምጦ ከመወያየት አያግድም። ሰዎች የተለየ ሐሳብን ይጠሉ ይሆናል እንጂ ሐሳቦች ሰዎችን አይጠሉም። እንዲያውም ሐሳቦች ጥራት እና ብቃት የሚያገኙት፤ የሕግ እና የቋሚ እውነት ማዕረግ የሚቀዳጁት በተቃራኒ ድጋፍ ሐሳብ ነው፡፡

ወጥ የሆነ የፖለቲካ ባሕል ባለመኖሩ ደግሞ ዴሞክራሲን ለመገንባት በሚደረገው ጉዞ ላይ ብዙ እንቅፋት ፈጥሯል፡፡ የአንድ ሀገርና ለአንድ ሀገር የሚተጉ ዜጎችን አንደኛው የሥልጣን ባለቤት ሌላኛው የችግር ባለቤት ሆነው የጎሪጥ እንዲተያዩ አድርጓል፡፡ ይህም በመሆኑ የጋራ የሆነ ፖለቲካ፣ የጋራ የሆነ ማንነት መፍጠር አልቻልንም፡፡ በዚህ ምክንያት ጠንካራ ኢትዮጵያዊ የሆነ የጋራ ማንነት መገንባት አልተቻለም፡፡ የፖለቲካ ባሕላችን የጋራ ማንነታችን ጋር መያያዝ መቻል አለበት፡፡ የኔ ነው የምንለው የኢትዮጵያዊነት ማንነት መኖር መቻል አለበት፡፡ ይህ ሲሆን የተሻለ ትርክት መፍጠር ይቻላል፡፡

የነገዋን ኢትዮጵያን ለመገንባት ያለፉ ታሪካዊ ገጠመኞቻችንን ልንጠቀምባቸው እንደሚገባ ሁላችንንም ያስማማናል፡፡ አሁንም ከመነሻው የት እንደምንደርስ አውቀን መንገድ መጀመር ያስፈልጋል፡፡ ሀገራችንን ወዴት እንደምንወስድ አውቀን በጋራ ተወያይተን በጋራ መወሰን አለብን። ቢያንስ አብዛኛው የሀገሬው ዜጋ የሚያምንበትን መንገድ መከተል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን የሚወስዱት ወዴት ነው? ትውልዳቸውን መቅረፅ የሚፈልጉት እንዴት ነው? የሚሉትንና መሰል ጥያቄዎች ተለይተው ምላሻቸው መታወቅ አለበት፡፡ ይህ ከታወቀ ያሳለፍናቸውን ታሪካዊ ገጠመኞቻችንን ግብዓት በማድረግ ጠንካራ ብሔራዊ ትርክት ማበጀት እንችላለን፡፡ ብሔራዊ ትርክት መገንባት ሀገረ መንግሥቱን በማፅናት ሰላሟ የተጠበቀ ሀገርን መፍጠር ነው፡፡ ለዚህም በልዩነት ዋልታ ረገጥ ሆኖ ከመቆም ይልቅ ብሔራዊ ማንነትን መቅረፅ ላይ መሥራት ለዘላቂ ኅብረ ብሔራዊነት መጠናከር ሚናው የጎላ ነው፡፡

ታላላቅ ሀገራዊ ትርክት በአብሮነት ጥላ ስር የተሰየመ፣ በአንድነት ሰንሰለት የተገመደ ከዘመን ዘመን የሚሻገር አንድነትን የመፍጠር ጥበብ ነው። በትውልድ መካከል በጊዜ መለዋወጥ ጥሩም መጥፎም ይፃፋል፡፡ ከትላንት መጥፎ ታሪክ ተምሮ ዛሬን ገንብቶ ያለህፀፅ ለትውልድ ለማስተላለፍ ታዲያ ታላላቅ ሀገራዊ ትርክት ያስፈልጋል። ታላላቅ ሀገራዊ ትርክቶች የጥንስሳቸው መነሻ የሚሆነው የጋራ ታሪክ ነው።

የጋራ ታሪክ ለመፍጠር የራሳችንን ብቻ ሳይሆን የሌሎችን መመልከት፣ ከቁምነገር መቁጠር፣ እንደራስ ማሰብና ቁጭ ብሎም በረጋ መንፈስ መወያየት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሳይሆን ከቀረ ለቀጣዩም ትውልድ የበለጡ የመጨቃጨቂያና የመነታረኪያ ብሎም የመጋጫ መንስኤዎችን አስቀምጠን እንዳለፍን ይቆጠራል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ሲመጡና ሲሄዱ የነበሩ መንግሥታት የሄዱበት የየራሳቸው መንገድ ጠንካራ ሀገራዊ የጋራ ትርክት መፍጠር አላስቻለም። ይህም ሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋቷን እንድታጣ አድርጓታል። እንደ ሀገር ከዚህ ችግር ለመውጣት ፣ ሀገርን በጠንካራ የጋራ ሀገራዊ ትርክት ማነጥ ነው።

ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ ጎዳና እንድታመራ ሁሉም ልዩነቱን ወደጎን በመተው በጋራ እሴቶች ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ ዋልታ በረገጠ ሀሳብ የሚፈጠሩ ንዑሳን ትርክቶች የተመሰቃቀለ የፖለቲካ ገፅታና ደህንነቱ ያልተጠበቀ ሀገርን ያወርሳሉ፡፡ በታላላቅ ሀገራዊ ትርክት የሚፈጠሩ መስተጋብሮች ግን ሀገርን ወደ እድገት ጎዳና ይወስዳሉ፡፡

ኢትዮጵያውያን አያሌ ዘመናትን የተሻገረ የጋራ ታሪክና የጋራ ዕሴት ቢኖረንም የጋራ ጉዳዮቻችንን በጥቂት ፖለቲከኞች አጀንዳ ተቀይሮ ቆይቷል። ዛሬ ላይ ለአዲሱ ትውልድ የጋራ ትርክትን ማውረስ ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው፡፡ የጋራ ትርክትን በመፍጠር ሂደት ትምህርት ላይ ትኩረት በማድረግ ትውልድ ላይ መሠራት አለበት፡፡ እነዚህ የጋራ ትርክቶቻችን በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካተው ትውልዱ እንዲማራቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ደግሞ ፖለቲከኞች፣ ምሑ ራን፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You