ለተከታታይ ሦስት ዓመታት በሽታው ከሰው ወደ ሰው እንዳልተላለፍ በሚያረጋግጠው ከወባ ነፃ የእውቅና (የምስክር) ወረቀት፤ በአውሮፓውያኑ በ1973 የምስክር ወረቀት ካገኘችው ሞሪሽየስ በመቀጠል አልጄሪያ ከወባ ነፃ የተባለች ሁለተኛዋ አፍሪካዊ ሃገር፤ እንዲሁም አርጀንቲና ደግሞ ከፓራጓይ በመቀጠል ከ45 ዓመት በኋላ ከወባ ነፃ የሆነች የደቡብ አሜሪካ ሃገር መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አረጋገጠ፡፡ በአልጄሪያና አርጀንቲና የወባ በሽታ ለብዙ መቶ ዓመታት ዜጎችን ሲገድል የነበረ በሽታ ሲሆን፤ ሙሉ በሙሉ በሽታውን ለማጥፋት ሃገራቱ መራር የሚባል ትግል ማድረጋቸው ታውቋል:: በድንበር አካባቢዎችም የሰዎች እንቅስ ቃሴና በሽታውን ለመቆጣጠር በተደረገ ከፍተኛ ጥረት እንዲሁም በየጤና ኬላዎች በሚደረግ ነፃ የወባ ምርመራና ህክምና አማካይነት ግባቸውን ሊያሳኩ እንደቻሉ የዓለም ጤና ድርጅት አክሎ ገልጿል፡፡
አልጄሪያ ከወባ ነጻ ሆኛለሁ ብላ በአውሮፓውያኑ 2013 ለዓለም ጤና ድርጅት አስታውቀ የነበረ ሲሆን በያዝነው ዓመት እውቅናውን አግኝታለች፡፡ ሁለቱም ሃገራት ወባን ለማጥፋት ባሳዩት ቆራጥነትና የመከላከል ብቃት የምስክር ወረቀቱ እንደሚገባቸው የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄነራል ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ማስታወቃቸውን፤ የአገራቱ ስኬት ወባን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማጥፋት በርትተው እየሠሩ ላሉ ብዙ አገራት ትልቅ ትምህርት መሆኑንም ቢቢሲ በድረ ገጹ አስፍሯል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር በ2018 ባወጣው መረጃ በዓመት ከ200 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ ይያዛሉ:: መረጃው እንደሚያመለክተው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2016 በወባ ከተያዙ ሰዎች መሀከል ግማሽ ሚሊዮኑ ህይወታቸው አልፏል፡፡ ከሟቾቹ አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት ደግሞ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው፡፡
ካምብሪጅ ውስጥ የሚገኘው ዌልካም ሳንገር ኢንስቲትዩት በዚሁ ወቅት ይፋ ያደረገው ጥናት የወባ ትንኝ የሰው ልጆችን ህይወት የሚቀጥፍ ነፍሳት ለመሆን ያለፈበትን የዕድገት ደረጃዎችን ያሳያል፡፡ የወባ ትንኝ ሁሌም አደገኛ ነፍሳት እንዳለነበርና የአደገኛነት መጠን አሁን ካለበት ደረጃ የደረሰው በአዝጋሚ ሂደት መሆኑን ያትታል፡፡ ጥናቱ የተሠራው ሰባት የወባ ትንኝ ዝርያዎችን በናሙናነት በመውሰድ ሲሆን ከ50 ሺህ ዓመታት በፊት ትንኙ አንድ ዓይነት ዝርያ ብቻ እንደነበረው ተመራማሪዎቹ ደርሰውበታል፡፡
በጥናቱ መሰረት የትንኝ ዝርያው ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰዎችን ወደሚያጠቃ አደገኛ ነፍሳትነት ተሸጋግሯል፡፡ በቢሲ በድኅረ ገጹ እንዳሰፈረው፤ ከተመራማሪዎቹ አንዱ ዶክተር ማት በርማን ‹‹ጥገኛ ህዋሳት ሰውነት ውስጥ ከገቡ በኋላ የሚቆዩበትን እንዲሁም እየተከፈሉ በመባዛት ሰውነት ውስጥ በወባ ትንኝ የሚሰራጩበትን ሂደት›› በሚዳስሰው ጥናት ትንኞች ከጊዜ በኋላ ያሳዩት የዘረ መል ለውጥ የሰዎችን ቀይ የደም ህዋስ ማጥቃት የሚችሉበት ደረጃ ላይ አድርሷቸዋል ይላሉ፡፡
ከጥገኛ ህዋሳቱ መሀከል ‹‹ፕላስሞድየም ፋልሲፓረም›› የተባለው ከፍተኛ የጤና እክልን ያስከትላል፡፡ ለህልፈት የምትዳርገው ሴት የወባ ትንኝ ሰዎችን ስትነድፍ የቺምፓንዚና ጎሬላ ዝርያዎችን የሚያጠቁ ነፍሳትም መኖራቸውን ነው አጥኚው የሚገልጹት፡፡ አጥኚዎቹ ጋቦን ወደሚገኝ የጦጣ ማቆያ አቅንተው ከእንስሳቱ የደም ናሙና መውሰዳ ቸውንና፤ ጤነኛ በሆኑት እንስሳት ደም ውስጥ ጥገኛ ህዋሳት መገኘቱን ይናገራል፡፡ ተመራማሪዎቹ የደም ናሙናዎቹ የወባ ትንኝን ዘረ መል ለማወቅና በዝግመተ ለውጥ ያሳዩትን ለውጥ ለመገንዘብ ችለዋል፡፡ የወባ ትንኝ አደገኛ የሆነበትን ሂደትም ደርሰውበታል፡፡
በጥናቱ ከተካተቱት ሰባት የወባ ትንኝ ዓይነቶች ሦስቱ ቺምፓንዚን፣ ሦስቱ ደግሞ ጎሬላ የሚያጠቁ ናቸው፡፡ ፕላስሞድየም ፋልሲፓረም የሚባለው አደገኛ የትንኝ ዝርያ ከ 50 ሺህ ዓመታት በፊት ቢገኝም የሰው ልጆችን ወደማጥቃት የተሸጋገረው ከ 3ሺ እና ከ 4ሺ ዓመት በፊት ነው፡፡ ‹‹የወባ ትንኝ ሰዎችን ወደሚያጠቃ ነፍሳትነት ለማደጉ የሰዎች ከቦታ ቦታ መዘዋወር ምክንያት ነው›› ሲል ዶክተር ማት መናገሩን የሚጠቅሰው ቢቢሲ፤ ሊቨርፑሉ ስኩል ኦፍ ትሮፒካል ሜዲሲን ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ጃኔት ሄሚንግዌይ በበኩላቸው ‹‹ብዙ ሰዎች ወባ ከእንስሳት ወደ ሰዎች የሚተላለፍ መሆኑን አያውቁም፡፡ የሰው ሰውነትን ተዋህደው ወደ አደገኛነት የተሸጋገሩትም በጊዜ ሂደት ነው፡፡
የወባ ትንኝ አደገኛ የሆነበትን ጊዜና ሁኔታ ስለሚያሳይ ጠቃሚ ነው፤ የትንኙ አደገኛ የሆነበትን ሂደት መገንዘብ ችግሩን ለመቅረፍ ያስችላል›› ማለታቸውን አስታውሷል:: የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያሳየው በወባ ትንኝ ንክሻ የሚተላለፈው በሽታው እስከአሁን ድረስ በዓለማችን ቀዳሚው ገዳይ በሽታ ነው። በየዓመቱ 219 ሚሊየን ሰዎች በወባ በሽታ የሚያዙ ሲሆን እስከ 400 ሺህ የሚደርሱት ሕይወታቸው ያልፋል። ከሟቾች 60 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2011
አዲሱ ገረመው