በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች በተለይም ሴቶች አሁንም ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሹ የሴቶች ፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴርና ጌጅ ኢትዮጵያ የተሰኘ በወጣቶችና ጾታ ጉዳዮች ላይ ጥናት የሚያከናውን ድርጅት ያካሄዱት ጥናት አመልክቷል።
በአፋር፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እድሜያቸው ከ10 እስከ 19 በሆኑ የጉርምስና ደረጃ ላይ በሚገኙ ወጣቶች ላይ በተደረገ ጥናት አሁንም በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጫና ከወንዶች ይልቅ ከፍተኛ መሆኑ በጥናቱ ተመልክቷል።
ወጣት ሴቶች ከወንዶች ይልቅ የማህበራዊ ጫና አለባቸው፤ በተለይ በማህበረሰቡ ልምዶች ምክንያት ሴቶች ከወንዶች ባነሰ እንቅስቃሴያቸው የመገታት እና ብዙ ጓደኞች እንዳይኖራቸው እክል ይገጥማቸዋል። በሌላ በኩል በልጅነት የመዳር አጋጣሚው በአገር ደረጃ የቀነሰ ቢሆንም በተወሰኑ አካባቢዎች ግን አሁንም ስጋት እንዳለ ጥናቱ አረጋግጧል።
በሌላ በኩል በጥናቱ ከተካተቱ ወጣቶች መካከል ስለ ጉርምስና ወቅተ የአካል ለውጥ ግንዛቤ ቢኖራቸውም ሴቶቹ ግን የመጀመሪያ የወር አበባ ስለሚመጣበት ወቅት ላይ ያላቸው አመለካከት በፍርሃት የተሞላ እንደሆነ ጥናቱ አመልክቷል።
ከጌጅ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ልማት ጥናት ኢንስቲትዩት እና ከተለያዩ አለም አቀፍ የምርምር ተቋማት በተውጣጡ ባለሙያዎች የተሰራው ጥናት አንድ አመት እንደፈጀ ተገልጿል። ጥናቱ በቀጣይም ለስድስት ዓመታት በአንግሊዝ መንግስት ድጋፍ ይከናወናል።
በጋዜጣው ሪፖርተር