የብዙዎች እናት

አንድ ድሮ የማውቃቸውን እናት ከዓመታት በኋላ መንገድ ላይ አገኘኋቸው። ጎስቆል ብለውብኛል። ጉስቁልናቸውን በቆንጆ የእጅ ፈትል የሀገር ልብስ የሸፈኑት እኚህ እናት «ጠይቁኝ ልጄ ጠይቁኝ እንጂ….. » በማለት የወቀሳ አዘል ቃል ሲሰነዝሩ «በቃ እሁድ እመጣለሁ፤ ቡና እንጠጣለን » ብዬ ተሰነባብተን ወደየጉዳያችን ሄድን።

የቀጠሯችን ቀን ደርሶ ለእኚህ እናት መጠየቂያ የሚሆነ ቡናና የቡና ቁርስ ይዤ በቀጠሮ ሰዓታችን ወደ ቤታቸው አቀናሁ። እለቱ እሁድ ስለነበረ ይሁን ሌላ፤ ቤት ስሄድ ሁሉም ልጆቻቸው ተኝተው ነበር። ቤቱ ንፁህ ቢሆንም ምንም ዓይነት የምግብ ሽታ የለበትም ነበር። «ቡናውስ?» ስል ነበር ወዲያው የ20 ብር ከሰል ተገዝቶ ተያይዞ ቡናው መቆላት የጀመረው። ቡናው ሲቆላ ሁሉም ከእንቅልፋቸው ተነስተው ለቁርስ ቀረቡ።

ለካ ወጣት ልጆቻቸው የተኙት ቁርስን በእንቅልፍ ሊያልፉት አስበው ነበር፤ ለእኔ የቡና ቁርስ ያልኩት ከቤቴ ብዙም ርምጃ ሳይርቅ፤ ቁርስ ሊሆን የሚችል ነገር መሆኑን የተረዳሁት በዚህ እለት ነበር። ለካ ደጅ መውጣት ፈርተው በራቸውን ዘግተው የሚላስ፤ የሚቀመስ አጥተው የተቀመጡ ወገኖቻቸን አሉ። በማለት አንድ ወዳጄ ያጫወተችኝን ታሪክ ያስታወስኩት የዛሬዋን እንግዳችንን ደግነት ስሰማ ነበር።

ድሮ መጠያየቅ የመኖር አንድ አካል በሆነበት ወቅት መረዳዳት እንደ ትልቅ ነገር አይታይም ነበር። ዛሬ ወገን ዘመድ ጎረቤትን መጠየቅ ለወገን መድረስ ጭንቅ በሆነበት ዘመን ላይ ደርሰናል። በዚህ ጊዜ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቤት ተከራይታ የምትኖር አንዲት የሶስት ልጆች እናት አንድ የጎዳና ተዳዳሪ አስጠግታ ለአምስት ዓመታት ስታስታምም ቆይታ ሲሞት አስቀብራ ኢትዮጵያዊ ሥርዓት እንደወገኗ ለቅሶ ስትደረስ ሰነበተች ቢባል ማን ያምናል። ህመሙ ተላላፊ ሆኖ አደገኛ ጉዳት ሊደርስባት እንደሚችል እያመነች እንኳን ርህራሄዋ ሳይጎድል ከልቧ አስታማ ሲሞት መሸኘቷ አስደንቆኝ ይህች ርህራሄን የተሞላች ሴት ይሄንን የደግነት ልብ እስከ ምን ደረስ ትጠቀምበታለች ስል ልጠይቅ ወደድኩ።

ይህች ለመስጠት የተፈጠረች ሴት ወይዘሮ ኩኩ ኃይሌ ትባላለች። በአርባዎቹ አጋማሽ እድሜ ላይ እንዳለች የምትናገረው ኩኩ ተወልዳ ያደገችው ጅማ ኪቶ የሚባል ሰፈር ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ኪቶ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ ሁለተኛ ደረጃውን ደግሞ ፌርማታ የሚባል ትምህርት ቤት እስከ አስራ አንደኛ ክፍል ከተማረች በኋላ ነው ከልጅነት ባሏ ጋር ተገናኝታ ወደ ትዳር የገባችው።

በትዳር ሕይወት ውስጥ ሆና ኑሮን ለማሸነፍ ስትል በስደት ከሀገር ወጥታ ዱባይ እና ሱዳንም ለዓመታት ስትሰራ ቆይታለች። የስደት ኑሮ በቃኝ ብላ ሀገሯ ከተመለሰች በኋላ ወይራ ሰፈር አካባቢ በተከራየችው ቤት ውስጥ እየኖረች በረንዳው ላይ በወጠረችው ላስቲክ ስር የተለያዩ ሥራዎችን የሚሰሩ መጠጊያ የሌላቸው ልጆችን ሰብስባ የእለት ጉርሳቸውን ታቃምሳለች።

የኩኩ ለረጅም ዓመታት በሴቶች ፀጉር ሥራ ላይ ብትቆይም አሁን ግን በአገልግል ሥራ ላይ ተሰማርታ እንደምትገኝ ትናገራለች። ሰዎች ለእዝን፤ ለማህበር፤ ለጉዞ በማለት የተለያየ ዓይነት ፓኬጅ ያላቸውን አገልግሎች ሲያዙ ከሚገኘው ትርፍ በተጨማሪ ያለውን ተረፈ ምርት በማውጣት የሷን እጅ ለሚጠብቁት ልጆች አቃምሳ ወደ ሥራቸው ትልካለች።

«አገልግል ለጉዞ፤ ለለቅሶ፤ ለቤተክርስቲያን ሰው እንደየፍላጎቱ ያዛል። አንድ 2500 ብር የሚያወጣ አገልግል ተሰርቶ የሚቆራረጠው እንጀራ የሚተራረፉት የወጥ ዓይነቶች በሙሉ ጎርሶ ማደር ለተሳነው ሕዝብ ይዳረሳል» የምትለው ወይዘሮዋ ዋና ገቢዋን የአገልግል ሥራ ላይ አድርጋ የገንዘብም ሆነ የዓይነት ትርፏን ለበጎ አድራጎት ሥራዋ ታውለዋለች።

በማንነት፣ በምንነት፣ ተከፋፈለን መላ በጠፋበት በዚህ ጊዜ፤ አጉራሽና አልባሽ ያጡ ሕፃናት በየሜዳው ሲንከላወሱ ከማየት የላቀ አረጋውያን እናቶችን ያለጧሪ ቀባሪ ያስቀረ ማንም በድሉ የማይደሰትበት የእርስ በእርስ ሽኩቻ ውስጥ ከገባንበት ከዚህ ጊዜ የባሰ፤ አይዞህ አይዞኝ መባባል እየናፈቀን ሰው ሁሉ በሩን ሲዘጋ፤ ጀርባ ስንሰጣጥ ፊት ስንዟዟር፣ ክፉ ዘመናችንን ተደጋግፈን ማለፍ ትልቅ አማራጭ እንደሆነ የምትናገረው ወይዘሮ ኩኩ በመስጠቱ ብቻ የሚየጣው ነገር አለመኖሩን አውቆ ከትርፉ መካፈል እንደሚኖርበት ትመክራለች።

ወደዚህ ሥራ ስትገባ የችግሩ ስፋት ይህን ያህል ይሆናል ብላ አለማሰቧን የምትናገረው ወይዘሮ ኩኩ ጨርሶ ለማላቃቸው ሰዎች የማደርገውን ደግነት በጣም ያስደስታል በማለት «ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል» በማለት ሥራውን መጀመሯን ትናገራለች።

በልግስና በደግነት ውስጥ ምንም ዓይነት ክፉ ስሜት አለመኖሩንና ሌሎችን ለመርዳት ጥረት ማድረግ የተለያዩ አሉታዊ ሃሳቦችን ከውስጥ በማውጣት ነፍስን በሀሴት የሚሞላ ተግባር መሆኑን ታስረዳለች። «እኔ በሥራዬ ደስተኛ ነኝ ፤ አንድም ቀን ምን እሰጣለሁ ምን አደርጋለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ፈጣሪ እራሱ እየሞላ የብዙዎች እናት አድርጎኛል » ትላለች።

ባለቤቷና ልጆቿ የዚህ በጎ ተግባር ተባባሪ መሆናቸው ነገሮች እንዳይከብዱባት እንዳደረጋት የምትናገረው ወይዘሮ ኩኩ ባለቤቷ የዚህ የበጎ ተግባር ደጋፊ ሆኖ አብሯት ደፋ ቀና በማለት እንደሚያግዛት ታስረዳለቸ። «ከባለቤቴ ጋር እጅግ ሰላማዊ ሕይወት ነው የምንኖረው። የልጅነት ባሌ ነው። 27 ዓመታትን በትዳር ቆይተናል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከመከባበር የዘለለ ይህ ነው የሚባል ፀብ በመካከላችን ተፈጥሮ አያውቅም» ትላለች ።

እንደ ወይዘሮ ኩኩ ገለፃ ሰውን ለመርዳት የልብ ፍላጎት ሊኖር ይገባል በመስጠት ውስጥ የሚገኘውን ደስታ ቢገባን ኖሮ በሀገራችን ውስጥ ይህን ያህል ችግር አይኖርም ነበር ትላለች። በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ በእናቶች ወግ በሚል ገፅ ስር የበጎ አድራጎት ሥራዋን ከማስተዋወቅም አልፋ ሥራዋንም በሚስቡ ፎቶግራፎች ስታስተዋውቅ አገልግሉን አይተው ለሚያምራቸው ነፍሰ ጡር ሴቶች ፈትፍታ ከአዳማ እስከ ጅማ፤ ከጅማ እስከ ሀዋሳ በመንቀሳቀስ የእናትነት እጇን እንደምታቀምሳቸው ትናገራለች።

አራስ ቤት እንኳን ቤት ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ ጠፍቶ ይቅርና ቤቱ ሞልቶም ሆድ በሚብስበት የእናትነት የመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ ጠያቂ ለሌላቸው አራሶች እንደ እናት ቅቤ ለአናታቸው ገዝታ፤ ያላትን ከቤቷ ፈተፍታ አጉርሰና አርሳ የምትመለሰዋ ይህች አስደናቂ ሴት እጅ ባያጥረኝ ኖሮ ሴቷ ቢኒያም በለጠን በሆንኩኝ ነበር ትለናለች።

የተለያዩ ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው መልእከት ለሚልኩላት ሰዎች ስታገኝ ከትርፏ ስታጣ ቤተክርስቲያን ደጅ ቆማ እስከመለመን የሚያደርስ የልብ ቅንነት የታደለችው ይች ሴት አራስ ጥየቃ በሄደችበት ጊዜ የገጠማትን ከእንባ ጋር እንዲህ አጫውተናለች።

«አንድ ቀን አንዲት ደጋፊ የሌላት ሴት እንዳለች ሰምቼ አገልግሌን ይዤ ቤቷ ሄድኩኝ። በቂ ምግብ ስላላገኘች ይሁን በሌላ ምክንያት የዚህች እናት ጡት ደርቆ ሕፃን ልጇን ማጥባት ተስኗት ተመለከትኩ። ለዚህች ሕፃን የጣሳ ወተት እስከሚገዛ ድረስ እኔም በቤቴ የምትጠባ ልጅ ሰላለችኝ ሕፃንዋን ሳጠባት ውያለሁ። ሕፃኗን እያጠባሁ በጎ አድራጊዎችን ፈልጌ ወተቱ ደርሶ ልጅቷ ከረሃብ እስክትገላገል ድረስ ሳጠባ ውዬ ነበር ወደ ቤቴ የተመለስኩት ̋ ብላለች።

በርካታ የስኳር ሕመም ያለባቸውን ሕፃናትን የያዙ ችግረኛ እናቶች፤ ልጆቻቸው በምግብ እጦት ሲያለቅሱባቸው የሚውሉ ቤተሰቦች፤ ለልጆቻቸው ቅርስ ላለማሳጣት ቤት እያላቸው የሚራቡ ትልልቅ ሰዎች ብቻ ተቆጥሮ የማያልቅ ችግር ያለባቸው ሰዎችን መድረስ አሰቃቂ ነው የምትለው ወይዘሮ እያንዳንዱ ሰው ሸክሙን ቢካፈል አንድም ሰው ስለ ምግብ እጦት አያለቅስም ነበር ትላለች።

አሁን የእናቶች ወግ በተባለው የፌስቡክ ገፅ ላይ የተመለከቱኝ እናቶች የአንደ አገልገል ሂሳብ በመክፈል የዛሬ ቁርስ እኔ እችላለሁ፤ የዛሬ ምሳ ደግሞ እኔ አለሁ እያሉ ሸክሙን ለማቅለል እየሞከሩ መሆኑን የምትገልጸው ወይዘሮ ኩኩ ይህን የሰፋ ማህበራዊ ችግር መደገፍ ማገዝ የሚፈልግ ካለ በገንዘብ ቢረዳ እኔ ደግሞ በጉልበቴ ነፍሴ እስካለች ማንም እንዳይራብ እሰራለሁ ትለናለች።

ሰው ማለት የድሃ እንባን ለገበያ ያላቀረበ፣ የድሃ እንባን የሚያብስ ነው። ዛሬ ያደከመን ችግር ዙሪያው ገደል የሆኖ እንዲሰማን ያደረገንን ለማቅለል በሃሳብ ብንደጋገፍ ለሌሎች ተስፋ የሚሆን ድጋፍን ብናደርግ ማህበራዊ ችግሮቻችንን አንድ በአንድ ማራገፍ እንችላለን።

በመጀመሪያ ደረጃ ሕይወት አጭር መሆኗን በመረዳት፤ አብዛኛው ሰው በሥራ ማጣት፣ በሰላም ማጣት፣ በገንዘብ ማጣት፣ በመከዳት ድብርት ውስጥ መሆኑን በመገንዘብ ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው ብለን ያለንን ብንሰጣጥ መልካም ይሆናል።

በምንኖርባት ዓለም ላይ እናት፣ አባት፣ ወንድም፣ እህት፣ አጎት፣ አክስት፣ ጓደኛ፣ ዘመድ አዝማድ ጎረቤት ጋሼ እቴቴ ብለህ የምትጠራቸው ሌላው ቢቀር በዓይን የምታውቃቸው የሚያውቁን ሰዎች በሙሉ የሆነ ጎዶሎ ነገር እንዳላቸው በማሰብ መደጋገፍን መርህ ማድረግ ተገቢ ነው ትላለች፡፡

አዳማጭ የሚፈልጉ አረጋዊያንን ማዳመጥ፤ ሰው ለረባቸው ጊዜ መስጠት፤ ለታረዙቱ ሳናስብ ቁም ሳጥናችንን ያጣበበውን ልብስ ቀንሰን መስጠት፤ ለተራበ ከተረፈን ላይ ሳይበላሽ ከምንጥለው ሌሎችን ብናጎርስ እመኑኝ ስለችግር ማውራት ትተን ስለሀገር እድገት የምናወራበት ጊዜ እሩቅ እንደማይሆን ታያላችሁ በማለት ታብራራለች። እኛም ለመልካም ሥራ አይረፍደምና እጅ ለእጅ በመያያዝ ወደ ነገ እንድንሻገር ይሁን በማለት እንሰነባበት።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2016

Recommended For You