የኢንፎርሜሽን ደህንነት መረብ አስተዳደር የሳይበር ደህንነት ወርን አስመልክቶ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን እያካሄደ ይገኛል፡፡ ከመርሀ ግብሮቹ አንዱ የሆነውን የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይም በቅርቡ አካሂዷል፡፡ ይህ የቴክኖሎጂ ድግስ በየዓይነቱ የቀረበበትና ሀገራችን በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለችበትን ደረጃ አሳይቷል፡፡ በዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዳችን በመድረኩ ከቀረቡት ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ውጤቶች ውስጥ ጥቂቶቹን እንዳስሳለን፡፡
አቶ አቤል ለገስ የኢንፎርሜሽን ደህንነት መረብ አስተዳደር የኤሮስፔስ የድሮን ኦፕሬሽንና ፓይሌት ኦፕሬሽን ባለሙያ ነው፡፡ በአውደ ርዕዩ አስተዳደሩ ‹‹ሱፕር ኤሮ›› ከተሰኘ ኩባንያ ጋር በመተባበር በሀገሩ ውስጥ የተገጣጠሙ ሁለት ዓይነት ድሮኖችን ይዞ ቀርቧል፡፡
አንደኛው በመጠን ከፍ የሚለው የድሮን ዓይነት አካባቢን ለመቃኘት (ለመቆጣጠር )እና የአንድ አካባቢን ካርታ ለማንሳት አገልግሎት የሚውል ሲሆን፤ ሁለተኛው በመጠን አነሰ የሚለው የድሮን ዓይነት ደግሞ ለደምና ለመድኃኒት ማመለላሻ አገልግሎት ይውላል፡፡
“የኢትዮጵያ መልካዓ ምድር ፈጣን የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ከባድ ነው” የሚለው አቶ አቤል፤ ለደምና መድኃኒት ማመላለሻ አገልግሎት የሚውለው ድሮን ለዚህ ችግር መፍትሔ ለመስጠትና ተደራሽ በማይሆኑ ቦታዎች (አካባቢዎች) ላይ ተደራሽ ለመሆን እንደሚጠቅም ይናገራል፡፡
ሁለቱም ዓይነት ድሮኖች “ከካርበንና ፋይበር ግላስ” የተሰሩ ሲሆን፤ ሞተሮቻቸውም በነዳጅና በባትሪ የሚሰሩ ናቸው፡፡ በባትሪ የሚሰራው ድሮን ሞተሮች ራሱን ከመሬት ላይ ከፍ ለማድረግና ለማረፍ የሚጠቅሙት ናቸው። በስተጀርባ ያሉት ሞተሮች ደግሞ ራሱን ለማብረር ( ለመግፋት) ይጠቀሙታል፡፡
አቶ አቤል እንደሚለው ፤ በነዳጅ የሚሰራው ድሮን በአየር ላይ ለስድስት ሰዓታት ያህል መቆየት ይቻላል፡፡ በባትሪ የሚሰራው ድሮን ደግሞ አንድ ሰዓት ያህል መቆየት ነው የሚቻለው፡፡ ሁለቱም ድሮኖች እስከ 150 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሄድ አቅም አላቸው፤ ከዚህ በላይ ርቀት እንዲጓዙ ከተፈለገ ግን የነዳጅና የባትሪ አቅምና መጠን የሚወሰን ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰዓት ያህል የሚበረውን በባትሪ የሚሰራውን ድሮን ብንመለከት በአንድ ሰዓት ውስጥ እስከ 80 ኪሎ ሜትር የመብራር አቅም ያለው ሲሆን፤ አንድ ቦታ ላይ አርፎ ባትሪውን ቀይሮ እንደገና ጉዞውን መቀየር ይችላል፡፡ ስለዚህ የድሮኑ የመብረር አቅም እንደተሰጠው ተልዕኮ ይወሰናል፡፡
የቴክኖሎጂ ውጤቶቹ በአውደ ርዕዩ ላይ የቀረቡበት ዋንኛ ምክንያት መሰል ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በሀገር ውስጥ መሥራት እንደሚቻል ለማሳየት እንደሆነ የሚገልጸው አቶ አቤል፤ አውደ ርዕዩ ቴክኖሎጂዎቹን ሕዝቡ እንዲያያቸውና እንዲያውቃቸው ለማድረግ መሆኑን ይናገራል፡፡ እነዚህን ድሮኖች በሀገር ውስጥ በመገጣጠም የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን እንደሚቻል ተናግሯል፡፡
በድሮን በመጠቀም የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል አቶ አቤል ይገልጻል፡፡ ድሮኖቹን ለመሥራት ሁለት ዓመታት ያህል መውሰዱን ጠቅሶ፣ አሁን ላይ ሥራው አድጎ ድሮኖቹን ለማምረት የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ነው ብሏል፡፡
‹‹ድሮን በሀገር ውስጥ መገጣጠም መቻላችን ለትራንስፖርት ተብሎ የሚወጣውን ወጪ ይቀንሳል፤ በቴክኖሎጂ ያለንን እውቀት እንድናደብር ያደርጋል፤ የማምረት አቅምንና የቴክኖሎጂ እውቀት ማግኘት ያስችላል›› የሚለው አቶ አቤል፤‹‹ድሮን ገበያ ላይ የሚገኝ እቃ አይነት አይደለም፤ ድሮን የሚፈልግ አካል ወይም ፍላጎት ያለው መኖር አለበት፡፡ አሁን ድሮን ሀገር ውስጥ የማምረት አቅም እንዳለ ለማሳወቅ ነው›› ሲል አብራርቷል፡፡
ድሮንን በሀገር ውስጥ ማምረት መቻላችን ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚያፎካክረን ደረጃ ላይ ባንድርስም አንድ ደረጃ ወደፊት ያራምደናል የሚለው አቶ አቤል፤ በቀጣይ የላቁ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ከውጭ የሚመጡ ቴክኖሎጂዎችን በማስቀረት የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን የሚደረገው ጥረት እንደሚቀጥልም አረጋግጧል፡፡
ሌላኛው በአስተዳደሩ የተሰሩ የድሮን ዓይነቶችን ይዞ ቀረበው የአስተዳደሩ የኤሮስፔስ ዲቪዥን ኤሮዳይናሚክ ተመራማሪ ወጣት የኔአባት ሰውአገኝ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ደግሞ ሦስት ዓይነት ድሮኖች ለእይታ ቀርበዋል፡፡
የመጀመሪያው የድሮን ዓይነት ለወታደራዊ አገልግሎት /ቦንብ ለመጣል/ ያገለግላል፡፡ በተጨማሪም የቅኝት ሥራዎች ለመሥራት ይውላል፡፡ ሁለተኛው የድሮን ዓይነት የአረም ማጥፊያ ለመርጨት አገልግሎት ይጠቅማል፡፡ ይህ ድሮን የአረም ማጥፊያ ኬሚካልን አንድ ቦታ ላይ ሆኖ እስከ አንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ እየዞረ ለመርጨት ይችላል፡፡ ሦስተኛው የድሮ ዓይነት ደግሞ ለማዕድን ፍለጋ አገልግሎት የሚውል ሲሆን፤ ማዕድኑ ባለበት ቦታ ላይ በሚልከው ጨረር አማካይነት ምን ዓይነት ማዕድን በቦታው ላይ እንዳለ ይጠቁማል፡፡ ይህ ማዕድኑ ያለበት ቦታ ሳይቆፈር በቴክኖሎጂ ስለሚያሳይ ባለሙያዎች ያገኙትን ዳታ በመያዝ ስለማዕድኑ ጥናት ለማድረግ ያስችላቸዋል፡፡
እነዚህ ሦስቱ ድሮኖች በባትሪ የሚሰሩ ናቸው፤ ባትሪውን በመሙላት(ቻርጅ በማድረግ/ እና በመቀያየር አንድ ቀን ሙሉ በምንፈልገው መልኩ የፍጥነት መጠንን በመጨመር ማብረር ይቻላል የሚለው ወጣት የኔአባት፤ ድሮኖቹን ለመሥራት በአብዛኛው ሶፍትዌር ለማበልጸጉ ላይ ትኩረት ተደርጎ የተሰራ መሆኑን ይናገራል፡፡ ድሮኖቹ ተፈትሸው፤ ሙከራ ተደርጎባቸው በትግባራ ላይ የዋሉ መሆናቸውንም ጠቅሶ፤ ድሮኖቹን ለሚጠቀሙባቸው አካላት የድሮን ስልጠና እንደሚሰጥ፣ ጥገና ሲያስፈልጋቸው ደግሞ ወደ ተቋሙ መጥተው አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚደረግ ተናግሯል፡፡
በተለይ ለግብርና ሥራ ድሮኑን የተጠቀሙ አካላት ስለድሮኑ የሚሰጡት አስተያየት በጣም ጥሩ እንደሆነና ሥራቸውን ያቀለለላቸው መሆኑን ነው የሚለው የኔአባት፤ ሌሎችንም ሥራዎች ሊያቀሉ የሚችሉ ድሮኖች እንዲሰራላቸው ፍላጎት እንዳላቸው ይገልጻል፡፡
እነዚህ ድሮኖች በአውደ ርዕዩ እንዲታዩ ማድረግ እንደዚህ ዓይነት ሥራዎችን በሀገር ውስጥ መገጣጠም መቻሉን ኅብረተሰቡ እንዲያወቅ ለማድረግ እንደሚረዳ ጠቁሞ፤ ይህ ደግሞ የፈጠራ ሥራዎችን ለማሳደግ እንደሚያስችልም ይገልጻል፡፡ ድሮኖቹን ለማምረት የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ የሚያቀርቡ ወይም ማምረት የሚፈልጉ ኩባንያዎች ካሉ የድሮኑ ዲዛይን ተሰርቶ የተጠናቀቀ ስለሆነ እንዲያመርቱ ማድረግ ይቻላል ይላል፡፡
የ12ተኛ ክፍል ተማሪው ተማሪ ጉተንበር አበራ፣ በሳይበር ታለንት ማዕከል ከታቀፉ ተማሪዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ውሃ የሚያጠጣ (ለግብርና ሥራ የሚውል) እና እንደ እጅ የሚያገለግል ሮቦት የፈጠራ ውጤቶቹ ናቸው፡፡ እንደ እጅ የሚያገለግል ሮቦት “አርም” የተሰኘው ፈጠራ በኬሚስትሪ ላብራቶሪ ውስጥ እና በተለያዩ ቦታዎች በሰው ልጆች ላይ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ በሰው እጅ የማይነኩ ሥራዎችን ለመሥራት ያግዛል፡፡ ይህ ሮቦት እቃዎችን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማንቀሳቀስ ይረዳል፡፡
እነዚህ ሮቦቶች አካባቢ ላይ ከሚገኙ ቀላል ከሚባሉ ቁሳቁስ የተሰሩ ሲሆን፤ ሮቦቶቹን በስልክ አማካይነት መቆጣጠር እንደሚቻልም ይገልፃል፡፡ አሁን ላይ የተሰራው ሮቦት 9 ኪሎ ግራም ቁሳቁስ በአንድ ጊዜ ማንቀሳቀስ እንደሚችል ተናግሯል፡፡ ከዚህም በላይ እስከ 20 ኪሎ ግራም የማንሳት አቅም እንዲኖረው አድርጎ መሥራት እንደሚቻልም አመላክቷል፡፡
ሌላኛው ውሃ የሚያጠጣ ሮቦት ሲሆን፣ አንድን የእርሻ ማሳ በአንድ ሮቦት ተጠቅሞ ውሃ ማጠጣት ያስችላል፡፡ አርሶ አደሩ ማሳው ድረስ ሄዶ ሰብሉን ውሃ ማጠጣት ሳያስፈልገው ሮቦቱ በተሞላለት ሰዓት ተመርቶ በራሱ የሰው ንክኪ ሳይፈልግ ውሃ ማጠጣት ይችላል። ሮቦቱ ባትሪው እስካላለቀ ድረስ ከአንድ ማሳ በላይ እስከምንፈልገው ሄክታር መሬት ውሃ ሊያጠጣ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዘር መዝራት የሚያስችል መሆኑን ነው ተማሪው የሚናገረው፡፡
ሮቦቱን የውሃው አቅርቦት ማለቁን ለሚቆጣጠረው አካል ወዲያውኑ ይጠቁማል፤ ከሌሎች ሮቦቶች አንጻር ሲታይ ሮቦቱን ለመሥራት የሚወጣው ወጪ ቀላል የሚባል ነው የሚለው ጉተንበርግ፤ ‹‹አብዛኛውን ሮቦቱ የተገጣጠመባቸው ቁሳቀስ በሀገር ውስጥ በቀላሉ የሚገኙ መሆናቸውን ይጠቁማል፡፡ በአስተዳደሩ ውስጥ ሮቦቱን ለመገጣጠም የሚያገለግሉ ቦርዶችን መሥራት ጀምረናል፤ ሀገር ውስጥ የማይሰሩትን ማይክሮኮንትሮል የሚባሉትን ከሀገር ውጭ እንደሚመጡም ይገልጻል፡፡
አሁን ላይ በተሰጥኦ ማዕከሉ ውስጥ ሁለቱንም የሮቦት ዓይነቶች በአንድ በማጣምር የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የሚያስችሉ ተደርገው እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ ‹‹ወደ ተሰጥኦ ማዕከል ከመጣሁ በኋላ ብዙ ትምህርቶች አግኝቼለሁ፤ ይህም ለፈጠራ ሥራዬ ብዙ እገዛዎችን እንዳገኝ አድርጓኛል፡፡ ሲል ገልጿል፡፡ በማዕከሉ ውስጥ አንዱ ከአንዱ የሚገኘው የልምድ ልውውጥ ቀላል የማይባል እንዳልሆነም የተናገረው፡፡ እነዚህ የፈጠራ ውጤቶች በአውደ ርዕይ እንዲታዩ መደረጉ የፈጠራ ውጤቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ቀላል እንዳልሆነም አስታውቋል።
ተማሪ ሶሬቲ ዘንባባና ኬና ተስፋዬ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች ሲሆኑ በሳይበር ታለንት ማዕከሉ ታቅፈዋል። ዘመናዊ የግብርና መቆጣጠሪያ ሲስተም” የተሰኘ የፈጠራ ፕሮጀክታቸውን ይዘው ቀርበዋል፡፡
የተማሪዎቹ የፈጠራ ሥራ የመጀመሪያው “የመስኖ ሲስተም” ሲሆን፣ የአፈርን እርጥበትና ድርቀት በመለካት እርሻ ላይ ያሉ ሰብሎች የሚያስፈልጋቸውን ውሃ ያህል ብቻ ማጠጣት የሚያስችል ነው፡፡ ለምሳሌ አፈሩ ደረቅ በሚሆንበት ጊዜ በራሱ በመለየት (sense በማድረግ) ውሃ ያጠጣል፡፡ የአፈሩ እርጥበት በቂ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ውሃ ማጠጣቱን ያቆማል፡፡
ሁለተኛው ሲስተም በሰብሎች ላይ የሚደርሰውን የእሳት አደጋ ለመከላከል የሚያስችል መሳሪያ /ሴንሰር/ ተገጥሞለታል፡፡ መሳሪያው ድምጽ ሲያሰማ ለሰዎች ያሳውቃል ወይም አካባቢው ላይ ሰዎች ከሌሉ ራሱ እሳቱን በማጥፋት ሰብሉን ከእሳት አደጋ መከላከል ይችላል፡፡
ሦስተኛው የውሃ መቆጣጣሪያ ሲስተም የተገጠመለት ሲሆን፤ ለመስኖ አገልግሎትና ለእሳት አደጋ መከላከል የተዘጋጀ ውሃ ከታንከር ውስጥ በሚያልቅበት ጊዜ ማለቁን የሚያሳውቅ ነው፤ በራሱ /አውቶማቲካሊ/ ውሃው እንዲሞላ ያደርጋል፡፡ በቅጡ ያልጠፋ /የተዳፈነ / እሳት ሰብሎች ላይ በሚነሳበት ጊዜም እሳቱ በፍጥነት ሳይስፋፋ ያሳውቃል፡፡ ሰዎች መጥተው አስፈላጊውን ርዳታ እንዲሰጡ ያደርጋል። የውሃ መቆጣጠሪያ ሲስተሙ ውሃ ለመስኖ አገልግሎት የሚውል ከትልቅ ታንከር ወይም በቀጥታ ከወንዞች ወይም ከውሃ ምንጭች መጠቀም የሚችል መሆኑን ተማሪዎቹ ገልጸዋል።
ሰፊ ማሳዎች ላይ በምንጠቀምበት ጊዜ ወደታች 12 ኢንች ጥልቀት ድረስ ‹‹ሴንስ›› ያደርጋል የምትለው ተማሪ ሶሬቲ፤ አገልግሎቱም በገጠር አካባቢ ላሉ እርሻዎች ብቻ ሳይሆን ከተማ ግብርና ላይም መጠቀም እንደሚቻል ትናገራለች።ለከተማ ውበት ለሚያገለግሉ ተክሎች ውሃ በማጠጣት መንከባከብ የሚያስችል መሆኑንም ገልጻለች፡፡
‹‹ሀገራችን ሰፊ የእርሻ መሬት ያላትና የአብዛኛው ሕዝብም መተዳደሪያ የግብርና ሥራ ቢሆንም፣ የግብርና ሥራው በቴክኖሎጂ ስላልታገዝ ካለንበት አሠራር አልተላቀቅንም” የምትለው ሶሬቲ፤ መሬት፤ ሰውም ቢኖር አጋዥ ቴክኖሎጂ ግን እንደሌለ አስታውቃለች፡፡ በዚህ የተነሳ ለውጭ ርዳታ ተዳርገን ኖረናል ስትል አመልክታለች። ስለዚህ የግብርናው ሥራ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማድረግ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ግብርና ለሀገራችን የበለጠ ገቢ እንዲያስገኝ ማስቻል ነው›› ትላለች፡፡
‹‹ማዕከሉ ያለንን ተሰጥኦ እንድናዳብርና የሀገራችንን ችግሮች እንድንለይ ትኩረታችንን እንድናደርግ አስችሎናል›› የምትለው ተማሪ ሶሬቲ፤ በቀጣይ ይህንን የፈጠራ ሥራ በማሳደግ በየትኛውም ርቀት ቦታ ላይ ሆኖ ለመቆጣጠር የሚያስችል ሲስተም እንዲገጠምለትና በእጅ ስልካችን መጠቀም እንድንችል አድርገን ልንሰራው እንችላለን›› ስትል ትናገራለች፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ባደረጉት ንግግር እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያን ጭምሮ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ሌሎች ሀገራት ያመረቷቸውን ቴክኖሎጂዎች ሲጠቀሙ ቆይተዋል። ይህም በብሔራዊ ደህንነታቸው ላይ ስጋት እየፈጠረ ነው። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የቴክኖሎጂ ባለቤትነት አቅምን መገንባት ያስፈልጋል፡፡
የነገውን ትውልድ የሳይበር ደህንነት ለማረጋገጥ ጥናቶችና ምርምሮችን የማጠናከር፣ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ የግል ተቋማትን የማበረታታት እንዲሁም ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ላይ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ፤ የሀገሪቱን የሳይበር ኃይል ለማሳደግ ውስጣዊ አቅምን ከማጎልበት ባሻገር በሀገራዊው የሳይበር ታለንት ማዕከል አማካኝነት ወጣቶችን በማሰልጠንና በማብቃት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በ2015 በጀት ዓመት የክረምት መርሐ ግብር ከአንድ ሺህ 500 በላይ ወጣቶች መካከል 62 ወጣቶች የተለያዩ ደረጃዎችን አልፈው ከ26 በላይ ቴክኖሎጂዎችን አልምተዋል ብለዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ ወጣቶቹ በጋራ በመሆን ሥራ ላይ መዋል የሚችሉ 14 ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት ላይ መሆናቸውን አስታውቀው፣ ቀሪዎቹ ደግሞ የአስተዳደሩ የሳይበር ወታደር ሆነው እያገለግሉ መሆኑን አመላክተዋል። በዘንድሮው የ2016 በጀት ዓመት በሀገራዊ የሳይበር ታለንት ማዕከል ለክረምት ትምህርት 5 ሺህ 600 ወጣቶች ማመልከታቸውን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
የሳይበር ደህንነት ወር ‹‹አይበገሬ የሳይበር አቅም ለሀገር ሉዓላዊነት›› በሚል መሪ ቃል በዓለም ለ20ኛ ጊዜ፤ በሀገራችን ደግሞ ለአራተኛ ጊዜ እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተመላክቷል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2016