ሀገር በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎች ጀግኖችን ታፈራለች:: እነዚህ ጀግኖቿ ደግሞ በተሰማሩበት መስክ ሁሉ የሀገራቸውን ስም ያስጠሩ ሰንደቋም ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደረጉ ናቸው:: ታዲያ እነዚህን ጀግኖቿን በሚገባቸው ልክ አክብራለች ወይ ከተባለ መልሱ አላከበረችም ነው:: ምክንያቱም የተለያዩ ዓይነት ማሳያዎችን ማቅረብ ስለሚቻል ነው::
የዛሬዋ የሕይወት ገጽ እንግዳችን ለሀገር ትልቅ ዋጋ ከፍላለች:: በወታደር ቤት ረጅም የእድሜዋን ዓመታት ኣሳልፋለች:: እስከ ሻምበልነትም ደርሳለች:: በኢትዮ ሶማሌ ጦርነት ወቅት ሴትነቷ ሳይገድባት ጦር ሜዳ ድረስ እየገባች ለሠራዊቱ ሞራል የሚሆኑ የጀግንነት ዜማዎችን ከመሥራትም ባለፈ ክላሽ ተሸክማ ተዋግታለች:: በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድም
………ሎሚ ተራ ተራ
ሎሚ ተራ ተራ
ሎሚ ተራ ተራ እናቴን አደራ:: በሚለው ልብ ሰርሳሪ ዜማዋ ትታወቃለች:: ከዚህ ዘፈኗ በኋላም ደግሞ በቪዲዮ ተቀናብሮ የተሠራው …
……እኮራበታለሁ በእኔነቴ
የጥቁር እንቁ ነው መሠረቴ
በኢትዮጵያዊነቴ እኮራለሁ
ለማንዴላ ክብር መሠረት ጥያለሁ…..
በማለት ከትልልቅ የሀገራችን መሪዎች እስከ ኢትዮጵያውያን የቁርጥ ቀን ጀግኖች አርበኞች ድረስ ያወደሰችበት ሙዚቃዋ መለያዋ ነው:: የባሕሏ እመቤት ሻምበል ደመቀች መንግሥቱ (ሎሚ ተራተራ):: እኛም የሀገር ባለውለታነቷን እንዘክር አሁን ያለችበትን አስከፊ የሕይወት ገጽታ አድናቂዎቿ እንዲሁም መላው ኢትዮጵያውያን ያውቁት ዘንድ በዚህ መልኩ አቅርበነዋል::
ሻምበል ደመቀች (ሎሚ ተራተራ) ተብላ ስትጠራ እጅግ ደስ እንደሚላት ትናገራለች:: እኛም በዚሁ ስሟ እየጠራን ታሪኳን እንጽፍ ዘንድ ወደናል::
ሎሚ ተራተራ የተወለደችው ወሎ ክፍለ አገር መካነ ሰላም አውራጃ ነው:: በተወለደችበት አካባቢም ከብት በመጠበቅ ቤተሰቦቿን አቅሟ በቻለው ሁሉ በማገዝ አስፈላጊውን የቤት ሥራ በመሥራት ስለማሳለፏ ትናገራለች::
በእነዚህ የልጅነት ጊዜዎቿም ከብት ስትጠብቅ የቤቱን ሥራ ስትሠራ ብቻ ምን አለፋችሁ ባለፈችበት ባገደመችበት ሁሉ ማንጎራጎር ደግሞ መገለጫዋ ነው:: ይህ እንጉርጉሮ እንጀራዋ እንደሚሆን ግን ምንም አልገመተችም ነበር::
“……እናቴ የትልቅ ሰው ዘር የምትባል ነበረች:: እኔና ወንድም እህቴን በጥሩ ሁኔታ ነበር ያሳደገችን፤ አባታችን በልጅነታችን ነው በሕመም ምክንያት አዲስ አበባ ለሕክምና መጥቶ የቀረው፤ ስለዚህ የልጅነት ጊዜዬን ከእናቴ ጋር ነበር ያሳለፍኩት” ትላለች::
ታዳጊዋ ሎሚ ተራተራም ከእናቷ ቤት ልትወጣ እንደ ሴት ሦስት ጉልቻ ልትመሠርት ጊዜው ደረሰና ሽማግሌ ተላከ ፤ ምንም እንኳን ለአቅመ ሄዋን የደረሰች ባትሆንም በባሏ እናት ቤት ከባሏ ጋር አብራ ታድግ ዘንድ በሚል ለማደጎ ጋብቻ ተሰጠች:: እሷም በልጅነቷ እናቷን ተለይታ የወደፊት ቤተሰቦቿ ወደሚሆኑት የባለቤቷ እናት ቤት አመራች:: በዛም ከባሏ ጋር እንደ እህት ወንድም ሆነው አብረው እየተጫወቱ የሚሠራውንም እየሠሩ መኖር ጀመሩ::
“…….የተዳርኩት በልጅነቴ ነው:: የባለቤቴ እናት ቤትም ገብቼ እንደ ልጅ ከእሳቸው ጋር እየተኛሁ ከእህት ከወንድሞቹ ጋር እየተጫወትኩ አደኩ:: ነገር ግን እኔም እሱም ለአቅመ አዳምና ሄዋን ስንደርስ ጎጆ ቀልሰውልን ጫጉላ ቤት እንድንገባ ሆነ፤ በዚህ ጊዜ ትዳር የያዝኩ ሴት መሆኔ ታወቀኝ፤ በፍጹም ስሜቱን ልቀበለው ከበደኝ:: ስለዚህ ከእሱ ጋር በአንድ ጎጆ ከመኖር ይልቅ ሌሎች አማራጮችን ማየት እንዳለብኝ ወሰንኩ” በማለት ትናገራለች::
እንዳሰበችውም አልቀረችም ከዛ ጫጉላ ቤት እየጠፋች በየጫካው ዛፍ ላይ ሳይቀር ማደር ጀመረች:: ብትመከረም ቢቆጧትም እንዲህ አይደለም ትለምጂዋለሽ ቢሏትም እሷ ግን አሻፈረኝ እንዳለች ቀረች:: አንድ ሌሊት ዋርካና ዋርካ መሐል ስታድር የመጡባትን ጅቦች ስታስብ አሁንም ድረስ ይዘገንናታል:: እንዲህ በማስቸገሯ የባሏም ቤተሰቦች ተከፉ፤ እሷ ግን ሁኔታው ግድ አልሰጣትም እንደውም ራቅ ብለው ወደሚገኙት እናቷ መሄድ እንዳለባት ወሰነች::
“…..እዛ ዋርካ ዛፍ ላይ ተንጠልጥዬ እነዛ ሁሉ ጅቦች በላዬ ሲዞሩ ካደሩ በኋላ በቀጥታ እናቴ ጋር መሄድ አለብኝ ብዬ ነው የወሰንኩት፤ እናም ሲነጋ ያንን ሁሉ መንገድ በሩጫ አቋርጬ ስሄድ ባለቤቴ ከኋላ ቢከተለኝም ማንም ሊደርስብኝ ሳይችል እናቴ ቤት ደረስኩ”::
ሎሚ ተራተራ እናቷ ጋር እያለከለከች ከገባች በኋላ በቀጥታ የተናገረችው “…..ከዚህ በኋላ ባል ቤት ሂጂ የምትይኝ ከሆነ ቦተር (በአገራቸው ትልቅ ወደሆነው ገደል) ራሴን እጨምራለሁ “በማለት ከመናገሯም በላይ አዲስ አበባ ወደሚገኙት አባቷ ዘንድ መሄድ እንደምትፈልገም ትናገራለች:: እናት የልጃቸው ሁኔታ ምንም ስላላማራቸው “እባክሽ ልጄ ትተሽኝም አትሂጂ የፈለግሽውን አደርገልሻለሁ ከብትም እሰጥሻለሁ፤ መሬትም ይቆረስልሻል ልብስም እገዛልሻለሁ” በማለት ልመናቸውን አቀረቡ፤ እሷ ደግሞ አንዴ ቆርጣለችና ምንም ቢመጣ አይሆንም እንደውም አባቴ ጋር ነው መሄድ እፈልጋለሁ በማለት በአቋሟ ጸናች:: እናትም በሁኔታዋ በጣም ስለተበሳጩ ተስፋም ስለቆረጡ በቃ ከበግ ነጋዴዎች ጋር በእግሯ አዲስ አበባ ትግባ ብለው እንደላኳት ትናገራለች::
“…….እናቴ እባክሽ ልጄ ጥለሽኝ አትሂጂ ብላ ብዙ ለመነችኝ:: እኔ ግን እምቢ አልኳት:: እረግምሻለሁ እንኳን ብትለኝ ልሰማት አልፈለኩም:: እሷም በጣም ስለተናደደች በእግራቸው ከሚሄዱ በግ ነጋዴዎች ጋር ላከችኝ፤ በዚህም ሰባት ቀን ሙሉ በእግሬ ተጉዤ ጎሐ ጽዮን ስደርስ መንቀሳቀስ አቃተኝ:: ሰዎቹም በጣም ተደናግጠው መኪና ለምነው በማሳፈር አዲስ አበባ እንድገባ አገዙኝ” ትላለች::
አዲስ አበባ ከተማም ስትገባ ለሕክምና ብለው ከሀገራቸው የወጡት አባቷ ልደታ ቤተክርስቲያን አካባቢ ይኖሩ ነበርና ወደሳቸው አመራች:: አባቷም ሲያዩት በጣም ቢደናገጡም ልጃቸውን ስላገኙ ደግሞ ደስታም ተሰማቸው:: ግን ደግሞ እሳቸው ባላሰቡት ሁኔታ ሀገራቸውን ጥለው መምጣታቸው የሁልጊዜ ቁጭታቸው ነበርና ልጃቸውም የእሳቸው አይነት እድል እንዲደርሳት ፍጹም አልፈለጉም፤ በዚህም “… እባክሽ የእኔ ወጥቶ መቅረት ይበቃል አንቺ እንኳን ሀገርሽ ግቢ” በማለት ለመኗት:: ሎሚ ተራተራ ግን የመማር ፍላጎት ነበራትና “….ሀገሬ አልመለስም ከቻልክ ትምህርት ቤት አስገባኝ” በማለት እሷም የራሷን ሀሳብ እየሰነዘረች ቀናት ተቆጠሩ::
ሎሚ ተራተራ አዲስ አበባ ልደታ ሰፈር ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው ታዋቂ የሆነችው፤ የመንደሩ ሰው ሁሉ ወደዳት:: እሷም እንደ ሀገሯ እያንጎራጎረች ከአካባቢው ሕጻናት ጋር ነበር የምትውለው፤ በተለይም እንጉርጉሮዋ ብዙዎች ይማረኩ ነበር:: ከአባቷ ጋር ሥራ የሚሠሩ የልብ ጓደኛቸው ታዳጊዋንና የሙዚቃ ፍቅሯን እንዲሁም ስታዜም ያላትን ችሎታ ተመልክተው ለአባቷ “…..ይህችን ልጅ ብሔራዊ ቲያትር ቤት ለምን አናስቀጥራትም” በማለት ሀሳብ አቀረቡ:: አባት ድምጿን የሰሙት በችሎታዋም የሚተማመኑ ቢሆኑም ሀሳቡን ግን ነገሬ ብለው መቀበልን አልፈለጉም:: ጓደኛቸው ደግሞ መቀጠር አለባት በማለት ይዘዋት ብሔራዊ ቲያትር ቤት ሄዱ::
“……..የአባቴ ጓደኛ እንደተመኙ አልቀሩም ብሔራዊ ቲያትር ቤት ይዘውኝ ሄዱ:: አቶ አውላቸው ደጀኔ ደግሞ “ሎሚ ተራተራ” የሚለውን የዘፈን ግጥም እንዳጠና ሰጡኝ:: ምክንያቱም ይህ ግጥም ለሌሎችም ተሰጥቶ ነበርና የተሻለ የተጫወተውን ለመምረጥ እንዲመቻቸው ነው:: በዚህ መሠረትም እኔ የተሰጠኝን ግጥም በደንብ አድርጌ አጥንቼ ዜማውም በደንብ ገብቶኝ ዘፈንኩት፤ እነሱም በጣም ወደዱት ለሬዲዮም ለቴሌቪዥን እንጨት አዝዬ እየዘፈንኩ ተቀረጽኩ ፤ ከዛማ በቃ ደስተኛ ሆንኩ፤ ዛሬም መጠሪያ ስሜ ሆነ” ትላለች::
በወቅቱ ብሔራዊ ቲያትር ቤት በጊዜያዊ ሠራተኝነት በ60 ብር ደመወዝ ቀጠራት:: ነገር ግን አሁን ለእኛ ልትገልጽልን ባልፈለገችው ምክንያት ከስድስት ወራት የሥራ ቆይታ በኋላ ተቀነሰች:: ለሥራው ከፍ ያለ ጉጉት የነበራት በመሆኑ መቀነሷ እጅግ ቢያሳዝናትም ተስፋ ግን አልቆረጠችም:: ከምንም በላይ ደግሞ ሎሚ ተራተራን ስትዘፈን የወደዷት ባለሙያዎች ሌሎች እድሎችን እንድታገኝ አመቻቹላት፤ በዚህም ዶክተር ተስፋዬ አበበ ጋር ምሥራቅ በረኛ ፖሊስ እንድትገባ ሆነና ኑሮዋን ከአዲስ አበባ ወደሐረር አደረገች::
ሐረርና ሎሚ ተራተራ
በሥራ አጋጣሚ የሄደችባት የሐረር ከተማ በፍጹም ፍቅርና አክብሮት ነበር የተቀበለቻት:: የሐረርን ሕዝብ ፍቅር አብሮ የመብላት የመተዛዘን ብሎም አብሮ የማደግ ፍላጎቱን ተናግራ አትጠግብም::
” ….ሐረር ከትወልድ መንደሬ የበለጠ የምወደው ብዙ የእድሜዬን ክፍልም የኖርኩበት በርካታ ወዳጆችን ያፈራሁበት፤ የተዳርኩበት ፤የወለድኩበት፤ ብቻ ብዙ መልካም ነገሮችን ያየሁበት ከተማ ነውና መቼም ቢሆን ከልቤ አይጠፋም” በማለት ትገልጸዋለች::
ሎሚ ተራተራ ሐረር ፖሊሲ በሲቪል የተቀጠረች ቢሆንም ወዲያው ወደሚሊተሪ ይዙሩ በመባሉ በቶሎ ነበር ወታደር የሆነችው:: ከሁሉም በላይ ደግሞ ወቅቱ ሶማሌ ሀገራችንን የወረረችበት ጊዜ ነበርና እነ ሎሚን ጨምሮ ሁሉም ሀገሬው ራሱንና ሀገሩን ከጠላት ለመከላከል ወታደር መሆንም የውዴታ ግዴታው ነበር:: ሎሚ ይህም ሁኔታ ቢሆን ለእሷ አስደሳች ነበር፤ ከሀገር ከወገን ከዳር ድንበር በላይ ምን አለ ብላ የወሰደቻትን መጠነኛ የውትድርና ሥልጠና አጋዥ አድርጋ ከሠራዊቱ
ጋር በሄደበት እየሄደች፤ በሙዚቃ ሥራዋ እያበረታታች አስፈላጊም ሲሆን ውጊያ ውስጥ ገብታ ዘራፍ ብላ እየተዋጋች ጀግንነቷን ያስመሰከረች እንስት ናት::
“…..በወቅቱ አሁንም ድረስ በጣም የሚያስደስተኝ ነገር እንኳን ወታደሩ ጋር መላው ሕዝቡ ጋር ለእኔ የሚል ወይም ሌብነት የሚባል ነገር አለመኖሩ ነው:: ሙስናማ ስሙም አይታወቅም :: በጣም የሚገርመው ነገር ሶማሌ ጅግጅጋን አስለቅቃ ወደሐረር ስትመጣ ሁላችሁም ራሳችሁን አድኑ ተብሎ የምንችለውን ሁሉ ስናደርግ እኔና አንድ ሌላ ድምፃዊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሄደን በጆንያ ገንዝብ አውጥተን መኪና ላይ ሲጫን እንድንጠብቅ ታዘዝን:: በጣም የሚገርመው ወቅቱ የግርግር ቢሆንም እኛ ጠባቂዎቹ ሆንን የባንክ ቤቱ ሠራተኞች ፍጹም የሀገራቸውን አደራ ለመዝረፍ ሀሳቡ እንኳን አልነበራቸውም:: ሌብነት የሚባል ነገር የለም፤ አደራን በተባለው ቦታና ጊዜ ለማስረከብ ብቻ ነው ሩጫው:: እና እኛም የተጣለብንን ኃላፊነት በአግባቡ ተወጥተናል” በማለት ትናገራለች::
እነ ሎሚና ሌሎች የሠራዊቱ አርቲስቶች በወቅቱ ሶማሌን ድባቅ ለመምታት እየተንቀሳቀሰ ለነበረው ሠራዊት ደጀን ሆነው በሄዱበት ሁሉ ሄደዋል፤
……የሀገሬ ጎበዝ ምን ወንዱ ብቻ
ሴ ቷም ብትሆን የላትም አቻ …እያሉ እያዜሙ ተከትለው “ፈዲስ” ገቡ :: ከዛም 34 ተኛው ፓራ ኮማንዶ እየዘፈነ መጣ:: ሁለቱም በአንድ ገጥመው ሶማሌን እያሯሯጡ ወደመጣችበት ሸኟት::
ሶማሌም በመጣችበት እግሯ ተሸኘች ሎሚና ጓደኞቿም በወታደር ቤት የሙዚቃ ሥራቸውን እየሠሩ ኑሮን ቀጠሉ:: ሎሚም ከምትወደው የሐረር ሕዝብ ጋር እየኖረች ነው:: የዳሯት የኳላት የሐረር ጓደኞቿ ናቸው::
“…….ሐረሮች ጀግኖች፣ ባለሙያዎች፣ ለሰው አሳቢዎች፣ አብሮ መብላት የሚያውቁ፣ የእምነት፣ የብሔር ልዩነትን የሚጸየፉ በጠቅላላው ሰውን ሰው በመሆኑ ብቻ የሚያከብሩና አብረው መኖርን ቀለል አድርገው የሚያዩ ምርጥ ሕዝቦች ናቸው” በማለት ትገልጻቸዋለች::
ሎሚ ትዳር ከመያዟ በፊት ጓደኛ ነበራት አገባዋለሁ ብላ አስባለች፤ ነገር ግን የእህል ውሃ ጉዳይ ሆኖ ፍጹም ባልገመተችው ይሆናልም ብላ ባላሰበችው መልኩ የልጇን አባት ባለቤቷን ተዋወቀች፤ ተዋውቃም አልቀረች አግብታው የልጅ እናት አደረጋት:: ሎሚ ሁኔታውን ስታስታውሰው በጣም ትገረማለች:: ጭው ብላም በሀሳብ ወደኋላ ትመለሳለች ፊቷ ላይ ኃዘን ይነበባል::
“………. ያገባሁት በጣም ትልቅ ወታደር፤ በጣም የሚፈራ እሱ በተቀመጠበት ቡና ቤት ሌሎች ለመግባት የሚሳቀቁለት አይነት ሰው ነበር:: መጀመሪያም ለትዳር ሲጠይቀኝ እምቢ ብዬ ነበር፤ ኋላ ላይ ግን በግድም በውድም ተስማምቼ ወደ ትዳር ከገባሁ በኋላ ትዳሬ በጣም የጣፈጠ ያማረ ሆነ፤” በማለት ትገልጻለች::
ሎሚ ከትዳሯ አንድ ልጅ ወልዳለች፤ የእህቷን ልጅም እንደራሷ ልጅ አድርጋ አሳድጋለች:: ባለቤቷ ትልቅ የጦር መሪ ነበርና በዋለበት ግዳጅ ሁሉ ድል የእሱ ናት፤ በዚህም ምክንያት ከትዳሩ ጋር አብሮ የመቆየት እድልን አላገኘም:: ወዲያውም በግዳጅ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ተላከ እሷም አንዳንድ ቦታዎች ላይ ብታገኘውም ለመጨረሻ ግዳጅ የተላከበት ቦታ ላይ ግን ማግኘት አልቻለችም::
“………ባለቤቴ ከውትድርና ብቃቱ ባሻገር ጦር ሠራዊቱን ወክሎ መረብ ኳስ (ቫሊቮል) ይጫወት ነበር፤ በዚህም ቀብሪደሐር ላይ ለውድድር እመጣለሁ እና እንገናኛለን ብሎኝ እየጠበኩት ሳለሁ የወታደራዊው ደርግ መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ኤርትራ ተከባለችና ግዳጅ ሂዱ በማለታቸው በዛው ሄደ፤ እኔም ከዛ በኋላ ተስፋ ቆረጥኩ” በማለት ልብ በሚሰብር ኃዘን ሁኔታውን ታስታውሳለች::
ሎሚና ሌሎች ጓደኞቿ እንዲሁም መላው የደርግ ሠራዊት የመንግሥት ለውጡን ተከትሎ በተፈጠረው መበተን ኑሯቸው አስከፊ ደረጃ ላይ ደረሰ:: ሎሚም ባለቤቷ ያለበትን ሁኔታ አታውቅም ልጅ ይዛለች ደመወዝ የለም፤ ሥራ የለም ብቻ ነገሩ ሁሉ ተገለባብጧል፤ ይህንን ሕይወት አይታው አታውቅም ምን እንደምታደርግ ግራ ገባት የመጨረሻ ውሳኔዋ ወደማያውቀኝ ሀገር ማለትም አዲስ አበባ ገብቼ ለምኜ ልጄን ላሳደግ የሚል ሆነና ቤት ንብረቷን ጥላ ለእሷና ለልጇ የሚለብሱትን ይዛ አዲስ አበባ ገባች::
አዲስ አበባ ላይ ከመጣች በኋላ ልደታ አካባቢ ባለችው እስከ አሁንም በምትጠለልባት አራት በአራት ቤት ውስጥ ከአንድ ወንድምና እህቷ እንዲሁም ከአባቷ ጋር ልጅ ይዛ ተጨመረችባቸው:: ይህ ኑሮ ደግሞ ለሁሉም አልተመቸም እንደልብ እንኳን እግር ዘርግቶ መተኛትን አላስቻለም:: ከሁሉም በላይ ደግሞ የእሷ ልጅ ባጋጠመው ድንገተኛ ሕመም እንደልቡ መንቀሳቀስ መውጣት መግባት አለመቻሉ ኑሮን የበለጠ አስከፊ አደረገው ::
የወደቀን ዛፍ ምሳር ይበዛበታል! እንዲሉ ሎሚ በመንግሥት ለውጥ ምክንያት ያጋጠማት መፈናቀል ብዙ ነገሮችን አሳጥቷታል፤ ከምንም በላይ የጣመ የጣፈጠ ትዳሯን አፍርሶባታል፤ “…….አንዳንድ ጊዜ ችግር ሲመጣ ይደራረባል፤ እኔና ባለቤቴም ተደራራቢ ችግር ነው የገጠመን፤ ለእናት ሀገራችን ብዙ ዋጋ የከፈልን ብሆንም መጨረሻችን ግን አላማረም ፤ በተለይ ባለቤቴ ቆስሎ ከግዳጅ መጥቶ አዲስ አበባ ሜዳ ላይ ተኝቶ ነው ያገኘሁት፤ ከሐረር ይዤው የመጣሁትን የሚሊተሪ ብርድ ልብስ ለሁለት ተካፍለን ደጋጎች የሚሰጡኝን ገንዘብ ይዤ 15 ብር ቤት ተከራይቼ ነበር ያስቀመጥኩት፤ ነገር ግን በእስትንፋሱ መጨረሻ ላይ ከልደታ የሺ ደበሌ የሚባለው ሰፈር መሄጃ የትራንስፖርት 5 ብር አጥቼ ባለቤቴን ቆሜ ሳልቀብረው ቀረሁ” በማለት አስከፊውን የችግሯን ጅማሮ ትገልጻለች::
ሎሚ የደረሰባት ችግር ከባድ ነው:: ከዛም አልፎ ማንም ከጎኗ የሌላት እና ይህንን በዚህ አድርጊው፤ በሙያሽ ይህንን ብትሠሪ ብሎ የሚያማክራት አንድም ሰው ባይኖራትም በተለይም የሙዚቃ ሙያዋን ለመቀጠል ብዙ ጥረቶችን አድርጋለች ስኬታማነቱ ላይ ግቡን ባይመታም ::
መልካሙ የሚባል የሙዚቃ ማቀናበሪያ ስቱዲዮ ያለው ግለሰብ ታሪኳን የሚያውቅ በመሆኑ “እኮራበታለሁ” የሚል ሥራ ሠርቶላት “ጋራ ዩቱብ” ለሕዝብ ጆሮ አድርሶላታል:: እንቁጣጣሽ የሚል ሙዚቃንም እንድትሠራ አግዟታል:: በቀጣይም ክሊፕ እንደሚሠራላት ቃል የገቡላት መኖራቸውንም ትናገራለች::
ሎሚ ከዛሬ 26 ዓመት በፊት ሙሉ የካሴት ሥራ ሠርታ ነበር፤ ነገር ግን ሥራዋ ተጠናቆ ፖስተሩ ሲለጠፍ ሙዚቃ ቤቶች ፈረሱ፤ ይህ ብቻ አይደለም በወቅቱ የአርቲስት አስቴር አወቀ ዘፈን ወጣና የእሷ ሙዚቃ ተዋጠ በዛም የትኛውም ሥራ ሳይሰማ ቀረ:: ሎሚ በዚህ ሁኔታ በጣም ልቧ ተሰብሮ ይህንን ትላለች:: “……. በወቅቱ አጋጣሚው ጥሩ አልነበረም ፤ እኔ ለሁሉም ሚዲያዎች እየዞርኩ ሙዚቃው በሬዲዮ እንኳን እንዲሰማ ሰጥቻቸው ነበር፤ ነገር ግን ሚዲያው ያዳላል፤ አንዳንድ ጊዜ መንገዱ ራሱ ምን እንደሆነ ለማወቅ ይቸግራል:: ቀኑን ሙሉ ሬዲዮም ሆነ ቴሌቪዥን ብትሰሚ የአንድ ሰው ሙዚቃ ከአምስትና ስድስት ጊዜ በላይ ይለቀቃል:: እኔ የራሴን ዘፈን በአንዱም ጣቢያ ላይ አዳምጬው አላውቅም:: እናም እንደእኔ ግምገማ ለሕሊናው የሚሠራ ሰው የለም:: ይህ አካሄድ ደግሞ እኔን ጨምሮ ብዙዎችን ቀብሮ ቀርቷል፤ በጣም ያሳዝናል” በማለት ቅሬታዋን ትገልጻለች::
ሎሚ የባሕል ዘፋኝ እንደመሆኗ በተለይም በፈንድቃ የባሕል ቤት ሥራዎችን አልፎ አልፎ ትሠራ ነበር፤ ነገር ግን ዘላቂ ባለመሆኑ አሁን ላይ አቁማለች:: ውለታዋንና ያለችበትን ሁኔታ ተገንዝቦ ኑሮ እንዳይከብዳት ያግዛት የነበረው ሙዚቀኛ ማዲንጎ አፈወርቅ ነበር:: ከእርዳታውም ባሻገር የጦር ሜዳ ዘፈኖቿን በካሴት ደረጃ ለመሥራት እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ነው ሞት የቀደመው:: አርቲስት ዓለማየሁ እሸቴም በተመሳሳይ ሰዎችን እያስተባበረ ይረዳት ነበር:: አሁን ሁሉም የሉም፤ ሎሚ ግን ከችግሮቿ ጋር አብራ አለች::
ሕዝቤ አላወቀኝም፤ መንግሥት ግን ወቀሳ ይገባዋል የምትለው ሎሚ፤ የቀድሞ ሠራዊት ለሀገሩ የተዋደቀ ነው:: ምናልባት መጥፎ ሥራም ሠርቶ ይሆናል ግን ደግሞ ጥሩም መጥፎም የሆነው ለሀገር ነውና ሁሉንም በልኩ አይቶ ማስቀመጥ ይገባል:: የሆነውና እየሆነው ያለው ነገር ከባድ ብሎም አሳፋሪ ነው::
አስከፊው የሎሚ አሁናዊ ኑሮ
ልጄ ለብዙ ልጆች ምሳሌ ነበር፤ የሚያውቁኝ ሁሉ ልጅ ከተወለደ እንደሎሚ ልጅ ነበር የሚሉት፤ በጣም ጨዋ በትምህርቱ ጎበዝ ነበር፤ ምን ዋጋ አለው በስተመጨረሻ በማናውቀው ምክንያት ተበላሸብኝ:: እኔም በደጄ እንኳን ሻይ አፍልቼ አልሸጥ ነገር ቤቴ እንኳን ለንግድ እግር ዘርግቶ ለመተኛት አይበቃም:: ቀኑን ሙሉ አእምሮዬ ሲረበሽ ይውላል ፤ አንዳንድ ጊዜ መኖሬ ያስጠላኛል፤ መለስ ብዬ ሳስብ ደግሞ ልጆቼስ እላለሁ::
እኔ አሁን የምመኘው ሰፋ ባለ ቤት ውስጥ አልጋ ላይ እንደልቤ ዧ ብዬ ተኝቼ በማግስቱ መሞትን ነው:: የሚገርምሽ ከዛሬ 21 ዓመት በፊት ጀምሮ ቤት እንዳገኝ በተለያዩ አካላት የተጻፈልኝ ደብዳቤ አለ:: ግን እህ ብሎ የሚሰማ ሥራ አስፈጻሚ ስለሌለ እስከ አሁን ተፈጻሚ አልሆነም በማለት ከፍ ባለ ኃዘን ትናገራለች::
ሎሚ በዚህን ያህል ደረጃ ኑሮ የከበዳት፤ ጓዳዋ ባዶ የሆነና ጎኗን ማሳረፊያ አይኑራት እንጂ በአቅሟ የበርካታ ድሆችም መጠለያ ነች:: እሷ ቤት መጥቶ ያለውን በልቶ ቡና ጠጥቶ ተስተናግዶ ባለችው አነስተኛ ቦታ ላይ አርፎ የሚሄድ አልፎ ሂያጅ ብዙ ነው በዚህም በጣም ደስተኛ ናት::
“…….እኔ የማውቀውም የማላውቀውም ብቻ ማረፊያ ያጣ ሁሉ ይመጣል፤ እውነት ለመናገር ያለ እንግዳ አድሬ አላውቅም:: የሚተኙበት ሳጣ ግን በጣም እናደድና ፈጣሪዬንም ለምንድነው እንደዚህ የምትፈትነኝ እለዋለሁ:: አንዳንድ ጊዜ ሰው ስለሚበዛብኝ ራስሽን ሁሉ አጥፊ አጥፊ የሚለኝ ጊዜ አለ:: ነገር ግን ቤቴ የድሃ ቤት ነው” በማለት ትናገራለች::
ሎሚ ዛሬ ላይ የምትፈልገው በሙያዋ ሠርቶ መኖርን ነው:: ለእኛም እንዳስደመጠችን ድምጿ ገና ብዙ የሚያሠራት ነው:: ስለዚህ በሙያው ያላችሁ ይህችን የሀገር ባለውለታ ሠርታ ኑሮዋን የምትደጉምበትን መንገድ ታመቻቻላችሁ ብለን እናስባለን:: በሌላ በኩልም በምትኖርበት ወረዳም ሆነ ሌሎች ወረዳዎች ወጥታ ወርዳ የሀገሯን ዳር ድንበር ላስከበረች አሁን ደግሞ ከሕመምተኛ ልጅ ጋር በችግር እየተሰቃየች ያለችን ምስኪን ወታደር ማረፊያ በመስጠት ትተባበራላችሁ ብለንም ተስፋ እናደርጋለን:: ለሚደረገው ትብብር ሁሉ እያመሰገንን ሎሚን ማግኘት የሚፈልግ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልን መጠየቅ እንደሚችልም ለመግለጽ እንወዳለን::
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25 ቀን 2016 ዓ.ም
እፀገነት አክሊሉ