ተስፋ መቁረጥ ለምን?

ልክ የዛሬ ዓመት አንድ ወጣት የዚህ ዓለም ኑሮ እንደመረረውና በራሱ ተስፋ እንቆረጠ ተናግሮ ይህችን ምድር በራሱ ፍቃድ ተሰናብቷል፡፡ በቅርቡ ደግሞ በተመሳሳይ አንዲት ወጣት ‹‹ዓለማዊ ኑሮ በቃኝ፤ ያኛው ዓለም ይሻለኛል እናንተም ወደእኔ ኑ›› ብላ ለሌሎችም የሞት ግብዣ አቅርባ ራሷን አጥፍታለች፡፡ ሌሎችም ወጣቶች በእንዲህ ዓይነቱ መንገድ ገና ብዙ መሥራት በሚችሉበት እድሜ ራሳቸውን አጥፍተዋል፡፡

ድሮ ድሮ በኢትዮጵያ ራስን ማጥፋት እንደ ትልቅ ነውር የሚቆጠር ተግባር ነበር፡፡ እንዲህ ታስቦበትና አስቀድሞ ለመሞት ተናዞ የሚደረግም አልነበረም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ራስን ማጥፋት በኢትዮጵያ ብዙም እንግዳ የሆነ ነገር አይደለም፡፡ ይሁንና አሁን አሁን እንዲህ ዓይነቱ ራስን የማጥፋት ተግባር ባልተለመደ መልኩ በኢትዮጵያ እየጨመረ መጥቷል። በዚህ መልኩ የሚከወነው ራስን የማጥፋት ተግባር ታዲያ በብዛት በወጣቶች ዘንድ እየተስተዋለ ነው፤ ድርጊቱ አንዱ ሌላኛውን እየሳበም ይገኛል፡፡

ሰው ራሱን ለምን አጠፋ ብሎ እንዲሁ በደፈናው መኮነን አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ራሱን ለማጥፋቱ በርካታ ምክንያቶች ይኖሩታል፡፡ ግን ደግሞ ራስን ከማጥፋት የሚገኘ ነገር የለም፡፡ ከመጥፋት መኖር ይሻላል፡፡ ሰው ራሱን ሲያጠፋ ‹‹የሞተ ተጎዳ›› የሚባለው ተረት ለእርሱ ብቻ አይሰራም፡፡ እርሱ በሕይወት እያለ የእርሱን መኖርና ድጋፍ የሚሹ አሉና ሞቱ ሌሎችንም ይጎዳል፡፡ ስለዚህ በአንድ ጊዜ ተስፋ ቆርጦ ለመሞት መወሰን እጅግ ይከብዳል፡፡

ዘመናት በተቀያየሩ ቁጥር የሕዝብ አኗኗር ሁኔታ፣ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ገጽታም አብሮ ይቀየራል፡፡ በተለይ ደግሞ በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን ነገሮች በሰከንዶች ውስጥ ይቀየራሉ፡፡ በርግጥ ያለፈውም የአሁኑም ጊዜ አንድ ዓይነት ቢሆንም የአሁኑ ጊዜ በፍጥነት እየበረረ እንደሆነ ብዙዎች ይሰማቸዋል። ይህም ሰዎች ከሥራ ባለፈ በተለያዩ የግልና የጋራ ጉዳዮች ላይ መወጠርና ጊዜ ከማጣት የመነጨ ነው፡፡ በዚህ የሩጫ ዘመን ታዲያ አንዱን ሲያገኙ ሌላ ማጣት ይኖራል፡፡ አንዱን ሲሳኩ በሌላ በኩል መውደቅ አለ፡፡ አንዱን ሲጨብጡ በዛኛው በኩል ሌላኛውን መልቀቅ ያጋጥማል።

ይህ በሕይወት ኡደት ውስጥ የሚያጋጥምና በሰዎች ተፈጥሯዊ ባህሪ ውስጥ የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ እንግዲህ እዚህ ጋር ነው የሰው ልጅ መከራው ሲበዛበት፣ ጥረቱ መና ሲቀር፣ ያሰበው ሳይሳካ ሲቀር፣ ልፋቱ ከንቱ ሲሆን ተስፋ ቆርጦ ራሱን ለማጥፋት የሚነሳው፡፡ ከራሱ ጋር ሲጋጭና መስማማት ሲያቅተው ነው የሞትን መንገድ የሚመርጠው፡፡ ብሎ ብሎ አልሆንለት ሲለው፤ ነገም ሌላ ቀን ነው እና ከዛሬ ነገ ይሻላል ብሎ ሌላ ሙከራ ማድረግ ሲያቅተው ነው ሞት አማራጭ መስሎ የሚታየው፡፡

ዛሬ ላይ የፖለቲካ ውጥንቅጥ፣ የኑሮ ውድነት፣ በሽታ፣ ጦርነት፣ ስደት፣ መፈናቀልና ሌሎችም ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች በምድራችን እየበዙ መጥተዋል። የሕይወት ትግሉ በርትቷል፡፡ የኑሮ ውጣ ውረዱ አይሏል፡፡ የእርስ በርስ ፉክክሩና ፍትጊያው ጨምሯል። ገንዘብ አልበረክት ብሏል፡፡ ፍቅርም እንደዛው፡፡ እነዚህና መሰል ስንክሳሮች ብዙዎችን ተስፋ እያስቆረጡ ነው፡፡ ከመንገድም እያስቀሩ ነው፡፡ ብዙዎች ሞትን እንደመጨረሻ አማራጭ እንዲወስዱ እያስገደደም ይገኛል፡፡

አንዳንዴ የትግላችን፣ የጥረታችን፣ የልፋታችን ውጤት መና የቀረ የሚመስልበት ጊዜ አለ፡፡ ውጥናችን ውሃ አልቋጥር፣ ጠብ አልል ሲለን፣ መንገዱ ሁሉ ረዥም፣ በሮች ሁሉ ዝግ፣ ጩኸቱ ሁሉ ሰሚ አልባ ሲመስለን በመጨረሻ የምንወስደው መፍትሄ ዓለምን ሁሉ መተውና መሸነፍ ይሆናል፡፡ ከዚህ በኋላ አበቃ ማለት እንጀምራለን። እንኳን እኛ ቀርቶ ሌሎች እንኳን እንዳይበረቱ ‹‹ባክህ እኛም ብለነው ብለነው አቅቶን ነው›› እያልን ተስፋ እናስቆርጣቸዋለን፡፡ የተስፋ መቁረጥ ሕመማችንን ሌሎች ላይም አጋብተን አጥፍተን መጥፋት እንፈልጋለን፡፡

ነገር ግን ሰው መልፋት፣ መትጋት፣ መታገልና መሮጥ ያለበት የት ነው? ሰው ተስፋ መቁረጥ ያለበት የት ደረጃ ሲደርስ ነው? የመንገዱ ማለቂያው የት ነው? ውጤቱን ዛሬ ያላየነው ነገ ሁሉ ውጤት አልባ ሆኖ ሊቆጠር ይችላልን? በታሰበው ጊዜ ያልተደረሰበት ነገር ሁሉ ሊደረስበት የማይችል ነገር ነው ማለት ነው? መንገዱስ እኛ የያዝነው ብቻ ነው? በሌላስ መንገድ ሊሞከር አይቻልምን? ለመሆኑ ከማቆምና ከመቀጠል የትኛው ይመረጣል? ከማቆም ምን ይገኛል? የሚሉትና ሌሎች መሰል ጥያቄዎችን መመለስ ይገባል፡፡

ተስፋ ቆርጦ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ከመድረስ በፊት ተስፋ ያስቀረጠንን ምክንያት ማወቅና በሚገባ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ተስፋ ያስቀረጠንን ጉዳይ በሚገባ ካወቅንና ከመረመርን ደግሞ ይህን ተስፋ ያስቀረጠንን ምክንያት እንዴት አድርገን መቀልበስና በሌላ አማራጭ መተካት እንደምንችል መንገዶችን መለየት ይገባናል፡፡ ሌሎች ወደ ተስፋ የሚመልሱ መንገዶች መልካም ሆነው ካገኘናቸው እሰየው ብለን ወደፊት መቀጠል ነው፡፡ ሆኖም አሁንም የመረጥናቸው መንገዶች ዳግም ተስፋ የሚያስቆርጡ ከሆኑ እንደገና ሌላ መንገድ መፈለግ እንጂ ተስፋ ቆርጦ ያልሆነ ውሳኔ መወሰን ተገቢ አይደለም፡፡

ከተስፋ መቁረጥ በቀር የሚጓዝ ሰው ጊዜው ይረዝም ይሆናል እንጂ አንድ ቀን የሚፈልገው ቦታ ይደርሳል። የቆመ ሰው ግን እንኳንስ ወደሚፈልግበት ለመሄድ ይቅርና ወደተነሳበት ቦታም ተመልሶ አይደርስም፡፡ የሚታገል ሰው አንድ ቀን ያሸንፋል። የቆመ ሰው ግን ሳይማረክ እጁን ሰጥቷል፡፡ ደጋግሞ የሚያንኳኳ ሰው ከተገኙት ሰዎች ውስጥ አንዱን መቀስቀሱ አይቀርም፡፡ ማንኳኳት ያቆመ ግን እንኳንስ ሊቀሰቅስ ቀርቶ እራሱም የተኛ ነው፡፡ አስቀድሞ በራሱ ላይ ሞት ፈርዷል፡፡

የሚሄድ መኪና ጋራዥ ይደርሳል፡፡ የቆመ መኪና ግን ባለበት ይወላልቃል፡፡ ለማሸነፍ ትልቁ መፍትሔ አቋምን መቀየር ሳይሆን መንገድን መቀየር ነው። የተለያዩ ነገሮችን መሞካከር ሳይሆን አንድን ነገር በተለያዩ መንገዶች መሞከር ነው፡፡ የተለያዩ ነገሮችን ማየት ሳይሆን አንድን ነገር በተለየ እይታ መመልከት መቻል ነው፡፡ ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን በውሳኔ ጊዜ መቁረጥ መቻል ነው፡፡ ራስን ማጥፋት ትልቁ የስንፍና ውጤት ነው፡፡ እናም ወዳጄ! የምታገኘውን ሞት ከመመኘት የማታገኘውን ሕይወት በሚገባ መኖር መቻል አለብህ፡፡

ከተሸነፉት መማር ያለብን እኮ ለምን ተሸነፉ የሚለውን እንጂ የጥረት መጨረሻው መሸነፍ አይደለም። ሽንፈት እኮ ትምህርት አያስፈልገውም። ሽንፈት እኮ ልምድ አያስፈልገውም፡፡ ሽንፈት እኮ እውቀት አያስፈልገውም። ሽንፈት እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ብቻ ይበቃዋል፡፡ ለሽንፈት ምሳሌ መጥቀስ አያስፈልግም፡፡ ሽንፈት ማለት በቀላሉ የሚደርስበት ነገር ነው፡፡ ሳይለፉ የሚያገኙት ነገር ነው፡፡ ምሳሌ፣ አርዓያ፣ ልምድ፣ እውቀት፣ ጥበብ የሚያስፈልገው ድል ብቻ ነው፡፡ ስኬት ብቻ ነው፡፡ እርሱ በቀላሉ ስለማይገኝ ካገኙት ሰው ልምድና ጥበብ መቅሰም ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ማድረግ ሲቻል ነው ከተሸናፊነት ወደ አሸናፊነት መሸጋገር የሚቻለው፡፡

ብርቱ ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች በጥረታቸው ውስጥ ደስታን ያገኛሉ፡፡ ጥረት የሚያደርጉና አስቀድመው የተሸነፉ ሰዎች ግን ሁሌም በሀዘን ውስጥ ናቸው፡፡ ጥረት እኮ ባይሳካ እንኳን ደስታን ያጎናፅፋል፡፡ ከቁዘማና ከድብርት ነፃ ያወጣል፡፡ የሚጥር ስለነገ ያቆመ ስለትላንት ያስባል፡፡ የሚጥር ስለኑሮው ያቆመ ስለሞት ያስባል። በሩጫ ዓለም በመጀመሪያው ዙሮች ቀዳሚውም መጨረሻውም እኩል ናቸው፡፡ እንደውም አንዳንዴ ተሸናፊው ከአሸናፊው የተሻለ መስሎ የሚታይበት ጊዜ አለ፡፡ ግን ደወል ይደወላል፡፡ ያን ጊዜ አሸናፊውም ተሸናፊውም ይለያል፡፡

የሌላ ሰው እገዛ ውጤት የሚያመጣው የራስ ጥረት ካለ ብቻ ነው፡፡ አፉን ያልከፈተ ሰው ማጉረስ፤ ላልተነፈሰውም ሰው ጉርሻ(ቦነስ) መስጠት አይቻልም። ከመቆም ምንም አይገኝም፡፡ በቃኝ ብሎ ተስፋ ከመቁረጥ አንዳች ትርፍ የለም፡፡ ነገር ግን በጥረት ውስጥ ደስታና ጥንካሬ አለ፡፡ በጥረት ውስጥ ተስፋና አሸናፊነት አለ። ትጋት ከቁዘማና ከድብርት ነፃ ያወጣል። አስተውል! የሚጥር ስለነገ ያቆመ ስለትላንት ያስባል፡፡ የሚጥር ስለኑሮው ያቆመ ስለሞት ያስባል፡፡

ዛሬ ላይ የሚታዩ ነገሮች ሰዎችን ለጊዜው ተስፋ ሊያስቆርጡ ይችላሉ፡፡ የኑሮው ሁኔታ፣ ውጣውረዱ፣ እንግልቱ ሊያሰለች ይችላል፡፡ እዛም እዚም የሚደመጡ የሰዎች ሞት፣ ስደት፣ መፈናቀልና ሰቆቃ ያሳምማሉ፡፡ ሰላምና መረጋጋጥ መጥፋቱም እጅግ ተስፋ ሊያስቆርጥ ይችላል፡፡ መከራና ግፉም ያስመርራል፡፡ ነገር ግን ከዛሬ ነገ ይሻላልና የነገውን ጥሩ ለማድረግ ዛሬ ላይ ተስፋ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ተስፋ ከመቁረጥ ተስፋ ማድረግ ይሻላልና፡፡

እናም ወዳጄ ብትወድቅ ብትከፋም ያለኸውና የምትኖርበት እዚቹ ምድር ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ተፍጨርጨርባት፣ ሥራባት፣ ሌላውን ሳታሰናብት አንተ አትሰናበት፡፡ እስከመጨረሻው ጣር፡፡ መቼም መብቴ ብለህ ወደህ መርጠህ ወደዚች ምድር አልመጣህም፡፡ ምድሯም አንተን ለማኖር ምንም አልጠበባትም፡፡ ስለዚህ ወደዚች ምድር እስከመጣህ ድረስ የመጨረሻውን የሞት ፅዋ እስክትጎነጭ ድረስ በምድሯ ላይ ሥራ፡፡

ተስፋ ለቆረጡ ሰዎች መድኃኒት ይሆን ዘንድ ጆኒ ራጋ፣ ዘሪቱ ከበደና አብነት አጎናፍር እንዲህ ሲሉ አቀንቅነዋል፤ አንተም ቢሆን ግድ የለም ተስፋ መቁረጡን ተወውና እስቲ ይህ ሙዚቃ አዳምጠው…….

አብነት አጎናፍር፡- ብትወድ ብትከፋህ የያዘችህ ቤትህ ዓለም

ሳታሰናበት መሰናበት በራስ የለም

መች መብቴን ብለህ ወደህ መርጠህ መጣህባት

መብትህ ነው ብላለች አንተን ማኖር መች ጠበባት

ዘሪቱ ከበደ፡- ኖሮ ሳይቀምሳት ማን ኑርባት ሞክር አለህ

እንዳንተ ሆኖ ኖሮም አይቶ እያት አለህ

ነፍሴን ጠላኋት ብለህ የውሸት አትካዳት

ለሌላው ሁንና ኖረህ የእውነት አትውደዳት

ጆኒ ራጋ፡- ግድ ነው ኑሮን መላመድ

ከኛ ጋር ሆነሃል ዘመድ

ላንተ የሚሆን መቼ አንሶን ቦታ

መሄድክን አናይ በቸልታ

መኖርህን ሌሎች ይሻሉ ይፈልጋሉ

በሕይወት እስካለህ ድረስ ይበረታሉ

የኔ መኖር ነው ላንተ መኖር ያንተም ለኔ

ለሕይወት አብረን እንዘምር ቁም ከጎኔ

በጋራ፡- ኑር ባታምንም ላንተ ባይመስልም

ለከንቱ አልተፈጠርክም

የዛሬው ሕይወትህ ባይሞቅም

ነገም ካንተ ውጭ አይደምቅም

ድፈር ክረም ኑር በሕይወት

ለሌሎች አቆያት

ፈሪ ነው የሰው ያልሞገተው

ሳይገሉት ቀድሞ የሚሞተው …….

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት  24/2016

Recommended For You