ፕሮክሲማ

ሁሌ ጠዋት ሥራ ስገባ ብቻዬን መሆን የምመርጥ ሰው ነኝ። ቤቴ ስገባም ዝምታዬን ከተለማመዱ ሚስትና ልጆቼ ጋር ሕይወቴን እቀጥላለሁ። ከሚስቴ ሌላ የማውቃት ሴት የለችም። እናቴን በልጅነቴ ስለቀበርኩ ወደፊትና ወደኋላ የምለው የለኝም። እርግጥ ድምጻቸውን በወር አንድ ጊዜ የምሰማው ከሀገር ውጭ የሚኖሩ ሁለት እህቶች አሉ። ዝምታዬን ጥሰው እንደፈለጉ የሚያደርጉኝ እነሱ ናቸው።

በዚህ ግዴለሽነቴ ውስጥ የምቀርባት ፕሮክሲማን ብቻ ነው። ከእሷ ውጭ በሬን ደፍሮ የሚያንኳኳ የለም። ትመጣና በአንድ እጇ አንገቴን አቅፋ በተቀመጥኩበት ጺማም ጉንጬ ላይ ትስመኛለች። በዛ ጠዋት ፈገግታና ጠረኗን ቢሮዬ ውስጥ ትታው ስትሄድ ቀን ሙሉ እንዳስባት ሴራ እየሸረበችብኝ ነው የሚመስለኝ። ጠረኗ ጠዋት የገባ ማታም አይወጣም በነጋታው ቢሮዬን ስከፍት ያ ጠረን ነው እንዴት አደርክ ሲል የሚቀበለኝ። ቢሮ የገባች ቀን ቀኑን ሙሉ እሷን እሷን ስሸት እውላለሁ። ቢሮዬ ያለማቋረጥ አንድ ሴት ብቻ የተመላለሰችበት ቢሮ ነው። ፊት ልነሳት አልቻልኩም። ያን የተዘጋን ልብ የሚያነቃ ሴትነቷን አትድረስብኝ ማለት ፈራሁ።

ደብቶኝ ውሎ ከእሷ ወሬ በቀር የሚያነቃኝ የለም። ቢሮዬ መጥታ ጉንጬን ሳትስመኝ ቀርታ አታውቅም። እና ከለበስኩት ልብስ ጀምሮ የተመሳቀሉ የመሰሏትን የቢሮዬን እቃዎች ታስተካክልልኛለች። በሆዷ ‹ምን አይነቱ ዝርክርክ ነው..ለዚች አራት በአራት ለሆነች ቢሮው መሆን አቅቶት ነው..? የምትለኝ ይመስለኛል። ግን አትለኝም ፕሮክሲ እንዲህ ዓይነት ሴት አይደለችም። ማለት ያለባትን ፊት ለፊት የምትናገር የንጉስ ዓይነት ግርማ ያላት ናት። እውነት ነው ዝርክርክ ነኝ…ዝርክርክነቴን አፌን ሞልቼ የምናገረው ገመናዬ ነው። እንደዛ ባይሆን እማ ቤት ውስጥ ሚስቴ ቢሮ ደግሞ ፕሮክሲ እየተቀባበሉ የለበስኩትን ልብስ አያስተካክሉልኝም ነበር። ከፕሮክሲ መግባት በኋላ ቢሮዬ ሌላ መልክ ስትይዝ አያታለሁ። ምኑን ከምን እንዳደረገችው አላውቅም ብቻ ቢሮዬ ሌላ ውበት… ሌላ ደም ግባት ተጎናጽፋ አገኛታለሁ። ከዛ የቢሮዬ መስተካከል በኋላ ነው ምን ያክል ዝርክርክ እንደሆንኩ የማውቀው። ከዚህ በኋላ ነው አንድ እጇን ትከሻዬ ላይ ጣል አድርጋ..። ‹ቁርስ አልበላሁም..አታባላኝም? የምትለኝ።

ቁርስ የበላሁ ቢሆንም እንቢ አልላትም። ከወንበሬ እስክነሳ ጊዜ ሳትሰጠኝ ዝምታዬን ተከትላ ከወንበሬ ላይ ጎትታ ታስነሳኛለች። እጇን ትከሻዬ ላይ ጣል አድርጋ እየተወለካከፍን ከቢሮ እንወጣለን። ያለ ልማዴ በእሷ በኩል የተለማመድኳቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ቤት ውስጥ ለሚስቴ ከዚህ በፊት አድርጌያቸው የማላውቃቸውን እንግዳ ባህሪያት እያሳየኋት ብዙ ጊዜ በጥርጣሬ ዓይን አይታኝ ታውቃለች። ፕሮክሲማ ብዙ ነጻነት ያላት ሴት ናት። እኛ የምንሸማቀቅባቸው ነገሮች እሷ ጋ ቦታ የላቸውም። ምግብ ስንበላ ሁልጊዜ አንድ ቦታ አትበላም። ግን በድርጊቷ ውስጥ ምንም ዓይነት ራስ ወዳድነት እንደሌለ ሳስብ ተውኩት። ለነገሩ ብናደድስ ምን አመጣለሁ? ከፕሮክሲማ ጋር የተነካካ እንዳሻት እንድትሆን ከመተው ውጭ ሌላ ኃይል አይኖረውም። እሷ ለሌሎች የነጻነት ቦታ ናት። ማንም ምንም እንዲሆንባት ሰፊ መንገድ አላት። በነጻነቷ ውስጥ ጣልቃ ለሚገባ ግን ሁለተኛ እድል የላትም። የሳቋን ያክል የሚጨልም ሴትነት አላት።

ጥሩ መስሎ የታየን ነገር ለይቶ ማድነቅ ሌላው ከፕሮክሲ የለመድኩት ባህሪ ነው። በዚህ ባህሪዬ ብዙ ጊዜ ብያት የማላውቃትን ሚስቴን በአለባበሷ፣ በተቀባችው ሽቶ፣ በሰራችው ምግብ አድንቄያት አውቃለሁ። ታዲያ መልሷ ሁሌም አንድ ዓይነት ነው..‹እንዲህ ብለኸኝ እኮ አታውቅም..› የሚል። ያኔ ዓይኖቿ መዐት መጠራጠርን ተሸክመው ለረጅም ሰዓት ሲያጤኑኝ አያቸዋለሁ።

የሆነ ጠዋት ፕሮክሲ በሬን በርግዳ ገባች። እንደ እስከ ዛሬው አልሳመችኝም፣ የለበስኩትን አላስተካከለችልኝም፣ የቢሮዬን እቃዎች አልተመለከተችም። መጥታ አጠገቤ ቆመች..። በሽቶ ኩሬ ውስጥ የምትዋልል ይመስል ሰውነቷ ሁሉ ተጠምጠሙብኝ..ተጠምጠሙብኝ የሚል ስሜትን ይፈጥራል።

አንዳንዴ እንደምታብድ አውቃለሁ። ብዙ ጊዜ እንዲህ እንደ አሁኑ አብዳብኝ ታውቃለች። ቀና ብዬ ሳያት አኩርፋለች። እንዴት ላድርግ እኔ ደግሞ ማባበል አልችልም። ዝምታዋን ወርሼ ዝም አልኳት። ‹አንተ ዝም ትለኛለህ? ስትል ጀርባዬን ደለቀችው።› ታዲያ ምን ላድርግ ብላ ነው እብደትሽ ሲለቅሽ ታወሪኛለሽ ብዬ እኮ ነው አልኳት።

አንድ እጇን ትከሻዬ ላይ ጣል አድርጋ ጺማም ጉንጬን ሳመችው። የለበስኩትን ኮትና ከረባት እያስተካከለች ‹ሥራ ላቆም ነው? አለችኝ›። ልብ ድካም ወይም ደግሞ ከድንጋጤ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ችግር ቢኖርብኝ አልቆልኝ ነበር። በዛ ድንጋጤ የትም ዶክተር ጋ ሳልሄድ ጤነኛ መሆኔን አረጋገጥኩ። ነፍሴ ልቤ ባይዛት ኖሮ ተቆራርጠን ነበር። ለምን እንደሆነ እንጃ ከእሷ በላይ እኔ ነበርኩ በድን የሆንኩት። ፊቷ ላይ የትካዜ ፈንግል ሲጥለኝ አላወቀችም። ሳላውቀው ይቺ ልጅ ውስጤ እንደቀረች ገባኝ። ምንም እንዳልመሰለው ለማስመሰል ብዙ ጣርኩ..ትወና ከየት ይምጣ?

አቅም አሰባስቤ ‹ለምን? አልኳት። ወደውጭ ልሄድ ነው። አባቢ ካልመጣሽ እያለኝ ነው› አለችኝ ወደኩርፊያዋ በመመለስ። የባሰ አዘቅት ውስጥ ወደኩ። መኖሯ ግድ ያልሰጠኝ ነፍስ ልሄድ ነው ስትለኝ የምገባበት ስምጥ ጠፋኝ። ራሳችንን ማጽናናት የማንችልበት አጋጣሚ በሕይወት አንድ ቦታ ላይ አለ..ያ ቦታ ፕሮክሲ ያለችበት አሁን መሰለኝ። የኩርፊያዋን ሚስጢር አልደርስበት አልኩ።

‹እና ደስ ሊልሽ ይገባል እንጂ ለምንድነው ያኮረፍሽው..? ስል ጠየኳት።

ፊቷ ልውጥውጥ ሲል አየሁት። በዓይኖቿ ውስጥ በጥያቄዬ የተፈጠረ ሰይጣን ታየኝ። ‹ከእኔ መለየት ደስ ይልሀል? ረጋ ብላ አወራች።› እንደዛ ለማለት አይደለም…!

‹ነው እንጂ..! እንዳውም ደህና ሁን› ብላ ትታኝ ወደበሩ ስትፈጥን እንደአቦ ሸማኔ ተምዘግዝጌ ያዝኳት። እጇን ከእጄ ለማላቀቅ ትንሽ ታገለችኝ። ‹ምን ሆነሻል ፕሮክሲ! ተረጋጊ እንደዛ ለማለት ፈልጌ እኮ አይደለም..?

‹ልቀቀኝ! ምንም ብትል ግድ የለኝም የፈለከውን ተናግረሀል›

‹እረ ባክሽ..ላስከፋሽ ፈልጌ አይደለም..! ስል እቅፍ አደረኳት። ጉያዬ ውስጥ ሆና ተረጋጋች። ማቀፍ የፍቅር ክንፍ እንደሆነ ድሮ ባውቅም ኩርፊያ ማብረጃ እንደሆነ ግን አላውቅም ነበር። በፕሮክሲ መረጋጋትና መብረድ እቅፍ ጥሩ ኩርፊያ ማብረጃ እንደሆነ አንድ እውቀት ሸመትኩ። ይሄንን ድንገተኛ ግኝት ኩርፊያ በሚቀናት ሚስቴ ላይ ለመተግበር ቸኮልኩ።› ‹ያኮረፍኩት ከአንተ መለየት ስለከበደኝ ነው› ስትል አንጋጣ እያየች መለሰችልኝ።

ዝም አልኩኝ። አፍቅራኝ እንዳይደለ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ። ልጅና ሚስት እንዳለኝ እያወቀች እንዲህ ዓይነት ታሪክ ውስጥ እንደማትገባ በሚገባ አውቃለሁ። ፕሮክሲ ልቧ በኤልክትሮ መሳሪያ ቢፈተሸ ከፍቅርና ከመልካምነት ውጭ ምንም የማይገኝባት ሴት ናት። ከዛን ቀን በኋላ ከፕሮክሲ ጋር አልተገናኘንም።

ገላዬ ላይ በታተመ የስንብት ሽቶዋ ወደቤት ሄድኩ። ማታ ቤት ስገባ ጠረኔ የተቀየረባት ሚስቴ ዓይኗን ለነገር አጥባ እያየችኝ ‹ጋቫና ማነው የቀባህ? ስትል ጠየቀችኝ። ሚስቴ ዘመናዊ ሴት ናት። ሽቶና ፋሽን እንደምትወድ ምንም አትወድም። ቤታችንን ካጠበቡ እቃዎች ውስጥ ቀዳሚው የሚስቴ ሽቶና ልብሶች ናቸው። በየቀኑ የምትገዛቸው የፈረንሳይ ሽቶና የቱርክ ፋሽኖች የሚስቴ ትልቁ ወጪ የእኔ ደግሞ ቀዳማይ መደነቂያዎች ናቸው። አንዳንዴ ሚስቴ ወዴትም እንዳልሄድባት በውበትና በማማር እያሰረችኝ ይመስለኛል። የትም ያላየኋቸውን ልብሶች በሚስቴ ገላ ላይና ቁም ሳጥኖች ውስጥ አይቸዋለሁ። ሚስቴን ሳይ ዘመነኛ ነን የሚሉ የከተማችን ሴቶችና ቡቲኮች ምን እየለበሱና እየሰቀሉ ይሆን ስል አስባለሁ።

ያን ቀን ማታ የሚስቴ መልክ አላማረኝም። ቅይርይር ብላ ሳያት ልትውጠኝ ማታን እየጠበቀች ነበር የመሰለኝ። ‹አልመለስክልኝም..ማነው ይሄን ሽቶ የቀባህ? ስትል ደግሞ ጠየቀችኝ።

‹የሆነች የሥራ ባልደረባዬ..! ብዬ ቆምኩ። አጀማመሬ አደገኛ እንደሆነ የገባኝ ቃሉን ከአፌ ካወጣሁ በኋላ ነበር። ‹ማናት የሆነች ልጅ? ፊቷ ሲለዋወጥ ይታየኛል።

‹የመሥሪያ ቤታችን ልጅ ናት› ብዬ የምትለውን ለመስማት በዛውም ትንፋሽ ለመውሰድ ቆምኩ። ‹አቅፋኝ› ብዬ መቀጠል አምሮኝ ነበር ግን ከዛ በኋላ የሚመጣውን ጣጣ ሳስብ ሃሳቤን ዋጥኩት። በምትኩ ‹ስትቀባ ቀብታኝ ነው› ስል አለዘብኩት።

ሚስቴን አየኋት..ቅሬታ ያዘለ ሰላማዊ ፊት አየሁባት። ብዙ አትናገርም። ተሰጥኦዋ ማድመጥ ነው። ግን እንደዚህ አድምጣኝ አድምጣኝ መጨረሻዋን እፈረዋለሁ። እርጋታ ባይኖራት ኖሮ ይሄ ሽቶ ብዙ ቁጣን የሚቀሰቅስ ነበር። በርግጥ እኔም ትዳሬን አክባሪ ነኝ። ሳቅ ጨዋታዬን እንጂ ልቤን ለማንም አልሰጥም። የትኛዋም ሴት እንዳታነሆልለኝ ለሚስቴ ባል የሆንኩ ሰው ነኝ። ሴት ልጅ ፈተና ስትሆንብኝ ፕሮክሲ የመጀመሪያዋ ናት። እንዴት እንደምረሳት ሌላ መከራ ይጠብቀኛል።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You