ሀገር አቅኚ የጋራ ትርክቶች ያስፈልጉናል

አንድ ሀገር ከትናንት የተዛቡ ትርክቶች ወጥታ አዲስ ወደ ሆነ ተራማጅ /አራማጅ ትርክት ለመሻገር ከሁሉም በላይ የቀደመውን ትርክት በአግባቡ መመርመር፤ ከትርክቱ በስተጀርባ ያሉ እውነታዎችን ማጣራት ያስፈልጋል። በተለይም ሀገር እንደ ሀገር ከትናንት የመውጣት ጉዳይ የህልውና የመኖርና ያለመኖር በሚሆንበት ወቅት ጉዳዩ ከፍያለ ትኩረት የሚሰጠው፤ ትልቁ ሀገራዊ አጀንዳ የመሆኑ እውነታ ለአፍታ እንኳን ሊዘነጋ የሚገባ አይደለም።

እንዳለመታደል ሆኖ ግን ብዙዎቻችን መፍትሔ ተኮር ሃሳብ ከማመንጨት ይልቅ መሠረት የሌለውን አሉባልታ የምናራግብ ነን። በዚህም ሳቢያ በአንድ ዓይነት ትርክት የተለያዩ በሽታዎች ተጠቅተን ትውልዱን ሀገር አልባ ለማድረግ እስከመጨረሻው እየተጓዝን ነን። ከትናንት የመውጣት ጉዳይ የህልውና መነሻ፣ የመከራችን ማብቂያ ነው ካልን ጣቶቻችንን የምንቀስርበት አካል ሊኖር አይገባም።

እኔ ለሀገሬ ምን እየሠራሁ ነው? ከሚል መጠይቅ አስተዋጽኦአችንን በመጀመር ንቅናቄውን ሕዝባዊ በማድረግ ማስፋት እንችላለን። ከዚህ አኳያ የመጣንበትን በመቃኘት የምንደርስበትን ማስላት እንችላለን። ችግር የሆነብን ከትናንት ሳንወጣ ወደነገ ለመሄድ መንደርደራችን ነው።

ዛሬ እኮ የትናንት መልክ ነው። ውጥንቅጡ በወጣ ዛሬ ላይ ውጥንቅጧ የወጣ ሀገር የታቀፍነው በትናንት የፖለቲካና የትርክት ስሌት ነው። መጪውን ጊዜ በበጎ ለመቃኘት አሁናዊ ትርክቶቻችንን ፈር ልናሲዛቸው ይገባል። ካልሆነ መከራን በቅብብሎሽ ይዘን ከዚህ ወደዛ በሆነ ከድጥ ወደማጥ ትውልዱ ጫንቃ ላይ ቀንበር እንጭንበታለን። በነፃነት ሀገር፣ በሰፋ ታሪክ ምድር፣ በጋራ እውነት በዘርና በብሔር በሌላም ሌላ ደዌ ተይዘን እንደመጻጉ ቀና ማለት ተስኖን አጎንብሰን ኗሪ ነው የምንሆነው።

ከዚህ ዓይነቱ የታሪክ ሽርፈትና ዝንፈት ለመዳን፣ ከዚህ ዓይነቱ ባለቤት አልባ የሀሰት ትርክት ለመንጻት የመነጋገር ባህል ልናዳብር ይገባል። አብዛኞቻችን ተናጋሪዎች ነን። ተናግረን ለማናገር እንጂ ተናግረን ለመግባባት የሚሆን የሞራል አቅም አላዳበርንም። ችግሮቻችን ደግሞ አድማጭ ነው የሚፈልጉት። በተከፈቱ የምክክር መድረኮቻችን ላይ የጽሞና ዝምታ ሰፍኖ መፍትሔ ተኮር ምክረ ሃሳቦችን ለመቀባበል ከመቼውም ጊዜ በላይ ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን።

ባለመነጋገር ደጃዝማችነት ቀርቶብን የክብር ሁሉ አናት የሆነውን አንድነታችንን አደጋ ውስጥ እየከተትን ነው። ዝምታ ወርቅ ነው በሚል ብሂል በምንም የማናገኘውን ወርቃችንን አደብዝዘናል። ወቅታዊም ሆኑ ነባር አጀንዳዎቻችን የመደማመጥ ጥበብ ነው የሚፈልጉት። በዚህ መንገድ ካልሆነ የተዛነፉ እና የተጣመሙ ትርክቶቻችንን መልክ ለማሲያዝ ይቸግረናል።

ከትናንት ወጥቶ ወደአዲስ የሕይወት ምዕራፍ ለመሸጋገር ለአፍታ ልንዘነጋው የማይገባን አንድ ጉዳይ አለ እርሱም ሠላም ተኮር የሃሳብ መዋጮ ነው። የመድረኮቻችን ዓላማ ከትናንት የራቀ አዲስ ሀገርና ትውልድ መፍጠር ከሆነ ወደአንድነትና ተግባቦት በሚወስዱን ጉዳዮች ላይ የጋራ ስምምነት ሊኖረን ይገባል። ለእርቅና ለሠላም የተከፈቱ በሮቻችን ያለግፊያ በሞገስ የሚያራምዱን እንዲህ ባለው መንፈስ ውስጥ ስንቆም ነው።

ሃሳቦቻችን ፍቅር ወላጅ፣ አንደበቶቻችን እርቅ ነጋሪ ሊሆኑ ይገባል። ትርክቶቻችን በእውነትና ምክንያት ተቀይረው ወደመጨባበጥ እና መተቃቀፍ የሚወስዱን በምናነሳው የሃሳብ ይዘት ልክ ነው። እርቅ የሚታወጅባቸው ሕዝባዊ መድረኮቻችን ያለፈውን ረስተው፣ ያለውን አጥርተው ወደላቀ ነገ የሚያሸጋግሩን እንደሚሆኑ ባለተስፋ ነን።

ታሪክና ትርክት ሀገር የሚፈጥሩና የሚያጎሳቁሉ ሁለት የተለያዩ እሳቤዎች ናቸው። ታሪክ ሀገር ሲፈጥር ትርክት ግን የተፈጠረን ሀገር የሚያፈርስ፣ የተሠራን ትውልድ የሚመርዝ የማኅበረሰብ ጠላት ነው። በታሪክ ፊተኞች ነን። ማንም ያልቻለውን የአብሮነት ገድል በአንድ ላይ ችለናል። ያ ጥንተ ታሪካችን መጠሪያችን ሆኖ ስማችንን በወርቅ ቀለም ጽፎልናል። አሁን አሁን ታሪኮቻችን መልካቸውን እየቀየሩ ወደትርክትነት እየተቀየሩ ነው።

በታሪክ የጸናች ሀገር በትርክት እየተንገዳገደች ያለችበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው። በታሪክ የበረታ ወንድማማችነት በአሉባልታ የጎሪጥ እየተያየ ያለንበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ለምን ብለን ስንጠይቅ ታሪክና ትርክት የተጣረሱበትን መልስ እናገኛለን። የመኖርና ያለመኖር ጥያቄአችንን ለመመለስ ትርክት ፈጣሪዎችን፣ ከትርክቱ ጀርባ ያሉ ኃይሎችን እንዲሁም ደግሞ እውነትን ሸሽገው ትውልዱ የሚጠላላበትን ተረት የሚነግሩንን ግለሰቦችና ቡድኖች ሀይ ልንላቸው ይገባል።

ከዚህ እውነት በመነሳት የሀገራችንን አሁናዊም ሆነ የሰነበቱ አጀንዳዎች መቃኘት ያስፈልጋል። የተዛቡ ትርክቶች መነሻቸው የተዛቡ አስተሳሰቦች እንደሆኑ አጠያያቂ ባይሆንም ሀገርን ከመታደግና ልዩነቶችን ከማቅናት አኳያ ግን የተቃኑ የታሪክ እውነታዎች ያስፈልገናል። ለዚህ ደግሞ ሀገር አቅኚ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ግድ ይሉናል።

ከትናንት የመውጣት፣ ዛሬንም የማስተካከል ጉዳይ የአንድና የሁለት ሰው ኃላፊነት ሳይሆን ከመንግሥት እስከ ተፎካካሪ ፓርቲ፣ እስከግለሰብ እስከ ማኅበረሰብ ድረስ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው። ያሳለፍናቸው ጊዜያቶች እንዴት እና በማን እንደተፈጠሩ በማናውቃቸው መነሻ አልባ ትርክቶች ዋጋ የከፈልንባቸው ናቸው። መነሻቸው በማይታወቅ ተረት መሰል ማስመሰሎች የምንከፍላቸው የሕይወት ዋጋዎች እንደሀገር የሁላችንንም በር አንኳኩተዋል።

የተዛቡ ትርክቶችን ማስተካከልና ልክ የሆነውን እውቅና መስጠት ሀገርን በቀና ፈር ውስጥ ከመምራት ጋር የሚመሳሰል ነው። በማይበጁን ነገሮች ላይ ዝለናል። የሄድንባቸው የእኔ እበልጥ እኔ የታሪክ ሽሚያዎች ማንንም ፊተኛ ሳያደርጉ እዚያና እዚህ አቁመውናል። ታሪኮቻችን ማንም እንዳሻው በገባውና በተረዳ መልኩ በይሆናል የሚተነትነው ሳይሆን በአንድነትና በኅብረት ክንድ የደመቁ ሆነው የመጡ ናቸው።

ሀገር በማሻገር ንቅናቄ ውስጥ ትርክቶችን አስተካክሎ መጪውን ትውልድ በአዲስ የሚቃኝ የብዙሀነት አስተሳሰብ ያስፈልጋል። ይህ እንዲሆን በእያንዳንዳችን ውስጥ የያገባኛልና የይመለከተኛል የቁጭት ስሜት መፈጠር ሀገር ለማቅናት እንደ መንደርደሪያ ሊወሰድ የሚችል ጉዳይ ነው።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You