አባት አልባ ሕልሞች

አባት አልባ ሕልሞች…ከእውነተኛው የሕይወት ተራራ ስር ፈልቆ ግዙፍ ጅረት ለመሆን በቅቷል። ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም በርካቶች ወደዚሁ ተጠርተው ከተራራው ስር ከፈለቀው ንጹህ ጅረት በመጎንጨት ጥማቸውን አርክተዋል። እኛም ከጥኡሙ የጥበብ በረከት ተካፋይ ሆነናልና ካየነው፣ ከሰማነውና አንብበን ከተረዳነው ጥቂቱን እናቋድሳችሁ።

‘አባት አልባ ሕልሞች’ የብዙዎቻችንን ያልተፈታ ሕልም…ያልተከተበ ሕይወት…እንዲሁም ያልተኖረ ልጅነትን ያዘለ መጽሐፍ ነው። የመጽሐፉ ደራሲ ደግሞ ጋዜጠኛና ደራሲ ማስረሻ ማሞ ነው። በባዕድ ሀገር በኔዘርላንድስ ምድር ለ14 ዓመታት ያህል ቆይቶ ሲመለስ እጅ መንሻ ይሆን ዘንድ አባት አልባ ሕልሞችን ከነቃጭሉ ይዞት መጣ። እዚሁ ታትሞ ተወለደና ኑ..ልጄን ስማችሁ መርቁልኝ በማለት ድግሱን በ’ስቴይ ኢዚይ’ ሆቴል አሰናድቶ በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ጥቅምት 18 ቀን ጠርቶ ነበር። እንዲህ ካለው ድግስ አይቀርምና በርካታ የጥበብ ቤተሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተው መጽሐፉን መርቀዋል። በእለቱ መጽሐፉ ብቻ ሳይሆን እጅግ ያማሩና የተዋቡ ባሕሎቻችን ክብረ በዓላቸው የነበረ ያህል በመድረኩ ገነው ታይተዋል። በመድረኩ ድባብ ከመንሰራፋታቸውም ባሻገር ተዳፍነው የቀሩ ባሕላዊ ትውፊቶችም በትርኢት ታጅበው ከነሙሉ ማንነታቸው ወደመድረክ የወጡበት አጋጣሚ ነበር።

ለመሆኑ ‘አባት አልባ ሕልሞች’ እንዴት ተወለደ? ማስረሻስ ይህን ታሪክ ለመጻፍ ልቡን የነሸጠው ጉዳይ ምን ይሆን?…እራሱ ማስረሻ በመድረኩ ላይ እንዲህ ሲል ባንደበቱ ገልጾታል፤ “ታሪኩ በሕይወቴ ሁሉ አብሮኝ የነበረ ቢሆንም የመጽሐፉ ጽንሰ ሀሳብ የተወለደው ግን በድንገተኛው የኮሮና ጎርፍ ነው። ከዚያም ኋላ በልቦለድ መልክ ልጻፈው ወይንስ እንደወረደ በሚል የሙግት ሜንጦ በስጋም በነፍስም ተሰቅያለሁ። በመጨረሻም ጥቂት የእውነት ጭብጦ ይዤ በብዙ አሻሮ የሚሽሞነሞን አሻሮ ከምጽፍ ብዙ አሻሮ እውነታዎችን ጽፌ ነብሴን ባሳርፋት ይሻላል ብዬ የግል ታሪክ ተረኬን ለልጆቼ ለማውረስ ቆጥሜ ተነሳሁ። መጽሐፌን ለመጻፍ ከመጀመሬ በፊት እራሴን የጠየኩት አንድ ጥያቄ ነበር፤ እንደ ሰው ልጅ መኖር ከጀመርኩ ወዲህ የመጀመሪያው ትውስታዬ የተመዘገበው መቼ ነበር? የሚል ነበር። የሰው ልጅስ ከትውስታ ውጪ ምንድ ነው? በዚህ ጥያቄ አማካይነት 45 ዓመታትን ወደኋላ ተጉዤ እራሴን ማሰስ ጀመርኩ። እራሴን ስፈልግ እናቴን አገኘኋት። የእናቴን ዱካ ተከትዬ ስዞርም የመጽሐፉን ሕብለ ሰረሰር ጨበጥኩት፤ ሕብለ ሰረሰሩም እናቴ ነበረች” ሲል በመጽሐፉ ውስጥ የታሪኩ ሁሉ ምንጭ መነሻና እምብርት ከሆነችው ወላጅ እናቱን ጋር አጣቅሶ ይገልጸዋል።

ደራሲው ማስረሻ ማሞ ለዚህ መጽሐፍ መወለድ ዋነኛ ምክንያት የሆነችውን እናቱን በዚህ ልክ ሲገልጻት ዘጠኝ ወር በሆዷ ተሸክማ በሰቆቃ ወልዳ በሰቆቃ ከማሳደጓም ባሻገር፤ እናት በግሏም ከልጅነት ሕይወቷ ጀምሮ በሴትነቷ ስትፈተን፤ በባይተዋርነቷ የመከራን ጎርፍ ስትጋት ስለመኖሯ ተናግሯል። “እናቴ በሕይወት ድንገቴ ጎርፍ ውስጥ በአንድ ዓመት ከ6 ወሯ እናቷን አጣች። በ3 ዓመቷ ደግሞ አባቷ ጥሏት ጠፋ። በ5 ዓመቷ ድጋሚ አያቷን በሞት ተነጠቀች። ከዚያ በኋላም በአደራ የተቀበሏት አሳዳጊ ዘመዶቿ አሳልፈው ለአገልጋይነት ሰጧት። ይህ ስቃይ አያብቃልሽ ሲላት አግብታ ልጅ የወለደችላቸው ባሎቿ አንዳችም እገዛ አያደርጉላትም ነበር። እናት አልባ…አባት አልባ…ዘመድ አልባ…ሰማይ ቁልቁል የተደፉባትና ምድር የተከነበለባት በሰቆቃ የተከበበች ምስኪን ነብስ ነበረች” በማለት የአሳዛኝ እናቱን ሆድ የሚያስብስ የሕይወት ቋጠሮ በታፈነ ውስጣዊ ስሜት ይተርከዋል። በመጽሐፉ ውስጥ ያሰፈራቸው አሳዛኝ የሕይወት ጠብታዎች በእናቱ የተቋጩ አልነበሩም። ‘ድንገቴ ጎርፍ’ ሲል የሚገልጸው የሕይወት ማዕበል ከእናቱ አስጨከነች አልፎ የእርሱንም ሕይወት በሰቆቃ አጥለቅልቆታል። ስለልጆቿ የምትታገለዋን እናት የአቅም ድንበሯን ጥሶ እንደወረደ ለማስረሻም ተላልፏል።

እናትነት ለዋጋዋ ልኬት የለውም። ለውለታዋም ምላሽ አይገኝም። የአብዛኛዎቹ የቀጨኔ ልጆች የእውቀት በር የተከፈተው በአዳምና ሔዋን የቄስ ትምህርት ቤት ነው። ማስረሻም እንደ እኩዮቹ ገና በለጋነቱ ወደዚሁ የቄስ ትምህርት ቤት በመግባት እውቀትን ከፊደላት ገበታ እንዲቀስም እናቱ የነበራት ጉጉትና የከፈለችው መስዋዕትነት ከቃላት በላይ ነበር። ልጇ ተምሮ ሰው ይሆንላት ዘንድ ከወገቧ ላይ ከጠመጠመችው መቀነቷ ሀምሣ ሀምሣ ሳንቲም ትመድብለት ነበር። ይህን ተመልክቶ የእምባ ሲቃ የተናነቀው ማስረሻም ከመጽሐፉ ውስጥ ከአንደኛው ገጽ ላይ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፤ “የእናቴን የመቀነቷን ጫፍ በተመለከትኩት ቁጥር የቤተሰባችን የሕይወት ሚስጥር እዚያ ውስጥ የተተበተበ መሆኑን አያለሁ…የሕይወታችን የሚስጥር ቋጠሮ የሚገኘው ከእናቶቻችን መቀነት ውስጥ ነው” አዎን እርግጥ ነው ማስረሻ እንዳለው ዛሬ የደረስንበትን የኛን ማንነት ያለ እናቶቻችን መቀነት ማሰቡ የማይሆን ነው። ትናንት የእነርሱን አንጀት በመቀነታቸው አስረው የኛን የዛሬ ሕይወት ፈተውበታል።

ከዚህች መጽሐፍ በስተጀርባ ያለው ግለታሪካዊ ልቦለድ ብቻ አይደለም። ከልቦለዳዊ የሰመመን ምጥቀትና ቋት ላይ ተመዞ ብቻም የተጻፈ አይደለም። ደራሲው ቀደም ሲል በንግግሩ እንዳመለከተው፤ የነበረውን ብዙ እውነት በፈጠራ ሳያሽሞነሙነው እንደወረደ አጣፍጦ አስፍሮታል። በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀማቸው ስሞችና መቼቶች እንኳን አንዳችም ለወጥ ሳያደርጉ እንደነበሩት አስቀምጧቸዋል። እናቱ አስጨከነች…ተራኪው ማስረሻ…ሁሉም በገሀዱ ዓለም መታወቂያቸው የቆሙ ናቸው። ዋናው ገጸ ባህሪ የሆነው ተራኪው ማስረሻ እራሱ ደራሲው ማስረሻ ማሞ ነው። በሕይወት ውጣ ወረድ ውስጥ አልፎ ለዛሬ የበቃባትን አሳዛኝ የታሪክ ሰበዝ ከምስኪኗ የቀጨኔ መንደር በመምዘዝ እውነታውን በብዕሩ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል። ብዙ አባት አልባ ሕልሞች ነበሩት፤ ነበረን። የራሱን ታሪክ ብቻ ሳይሆን የብዙዎቻችንን እውነተኛ የኑሮ ሕቅታ አንዳችም ሳይደነቃቀፉ እኛነታችንን ይገልጻሉ። ማንነትና ባሕላችንን እስከዛሬ ባላየንበት አዲስ መነጽር እንድንመለከተው ያደርገናል። ማሕበራዊና ፖለቲካዊ እኛነታችንን አጉልቶና አቅርቦ ያሳየናል።

በመጽሐፍ ምረቃው ወቅት መድረኩን ሲያጋፍር የነበረውና የማስረሻ አብሮ አደግ ጓደኛ የሆነው ከፈለኝ እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር። “የደራሲው ወንድሜ የቀጨኔ ሕይወት ልክ እንደ ቀጭኔ ነበር። ቀጭኔ ልጇን የምትወልደው በቁም ነው። የቀጭኔን ቁመት ተመልክቶ ልጇን ስትወልደው ያን ከሚያህል ከፍታ ላይ ወደ መሬት ስትፈጠፍጠው ማሰብ ለአዕምሮ ይከብዳል። የልጇ ስቃይ በዚህ አያበቃም፤ ተወልዶ መሬት ላይ ከወደቀበት ቅጽበት አንስቶ፤ እናት በዚያ ከባድ ሸኮናዋ ያላትን ኃይል በሙሉ ተጠቅማ እየደጋገመች ልጇን ትረግጠዋለች። ይህን ሁሉ የእናትነት አንጀቷ የወለደው ጥበብ እንጂ በጭካኔ አሊያም የልጇ ስቃይ ሳይሰማት ቀርቶ አይደለም። ምክንያቷ በዙሪያዋ ሆነው ልጇን ለመብላት ካሰፈሰፉት አውሬዎች ለመታደግ ነው። እንዲህ የምታደርገውም ከዱላዋ ለማምለጥ በሚያደርገው መፍጨርጨር ቆሞ መሄድና ማምለጥ እንዲችል ነው። በአራት እግሩ ቆሞ መሮጥና ማምለጥ መቻሉን ስታረጋግጥ አሁን ብቁ ሆኗል በማለት መርገጧንም ታቆማለች። ለመጽሐፍ የበቃው የቀጨኔው ማስረሻ ሕይወትም እንዲሁ በቀጭኔ የተመሰለ ነበር”፡፡

በዚህ ታላቅ መድረክ ላይ ከተገኙ የጥበብ ሰዎች መካከል አንደኛው ተፈሪ ዓለሙ ነበር። መገኘት ብቻም ሳይሆን አጣፍጦ ለማቅረብ በተሰጠው ድንቅ ችሎታው ወደ መድረኩ በመውጣት ከመጽሐፉ ውስጥ ጥቂት ገጾችን ባማረ የትረካ ዘዬው ተርኮታል። ተርኮም ብቻ አልወረደም ስለ መጽሐፉ መሳጭ ታሪክና የደራሲው ችሎታ አድናቆቱን ከመግለጽ አልተቆጠበም። ከእርሱም ሌላ የቋንቋና ስነ ጽሁፍ ሊህቃን ከብዙ ነገሮች አኳያ በመገምገም አስተያየታቸውን ሰጥተውበታል። ከመጽሐፉ ዘውግ በመነሳትም አንድ መጽሐፍ ሊያካትታቸው የሚገባውን ዘውጎች ከመያዙም በላይ፤ በምርመራ ሂደት ቢያልፍ ምናልባትም ሁሉንም የዘውግ አይነቶች ልናገኝበት የምንችልበት ድንቅ ሥራ ነው ሲሉ አሞካሽተውታል። 14 ዓመታትን ከባሕር ማዶ ያሳለፈውን ማስረሻን በአባት አልባ ሕልሞች ውስጥ በተከማቸው የቃላትና የቋንቋ ችሎታ አጮልቀን ለማየት ስንሞክር ምናልባትም እራሳችንን እንታዘብ ይሆናል። እንደ ምናባዊ ትውስታዎቹ ሁሉ ቃላቱም ከጊዜው ጋር አብረው በያኔው የማወቅ ልኬት የተገለጡለት ይመስላል።

‘አባት አልባ ሕልሞች’ የአንድ ማስረሻ ግለታሪክ ብቻ አይደለም። እራሱ ደራሲው በመጽሐፉ ውስጥ ያስቀመጠውን የእርሱን የሕይወት መልክ ከሀገራችንና ከሕዝባችን ጋር አቆራኝቶ ብዙ እውነታዎችን ይነግረናል። የመጽሐፉ የጀርባ አጥንት የተገነባውም በሀገራዊ የፖለቲካና ማሕበራዊ ትስስር ውስጥ ነው። በአንድ ሰው ውስጣዊ መልክና ቁመና ውስጥ ቤተሰብ፣ ሀገርና ማሕበረሰብ አለ። “በዚህ ሁሉ ውስጥ አጨንቁሬ ኢትዮጵያን ለመመልከት ሞከርኩ። ኢትዮጵያ ግን ማናት? ለዚህ ሁሉ የዳረጋትስ ማነው? ብዬ ጣቴን ወደ መንግሥት ልጠቁም ስል አንድ ነገር ትዝ አለኝ። የአንድ ሀገር መሠረቱ ቤተሰብ ነው። እንደ ቤተሰብ የቤት ሥራችንን ያልጨረስን በመሆኑ እንዲህ አይነቷን ሀገር ፈጥረናል” ይላል ማስረሻ በቁጭት ውስጡን እየሸነቆጠው። ከመጽሐፉ ጭብጦች መካከል አንደኛው በዚሁ የሀገርና የቤተሰብ ሥርዓት ውስጥ ይዘዋወራል። የኢትዮጵያ ቤተሰብ በሁለት ነገሮች ተሠንጎ ስለመያዙ ያወጋናል። አንድም በውርስ ሁለትም በወሰን ተተብትቦ በአንድም ሆነ በሌላ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ሕይወታችንን አወሳስቦታል፡፡ አባት አልባ ሕልሞች ከእነዚህ ሁሉ እውነታዎች ጋር በመጋፈጥ ያለንበትን አስቀያሚ ሁኔታ እንድንለውጥ መንገዱን ያሳየናል። ስግብግቡ የሺጥላ፣ ራሷን ችላ መቆም ያልቻለችው ፋንቱ፣ ምስኪኗ የማስረሻ እናት…የመጽሐፉ የእውነት ፍልቃቂ ገጸ ባህሪያትና ማሳያዎች ናቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ የቤተሰቡ አውራ የነበሩት የእትየ ጣፈጥን ሞት ተከትሎ እነዚህ ሰዎች በውርስ ምክንያት ተፋጠዋል፡፡ እነርሱን ለመዳኘት በሸንጎ የዳኝነት ሥርዓት የተሰየሙት ዳኞች የፍትህ አሰጣጥ በእጅጉ የሚያኮራና ወደኋላ ዞረን ያሉንን እንቁ ባሕሎቻችንን እንድንናፍቅ የሚያደርግ ነው። ደራሲው ተወልዶ ያደገበትን የባለ እጅ ማሕበረሰብ ባሕልና እሴት ከተደበቁበት ፈልፍሎ በማውጣት የመጽሐፉ ዋነኛ ግብዓት አድርጓቸዋል። በመጽሐፉ ውስጥ ከማንጸባረቁም በተጨማሪ በምርቃቱ መድረክ ላይ ምንም ሳይቀባባ ለታዳሚው በቀጨኔ እናቶች የቀረበው ‘የእንጀራ ቆረሳ’ የሚባለው የሴቶች የሽምግልና ሥነ ሥርዓት እጅን በአፍ የሚያስጭን ትዕይንት ነበር። ሴቶቹ “ልጃችሁን ለልጃችን” በማለት የትጭጭት ሥነ ሥርዓቱን የሚከውኑት በወንድ የተለመደውን ባሕላችንን በማፍረስ አይደለም። ይልቁንስ ነገሩ ‘ሴት ያውቅ በወንድ ያልቅ’ አይነት ነው። ሴት አምጣና ተጨንቃ የወለደች በመሆኗ ከወንዶቹ በፊት የልጆቻቸውን የትዳር መንገድ አስቀድመው በማጥራት የሚያስኬድ ከሆነ ጉዳዩን ወደ ቀጣዩና ወደ ዋነኛው የወንዶች ሽምግልና ያስተላልፉታል። ይህ የሴቶች እኩልነት፤ የእናትነት ክብር ነው። ዛሬ ላይ ‘ሌዲስ ፈርስት’ በማለት ነጮቹ የሚመጻደቁበት ሥርዓት ቀድሞ እኛ ጋር በባለ እጅ ማሕበረሰብ ዘንድ ነበር።

ሌላው የዚህ መጽሐፍ ምረቃ ከብዙ የመጽሐፍት ምረቃዎች ለየት ያደረገው አንድ ነገር ቢኖር በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱና በሕይወት ያሉ ሰዎችም በመድረኩ መገኘታቸው ነው። ከእነዚህም አንዷ ያቺ ምስኪኗ የማስረሻ እናት ነበረች። …ለመሆኑ ክፍልፍልን የምናውቅ ስንቶቻችን እንሆን? “ክፍልፍል የስም ክህደት ተፈጽሞበታል” ይላል ማስረሻ በመጽሐፉ። እርግጥ ነው እንዲያ ቢል ውሸት አይሆንም። ዛሬ በብጣሽ እንጀራ አፈርፍረን የምራቅ ጠብታ በምታህል ዘይትና በርበሬ እንደነገሩ ለውሰን የምንውጣት ፍርፍር፤ የቀድሞ መጠሪያዋ ክፍልፍል ነበር። ለነገሩ ስሟን ብቻ ሳይሆን ማንነቷንም ቀይረነዋል። ድሮ ድሮማ ቋንጣና በእንጀራ ድርቆሽ እንዲሁም በቅቤ ተለውሳና ተከሽና ነበር የምትወጣው። ክፍልፍል ዘመናትን ተሻግራ አለሁ ስትል ከባለ እጆች ዘንድ ከነጉርሻዋ ለመድረክ በቅታ ነበር። ስትቀርብም ወዘናዋን እንዳጣችው እንደዛሬይቱ ፍርፍር በሳህንና በትሪ ሳይሆን በባሕሉ መሠረት በጣባ መሳይ ውብ ሸክላ ነበር የቀረበችው። ዋንጫ መሳይ የሸክላ መጠጫዎቹም ከነቅርጻቸው፤ ቀደምት ባሕላዊ ቅርሶቻችንን ያለ እውቅና መዘረፋችንን የሚናገሩ ነበሩ። ምስጋና ለአባት አልባ ሕልሞች ይግባና ከመጽሐፉም ሆነ ከምረቃው በስተጀርባ ብዙ እሴቶቻችንን ገልጦ አሳይቶናል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ውብ ባሕሎቻችን ታጅቦ የዋለው የእለቱ የመጽሐፍ ምረቃ ሥነ ሥርዓት እንዲህ ባለ መልኩ ተጀምሮ… አለቀ፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You