«ከታላቁ ትርክት» በፊት…!?

በአአዩ የተዘጋጀ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፦” ተረከ ስለአለፈ ነገር ዘርዝሮ ተናገረ ፣ አወራ፣ አወጋ፣ አተተ ማለት ነው ይለናል።”ትርክት ደግሞ ስለአለፈ ነገር ዘርዝሮ የመናገርና የማውራት ሒደት ነው ። መንግሥታት ፣ ገዢዎችና የፖለቲካ ቡድኖች ቅቡልነትን ለማግኘትና ከተነሱበት ዓላማ አንጻር የዜጎችን ወይም የተከታዮቻቸውን እምነት፣ አመለካከትና እይታ ለመቃኘት ታሪኮችን ፣ ማስረጃዎችንና ገለጻዎችን አደራጅቶ ገዥ ሃሳብ አንጥሮ የመለየትና የማኸዘብ ስልት ነው ።

በእርግጥ ትርክት የጋራ ማንነትን ለማነጽ ያግዛል። በተለያዩ ማኅበረሰቦች ዘንድ አንድነትን ለመፍጠርና የጋራ ተግባር ለመትለም፤ የጋራ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ አላባውያንን በመጠቀም ብሔራዊ ማንነት ለመፍጠር ያስችላል። ከዚህ ባሻገር ትርክት ብሔራዊ እሴቶችንና ሕልሞችን ለመቅረጽ፤ ማኅበራዊ ስምምነት ለመፍጠር፤ ታሪካዊ ትውስታ ለመጫር፤ ሕዝብን ለአንድ ዓላማ ለማነሳሳት ንቅናቄ ለመፍጠርና ዓለምአቀፍ ገጽታ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የማይተካ ሚና አለው።

በርግጥ ትርክት አዎንታዊና አሉታዊ ሊሆን ይችላል። ሀገርን ለመገንባት የሚውል አዎንታዊ ትርክት እንዳለ ሁሉ ሀገርን ለማፍረስ የሚውል አሉታዊ ትርክት እንዳለ በዘርፉ የተጻፉ ድርሳናት ያትታሉ። አዎንታዊ ወይም አካታች ትርክት አካታችነትን፣ ብዝኀነትንና ማኅበራዊ ውህደት ይሰብካል። አሉታዊ ትርክት በዜጎች መካከል ልዩነትን፣ ጥላቻን፣ አለመተማመንና መጠራጠርን የሚጎነቁል ከመሆኑ ባሻገር ሀገርን እስከማፍረስ ሊደርስ ይችላል። የሀገራችንን መልክና ሰማይ የሞላው ይህ አሉታዊ ትርክት ነው። ይህ አደገኛ ትርክት ሥራ ላይ እያለ አዲስ “ታላቅ ትርክት” ማንበር ያዳግታል። ለመሆኑ የዚህ ትርክት መነሻ ከወዴት ነው።

በተማሪዎች የ1960ዎች እንቅስቃሴ ከእነ ግርማቸው ለማ፣ መለስ ተክሌ (የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ስሙን የወረሱት )፣ ሰለሞን ዋዳ፣ ጥላሁን ግዛው ይልቅ ዛሬ ድረስ በበጎም፣ በክፉም ስሙ ከፍ ብሎ የሚወሳው የደሴው ዋለልኝ መኮንን ነው። ከእነ ሌኒን ማንፌስቶ እንዳለ ገልብጦ /ኮርጆ / ማታገያውን ከመደብ ጭቆና ወደ ጠባቡ የብሔር ጭቆና በማውረዱ ተደጋግሞ ቢወቀስም፤ አንዳንዶቹ ዋለልኝ የተማሪዎች ማህበር መሪዎች ያሳለፉትን ውሳኔ አነበበ፣ ጻፈ እንጂ የብሔር ጥያቄን ቀድሞም ሆነ ለብቻው አላነሳውም በማለት ጥያቄው የተማሪዎች እንቅስቃሴ የወለደው ስለሆነ ከዋለልኝ ጫንቃ ውረዱ የሚሉ ወገኖች አሉ።

ያም ሆነ ይህ በፈጠራ ትርክትና በግልብ ትንተና መታገያና ማታገያ ሆኖ የመጣው የብሔር ጥያቄ ሀገራችን ዛሬ ድረስ ለምትገኝበት ምስቅልቅል እና አጣብቂኝ መግፍኤ ከመሆኑ ባሻገር፤ ሀገር፣ ሕዝብ ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ልሒቃኑን በሁለት ጎራ ከፍሎ እያጨቃጨቀ ይገኛል። በሀገራችን ተንሰራፍቶ የነበረው ጭቆና የመደብ ነው አይደለም የብሔር ጭቆና ነው በሚሉ ሁለት የማይታረቁ ቅራኔዎች ተጠምዷል።

የብሔር ጭቆና በተጠየቃዊነት በምክንያታዊነት የሚተነተን ሳይሆን በማንነት በስሜት የሚቀነቀን የሚራገብ መሆኑ ልዩነቱን የማጥበብ ሂደቱን አዳጋች አድርጎታል። እዚህ ላይ በብሔርተኞች እና ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን በሚያራምዱ ወገኖች መካከል ያለውን ልዩነት በአብነት ማንሳት ይቻላል። ሆኖም የተማሪዎች እንቅስቃሴ ለትህነግ፣ ለኦነግና ለሌሎች የብሔር ድርጅቶች መፈጠር እርሾ ሆኖ ማገልገሉ አይካድም። ጉዳዩን በአግባቡ ለመረዳት በሰከነ መንፈስ ነገሮችን ማየት የሚጠይቅ ነው።

ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴና ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ደጋግመው ባቀረቡት ምክረ ሃሳብ መሠረት ታሪካችንን መፈተሽ እንደገና መበየን ይጠይቃል። ይህን ስል እንደ በጀት ታሪካችን በቀመር ይደልደል ማለቴ ሳይሆን፤ ፍርጥርጥ፣ ግልጥልጥ ይበል፤ ሲለፈፍ በኖረው ትርክት ላይ በግልጥ ተነጋግረን እልባት እንስጠው ማለቴ ነው።

ወደ አገዛዝ ለመምጣት ሆነ በአገዛዝ ላይ ለመቆየት፤ ላለፉት 50 አመታት ልዩነቶችን የሚያሰፉ ጥላቻን መሠረት ያደረጉ ሥራዎች መዋቅራዊና ተቋማዊ ቅርጽ ይዘው በስፋት ተሠርተዋል፤ በዚህም ታሪክ ተበርዟል ፤ ሀሰተኛ ትርክት ተፈጥረሯል። ይህ አልበቃ ተብሎም ሀሰተኛ ትርክቶች ለገበያ ቀርበው እንዲሸጡ ተደርገዋል።

ይህንን ያልተገባ ትርክት ይዞ ብልጽግናናን በምልዓት ማረጋገጥ አይቻልም። ከፍ ሲልም ከ50 አመታት በኋላ ሒሳብ ስንተሳሰብ ከአተረፍነው ይልቅ የከሰርነው የትየለሌ ነውና። ከልዩነት ይልቅ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ላይ ተጠናክሮ ሊሠራ ፤ፖለቲካችንም በማንነት ሳይሆን በሃሳብ ሊጎለብት ሊታነፅ ይገባዋል። ለዚህ ደግሞ አዲስ ትርክት መቅረጽ ይጠይቃል።

ለዚህ ይረዳ ዘንድ በከፊል አቅጣጫውን የሳተውና የጥራት እጥረት ያኮሰመነው እንዲሁም የአገዛዙ ነጸብራቅ የነበረው ሥርዓተ ትምህርትም መለስ ብሎ የመፈተሹ ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ከዚህ ጎን ለጎን ብሔራዊ እርቅና እውነትን የማፈላለግ እና በሀሰተኛ ትርክት የሴራ ደማሚት የፈረሱ የሕዝብ ለሕዝብ መገናኛ ድልድዮች መልሰው መጠገን አለባቸው ።

ግማሽ ክፍለ ዘመን የተሻገረው ከብጥብጥና እርስ በእርስ በጥርጣሬና በጥላቻ ከመተያየት በቀር ብዙ ያላተረፈልን የፈጠራና የሀሰት ትርክት ልፋፌ ነቢብ እስከ ገቢር ያለው ምዕራፍ እልባት ሊያገኝ ይገባል።

የፈጠራ ትርክት ልፋፌ ነቢብ ከተቀዳበት ታሪካችን ብንነሳ ሁላችንም ባለዕዳ ነን። ሁላችንም ባለዕዳ ከሆን ደግሞ የየራሳችንን የፈጠራ ትርክት መቅረጽ እንችላለን። ችሎታችን ግን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነው የሚሆነው። ማናችንም አናተርፍም። የዜሮ ድምር ፖለቲካ እንዲሉ ።

በአጭርና በጅምር ቀሩ እንጂ ታሪካችንንም እና አሁን “ሥራ ላይ ያለውን” ትርክት ለመፈተሽ እዚህም እዚያም ያልተቀናጁ ጥረቶች ተሞክረዋል። የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማሰባሰብ በኢትዮጵያ የታሪክ ትርክት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ እንደነበር ይታወሳል። እስካሁን ባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያሉ አተያዮች ላይ ትኩረቱን ባደረገው የውይይት መድረክ፣ ኢዜማ ፣ አብን፣ኦነግ፣ ኦፊኮ፣ የሲዳማ ሕዝብ እና ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥት ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበራት እንዲሁም ምሁራን ተሳትፈዋል።

በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ከ175 በላይ ሀገር በቀል የሲቪክ ማኅበራትን አቅፎ የያዘው ነው “የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ”። በመድረኩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ፣ የታሪክ መጽሐፍ ሀያሲ እና «የድንቁርና ጌቶች» የተሰኘው መጽሐፍ ጸሐፊ በሆኑት በአቶ ብርሃኑ ደቦጭ አማካኝነት አከራካሪ ነው በተባለው በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የተጻፉ አተያዮችን በተለያየ ክፍል በማስቀመጥ በዝርዝር ቀርበዋል።

የሀገር ታሪክ፣ የመንግሥት ታሪክ፣ የብሔር ታሪክ የጎሳ/ዘር ታሪክ ሁሉም የራሱ ታሪክ ይኖረዋል ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ ብሔራዊ ታሪክ ማለት እነኚህ ሁሉ በጋራ የሚቀመጡበት መሆኑን አስረድተዋል። እንዲህ ዓይነቱ ሥራ ብዙ ነገር እንደሚፈልግ፤ በተጨማሪም ጊዜ ፣ እውቀት፣ ልምምድ፣ ንግግር እና የሃሳብ ልውውጥም ይፈልጋል ብለዋል። ለዚህ ይመስላል ምን እየሠራ እንደሆነ መረጃ ባይኖረኝም ቀደም ባለው ጊዜ የታሪክ ምሁራን ያሰባሰበ ምክር ቤት እስከመመስረት የተደረሰው ።

ሻሎም ! አሜን።

 በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You