ኢትዮጵያ የባሕር በር ከሌላቸው አገሮች መካከል አንዷ ነች። አገሪቱ ያለ ባሕር በር መኖር ከጀመረች ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ተቆጥሯል። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ስትሄድ የአሰብንና የምፅዋን ወደቦች ይዛ በመሄዷ ወደብ አልባ አገር ሆናለች።
የባሕር በር ወይም ወደብ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ወሳኝ ከመሆኑ ባሻገር ፖለቲካዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ጂቡቲ ከአራት በላይ ወደቦች አሏት። ይህች ትንሽ አገር ተፈላጊነቷም ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ እንዲሁም ከአሜሪካ እስከ እስያ ድረስ ደርሷል። የተወሰኑ አገሮች ቻይናን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት በዚች ትንሽ አገር ወታደራዊ ቤዝ ገንብተዋል። እነዚህ አገሮች ወደዚች ትንሽ አገር መጥተው ወታደራዊ ቤዝ እንዲኖራቸው ካስፈለጓቸው ምክንያቶች መካከል የአካባቢው ተፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ እንደሆነም ባለሙያዎች ያብራራሉ ፡፡
በሌላ በኩልም ሳዑዲ ዓረቢያ ከአሰብ ወደብ ከፊሉን ከኤርትራ በሊዝ ገዝታ ለብዙ ዓመታት ለማስተዳደር ፈቃድ አግኝታለች። በአሁኑ ወቅት የአሰብና የምፅዋ ወደቦች የዓረብ አገሮች በተደጋጋሚ ጊዜ ወደዚህ አካባቢ ሲሄዱና ወታደራዊ ሠፈር ሲያቋቁሙ ታይቷል። በአሁኑ ወቅት የጂቡቲ ወደቦች በሁለት ሳምንት የሚያንቀሳቅሱትን ያህል በዓመት ማንቀሳቀስ እንደማይችሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አሁንም ድረስ ግን ተፈላጊ መሆናቸው የማይካድ ነው፡፡
የጂቡቲን ወደቦች ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ይጠቀሙበታል። እነዚህ አገሮች የጂቡቲ ወደቦችን የኢትዮጵያን ያህል የሚጠቀሙ ባይሆንም፣ በአካባቢው ላይ ያላቸው ፍላጎትና ዝንባሌ ግን ከፍተኛ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በዓመት ለወደብ ኪራይ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለጂቡቲ እንደምትከፍል መረጃዎች ያመለክታሉ። ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን ወጪና ገቢ ንግዷን የምታካሂደውም በጂቡቲ ወደቦች አማካይነት ነው። የጂቡቲ መንግሥት ከቻይና ባገኘው ሦስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍም አዳዲስ ወደቦችን እየገነባና እያስፋፋ ሲሆን የወደብ ማስፋፋት ፕሮጀክቱ በዋናነት ታሳቢ አድርጎ የሚንቀሳቀሰውም ኢትዮጵያን ነው፡፡
በሌላ በኩል ንብረትነቱ የሶማሌላንድ የሆነው የበርበራ ወደብ ተፈላጊነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ኢትዮጵያ ይህን ወደብ የማስተዳደር 19 በመቶ ሥልጣን ቢኖራትም፣ በዋናነት የሚተዳደረው ግን በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግሥት ነው። ሶማሌላንድ 35 በመቶ፣ ኢትዮጵያ 19 በመቶ ድርሻ ያላቸው ሲሆን፣ 46 በመቶ ወደቡን የማስተዳደር ሥልጣን የኤምሬትስ መንግሥት ነው፡፡
በዚህ የአፍሪካ ክፍል በተለይም በቀይ ባሕር አካባቢ ያለውን የባሕር በር በቅርብ ሆኖ ለመከታተል፣ እንዲሁም አማራጭ ወደብ ለማግኘት በማለት የተለያዩ ሀገሮች በእነዚህ ወደቦች ላይ ፍላጎት ያሳያሉ፡፡ኢትዮጵያም በበኩሏ የባሕር በር የሌላት አገር ከመሆኗ አንፃር የጂቡቲ ወደቦችን በመከራየት የገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴዋን ስታካሂድ ቆይታለች።
አገሮች የወደቦች ሽሚያ በሚመስል ውድድር ውስጥ በመግባት የባሕር በርና ወደብ ወዳላቸው ሀገራት ፊታቸውን እያዞሩ ነው። ኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት የጅቡቲ ወደብን የወጪና ገቢ ንግዷን ለማሳለጥ አብዝታ እየተጠቀመችበት ነው፡፡
የጂቡቲ መንግሥት እንደሚለው በዓመት 35 ሺ የተለያዩ አገሮች መርከቦች በጅቡቲ በኩል ያልፋሉ። በዚህ የተነሳ ጂቡቲ በዓመት በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ታገኛለች። በእነዚህ ወደቦች በዋናነት ኢትዮጵያ የምትጠቀም ቢሆንም ኡጋንዳና ኬንያም ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡
የሶማሌላንድ የበርበራ ወደብም ዓለም አቀፍ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ይህ አካባቢ ከወደብ አገልግሎት ባሻገር ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እንዳሉት ይነገራል። ለአብነት ያህልም በአካባቢው የኤምሬትስና የኳታር ወታደሮች ይገኛሉ። በተለይ የገልፍ አገሮች ይህንን አካባቢ እንደሚፈልጉት ይነገራል። በዚህም የተነሳ በአካባቢው እየተፈጠረ ያለውን ወታደራዊ አሰላለፍና ጫና በቅርብ ሆኖ ለመከታተልና አካባቢውን አሳልፎ ላለመስጠት፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ፊታቸውን ወደዚያ እንዳዞሩ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይሰማል፡፡
ነገር ግን ኢትዮጵያ ለአያሌ ዓመታት ታስተዳድረው በነበረው የቀይ ባሕርና የባሕር በሮቿ ግዛቶችም ከላይ ከተጠቀሱት ሀገራት ጋር የዝሆን ጥርስ የቅመማ ቅመም ምርቶችን የሙጫ ተክሎችን እንዲሁም ሌሎች ወጪና ገቢ ሸቀጦችን አልባሳት ሽቶና ጌጣጌጦችን በመላክና ወደሀገር ውስጥ በማስገባት የተቀላጠፈ የንግድ እንቅስቃሴ ታካሂድ እንደነበርም የአባቶቻችን የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ይህ ብቻም አይደለም የቀይ ባሕር ወደብን እንደ አሸዋ ትናኝበት በነበረበት ጊዜ ከየመን እስከ ሕንድ ከሶሪያ እስከ እስራኤል ከሳውዲ ዓረቢያ እስከ ግብጽ ከቻይና እስከ አውሮፓና ኤዤያ ድረስ ጠንካራ የመንግሥታት ግንኙነትን በመፍጠር የልዕለ ኃያልነት አስፈሪነቷን ለዓመታት እንደቆየችበት የሀገሪቱ የዲፕሎማሲ ታሪክ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው እውነት ነው። ይህም በዘመኑ በቀይ ባሕር ቀጠና ከፍ ያለ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማኅበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ብልጽግናን ካነገሡ ሀገራት ቀዳሚዋና ፋና ወጊ ሲያስብላት ቆይቷል።
በዚህ ገናናነቷ ዓለምን ሊቀይር የሚችል አቅምን መፍጠርን እንደቻለችም በብዙ የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች ሳይቀር ዛሬም ድረስ የምትታወስ ሀገር ስትሆን የዚህ ታላቅነቷ ምስጢር ሲገለጽ ደግሞ ግርማቸው ከሩቅ የሚያስፈራ በጥበብም ቀድመው የነቁ የበቁ መሪዎችና በሥነ ምግባር በሀገር መውደድና አርቆ በማሰብ ውስጥ የነበሩ ተመሪ ሕዝቦችም የነበሯት ሀገር እንደነበረች የሚያሳይ ነው። በአንጻሩ የአገሪቱን የቀዳሚነት መንገድ ይዞ ካለመዝለቅ የመነጩ ክስተቶችን ያስተናገደችው ኢትዮጵያ በተለይም ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በኋላ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ መቀየር በራሷ በሀገሪቱም የመሪዎች መለዋወጥ ምክንያት አገሪቱን ካለወደብ በሚያስቀር ውል ኤርትሪያ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ሆነ። ይህ መሆኑ ደግሞ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ኩነቶች በመቀያየር ሀገሪቱን ወደብ አልባ ከማድረጉም ባሻገር ለዘመናት የቀይ ባሕርና የበርካታ ወደቦች ባለቤት የነበረች ኃያልና ክቡር ሀገር አሁን ላይ ወደኋላቀርነት ድህነት የገባችበት ሁኔታ ነው ያለው ባሕርና ከኤደን ባሕረሰላጤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነቷ ውጪ እንድትሆን አስገድዷታል።
በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር በመሆኗ በወጪ ገቢ ምርቷ ላይ የሌላ ሀገር ጥገኛ እንድትሆን አስገድዷታል። ይህም ለራሷ ታውለው የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማቀጨጭ በኢኮኖሚዋ ላይ እድገት እንዳይመዘገብ የፊጥኝ አስሯታል። ከቀይ ባሕር በ60 ኪሎ ሜትርና ከሕንድ ውቂያኖስ በ2 መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ቢሆንም እነዚህን አካባቢዎች ተጠቅማ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን እንዳታደርግ የማግለል ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። የአፍሪካውያን የነፃነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ በጥንታዊው ሥልጣኔዋና ገናናነቷ ከቀይ ባሕር እስከ ሕንድ ውቅያኖስ የነበራትን ኃያልነት መርምሮ ዘመኑን ታሳቢ ባደረገ ዓለም አቀፍ የወደብ አጠቃቀም መርሕን ፈትሾ የምሥራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ፖለቲካዊ አካሄድ ተረድቶ በሰላማዊ ንግግርና ምክክር የኢትዮጵያም የወደብ መጠቀም መብት ሊከበር የሚገባበት ወቅት ላይ ነን።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም በዚህና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከረዳት ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ ጋር ቆይታ አድርጓል።
አዲስ ዘመን፦ በቅድሚያ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን እንዴት ይገልጹታል?
ረ/ፕሮፌሰር አሕመድ፦ የአፍሪካ ቀንድ ብዙ ታሪክ ያለው ተዓምራት የሚመስሉ ነገሮች ሁሉ የተከናወኑበት አካባቢ ነው። በተለይም ኢትዮጵያ ደግሞ የሰው ዘር መገኛ ከመሆኗ የተነሳም ብዙ ታሪክ ያላት ናት። የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ በብዙ ችግር የተተበተበ ነው። በአካባቢው ሁለት ዓይነት እረፍት የለሽ ተቀናቃኝ ሁኔታዎች አሉ። ይህ ደግሞ ይበልጥ ኢትዮጵያን ነው የሚመለከተው። በኢትዮጵያ ላይ አንደኛ ታሪካዊ ተቀናቃኞች፤ ሁለተኛ ደግሞ ተፈጥሯዊ ተቀናቃኞች አሉባት። ታሪካዊ ተቀናቃኝ የምንላቸው ሰፊና ረጅም ታሪክ ያላቸው ናቸው። እነዚህ በታሪክና በባሕል የሚቀናቀኗት ናቸው። ተፈጥሯዊ ተቀናቃኞቿ ደግሞ በሃብት የሚቀናቀኑ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፦ በቀጣናው በተለይም በቀይ ባሕር አካባቢ ያለውን የኢትዮጵያ ሚና እንዴት ይገለጻል?
ረ/ፕሮፌሰር አሕመድ፦ ብዙ ጊዜ የውሃ እንቅስቃሴዎች የሥልጣኔ ምልክቶች ናቸው። ይህ ደግሞ በትልልቅ ወንዞችም ሆነ በባሕር ጠረፎች ላይ የሚገለጽ ነው። እስከ ዛሬ ድረስም የታዩት ሥልጣኔዎች በሙሉ በዚህ ዙሪያ ናቸው። ለምሳሌ የሰው ልጅ በእግሩ ፤በፈረስ ፤በበቅሎ በግመል አለፍ ሲልም በመኪና በባቡር በአውሮፕላን ይንቀሳቀሳል። ነገር ግን በመርከብ አማካይነት በባሕር ላይ የሚደረግ እንቅስቃሴ ትልቅ ቦታ የሚይዝ ነው። በተለይም በትልልቅ ንግድ ሥርዓት እንዲሁም ሀገራዊ ጥቅሙ የመርከብን ያህል አገልግሎት የሰጠ የለም። እስከ ዛሬ ድረስ ግን ኢኮኖሚያችን በተወሰኑ ነገሮች ላይ የተገደበ ስለነበር ባሕር ቢኖረንም ባይኖረንም የመርከብ ጥቅም ብዙ ሳይሰማን ቆይቷል። ዛሬ ላይ ግን አንደ ሀገር የሕዝብ ቁጥራችን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ይህንን ተከትሎም የፍላጎት እቃዎች መብዛታቸው ከሁሉም በላይ ደግሞ እያሳየን ያለነው ኢኮኖሚያዊ እድገት መርከብን እንድናማትር አድርጎናል ማለት ይቻላል።
ይህ መርከብን ማማተራችን ደግሞ ማሳረፊያውን ወደብ እንድንፈልግ ምክንያት እየሆነን ነው። በመሠረቱ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ባለቤት በነበረችበት ጊዜ ምርቷ በሙሉ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚከፋፈል ነበር። ለዘመናት የቀይ ባሕርና የበርካታ ወደቦች ባለቤት የነበረች ሀገር ነበረች ። አሁን ላይ ወደኋላቀርነት ድህነት የገባችበት ሁኔታ ያሳዝናል።
ይህም በዘመኑ በቀይ ባሕር ቀጣና ከፍ ያለ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማኅበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ብልጽግናን ካነገሱ ሀገራት ቀዳሚዋና ፋና ወጊ ሲያስብላት ቆይቷል። በዚህ ገናናነቷ ዓለምን ሊቀይር የሚችል አቅምን መፍጠርን እንደቻለችም በብዙ የውጭ አገር ዲፕሎማቶች ሳይቀር ዛሬም ድረስ የምትታወስ ሀገር ስትሆን የዚህ ታላቅነቷ ምስጢር ሲገለጽ ደግሞ የወደብ ባለቤትነቷ ነው።
የቀይ ባሕር ታሪክ በጣም ሰፊ ነው፤ ከክርስትና እስልምና አይሁድ ጋር በጣም ቁርኝት ያለው ነው። ከዛም በፊት የዓባይ ሸለቆን ሥልጣኔ ያማከለ ቦታ ከመሆኑ አንጻር በታሪክ ሂደትም ብዙ የምንናገርለት ሂደት አለ። በተለይም ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን የንግድ እንቅስቃሴ በመቆጣጠሯ ምክንያት በወቅቱ የአክሱም ሥልጣኔ እንዲያብብ ምክንያት ሆኗል። በወቅቱም በዓለም ላይ ከነበሩት ሥልጣኔዎች አንዱ ሆኖ ለመውጣቱም ምክንያቱ የባሕሩ ንግድ ነው።
አዲስ ዘመን፦እንዴት በቀይ ባሕር ላይ የነበራትን የበላይነት ልታጣ ቻለች፡፡
ረ/ፕሮፌሰር አሕመድ፦ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ለመጀመሪያ ጊዜ ያጣችው በቅኝ ግዛት (በኮሎኒያል) ጊዜ ነው። የአፍሪካ ቀንድ የበርካታ ኃያላን ሀገራትን ትኩረት የሚስብ ስትራቴጂክ ስፍራ ነው። በተለይም አካባቢው በቀይ ባሕር እና በናይል ውሃ ተፋሰስ መሐል መገኘቱ የበርካታ ሀገራትን ቀልብ ሊስብ ችሏል። የቀይ ባሕር እና የናይል ፖለቲካ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትን በማወዳጀትም ሆነ በማራራቅ ከፍተኛ ሚና ያለውን ያህል አካባቢውን በቁጥጥራቸው ለማዋል ሕልም ያላቸውም ሀገራት የሚራኮቱበት ነው።
ቀይ ባሕር በተለይ ከስዊዝ ካናል መከፈት ጋር ተያይዞ የዓለም የንግድ ኮሪደር ለመሆን ችሏል። ቀይ ባሕርን የመቆጣጠር ፍላጎት የዓለም ኃያልን ሀገራት ሁሉ ምኞት ነው። እነዚህ ሀገራት ኢትዮጵያ እንዳትቀናቀናቸው የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ከአካባቢው እንድትርቅ አድርገዋታል።
የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና በአጠቃላይ 8 አገ ሮች አሉ። እነዚህ አገሮችም በሚጠቅማቸው በሚያዋጣቸው አካሄድ ላይ እየተመካከሩ ያለውን ችግር ለመፍታት በቂ እውቀትም ችሎታም ያላቸው ናቸው። ኢጋድ መጀመሪያ ሲቋቋም ዓላማው ረሀብንና ድርቅን መቋቋም ነበር። ነገር ግን ይህም ሌላኛው ድርቅ በመሆኑ የተፈጥሮ ሀብታችንን አብረን የምናለማበት የምንጠቀምበት ሁኔታ ሊመቻች ስለሚገባው ይህንንም አብሮ ማየት ሳያስፈልግ አይቀርም።
ኢትዮጵያም ለጎረቤቶቿ በሙሉ ውሃ ታቀብላለችና ይህንን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ሂደቷን ደግሞ በባሕር ወደቡ በኩልም በማምጣት ከጎረቤቶቿ ጋር ተስማምታ መጠቀምን ማስቀደም ይገባታል።
ይህ እንዲሆን ደግሞ ምናልባትም ብዙ ምክክር ውይይት የሚያስፈልግ ሲሆን ይህንን ካደረግን ደግሞ ችግሩን ፈተን በጋራ ተጠቃሚነታችን እንደሚጠናከር አምናለሁ።
ወንድም እህቶቻችን አፋሮች የድንበር ጠባቂ ሆነው አገልግለውናል፤ አሁንም እያገለገሉን ነው። የጠረፉ ንግድም በቀጥታ የሚያያዘው ከእነሱ ጋር ነው። ደገኛው ቆላ ውስጥ መኖር አይችልምና ሥልጣኔዎች ደግሞ በብዛት ያሉት ደጋው ላይ ነው፤ ቆላው ከአየር ንብረቱ የተነሳ ለመኖር ምቹ ስላልሆነ ሰፋ ያለ ሕዝብ ላይሰፍርበት ይችላል፤ በመሆኑም ደጋው ወደ ቆላ ወርዶ የሚነግድበት ሁኔታ ነበር፤ እስከአሁንም አለ። የወደቡ ጥያቄ በ16ተኛው ክፍለ ዘመን ኦቶማኖችና ቱርኮች ያደረጉት መራኮት አካባቢውን አናውጦት የነበረ ሲሆን እኛም ብዙ ጉዳቶችን አስተናግደናል። በዚህም ምፅዋንና ሌሎች ቦታዎችን እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ኦቶማኖች ይዘውት ነበር።
ከዛ ደግሞ ሲውዝ ካናል ሲከፈት መራኮቱ በረከተ። ሁሉም ቅኝ ገዢዎች የሚፈልጉት ቦታ ሆነ። በተለይም ሕንድን ቻይና አፍሪካ ላይ የሚያደርጉትን የንግድ አንቅስቃሴ በግማሽ ስላሳጠረላቸው በሂደት ደግሞ አካባቢው የነዳጅ ሀብት የሚተላለፍበት መሆኑ ተፈላጊነቱን ጨመረው። እዚህ ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ድርሻ አለና ቅኝ ገዢዎቹ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ያደረጉት ደባ ጅቡቲንም ኤርትራንም ሱማሊያንም ከአፍሪካ ቀንድ በታተነው። የኢትዮጵያ የወደብ ድርሻዋም ራቀ።
ከፋሺስት ጦርነት በኋላ በነበረው ጊዜ ደግሞ ኤርትራ ወደእናት ሀገሯ ተመልሳ በሰላም እንኖር የነበረ ቢሆንም በየጊዜው የነበሩ መሪዎቻችን የማይሆን አይነት ውሳኔ ወስነው አሰብን አስወሰዱ።
ነገር ግን በወቅቱ አሰብን ልናስቀርበት የምንች ልበት ታሪካዊ ሕጋዊና ሌሎች ብዙ ነገሮች እያሉ የተሳሳተ ውሳኔ በመወሰናቸው ምክንያት ዛሬ የደረስንበት ደረጃ ላይ እንድንደርስ ምክንያት ሆኗል።
አሁንም ቢሆን ግን የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት ወይም ጥያቄ በሰላምና በውይይት በምክክር ይፈታ ዘንድ እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብታችንን በጋራ የምናለማው እንጂ የምንራኮትበት ሊሆን አይገባም።
አሁን ባለው ሁኔታ የሕዝብ ቁጥራችን ከ120 ሚሊዮን በላይ ደርሷል። ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የያዘችን ሀገር ያለወደብ ትቀጥል ማለት ኢ-ፍትሐዊነት ነው። ለቀጣናውም አስቸጋሪ ነው። በመሆኑም ይህንን ሰፊ መስመር በሰላም ለመጠቀም ውይይት ምክክር የምሑራን ሚና ከፍተኛ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በአካባቢው ኢትዮጵያ ሚናዋ እየቀጨጨ መምጣቱ እንደሀገር ምን አሳጥቶናል?
ረ/ፕሮፌሰር አሕመድ፦ ባለፉት ሠላሳና ምናምን ዓመታት ባሕር በር አልባ መሆናችን ስፍር ቁጥር የከሌለው ጉዳት አስከትሎብናል ያጣናቸው ነገሮችም ብዙ ናቸው። እንደ አገር ወጪ ገቢ ንግዳችን ተስተጓጉሏል፤ ወጪያችንም በጣም በዝቷል፤ እንደልባችን የጦር መሣሪያም ሆነ ሌሎች ነገሮችን ማስገባት ሳንችል ቀርተናል። ይህንን ችግር ለማስቀረት ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንዳሉት በርካታ አማራጮችን ማየት ያስፈልገን ይሆናል። ለምሳሌ ወደብ አልባ ከሆኑ ጎረቤቶቻችን ጋር ወደብን በጋራ ማልማት፤ ኢትዮጵያ ከምታለማቸው መሠረተ ልማቶች ጥቂቱን ሰጥቶ ወደብ ማግኘት፤ የቦታ ቅይይር ማድረግና የመሳሰሉትን መጠቀም ይጠቀሳል። ይህንን ሁሉ ስናደርግ ሰላማዊ ሂደትን በመከተል ግን የመጀመሪያ አማራጫችን ማድረጉንም መዘንጋት አያስፈልግም።
በሌላ በኩል ግን ውስጣዊ ሰላም ማረጋገጥ የቅድሚያ ቅድሚያ ሊያገኝ የሚገባው ነገር ነው። ምን ጊዜም ቢሆን የሀገር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረት ማደረግ ከመንግሥትም ይሁን ከእኛ ከዜጎች የሚጠበቅ የቤት ሥራ ነው። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የውስጥ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል። ሌላው ደግሞ በእያንዳንዱ ዜጋ ውስጥ የአገር ፍቅር ስሜት ዘልቆ ሊገባ ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ ከለውጡ ወዲህ በቀጣናው ላይ የኢትዮጵያን ሚና ለማጎልበት እየተሠራ ያለውን ሥራ እንዴት ይመለከቱታል ?
ረ/ፕሮፌሰር አሕመድ፦ ጥሩ ነው መሪዎችም በብዛት ንግግሮችን እያደረጉ ነው፤ ምናልባት ሁሉም ነገር መስመር እስኪይዝ ድረስ አንዳንድ አስቸጋሪ ነገሮች መኖራቸው የማይቀር ነው። ለምሳሌ ሶማሊያና ኢትዮጵያ አንዳንድ ስምምነቶችን አድርገው ነበር፤ የራሱ የሆነ ድክመት የነበረበት ቢሆንም፤ ነገር ግን አሁን ደግሞ 8ቱንም የኢጋድ አባል ሀገራት በማወያየት ሥራዎች እየተሠሩ ነው። በመሆኑም ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል የዓለምን ነባራዊ ሁኔታዎች እያዩም ውይይትና ምክክሮቹ በዛም መልክ እንዲሄዱ ማስቻል ወደውጤቱ ያቀርበናል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፦ ሰላማዊ አማራጮችን በመጠቀም የወደብ ባለቤትን ለማረጋገጥ የተወሰዱ ዓለማቀፋዊ ተሞክሮዎች ካሉ ቢያብራሩልን ?
ረ/ፕሮፌሰር አሕመድ፦ የዓለም ተሞክሮ የሚያሳየን ሁሌም ቢሆን ሰጥቶ መቀበል ወሳኝ መሆኑን ነው። በመሆኑም የፖለቲካ ሂደቶቻችን ችግር የሚመዝ ሳይሆን ችግር ፈቺ ይሆን ዘንድ መጀመሪያ በኢጋድ በኩል ያሉ አባል አገራት ቁጭ ብለው መወያየት መቻል ይኖርባቸዋል።
በመሠረቱ ሁሉም ቢሆኑ የውጭ ጫና ውስጥ ስለመሆናቸው እንገነዘባለን። ነገር ግን ውይይታቸውም እነሱን ታሳቢ ያደረገ አድርገው በአጠቃላይ ግን የራሳችንን ችግር ራሳችን እንፈታለን ብለው በአንድነት መቆምን መልመድ ይገባቸዋል።
ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን ከባልሽ ባሌ ይበልጣል አይነት ግብ ግብ ውስጥ ከተገባ ግን ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። በመሆኑም ደግሞ እለዋለሁ 8ቱ ሀገራት መሪዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ በሁኔታው ላይ እንዲወያይ መድረክ ማመቻቸትና መክፈት ይገባል። ይህንን ማድረግ ከተቻለና መሠረት ከተያዘ ማስማማቱ ብዙም ከባድ አይሆንም።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ጊዜ በጣም አመሰ ግናለሁ።
ረ/ፕሮፌሰር አሕመድ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም