ቴክኒክና ሙያ ተቋማት 600 ሺህ ተማሪዎችን ለመቀበል ተዘጋጅተዋል

አዲስ አበባ፡- 12ኛ ክፍል ካጠናቀቁት ተማሪዎች ውስጥ በዘንድሮው ዓመት በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚገቡ 600 ሺህ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት መደረጉን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር ከ700 በላይ የመንግሥትና ከ900 በላይ የግል የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት አሉ። እነዚህ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት 600 ሺህ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት አድርገዋል።

የትምህርት ተቋማቱ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የ2016 ዓ.ም የቴክኒክና ሙያ ሠልጣኞችን እንደሚቀበሉ የገለጹት ዶክተር ተሻለ፤ በዘንድሮው ዓመት 600 ሺህ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሠልጠን የሚያስችል በቂ የትምህርት ግብዓት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በቴክኒክና ሙያ ሥርዓተ ትምህርት በየዓመቱ ከሚሠለጥኑት የመደበኛ ፕሮግራም ሠልጣኞች በተጨማሪ በአጫጭር ሥልጠናዎች ሁለት ሚሊዮን ዜጎች የሚሠለጥኑበት ዘርፍ መሆኑን አስታውቀዋል።

የቴክኒክና ሙያ ሥርዓት ሰፊና በርካቶችን የሚያገለግል መሆኑን ገልጸው፤ ዘርፉን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ግብዓት እየተሟላ መሆኑንም አስረድተዋል።

የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሩክ ከድር በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት አሠልጣኞችንና አመራሮችን የሚያሠለጥን በመሆኑ ከመላ ሀገሪቱ ለሥልጠና የሚመጡ ሰዎች በመመልመል ለማሠልጠን የሚያስችል ዝግጅት እያከናወነ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።

በኢንስቲትዩቱ አዲስ የቅበላ ፖሊሲ የተዘጋጀ መሆኑን በመግለጽ፤ በርካታ ሠልጣኞችን ተቀብሎ ለማሠልጠን የሚያስችል አቅም መፈጠሩን አመልክተዋል።

ኢንስቲትዩቱ ከደረጃ 6 ጀምሮ የሚገኙ መደበኛ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናዎችን እንዲሁም በተለያዩ የሥልጠና ደረጃዎች ተማሪዎችን ተቀብሎ ያሠለጥናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሠልጣኞችን ብቃት ያላቸው ሙያ እንዲሆኑ የሚያስችል ትምህርት ይሰጣል ብለዋል።

በአጫጭር ሥልጠናዎች በርካታ ዜጎችን በተለያዩ ሙያዎች በማሠልጠን ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሠልጣኞችን በመቀበል እንደሚሠራ ተናግረዋል።

በሀገሪቱ በርካታ የመንግሥትና የግል የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት መኖራቸው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ማዕከላትን የሥልጠና ጥራትና ፍትሐዊ ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሠራ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You