የትግራይ ክልል የተደራጁ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- በትግራይ ክልል የህብረተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅና ሰላምን ለማረጋገጥ የተቋቋመው ግብረ ሃይል ወደ ሥራ መግባቱን በትግራይ ክልል የጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ተናገሩ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፤ የትግራይን ሰላም እና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሥራዎች ተጀምረዋል። በመሆኑም መቐለ ከተማ ላይ ማዕከል ያደረጉ የዝርፊያ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር ግብረሃይሉ ተቀናጅቶ በመሥራት ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሠራ ነው።

በከተማው ከ2013 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም የተሰሩ ከባድ ወንጀሎችን በተመለከተ የምስል ማስረጃ መያዙን በመጥቀስ፤ እነዚህን ወንጀለኞች ወደ ሕግ ለማቅረብ በቁጥጥር ስር የማዋሉ ሥራ መጀመሩን አመልክተዋል።

በተለይ ከመሬት ወረራ ጋር ተያይዞ ግልፅ መረጃ መያዙንና መሬት መሸጥ እና መለወጥ እንዲቆም በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ለህብረተሰቡ ግልፅ መደረጉን ተናግረዋል። በዚህ ዙሪያም ራሱን የቻለ ግብረ ሃይል ተደራጅቶ ሥራውን መጀመሩን አስረድተዋል።

እንዲሁም ኮንትሮባድ እና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚያከናውኑ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ግብረ ሃይል መቋቋሙን ጠቅሰው፤ የተደራጁ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ሥራ ዋነኛው ዓላማ የትግራይ ሕዝብ ሰላም እና ፀጥታ እንዲጠበቅ እንዲሁም የሕግ ልዕልናን ለማስከበር መሆኑን ጠቁመዋል።

የግብረ ሃይሉ ዋነኛ አካላት ፖሊስ፣ የከተማ መስተዳድር እና የሕግ ባለሙያዎች መሆናቸውን የገለፁት ሌተናል ጀነራሉ፤ ሥራው በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑንም ገልፀዋል። ሕዝቡ አሁን የተጀመረውን ሕግ የማስከበር ሥራ በመደገፍ ከአስተዳደሩ ጎን ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።

እስከ አሁን በተገኘው መረጃ መኪኖች እና ሌሎች ንብረቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጠቅሰው፤ ሥራው ሲጠናቀቅ ግብረ ሃይሉ ሙሉ መረጃ እንደሚሠጥ አብራርተዋል። በመሆኑም በትግራይ ክልል ውስጥ የሕግ ልዕልና ለማረጋገጥ የማያስችሉ እና ሌሎች ወንጀሎች እንዳይበራከቱ እንዲሁም ሕገ ወጥ ተግባራትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሥራዎች እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም

Recommended For You