መቻል የራሱን ሜዳ ለመገንባት ጥረት ጀምሯል

በኢትዮጵያ ስፖርት እድገት ውስጥ የጎላ ሚና ካላቸው ክለቦች መካከል አንጋፋው መቻል የስፖርት ክለብ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። መቻል በተለይም በእግር ካሱ የቀድሞ ገናናነቱን ለማስመለስና ከውጤታማ የአህጉሪቱ ክለቦች ተርታ ለመሰለፍ 80ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ምክንያት አድርጎ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በዚህም በዘመናዊ መልኩ የተደራጀ፣ የራሱ የስፖርት ማዘውተሪያ ያለው እና የስፖርት ክለብነት መስፈርትን ያሟላ የማድረግ እንቅስቃሴው ከ80ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓሉ ጋር ተቆራኝቶ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

‹‹መቻል ለኢትዮጵያ›› በሚል ሃሳብ ሲከበር የቆየው የምሥረታ በዓሉ በተለያዩ ኩነቶች ክለቡ ለኢትዮጵያ ስፖርት እድገት ያበረከተውን አስተዋጽኦ በመዘከር እና ወደ ፊትም አጠናክሮ ለማስቀጠል ባለመ ሁኔታ መከበሩ ይታወሳል። በዚህም ክለቡን ሊያጠናክሩና ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ግብዓቶች መገኘታቸውን ክለቡ አስታውቋል። 30ሺ ሰዎችን ያሳተፈው የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድርም ውጤታማ በመሆኑ በየዓመቱ የመቻል ዓመታዊ የሩጫ ውድድር በሚል ቀጣይነት እንዲኖረው ታስቧል። ክለቡን በገንዘብ አቅም ለመደገፍና ለማጠናከር ታስቦ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የታደሙበት የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶንም ከፍተኛ ገንዘብ የተሰበሰበበትና ውጤታማ ነበር። ከ500 በላይ ሕዝብ በተሳተፈበት የገቢ ማሰባሰቢያ ከ500 ሚሊዮን በላይ በጥሬ ገንዘብ እና ከ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በዓይነት ተገኝቷል። በዚህም መሠረት ክለቡ ከእቅዱ 99 ከመቶ የሚሆነውን እንዳሳካ አሳውቋል።

ክለቡ በያዘው እቅድ፣ በተገኘው የገንዘብና የሃሳብ ግብዓቶች መሠረትም በቅርቡ የማዘውተሪያ ሜዳ ግንባት ሥራ ለመጀመር ማሰቡን ቦርዱ ጠቁሟል። በ80ኛ ዓመት ክብረ በዓሉ ላይ የተገኙትን ጠቃሚና ክለቡን የሚያጠናክሩ ግብዓቶችን በመያዝ ክለቡ የሚጠቀምበትን የመለማመጃና የመጫወቻ ሜዳ ግንባታን ለማስጀመርም ነው ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

ክለቡ በክብረ በዓሉ ያገኘውን ስኬት ተከትሎም አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋናውን ያቀረበ ሲሆን የምስክር ወረቀትም ሰጥተል። የክለቡ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ሰይፉ ጌታሁን በ80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ለመሥራት የታቀዱት ሥራዎች በስኬት መጠናቀቃቸውን አስረድተዋል። በገቢ ማሰባሰቢያው ቴሌቶን ከፍተኛ ገንዘብ በመሰብሰቡ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሜዳና የፋሲሊቲ ሥራዎች እንደሚጀመሩም ጠቁመዋል። የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋች ፖርቹጋላዊ ሉዊስ ካርሎስ አልሜይዳ (ናኒ) ክለቡን በመጎብኘቱ ከአፍሪካም አልፎ በዓለም እንዲተዋወቅ ማድረግ ችሏል። ከክለቡ ጋርም ለመሥራት አጋርነቱን በማሳየት ጉብኝቱን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

የክለቡን የቀደመ ዝና ለመመለስ ጥረት የተደረገ መሆኑን በማስታወስም ይህን ወደፊት አጠናክሮ ለመቀጠል የራሱ ሜዳ ኖሮት ተፎካካሪና ውጤታማ የስፖርት ክለብ ለማድረግ እንደሚሠራም የቦርድ ሰብሳቢው አክለዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የስፖርት እንቅስቃሴ እንዳለ ቢታሰብም የማዘውተርያ ሥፍራዎች ግን በበቂ ሁኔታ የሉም። ክለቡ በ80 ዓመታት ጉዞው ብዙ ፈተናዎችን ያሳለፈና ድጋፎች እንዳይደረጉለትም ጥረት የሚደረግበት ተቋም ነበር። ችግሮችን አልፎ እዚህ የደረሰው መቻል ወደ ተሻለ ደረጃ እየሄደ ያለ በመሆኑ የቦርዱ ትልቁ ሥራ ክለቡ ጥራቱን የጠበቀ የራሱ የመለማመጃ ሜዳ እንዲኖረው ማድረግ ነው። የኢትዮጵያ ስፖርት በመንግሥት በጀት የሚንቀሳቀስና የራሱን ገቢ የማያመነጭ ነው። መቻል ደግሞ በያዘው እቅድ መሠረት ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ወደ እንቅስቃሴ ገብቷል።

የክለቡ ዳይሬክተር ኮሎኔል ደረጄ መንግሥቱ በበኩላቸው፤ ለክብረ በዓሉ ከተያዙ አብዛኞቹ እቅዶች መሳካታቸውን ተናግረዋል። ይኸውም በአመራሩ ብቻ ሳይሆን በጸጥታ አካል፣ ከተማ አስተዳደሩ እና የመገናኛ ብዙሃን ጥረት ነው ብለዋል። በመሆኑም ለክለቡ እቅድ መሳካት ከፍተኛ ድርሻ ለተወጡት አካላት ምስጋና አቅርበዋል። የክለቡ የቴክኒክ ዳይሬክተር ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱም የተደረጉት እንቅስቃሴዎች ክለቡን ለማጠናከር የሚችሉ ግብዓቶች የተሰባሰቡበት መሆኑን ገልፀዋል። ክለቡ ዘንድሮ በፕሪሚየር ሊግ ተፎካካሪ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን በቀጣይ ክፍተቶቹን በማረም ጠንካራ ቡድን ይዞ ለመቅረብ ዝግጅት መጀመሩንም ጠቅሰዋል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You