በከተማዋ በክረምት በጎ ፍቃድ 250 የአረጋውያን ቤቶች እድሳትና ግንባታ ሥራ ተጀምሯል

ሃዋሳ፡- በሀዋሳ ከተማ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት 250 የአረጋውያን እና የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች እድሳትና ግንባታ ሥራ መጀመሩን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።

የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በከተማዋ በዘንድሮ በ2016 ዓ.ም ክረምት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት 250ሺህ ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ።

ከሚከናወኑት የበጎ ፍቃድ ሥራዎች ውስጥ አንዱ በሰው ተኮር ተግባራት የአረጋውያን ቤቶች እድሳትና ግንባታ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መኩሪያ፤ በያዝነው ክረምት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የ250 ቤቶች ግንባታና እድሳት መጀመሩን ገልጸዋል።

በከተማዋ በክረምት በጎ ፍቃድ ሥራዎች 17 ተግባራት ተለይተው ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመው ፤ በመርሃ ግብሩ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለዕረፍት ወደ ቤተሰቦቻቸው የተመለሱ ተማሪዎችን እና መደበኛ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶችን በማስተባበር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት 130 ሺ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ገልጸው፤ ወጣቶቹ በሚሠጡት አገልግሎት ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚያስቀር አመላክተዋል።

የከተማዋ ወጣቶች በተነሳሽነት ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ተናግረው፤ በበጎ ፍቃድ የደም ልገሳ መርሃ ግብር ወጣቶቹ በነቂስ እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

የከተማዋ ከንቲባን ጨምሮ የከተማዋ አመራሮችም አስቀድመው የደም ልገሳ በማከናወን ለወጣቶቹ የአርዓያነት ተግባር ማከናወናቸውንም አውስተዋል።

የወጣቶቹ ተሳትፎ አበረታች መሆኑን ጠቁመው፤ የከተማዋን መሠረታዊ ችግሮች በሚፈታ መልኩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ትልልቅ ባለሀብቶች ጭምር እንዲሳተፉ በማድረግ በሕዝብ ተሳትፎ የላቀ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የዘንድሮ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር እቅዱ ከፍ ተደርጎ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አመልክተው፤ በሰው ተኮር ተግባራት ባለፈው ዓመት 100 ቤቶች መገንባታቸውንና በዘንድሮም ከዓምናው የተሻለ ዕቅድ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

በመተባበር እና በጋራ በመሆን ችግሮቻችንን መቅረፍ እንችላለን ያሉት አቶ መኩሪያ፤ ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በመሳተፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You