የዓለማችን ዋነኛ የጤና ስጋት ከሚባሉት መካከል የካንሰር ሕመም አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት እ.ኤ.አ በ2030 ባላደጉ ሀገራት የካንሰር ሕመም 70 ከመቶውን ድርሻ ይሸፍናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይህ መረጃ ካንሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ በየጊዜው አድማሱን እያሰፋ ስለመምጣቱ ይጠቁማል፡፡
ዶክተር ናትናኤል ዓለማየሁ የካንሰር ሕክምናና የፓሌዬቲፍ ኬር ባለሙያ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ በሜዲካል አስተባባሪነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ዶክተር ናትኤል እንደሚሉት ባላደጉት አገራት የካንስር ሕመም ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ ችግሩን በአግባቡ ለመቆጣጠር የሚያስችል ዕድል ጠባብ እየሆነ መጥቷል፡፡
ይህ እንዲሆን ያስገደደው ደግሞ በእነዚህ አገራት ያለው የድህነት እውነታ ነው፡፡ በቂ የሕክምና አገልግሎት፣ ተገቢ የግንዛቤ ዕውቀትና፣ አመቺ መሰረተ ልማት አለመኖሩ የካንሰር ሕሙማን ቁጥር እንዲበራከት ዕድል ፈጥሯል፡፡ ኢትዮጵያም በተጠቀሱት ችግሮች የምታልፍ ናትና የነዚህን አገራት ታሪክ ትጋራለች፡፡ በሀገራችን የካንሰር ሕክምናው ተጠናክሮ የተጀመረው ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ ይህ እስኪሆን ግን በተለያዩ ምክንያቶች በርካታ ወገኖቻችንን በሞት ተነጥቀናል፡፡
እንደ ዶክተር ናትናኤል ማብራሪያ፣ በየጊዜው ከሕመሙ ጋር በተያያዘ የሚመዘገብ ተጨባጭ መረጃ የለም፡፡ ይሁን እንጂ ለዓለም ጤና ድርጅት ከሚቀርበው ሪፖርት በመነሳት በዓመት ከ 66 ሺህ በላይ የካንስር ሕሙማን ሕክምናውን ይወስዳሉ፡፡
አሀዛዊ መረጃው ግን በአዲስ አበባ ሕክምናውን መውሰድ የቻሉትን ብቻ የሚመለከት ነው፡፡ የካንሰር ሕመም በየቦታው ከመስፋፋቱ ጋር ታይዞ ይህ ቁጥር ሁሉንም አካታች እንደማይሆን ይታመናል፡፡ የካንሰር ሕሙማንን ሕይወት ፈታኝ የሚያደርገው ሕመሙ መኖሩ የሚታወቀው የካንሰር ደረጃው የመጨረሻ በሚባል ሁኔታ ላይ ከደረሰ በኋላ መሆኑ ነው፡፡
‹‹እንዲህ አይነቶቹ ታካሚዎችም 70 በመቶውን የሕሙማን ድርሻ ይሸፍናሉ፡፡ ይህ አጋጣሚ በሰፋ ቁጥር የሕክምናውን ሂደት ፈታኝ ያደርገዋል›› የሚሉት ዶክተር ናትናኤል በሕመሙ ላይ የሚኖረው የመዳን ተስፋም አሳሳቢና የመነመነ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በሀገራችን የካንሰር ሕሙማን ቁጥር ለምን ጨመረ ለሚለው ብዙ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ አንደኛውና የመጀመሪያው የአብዛኛው ሰው የአኗኗር ባህርይ መቀየር ነው፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን በርካቶች ከተለመዱ አካላዊ እንቅስቃሴዎች የተገደቡ ሆነዋል፡፡
በእግር መጓዝ የሚቻለውን መንገድ በመኪና መሄድ፣ በደረጃዎች መራመድ ሲቻል በአሳንስር መጠቀም፣ አመጋገብ ላይ ምርጫ ባለማድረግና ሌሎችም እውነታዎች ለሕህመሙ መስፋፋት ሰበብ እንደሆኑ ይታሰባል፡፡
እንዲህ አይነቱ ምክንያት በከተማ ነዋሪዎች ላይ በግልፅ ቢስተዋልም በገጠር በሚገኙ ሰዎችም ከነዚህ አጋጣሚዎች በራቀ መልኩ ካንሰር እየተስፋፋ ይገኛል። ለዚህ ችግር በዋነኛኘት ምክንያት ይሆናሉ ተብሎ የሚገመቱ ከሰብል አያያዝ ጋር ተያይዞ የሚመርጧቸው የርጭት ግብአቶችና በአጠቃቀም ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ገበሬዎች ለምርቱ እንጂ ለራሳቸው ደህንነት ትኩረት አይሰጡም፡፡ እንዲህ አይነቱ ልማድም ለካንሰር ተጋላጭ ያደርጋቸዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡
ከኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚስተዋለው የኬሚካል አቅርቦት አካባቢን ለመበከል ታላቅ አቅም ይኖረዋል፡፡ ከምንም በላይ ግን ለካንሰር ሕሙማን ቁጥር መበራከት እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው በየጊዜው የምርመራ አቅም መጨመርና የሕክምና ልማድ መጠናከር ነው ይላሉ ዶክተር ናትናኤል፡፡
ቀድሞ በሌላ ሰበብ ይፈረጁ የነበሩ በሽታዎች ሁሉ አሁን የካንሰር ሕመም መሆኗቸው እየተረጋገጠ ነው፡፡ እንዲህ ለመሆኑ አንዱ ምክንያት የረቀቀ የምርመራ መሳሪያ መኖሩና በሕብረተሰቡ ዘንድ ሕክምና እየተለመደ መሄዱ እንደሆነ ይታመናል፡፡
የካንሰር ሕመም በአንድ ወቅት አስበውት ብቻ የሚተውት አይደለም፡፡ ችግሩ ውስብስብና አሳሳቢ በመሆኑ ከመነሻ እስከ መድረሻ በጥልቀት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ካንሰርን በተመለከተ ሕብረተሰቡ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሊጠናከር ይገባል፡፡ ከብዙ ተሞክሮዎች ለማወቅ እንደሚቻለው በርካታ ሰው ሕመሙ እየታየበት ‹‹ይሻለኛል›› በሚል መዘናጋት ቀን የሚቆጥር ነው፡፡ ይህ ልማድ ቀጥሎ ታማሚው እንዳይጎዳ አስቀድሞ ሕክምና የሚያገኝበት መንገድ ሊኖር ግድ ይላል፡፡
ችግሩ በምርመራ ታውቆ አስቸኳይ ሕክምና እንዲጀመር አለማድረግ ከወንጀል እንደሚቆጠር የሚናገሩት፤ ዶክተር ናትኤል በዚህ ሂደት ያለው ክትትል በወጉ ሊጠናከር እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ በሀገራችን በአሁኑ ጊዜ ከስድስት በማያንሱ ቦታዎች ላይ የካንሰር ማዕከላት ተከፍተዋል፡፡ በነዚህ ማዕከላት የራዲዮ ቴራፒ በማካሄድም ሕክምናውን ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ማዕከል ሳይጨምር በጅማና ሀሮማያ የጨረር ሕክምና ተጀምሯል፡፡ በተመሳሳይ በሀዋሳም በቅርብ ጊዜ ይጀምራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በጎንደርና መቀሌም አገልግሎቱን ለመጀመር እንቅስቃሴ ላይ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልም ሕክምናውን የመጀመር ውጥን ተይዟል፡፡
ዶክተር ናትናኤል እንደሚናገሩት፣ በካንሰር ጉዳይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድሀ አገራት ወሳኝ የሚባሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንዱና አማራጭ የሌለው የ‹‹ፓሊዬቲፍ ኬር›› ሕክምና ነው፡፡ የዚህ ሕክምና ዋና ትኩረት አንድ ሰው ካንሰር እንዳለበት ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ የሚደረግለት የድጋፍ ሕክምና ይሆናል፡፡
ከተለመደው ሕክምና ወጣ ባለ መልኩ በሚካሄደው ጉዞ የስነልቦና፣ የመንፈሳዊና አካላዊ ይዘት ያለው ድጋፍ ለታማሚው በሚያመች መልኩ እንዲደርስ ይሆናል፡፡ በዚህ የሕክምና ሂደት ማሕበረሰቡን ጨምሮ ቤተሰብን በሚያካትት መልኩ የሚሰጥ ሲሆን ለታማሚው የመኖር ሕልውና በእጅጉ አስፈላጊ የሚባል ነው፡፡
ዶክተር ናትናኤል በሙያቸው በሚያገለግሉበት የማቲዎስ ወንዱ ድርጅት ለካንሰር ሕሙማን በተለየ መልኩ የሚደረገው የስነ-ልቦና ድጋፍ ወሳኝ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር ያሉበት ሙያና ተቋም ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጎን ተሰልፎ በአጋርነት በመቀናጀት የጤና ፖሊሲዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የራሱን ጡብ አኑሯል፡፡
ለካንሰር አጋላጭ የሆኑ ምክንያቶችን ለማስቀረት በሚኖረው ኃላፊነትም ለአመጋገብ፤ ለትንቧሆ ልማድ፣ ለአካላዊ እንቅስቃሴና መሰል ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት በሕህክምናው ዘላቂ መፍትሄ እንዲገኝ አበክሮ መስራት የግድ ይላል፡፡
የካንሰር ሕመም ፈተና በታማሚው ላይ ብቻ አይወሰንም፡፡ ከችግሩ መከሰት በኋላ ቤተሰብ ጭምር በእኩል ይጋራዋል፡፡ ለሕክምናው ሲባል ከገጠር አዲስ አበባ የሚመጡ ሕሙማን ከእጃቸው አቅም ሲያጡ ከብቶቻቸውን ይሸጣሉ፤ ጥሪታቸውን አራግፈው ቤታቸውን ይዘጋሉ፡፡
እንዲህም ሆኖ ካሰቡት ደርሰው የልባቸውን አያገኙም። ለሕክምና ቀጠሮ ደጅ መጥናታቸው የግድ ነው፡፡ አቅም ሲጠፋ፣ መጠለያ ሲታጣ ደግሞ ከጎዳና የሚወድቁ የሌሎችን ምጽዋዕት የሚሹ ብዙ ናቸው፡፡ ዶክተር ናትኤል ለዚህ መረጃ አዲስ አይደሉም፡፡ ብዙሀኑ የገጠር ነዋሪ የካንሰር ሕሙማን የነዚህ ችግሮች ሰላባ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
ስለ ካንሰር ቀድሞ ከነበረው አመለካከት አሁን ያለው ግንዛቤ የተሻለ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ በሀገራችን ያለው የሕክምና አሰጣጥ ጠባብ መሆን በተለይ የገጠር ነዋሪውን ለእንግልት እየዳረገው ይገኛል፡፡ እንዲህ አይነቱ አሳዛኝ አጋጣሚ ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲን የመሰሉ ድርጅቶች ለመፍትሄ እንዲበረቱ አድርጓል፡፡
የካንሰር ሕሙማን ቀጠሮ በተሰጣቸው ጊዜ አካላቸውን አሳርፈው፣ አዕምሯቸውን እንዲያረጋጉ በማዕከላቱ የማረፊያ ቦታ ተዘጋጅቷል፡፡ በነዚህ ስፍራዎች የእንግድነት ስሜት የለም፡፡ በሁሉም ዘንድ የሚስተዋል ቤተሰባዊ ትስስርም ተፈጥሯል፡፡
አስታማሚ ቤተሰቦች ተካተው በሚስተናገዱበት ዕልፍኝ ምግብ፣ ትራንስፖርትና አስፈላጊ አቅርቦቶች ይሟላሉ፡፡ ለነዚህ ማዕከላት መቋቋም ምክንያት የሆነው ከገጠር ወደ አዲስ አበባ ለሕክምና የሚመጡ የካንሰር ሕሙማንና ቤተሰቦቻቸው እንግልት ነው፡፡
ዶክተር ናትናኤል አሁንም ድረስ በካንሰር ላይ ያለው አመለካከት ብዙ ስራ እንደሚያስፈልገው ይናገራሉ፡፡ ለዚህም እንደማሳያ የሚጠቅሱት ምሳሌ አለ፡፡ በሕክምናው አጋጣሚ የሚያገኙዋቸው አንዳንድ ሰዎች ‹‹ካንሰር ›› የሚሉትን ቃል ለመጥራት እንኳን አይደፍሩም፡፡ እንዲህ አይነቶቹ ቃሉን ደጋግመው ከጠሩት በሽታው ይበዛል፣ ይበረታል ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡
ይህ አይነቱ ግንዛቤ ከራስ አልፎ ቤተሰብ የሚጋራው በመሆኑ ለበሽታው መስፋፋት አንደኛው ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ በግልጽ ማውራትና መወያየት መገለልን አስወግዶ ለመፍትሄ የሚበጅ በመሆኑ ሁሉም ሊተገብረው ይገባል፡፡
የካንስር ምርመራና ሕክምናው በየትኛውም ዓለም ከፍተኛ የሚባል አቅምን የሚጠይቅ ነው፡፡ በአንዳንድ ያደጉ ሀገራትም የሕክምናውን ክፍያ ከኢንሹራንስ ለማስወጣት እስከ ክርክር የሚያደርስ ውዝግብ የሚታይበት ነው፡፡ ባላዳጉት አገራት ያለው እውነታ ደግሞ ከዚህም የከፋ ነው። ለምሳሌ አንድ ራዲዮ ቴራፒ ማሽን ለመትከል ከአምስት ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ወጪ ይጠይቃል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን አምስት ራዲዮ ቴራፒ ማሽኖች ተገዝተዋል፡፡ እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ስሌት ግን ለአንድ ሚሊዮን ሕዝብ የሚያስፈልገው አንድ ራዲዮቴራፒ ነው፡፡ በተመሳሳይ መድሀኒቶችን ገዝቶ ተደራሽ ለማድረግ የዋጋው ማሻቀብ ዋነኛ ፈተና ሆኖ ይጠቀሳል፡፡
መንግስት ለካንሰር ተብለው በሚገቡ መድሀኒቶች ላይ ሀምሳ በመቶው ድጎማ ያደርጋል፡፡ እንዲያም ሆኖ የዋጋው መናር ለብዙሀኑ የካንሰር ሕሙማን ከአቅም በላይ እየሆነ ነው፡፡ ይህን ግልጋሎት ከታሰበው ደረጃ ላለመድረስ ደግሞ ድህነትና የአቅም ማነስ ችግሮች እንቅፋት መሆናቸው አልቀረም፡፡
በዶክተር ናትናኤል የስራ ተሞክሮ በተለይ ከጡት ካንሰር ጋር ተያይዞ ያለው አመለካከት በርካታ ሴቶችን ይፈትናል፡፡ ለሕመሙ ቀዶ ሕክምና ባስፈለገ ጊዜ አብዛኞች አካላቸው እንዲወገድ አይሹም፡፡ ሕክምናው በስኬት ቢጠናቀቅ እንኳን ሁሉም ጉዳይ እንዳለቀ፣ እንዳበቃ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡
ይህ እምነታቸውም በናሙና ውጤቱ መሰረት ቀጥሎ ለሚኖረው የጨረር፣ የኬሞ ቴራፒና መሰል ሂደቶች ራሳቸውን እንዳያዘጋጁ ያደርጋቸዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ግን እንዲህ አይነቱ አመለካከት ፍጹም የተሳሳተ፣ ራስን የማይጠቅምና ጤናን አብዝቶ የሚጎዳ ነው፡፡
ይህ አይነቱ ችግር ባጋጠመ ጊዜ በጤና ባለሙያዎች ምክርና ድጋፍ የሚፈታ ይሆናል፡፡ እንደ ‹‹ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ›› የመሰሉ ድርጅቶች አስፈላጊው የመድሀኒት አቅርቦት እንዲኖር በማመቻቸት፣ የአቅም ችግር ላለባቸውም በውድ ዋጋ ጭምር ገዝቶ በመስጠት፣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ ይህ አይነቱ በጎ እንቅስቃሴም በካንሰር ምክንያት ሰዎች ተስፋ እንዳይቆርጡና ቤት ውስጥ የሚራብ ሰው እንዳይኖር ሚናው የጎላ ነው፡፡
እንደ ዶክተር ናትኤል አባባል 70 በመቶ የሚሆነው ካንሰር ከፍ ያለ ሕመም ይኖረዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ለሕሙማኑ ስቃይ ማስታገሻ የሚሆኑ መድሀኒቶች ሊኖሩ ግድ ይላል፡፡ በሀገራችን ቀደም ባሉ ዓመታት እነዚህ መድሀኒቶች ከውጭ ሀገራት በግዢ ይገቡ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ከገበያው ከጠፉ ቆይቷል፡፡
ለሕመሙ የሚያስፈልገውን ‹‹ሞሪፊን‹‹ መጠቀም በእኛ ሀገር ደረጃ በእጅጉ ፈታኝ የሚባል ነው፡፡ በግል የሚያስመጡ አቅራቢዎች እጅ ቢገኝ እንኳን ትክክለኛነቱን ጨምሮ ዋጋው የሚቻል አይደለም፡፡ ባደጉት አገራት ግን ‹‹ሞርፊን›› የሰብአዊ መብት ጉዳይ ነው፡፡ ዋጋውም ከአንድ ዶላር በታች መሆኑ ይታወቃል፡፡
ዶክተር ናትኤል ሞርፊንን ለሕሙማኑ ተደራሽ ለማድረግ እንደ ሌሎች አፍሪካ አገራት በሆስፒታል ደረጃ ቢገኝ በቀላሉ ቀምሞ መስጠት እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡ ለዚህ ተግባራዊነትም ሚዲያውን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ያሻዋል ባይ ናቸው፡፡
ካንሰርና የሕክምና ባሕርይው እንደ የአገራቱ ልምድና የኑሮ ሁኔታ ይለያያል፡፡ ባደጉት አገራት ሕሙማኑ መወሰድና መተው የሚፈልጉት መድሀኒትና ሕክምና የሚወሰነው በራሳቸው ፍላጎት ተመስርቶ ነው፡፡ በተመሳሳይ ይህን የግልጽነት ተሞክሮ በእኛ አገር ለመጠቀም ያዳግታል፡፡
በሕይወት ዘመን ፍጻሜ ስለሞት አስቀድሞ ማውራት በኢትዮጵያውያን ባህል የተለመደ አይደለም፡፡ እስካሁን ባለው ተሞክሮም አብዛኞቹ የመጨረሻ ሕቅታቸው በቤታቸው እንዲሆን የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ዶክተር ናትኤል እንደሚሉት ግን እነዚህን ፍላጎቶች ተሻግሮም ለካንሰር ሕሙማን አቅም የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይቻላል፡፡
የካንሰር ታማሚውን ባሕል ፍላጎትና ዕምነትን በማይጋፋ መልኩ የስነልቦና፣ የመንፈሳዊ ጥንካሬና የአካል ብቃትን ማጎልበት የተለመደ ነው፡፡ በዚህ ሂደትም በቤት ውስጥ ለሚኖር እንክብካቤና ሕክምና መልካም የሚባል ውጤትን ማየት ይቻላል፡፡
ከካንሰር ጋር ተያይዞ በተለይ በእኛ አገር ታማሚዎቹ የሚሞቱበት ጊዜ ተወስኖላቸው፣ ቀንና ሰዓት እየቆጠሩ የመጨረሻዋን ደቂቃ በጭንቀት እንዲጠብቁ ሲገደዱ ይስተዋላል፡፡ ይህ አይነቱ እውነትም ቤተሰብን ጨምሮ ጉዳዩን ለሚሰሙ ሁሉ የሚያሳቅቅ ይሆናል፡፡ ዶክተር ናትኤል ግን እንዲህ ዓይነቱን መሰረት የለሽ መላ ምት ፈጽሞ አይስማሙበትም፡፡
መረጃው ከየት እንደመጣ ባያውቁትም መልዕክቱ ግን ታማሚው ከተተነበየለት ጊዜ ቀድሞ እንዲያልፍ የማድረግ ኃይል እንደሚኖረው ይናገራሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ልማድ ስር ሰዶ እንዳይስፋፋም ሚዲያው፣ ማሕበረሰቡና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ሊታገሉት ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም