አዲስ አበባ፡– በኮንስትራክሽን ማኑፋክቸሪንግና በሲሚንቶ ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት መኖሩ ለሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች ቁልፍ ማነቆ መሆኑ ተገለጸ።
የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሃላላ በሸራተን ሆቴል የሲሚንቶ ቴክኖሎጂ መሪ መዛኞችና ባለሙያዎች የማጠቃለያ መርሃ ግብር በተካሄደበት ወቅት እንደተናገሩት በዘርፉ ከፍተኛ የሆነ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት መኖሩ ለኢንዱስትሪው ማነቆ ሆኗል።
ችግሩን ለመፍታትም ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም የኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ትስስሩን የበለጠ ማጠናከርና በሀገሪቱ ከሚገኙ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ከደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ጋር በትብብርበተዘጋጀው መድረክ ላይ የሲሚንቶ ቴክኖሎጂ መሪ መዛኞችና ባለሙዎችን በማስመዘንና ስልጠና በማስጀመር ሂደት የተገኙ ውጤቶችና ያጋጠሙ ችግሮችን የሚመለከት ሪፖርት ቀርቦ ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች ባለቤቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዶበታል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮንስትራክሽን ዘርፍ ቡድን መሪ አቶ ግርማ ለማ ችግሩ የተፈጠረው በሀገሪቱ ባሉ በሁሉም ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኮንስትራክሽን ማኑፋክቸሪንግና በሲሚንቶ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ምንም ዓይነት የትምህርትና የስልጠና መስክ ባለመኖሩ ነው ብለዋል። በተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች በሲሚንቶ ቴክኖሎጂና በማቴሪያል ሳይንስ የልቀት ማዕከል ለማቋቋም የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም ወደ ሥራ ባለመግባታቸው ዘርፉን መደገፍ አልቻሉም።
በመሆኑም የሲሚንቶ ማሰልጠኛ ማዕከላትና የስልጠና ማቴሪያሎች አለመኖራቸው ለሲሚንቶ ኢንዱስትሪው ማነቆ ሆኖበት ቆይቷል። ኢንስቲትዩቱ ከፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲና ልምድ ካላቸው የሙገር፣ መሰቦ፣ ደርባና ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ባለሙያዎችና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ጋር በመተባበር የሲሚንቶ ቴክኖሎጂ ሞዴል ካሪኩለም ተዘጋጅቷል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው መስራት የሚገባቸው መሆኑን አመላክተዋል።
የደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅና ሲሚንቶ ዘርፍ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኃይሌ አሰግዴ በበኩላቸው በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ ሰው ኃይል እጥረት ችግር ለመፍታት በሀገሪቱ ውስጥ የሲሚንቶ ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል አንድ ተቋም ሊኖር የሚገባ መሆኑን አመላክተዋል። ለዚህም በዘርፉ የተሰማሩ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ባለሀብቶችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለነገ ሳይሉ ቅድሚያ ሰጥተው መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2011
በይበል ካሳ