–ምርቱ የመጠቀሚያ ጊዜው ካለፈ ለማስወገድ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል፤
አዲስ አበባ፡- 400 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት 190 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ሳይውል ከአራት ዓመት በላይ መቆየቱን የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ከፍያለው ብርሃኑ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በግብርና ሚኒስቴር ትዕዛዝ በ2006 እና በ2007 ዓ.ም ፖታሽ፣ ዚንክና ቦሮን የተሰኙ ማዳበሪያዎችን ከውጭ ሀገራት ለማስገባት የወጣውን 320 ሚሊዮን ብር ጨምሮ ለመጋዘን ኪራይ፣ ለኢንሹራንስና ለሌሎች ጉዳዮች እስካሁን ድረስ 400 ሚሊዮን ብር የፈጀው ምርት ጥቅም ላይ አልዋለም።
ማዳበሪያዎቹ ሌሎች ግብዓቶችን በመጨመር በዩኒየኖች ተቀነባብሮ ለአርሶ አደሮች በማቅረብ ጥቅም ላይ እንዲውል ታስቦ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን ስራ አስፈፃሚው አስታውሰው ማዳበሪያ የሚያቀነባብሩ ዩኒየኖች ምርቱን ወስደው ለማቀነባበር ቢሞክሩም ማዳበሪያዎቹ አስቸጋሪ መሆናቸውን በመግለጽ መውሰድ አቁመዋል። በዚህም ምክንያት ማዳበሪያዎቹ ከአራት ዓመት በላይ መጋዘን ውስጥ ተከዝነው ለመቆየት ግድ መሆኑን አስረድተዋል።
ማዳበሪያዎቹን ዩኒየኖች ወስደው ለመጠቀም ፈቃደኛ አለመሆናቸውንና መፍትሄ እንዲፈለግለት ለግብርና ሚኒስቴር፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለሌሎች ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ማሳወቁን አብራርተዋል። የፓርላማ አባላትም በቦታው ሄደው ማዳበሪያውያለበትን ሁኔታ ጎብኝተዋል።
እንደ አቶ ከፍያለው ማብራሪያ፤ የግብርና ሚኒስቴር ከዩኒየኖቹ ጋር በመነጋገር እንዲጠቀሙ እንደሚያስደርግ የገለጸ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ዩኒየኖች ወስደው ለመጠቀም ፈቃደኛ አልሆኑም። እንዲያውም ከዚህ ቀደም የወሰዱት ማዳበሪያም ኪሳራ እንዳስከተለባቸው አመልክተዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ሄደው ማዳበሪያው ያለበትን ሁኔታ ተመልክተው የተመለሱ ቢሆንም እስካሁን መፍትሄ አልተሰጠም ይላሉ።
ለማዳበሪያው ግዥ ኮርፖሬሽኑ ከራሱ ካወጣው ወጪ በተጨማሪ ከባንክ ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ መበደሩን የሚያነሱት አቶ ከፍያለው፤ ማዳበሪያው ጥቅም ላይ ባለመዋሉ ብድሩን መመለስ አልቻለም። በመሆኑም የባንክ ብድር ወለዱም እያሻቀበ ነው።
የማዳበሪያው ዝርዝር መረጃ (ስፔሲፊኬሽን) በአግባቡ ሳይታወቅና እነዚህን ማዳበሪያዎችን አቀነባብሮ ለመጠቀም የሚያስችል ቴክኖሎጂ ሳይኖር ማዳበሪያው እንዲገባ መደረጉ ለተፈጠረው ችግር ምክንያት ሆኗል የሚሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ግዥው እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሰጠው የግብርና ሚኒስቴር በመሆኑ ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር በመሆን ማዳበሪያው ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ ሳይሆን መፍትሄ ሊያፈላልግለት ይገባል ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ ለመጋዘን ኪራይ በወር በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ገንዘብ እያወጣ የነበረ ሲሆን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኪራዩ አነስተኛ የሆነ መጋዘን ውስጥ በማስቀመጥ የመጋዘን ወጪ መቀነስ እንዳለበት አቅጣጫ ባስቀመጠው መሰረት በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በአሰላና በሌሎች የክልል ከተሞችም በሚገኙ አነስተኛ መጋዘኖች በማከማቸት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመጋዘን ኪራይ ወጪ መቀነስ የተቻለ ቢሆንም አሁንም ማዳበሪያው የተከማቸባቸው የኮርፖሬሽኑ መጋዘኖችም ለሌሎች አገልግሎቶች ሊውሉ የሚችሉና የገቢ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ መሆናቸውን ያብራራሉ።
እንደ አቶ ከፍያለው ማብራሪያ፤ ማዳበሪያዎቹ ከጥቅም ውጪ ሳይሆኑ የትኛው አፈር ላይ ሊውል እንደሚችል ጥናት ተደርጎ ያለ ክፍያም ቢሆን
ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ ቢደረግ በኮርፖሬሽኑ ብሎም በሀገር ሀብት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ተጨማሪ ኪሳራ መቀነስ ይቻላል። መፍትሄ ተፈልጎለት ጥቅም ላይ እንዲውል ሳይደረግ የመጠቀሚያ ጊዜው የሚያልፍ ከሆነ ወደ ውጭ ሀገራት ወስዶ ለማስወገድ የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪም መቀነስ ይቻላል። የመጋዘን ኪራይ ወጪም ማስቀረት ይቻላል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የገንዘብ ሚኒስቴር የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ውይይት ባደረገበት ወቅት፤ ተጠሪነቱ ለገንዘብ ሚኒስቴር የሆነው የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን በግብርና ሚኒስቴር ትዕዛዝ ከውጭ ሀገራት ያስገባው ማዳበሪያ ኮርፖሬሽኑንና ሀገሪቱን ለከፋ ችግር ሳይዳርግ ገንዘብ ሚኒስቴር ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ተገቢው የማጣራት ስራ ተሰርቶ ማዳበሪያው ለአርሶ አደሮች መከፋፈል ካለበት በነጻም ቢሆን ለአርሶ አደሮች እንዲከፋፈል በማድረግ፤ የማይከፋፈል ከሆነም ሌላ መፍትሄ ሊያበጅ እንደሚገባ መጠቆሙ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2011
በመላኩ ኤሮሴ