-የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ሊጠናከር ነው
አዲስ አበባ፡– አዲስ አበባ ከተማ በጦር መሣሪያ በታጠቁ ኃይሎች ጭምር በመታገዝ ከባድ ወንጀሎች ሲፈጸሙባት እንደነበር የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። ተቀዛቅዞ የነበረው የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎትን ለማጠናከር ከነዋሪዎች ጋር በመወያየት ሥራ መጀመሩ ታውቋል።
በኮሚሽኑ የኢንዶክትሬሽንና የህዝብ ግንኙነት ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት የፀጥታ ኃይሉ በሀገሪቷ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ይከሰቱ በነበሩ ሁከትና ግርግሮች ላይ ትኩረት በማድረጉና መረጋጋት አለመኖሩን ተከትሎ ለወንጀል ድርጊቱ መስፋፋት መንገድ ከፍቷል።
አንዳንዱ የወንጀል ድርጊትና ተሳታፊዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተለመደ መሆኑን የጠቆሙት ኮማንደር ፋሲካ ከፀጥታ ኃይል ጋር በመሣሪያ እስከ መከላከል የደረሰ መሆኑን አስታውሰው በተግባሩ የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ታርመው ከማረሚያ ቤት የወጡ ታራሚዎች በድርጊቱ ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸው የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙ ሰዎችን ለመያዝ በሚደረገው ጥረት የሚከላከሉ ሰዎች ማጋጠማቸውና የወንጀሉ ተለዋዋጭነት ወንጀሉን ከባድ እንዳደረገውና ስጋት መፍጠሩን አመልክተዋል።
እንደ ኮማንደር ፋሲካ ማብራሪያ ኮሚሽኑበጦር መሣሪያ በመታገዝ በቡድን በመደራጀት መኪናን ጨምሮ ሲከናወኑ የነበሩ የስርቆት፣ የቅሚያ፣ የዘረፋ፣ የነፍስ ግድያና ሙከራ፣ በድምሩ ለህብረተሰብ ስጋት ናቸው ብሎ በለያቸው 10 የወንጀል አይነቶች ላይ በተደራጀ መልኩ በመስራቱ በአሁኑ ጊዜ በጦር መሣሪያ የታገዘውን ዘረፋ ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት ችሏል።
በተለይ ከማረሚያ ቤት ወጥተው በዝርፊያ ላይ አግኝቶ የያዛቸውን የቀድሞ የወንጀል መዝገባቸውንና ሌሎችንም አሳማኝ ማስረጃዎች ለፍርድ ቤት በማቅረብ በጊዜ ቀጠሮ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ በማድረግ ችግሩን ለማስወገድ ተችሏል።
በመኪና፣በሞተርሳይክልና በተለያየ መንገድ ሲከናወን የነበረውን ዘረፋ የመቀነስ ሥራም ተሰርቷል። በዘጠኝ ወራት ጊዜ ከ12ሺ326 ወንጀሎች ወደ 825 ለመቀነስ ተችሏል። ኮሚሽኑ ተቋማዊ ማሻሻዎችን በመሥራት፣የፖሊስ ኃይሉንም በስልጠና በማብቃትና ከነዋሪው ጋር በትብብር በተሰራ ሥራ ውጤቱ መገኘቱን አመልክተዋል።
ኮሚሽኑ በሰራው ሥራ 24 ቡድን ያለው 124 ተጠርጣሪዎችን መያዙንና ከእነዚህ መካከል 49ኙ ከማረሚያ ቤት ታርመው የወጡ መሆናቸውን የጠቆሙት ኮማደር ፋሲካ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩትን ጨምሮ በሀሰተኛ መንጃ ፈቃድና ያለፈቃድ በወንጀል ድርጊት ውስጥ የነበሩ ከ10ሺ በላይ ሞተር ሳይክሎች፣ 10ሺ 732 በላይ ሽጉጦች፣ 30 ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎች፣ 99ሺ 785 የተለያዩ የጦር መሣሪ ጥይቶች፣18ሺ974 የክላሽንኮቭ እና የመትረየስ ጥይቶች፣ብረታብረቶች፣ አምስት ተሽከርካሪዎች፣መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ መያዛቸውን አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ሞዴል እንደነበር ያስታወሱት ኮማንደሩ አገልግሎቱ ከመቀዛቀዝ ወጥቶየተጠናከረ ሥራ ለመስራት በመጋቢትና ሚያዚያ ወራቶች ከ20ሺ በላይ ከሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ምክክር መደረጉንና ነዋሪዎችም የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት መግባባት ላይ መደረሱን አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ ውጤታማ የሆነ የወንጀል መከላከል ሥራ ለመስራት በሥራ አፈጻጸማቸው ልል የሆኑ የፖሊስ አባላትን ለህግ ተጠያቂ በማድረግና 824 የፖሊስ አባላትን ከሥራ በመቀነስ እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል።
በ56 ፖሊስ ጣቢያዎች ደረጃቸውን የጠበቁ የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ማዕከላት መኖራቸውን ጠቁመው ቢያንስ ግን በ808 የልማት ቀጠና ላይ አገልግሎቱ መኖር እንዳለበት በኮሚሽኑ እምነት ተይዟል።
ወንጀልን መከላከል ከቤት መጀመር እንዳለበትና በከተማዋ ወጥቶ መግባት ሥጋት እንደሆነ በሚናፈሰው አሉባልታ ነዋሪው ፍርሃት ውስጥ መግባት እንደሌለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2011
በለምለም መንግሥቱ