አዲስ አበባ፡- ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ላለው ለውጥ እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ።
የኢፌዴሪ 28ኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን በቅርቡ የተሾሙት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ጋር በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ በስካይላይት ሆቴል ትውውቅ አድርገዋል።
በዚህ ወቅት ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በመካሄድ ላይ ናቸው። ለውጡ ከመጀመሪያው ግልጽ ግብ አስቀምጦ የተካሄደ ነው ብለው በፖለቲካው ዘርፍ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታትና በስደት የነበሩ ፖለቲከኞች በሀገር ውስጥ ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ተደርገዋል።
ከእስር የተለቀቁና ከውጭ ሀገራት የገቡ ፖለቲከኞች በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል።ከዚያ ባሻገር የፍትህ ሥርዓቱንና የምርጫ ቦርድን ሪፎርም በማድረግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራበት መሆኑንም አቶ ገዱ አስረድተዋል።
የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ ዘርፉ ለግሉ ዘርፍ ኢኮኖሚውን የበለጠ ክፍት የማድረግ ስራ መሰራቱን የተናገሩት አቶ ገዱ ፤የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይም ማሻሻያዎች በመካሄድ ላይ መሆኑን አንስተዋል።
እንደ አቶ ገዱ ማብራሪያ የተካሄዱና በመካሄድ ላይ ያሉ የማሻሻያ እርምጃዎች ሀገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የምታደርገውን ሽግግር ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርጉ ናቸው።የማሻሻያ እርምጃዎቹ በታሰበው አቅጣጫ እየሄዱ ቢሆንም የተለያዩ ተግዳሮቶች እያጋጠሙ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የተለያዩ አጋር አካላት በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ለተወሰዱ የፖለቲካና ኢኮኖሚ
ማሻሻያዎች በተለያዩ መንገዶች ድጋፋቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።አሁንም ቢሆን ለውጡን ቀጣይነት ያለው ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ በመቀጠል ለለውጥ ሪፎርሙ ስኬታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡጠይቀዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደምም ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላም፣ መረጋጋትና የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስታበረክት ቆይታለች ብለዋል።በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በመካሄድ ያለው የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ለሀገሪቱ ለሰላምና መረጋጋት ከሚኖረው አስተዋጽኦ ባሻገር ለቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ውህደትም ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2011
በመላኩ ኤሮሴ