በሀገሪቱ ውስጥ ከ108 በላይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቢኖሩም እንወክለዋለን ከሚሉት ሕዝብ ጋር ያላቸው ግንኙነት ደካማ መሆኑ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ያሳያል። የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የሚያውቁ አካላትም የሚመሰክሩት ይህንኑ ሀቅ ነው። የዚህ ችግር መንስኤ ምንድነው? ፓርቲዎቹ ከሕዝቡ ጋር በበቂ ሁኔታ ላለመገናኘታቸው ተጠያቂው አካልስ ማንነው?
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ፤ ቦርዱ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና ድህረ ምርጫ ወቅቶች ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በስተቀር ፓርቲዎች ከሕዝብ ጋር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አይከታተልም። ከእነኝህ ወቅቶች ውጪ ባሉት ጊዜያት ማንኛውም ፓርቲ በማንኛውም ጊዜ በፈለገው መንገድ ከሕዝብ ጋር እንዳይገናኝ የሚከለክል ሕግ እንደሌለ አማካሪዋ ግልጽ አድርገዋል።
ስለሆነም የቦርዱ ዋና ኃላፊነት ምርጫና ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መምራት መሆኑን አስረድተው፤ «ፓርቲዎች ከሕዝቡ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተ ሥራው የራሳቸው የፓርቲዎች ነው» ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል።
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ፓርቲዎች ከሕዝብ ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት በሦስት ይከፍሉታል። ፓርቲ ያልሆኑና ከሕዝብ ጋር መገናኘት የማይፈልጉ በስመ ፓርቲ የሚኖሩ አሉ የሚሉት ሊቀመንበሩ «እነዚህ የመንግሥት ቅልቦች ስለሆኑ ፓርቲ አይደሉም። ፓርቲ ስላልሆኑም መመረጥ ሥራቸው አይደለም» ብለዋል።
«ከሕዝብ ጋር መገናኘቱም አስፈላጊያቸው አይደለም፤ እነዚህ ፓርቲዎች ባለፉት ጊዜያት ከመንግሥት ጎን ተሰልፈው የሕዝቡን ድምጽ ሲሸጡ የነበሩም ስለሆኑ ሕዝቡ ድንጋይ ሊወረውርባቸው ይችላል» ሲሉም ፕሮፌሰሩ ወቀሳ አዘል ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።
በሁለተኛነት የሚያነሱት ፓርቲዎቹ የማይንቀሳቀሱበት አሊያም ከሕዝብ ጋር የማይገናኙበት ምክንያት ጉዳት ሊደርስብን ይችላል በሚል ፍራቻ ሊሆን ይችላል የሚል ነው።በሁለተኛ ደረጃ ፓርቲም ሆነው ከመንግሥት ጋር ባላቸው መልካም ያልሆነ ግንኙነት ምክንያት በሚፈለገው መንገድ የማይንቀሳቀሱና ከሕዝብ ጋር የማይገናኙ እንዳሉም ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።
ስለሆነም በዚህ ምክንያት እንቅስቃሴያቸው የተገደበ ፓርቲዎች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ሌሎች ደግሞ የቻሉትን ያህል ከሕዝቡ ጋር የሚገናኙ አሉ ብለዋል።ያም ሆኖ የአቅም ውስንነትም ፓርቲዎች እንደ ልብ እንዳይንቀሳቀሱና ከሕዝብ ጋር እንዳይገናኙ እያደረጋቸው ነው ሲሉ አመልክተዋል።
ፓርቲዎች ከሕዝብ ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት የሚኖረውን ፋይዳ በተመለከተም ፕሮፌሰር መረራ፤ «ከሕዝብ ጋር የማይገናኝ ፓርቲ ፓርቲ አይደለም» በማለት በአጭሩ ያስቀምጡታል።እንደ እርሳቸው ገለጻ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ፓርቲ ለመባል ሕዝብን ማንቃት፣ ማስተማርና ማደራጀት አለበት።
«ፖለቲካ ፓርቲዎች ብሔርን ወይም ማንነትን መሠረት አድርገው መደራጀታቸው ብሔሩ ከሚገኝበት ክልል ውጪ ባሉ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዳይንቀሳቀሱ ስለሚያደርግ ይህስ በራሱ ፓርቲዎች ከሕዝብ ጋር ለሚያደርጉት ግንኙነት ችግር አይሆንም ወይ?» ተብለው የተጠየቁት ፕሮፌሰር መረራ «የሕዝብ ድጋፍ በሚያገኙበት አካባቢ መንቀሳቀስ ይችላሉ፤ ፓርቲዎች ድጋፍ በሚያገኙባቸው አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ከሕዝቡ ጋር መገናኘት ይገባቸዋል» ሲሉም ፕሮፌሰሩ አመላክተዋል።
አዲስ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ዜጎች ማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ «ፓርቲዎች በአሁኑ ሰዓት በበቂ ደረጃ ነው ባይባልም ከበፊቱ የተሻለ እየተንቀሳቀሱ ከሕዝብ ጋር እየተገናኙ ሃሳባቸውን እየገለጹ ነው ብዬ አምናለሁ» ይላሉ።
እንደ አቶ የሺዋስ ገለጻ ፓርቲዎቹ ከሕዝቡ ጋር የሚገናኙበት መንገድ በመገናኛ ብዙኃን በኩል ነው።ከዚህ አኳያ በተለይም ባለፉት ሰባትና ስምንት ወራት ውስጥ የተሻለ የሕዝብ መሠረትና የሃሳብ ልዕልና አላቸው ተብለው የሚታሰቡ ፓርቲዎች ከሕዝብ ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል ማለት ይቻላል።ያም ሆኖ ከሕዝብ ጋር የተደረገው ግንኙነት በሚፈለገው ደረጃ የተከናወነ ነው የሚል ዕምነት የለኝም በማለት የፕሮፌሰር መረራን ሃሳብ ይጋራሉ።
ሕዝብን ማንቃትና ማደራጀትን በተመለከተ ግን «ራሳቸው ፓርቲዎችና ምርጫ ቦርድም እኮ ገና በመደራጀት ላይ ናቸው» ሲሉ ሂደቱን ጠቁመዋል።በመሆኑም ሕዝብን ለማደራጀትና በቅድሚያ ፓርቲዎችና ምርጫ ቦርድ የጀመሩት ሪፎርም መጠናቀቅ ይኖርበታል።እናም ሕዝብን የማደራጀት ሥራ ከመሰራቱ በፊት አራትም አምስትም አባላት ኖሯቸው ለስም ያህል የሚንቀሳቀሱና የሕዝብ መሠረት ያላቸው ትክክለኛ ፓርቲዎች የሚለዩበትና ለውድድር ዝግጁ የሚሆኑበትን አደረጃጀትና አሠራር ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ይቀድማል ብለዋል።
የዴሞክራሲ ባህል አለመዳበር ከአደረጃጀት በአሻገር ፓርቲዎች ከሕዝብ ጋር እንዳይገናኙ እንቅፋት ሆኗል የሚሉት አቶ የሺዋስ የሃሳብ ልዩነትን በአግባቡ የማስተናገድና ያለመደማመጥ ዋነኛው ችግር ነው።ስለሆነም ሁሉም ይመለከተኛል የሚሉ አካላት መንግሥት ውስጥ ያሉ አስፈጻሚ አካላት በተለይም በወረዳና በዞን ያሉት፣ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አክቲቪስቶችና ልዩ ልዩ ቡድኖችና ስብስቦች በመቀራረብና በመወያየት የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለማምጣት በጋራ መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ውሂበእግዜር ፈረደ እንደገለፁት «ከመሰረቱ በእኛ ሀገር ያለው ፖለቲካ የሕዝብን ፍላጎትና ጥቅም መሠረት ያላደረገ በመሆኑ የፖለቲካ ነጋዴ እንጂ የፖለቲካ ፓርቲ የለም» በማለት የፕሮፌሰር መረራን ሃሳብ የበለጠ ያጠናክራሉ።
አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሕዝብ ጋር የማይገናኙበት ዋነኛው ምክንያት ዓላማና መርኋቸው ከሕዝብ ያልመነጨ በመሆኑ ሕዝቡን ለመቅረብና ለመግባባት ስለሚያዳግታቸው ነው የሚሉት ምሁሩ ስለሆነም መርኋቸው የፖለቲካ ሥልጣንና ገንዘብ ለማጋበስ በመሆኑ ሥራቸው በፖለቲካ ስም መነገድ ነው፤ ሕዝቡን አያውቁትም፣ ሕዝቡም አያውቃቸውም ብለዋል።
በዚህ የተነሳም የሕዝብን ፍላጎት መሠረት ያደረገ፤ በሕዝብ ቅቡልነት ያለው የፖለቲካ ፓርቲ አምብዛም በመሆናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በፓርቲና በምርጫ ፖለቲካ ዴሞክራሲን ማስፈን አስቸጋሪ ነው።አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ በሀገሪቱ ያለውን ግጭት የበለጠ ሊያባብሰውና አገሪቱን ወደባሰ ቀውስ ሊከታት ይችላል የሚል ስጋት አለኝ ይላሉ።
አስተያየት ሰጪዎቹ በሀገሪቱ ትክክለኛ የሕዝብ መሠረት ያላቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲመሰረቱና እውነተኛ ዴሞክራሲ ሽግግር እንዲኖር መፍትሔ ያሉትን ያመላክታሉ።ለዚህም መሰራት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ።ሕዝቡ ላይ መሰራት አለበት።ኢትዮጵያዊ አንድነት ላይም መሰራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ።
አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ ስለ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ስለ ቀጣዩ ምርጫ ከመታሰቡ በፊት ለውጡን ተከትሎ «ሀገሪቱ ከየት ወደ የት መሄድ አለባት፣ ወደ የት ነው እየሄድን ያለነው፤ መዳረሻችንስ የት ነው?» የሚለውን የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀት እንደሚገባው ተጠቁሟል።
ይህ ደግሞ የመንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥራ ብቻ ሊሆን አይገባም ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ሴት ወንድ፤ ወጣት አዛውንት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎችና መንግሥት የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ ቁጭ ብሎ መምከርና የሀገሩን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በሚወስን መልኩ ፍኖተ ካርታው ዝግጅት ላይ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2011
በይበል ካሳ