
ብዙ ዓይነት ዐውደ ርዕዮች ይካሄዳሉ። የስዕል፣ የፎቶግራፍና የመጽሐፍት ዐውደ ርዕዮች የተለመዱ ናቸው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የጤና፣ የንግድ፣ የቱሪዝም ወዘተረፈ እየተባለ በየዘርፉ የሚካሄዱ ዐውደ ርዕዮች ተበራክተዋል። ለሀገራችን እንግዳ ከሆኑ የዐውደ ርዕይ ዓይነቶች አንዱ «የሥራ ገበያ» ዐውደ ርዕይ ነው።
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከደረጃ ዶት ኮምና ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የሥራ ገበያ ዐውደ ርዕይ ላለፉት አምስት አመታት በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ሲካሄድ ቆይቷል። ዐውደርዕዩ በእስካሁኖቹ መድረኩ በድምሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል በማመቻቸት እንጀራቸውን ያቀረበ ምጣድ ሆኗል።
ዘንድሮም ከ20ሺ በላይ አዲስ ተመራቂ ተማሪዎችና ከ200 በላይ ከተለያየ ዘርፍ የተውጣጡ ቀጣሪ ድርጅቶች የተሳተፉበት ሥራ ፈላጊዎችንና ቀጣሪ ድርጅቶችን ያገናኘ ዐውድ ርዕይ ባሳለፍነው ሳምንት በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል። መድረኩ በተለያዩ የሥራ መስኮች ስድስት ሺ የሚደርሱ የሥራ ዕድሎች የተፈጠሩበት ነው።
አዲስ ተመራቂዎችን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር በማገናኘት፤ የምልመላ ሂደትን በማቀላጠፍ ብሎም ተቀጣሪዎችንና ቀጣሪ ድርጅቶችን ውጤታማ በማድረግ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትም ተነግሮለታል። በአካል በመገኘት መሳተፍ የማይችሉ ተመራቂዎችም በየነመረብን በመጠቀም እንዲሳተፉ የተደረገበት ሆኗል።
ትንሳኤ ጌቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛለች። ከመመረቋ በፊት በምትማርበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተዘጋጅቶ በነበረው አዲስ ተመራቂዎችንና ሥራ ቀጣሪዎችን ማገናኛ አውደ ርዕይ ከሦስት ወር በኋላ ተመራቂ መሆናን ጠቅሳ ጥቂት ድርጅቶች ጋር ተመዘገበች። ከተመረቁ ከአንድ ወር በኋላ ከአንዱ ድርጅት ስልክ ተደወለላትና የጽሑፍና የቃለ መጠይቅ ፈተናዎችን አልፋም ለመቀጠር በቃች።
ሥራ ከጀመረች ከአንድ ወር ተኩል በላይ ቀን የሆናት ትንሳኤ፣ በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው ዐውደ ርዕይ ላይ የተገኘችው የሰው ኃይል አስተዳደር ሠራተኛ ሆና የምትሠራበት ድርጅት አዲስ ሠራተኞችን ለመቅጠር የያዘውን ውጥን ለማሳካት ነው።
የእርሷን ሥራ ማግኘት የሰሙ ብዙ ጓደኞቿ ወደ ዐውደ ርዕዩ ይመጣሉ ብላ ተስፋ ያደረገችው ወጣቷ፣ «ይሄ ዕድል መዘጋጀቱ በጣም ጥሩ ነው፤ አንዷ ተጠቃሚ በመሆኔም ደስተኛ ነኝ። በጣም ብዙ ሥራ ያላገኙ ወጣቶች አሉ። በተለይ በዚህ አመት መንግሥት የአዲስ ሠራተኛ ቅጥር አይፈጽምም መባሉ አስጨንቆን ነበር። በበኩሌ ይህን ዕድል ስላገኘሁ መድረኩን ያዘጋጁትን አካላት ማመስገን እፈልጋለሁ።» ብላለች።
የትምህርት ማስረጃውን ለቀጣሪ ድርጅቶች ለማስገባት ሲታትር የነበረው ገዛኸኝ ቶላም አዲስ ተመራቂ ነው። በኬሚስትሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን ይዟል። የእግር ጉዳት ያለበት ወጣቱ፤ እንደዚህ ዓይነት መድረክ መመቻቸቱ ለተመራቂ ተማሪዎች ትልቅ ዕድል ነው፤ በተለይ ለአካል ጉዳተኞች ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ይላል።
አካል ጉዳተኞች ሥራ ለመፈለግ ሲንቀሳቀሱ ብዙ ችግር ያጋጥማቸዋል ያለው ገዛኸኝ፣ «በተለይም እንደ እኔ የእግር ጉዳት ላለበትና በሁለት ክራንች ለሚንቀሳቀስ ሰው፣ መንገዶች ምቹ ስላልሆኑ ቀጣሪ ድርጅቶቹ ያሉበት ድረስ ሄዶ ማመልከት በጣም አስቸጋሪ ነው» በማለት በመቶዎች የሚቆጠሩ ድርጅቶች በአንድ ቦታ ተሰባስበው ማግኘቱ ብዙ ውጣ ውርድ እንዳቀለለለት ይናገራል።
ሌላኛዋ በዐውደ ርዕዩ ላይ የተገኘችው ተመራቂ ከደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪዋን የያዘችው ሰሚራ አህመድ ነች። ዐውደ ርዕዩን በጣም ወድጄዋለሁ የምትለው ሰሚራ፣ 10 ድርጅቶች ጋር አመልክቼ በተለይ አንዱ ድርጅት ይቀበለኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ስትል ተናግራለች።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና የሥነ-ተግባቦት ትምህርት ክፍል ምሩቁ መስፍን ከተማ በበኩሉ የዐውደ ርዕዩን ፋይዳ ሲገልጽ፣ በርካታ ድርጅቶች በአንድ ቦታ ተሰባስበው መገኘታቸው ብዙ ጥቅም አለው። ብዙ ምርጫ ስለሚኖር በአንድ ጊዜ ብዙ ድርጅቶች ጋር ማመልከት ይቻላል፤ ይበልጥ መረጃ ለማግኘትም ያግዛል ብሏል።
ጸጋዬ ታደሰ (ዶ/ር) የሞርቴክ ኢንዱስትሪ ፒ ኤልሲ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው። ድርጅታቸው ለኢትዮጵያ የሳይንስ ማኅበረሰብ የሚያገልግሉ ሳይንሳዊ ዕቃዎችን ከውጭ አስመጪ ነው። የውጭ ሀገር ልምዶች እንደሚያሳዩት የሥራ ቅጥር ዐውደ ርዕይ ለብዙ ተማሪዎች ዕድል ይፈጥራል።
ለቀጣሪ ድርጅቶችም የተሻለ ብቃት ያላቸውን ሠራተኞች እንዲገኙ ይረዳቸዋል ይላሉ። ድርጅታቸው በዐውደ ርዕዩ ላይ ሲሳተፍ የመጀመሪያው መሆኑን በመጥቀስም የተሻሉ ሠራተኞችን እናገኛለን ብለው ተስፋ እንዳደረጉ ይናገራሉ።
የትምህርት ጥራቱ ወድቆ ስለነበረ ገበያው ላይ የተሻለ ብቃት ያላቸው ሰዎችን ማግኘት አልቻልንም የሚሉት ዶክተሩ፣ «የሥራ ቅጥር ማስታወቂያ ስናወጣ አንድ ሺ አመልካቾች ቀርበው ከእነዚያ ውስጥ ሁለት ሦስት ማውጣት ከባድ የሚሆንበት ጊዜ አለ። መንግሥት የተሻለ የሰው ኃይል ማፍራቱ ላይ መሥራት አለበት።» በማለት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ያሳስባሉ።
በዐውደ ርዕዩ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ከ10 ሺ በላይ ሠራተኞች ያሉት የቀርጫንሼ ግሩፕ የቅጥርና ዝውውር ሥራ ክፍል ኃላፊ አቶ ጌዲዮን አቶምሳ በበኩላቸው፣ መድረኩ እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ነው። ድርጅታችን ከዚህ ቀደም በተካሄዱት ዐውደ ርዕዮች 270 ሠራተኞችን ቀጥሯል። በዚህኛው መድረክ ደግሞ 60 ሠራተኞችን ለመቅጠር ዕቅድ ይዘናል ብለዋል።
ለሁለት ቀናት የቆየውን ዐውደ ርዕይ መርቀው የከፈቱት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሡ ጥላሁን ሚኒስቴር መሥሪያቤታቸው ባለፉት አመታት ከደረጃ ዶት ኮምና ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ባዘጋጃቸው የሥራና ሠራተኛ ማገናኛ መድረኮች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
የተማሪዎችን የመቀጠር ብቃት ማሳደግ እንዲቻልም ለተመራቂ ተማሪዎችና ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ሲሰጡ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።
መድረኩ የሥራ ዕድልን ከሥራ ፈላጊዎች ጋር በወቅቱ ለማገናኘት እንዲሁም የሥራ ገበያውን አቅርቦትና ፍላጎት ለማጣጣም ያስችላል ያሉት አቶ ንጉሡ፤ ሥራ ፈላጊዎችንና ቀጣሪ ድርጅቶችን የሚያገናኙ ተመሳሳይ መድረኮች ወደፊትም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም