አዲስ ዘመን ድሮ

በሆነ ወቅት የተፈጠረን አንድ ጉዳይ ጥሩም ይሁን መጥፎ ዛሬ ላይ ዳግም ባልጠበቅነው አጋጣሚ ድንገት ስንሰማው ወይም ተጽፎ ስናገኘው ቀልባችንን መግዛቱ አይቀሬ ነው። ጉዳዩና ወይም ሁኔታው ሲፈጠር ከነበርን ደግሞ ‘ኧረ እኔም እኮ ነበርኩ…’ ስንል በኩራት ማውራታችን አይቀርም። ዛሬ ላይ ከብዙ ዓመታት በፊት የተከወነውንና ያሳለፈውን ጉዳይ ድንገት ከዚሁ ዓምድ ላይ ስናገኘው ምን ይሆን የሚሰማን? በአዲስ ዘመን ድሮ ትናንትናዎቻቸውን የሚያገኙ ብዙዎች ናቸው። የዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዘመናትን ወደ ኋላ ተመልሶ ‹በደረሰው የባቡር አደጋ በርካቶች ለሞትና ከባድ አደጋ ተጋልጠዋል፣ ታላቁ ደራሲና ጋዜጠኛ ብርሃኑ ዘሪሁን በሞት ተነጠቀ› በማለት ያስታውሰናል:: አሁኑ ወቅት በጦርነት እየተናጠች ያለችው ሀገረ እስራኤልን መለስ ብለን ሌላኛውን የጦርነት ታሪኳን የሚያስታውሰንን ዘገባም እናስታውሳለን:: ከጳውሎስ ኞኞ ደብዳቤዎችም ገልጠን እናስታውሳለን::

በባቡር አደጋ 9 ሰዎች ሞቱ

ከጅቡቲ ወደ ድሬዳዋ ይጓዝ የነበረ አንድ የሕዝብ ማመላለሻ ባቡር የካቲት 29 ቀን 1979 የሐዲድ መስመር ስቶ በመውጣቱ ዘጠኝ ሰዎች ሲሞቱ 37 ሰዎች ደግሞ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን የጅቡቲ ሪፐብሊክ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ::

(አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 1979ዓ.ም)

የጓድ ብርሃኑ ዘሪሁን የቀብር ሥነ ሥርዓት ተፈጸመ

የአንጋፋው ጋዜጠኛና የታዋቂው ደራሲ የጓድ ብርሃኑ ዘሪሁን የቀብር ሥነ ሥርዓት ትናንት ሚያዚያ 17 ቀን 1979ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ:: ጓድ ብርሃኑ ዘሪሁን የሞቱት ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ57 ዓመታቸው ነው::

(አዲስ ዘመን ሚያዚያ 18 ቀን 1979ዓ.ም)

በእሥራኤል ጦር አውሮፕላኖች የቦምብ ድብደባ ስምንት ሰዎች ተገደሉ

የእሥራኤል ጦር አውሮፕላኖች በአንድ ሳምንት ውስጥ በደቡብ ሊባኖስ ውስጥ ከትናንት በስቲያ ባካሄዱት የቦንብ ድብደባ ስምንት ሰዎች ሲገደሉ ሃያ ስምንት ደግሞ መቁሰላቸውን ከሥፍራው የደረሰ ዜና ገለጠ::

የእሥራኤል ጦር አውሮፕላኖች ባለፈው ዓርብ በሚይህ ሜይህ አቅራቢያ በሚገኙ የስደተኞች ሰፈሮች ድብደባ በመፈጸም አሥራ አራት ሰዎች ከተገደሉና ሰላሳ ሰባት ከቆሰሉ ወዲህ ስደተኞች ከአካባቢ እንዲወጡ መደረጉን ዜናው በተጨማሪ ያመለክታል::

በሌላ በኩል የአረብ ሊግ በእሥራኤል የጦር አውሮፕላኖች በደቡባዊ የሊባኖስ ውስጥ የፈጸሙት የቦንብ ድብደባ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚካሄድ ሽብር መሆኑን በማስመልከት ድርጊቱን በጥብቅ አወገዙ::

(አዲስ ዘመን ሚያዚያ 10 ቀን 1979 ዓ.ም)

ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ

*በሀገራችን አባባል ማርያም የሳመችው የሚባለው ልክ አፍንጫዬ መሐሉ ላይ አለ:: ሰዎች እንደሚሉኝ አንዳንድ ጊዜ ሴቶቹ “ውይ ታድለህ ማርያም አፍንጫህን ስማሃለች” ይሉኛል:: እኔ ግን በዚህ አባባል አላምንም:: ይህ ነገር በእርግጥ ማርያም የሳመችን ነው?

አ-ለማ

 – አይደለም:: ከመወለድ የሚመጣ ነው:: ይህ ነገርም እስከ እድሜ ልክዎ ድረስ አይለቅም:: አንዳንዱ ሊሰፋ ወይም ሊጠብ ይችላል:: ሐኪሞች ግን በኦፕሬሽን ያስለቅቁታል:: ለምን እንደሚያስለቅቁት ልናገር? በእሱ ብዙ ጥንቆላ ስላለበት ነው:: እንደየአቀማመጡ ወይም እንደየቦታው ሁኔታ የሰውን ጠባይ ወይም ዕድል ይነግረናል ስለሚሉ ነው:: ለምሳሌ ያህል አፍንጫው ላይ ያለውን እንዲህ ይሉታል:: “የተጓዥነት ምልክት ነው:: አፍንጫቸው ላይ ጥቁር ነገር ያለባቸው ሰዎች አንድ ቦታ አርፈው ከሚሠሩት ሥራ ይልቅ በመዞር ሲራራ ነጋዴ በመሆን የሚሠሩት ሥራ መልካም ውጤት አለው:: በአንድ ቦታ ተቀምጦ የሚሠራ ሥራ አይሳካላቸውም” ይላሉ:: የእርስዎ ሥራ ምንድነው?

(አዲስ ዘመን የካቲት 12 ቀን 1979 ዓ.ም)

*የካቲት 27 ቀን በወጣው ዓምድህ አንዲት የ15 ዓመት ወጣት ነኝ ያለች “ከንፈሬ ትልቅ በመሆኑ እጮኛ እየተመለሰ ተቸገርኩ:: ከንፈሬን ምን ላድርገው ?” ብላ ጠይቃ ነበር:: አንተም ሐኪሞችን ጠይቂ ምናልባት ሳይችሉ አይቀሩም ብለሃታል:: አሁን የምለው በየሆስፒታሉ ከምትንከራተት ቢጤው ከቢጤው ይስማማል እንደሚባለው ሁሉ እኔም ከንፈሬ ትልቅ ስለሆነ “ለንቦጫም አንተን የምንይዘው ከንፈርህን ለመሸከም ነው?” እያሉኝ እጅግ ተቸግሬ ነበር::አሁን ቢጤዬን በማግኘቴ በደብዳቤ ተገናኝተን እንድንጋባ ታደርግልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ:: ለእኔ ለመጻፍ ብትፈልግ አሰላ ለአቶ ባዩ በየነ ብለህ ብትልክ ይደርሰኛል:: ግን እንድትገልጥላት የምፈልገው ቁመተ ረዥም፣ ቀጭን፣ ጠጉረ ሉጫ መሆኔን አስረዳልኝ:: አድራሻዋን እንድትገልጥልኝ አሳስብልኝ:: በስልክ ቁጥር 158 ልታገኘኝም ትችላለህ::

ባዩ ዘነበ

አሩሲ አሰላ

 -እቱ ትባያለሽና ምን ትያለሽ? ከተጋባችሁ የውል አባት ለመሆን ደስ ይለኛል::

(አዲስ ዘመን ግንቦት 22 ቀን 1979 ዓ.ም)

*ፋንታ በየሱቁ ከጠፋ ቆይቶአል:: ለምንድነው?

– እኔ ለምን እንደሆነ አላውቅም:: ባለቡና ቤቶች ሁሉ እንደድሮው አልሆን አሉን እያሉ የሚያወሩት አለ:: የቢራውስ ሜሎቲ ስለቀረ ምን ለማጣጣት የቢራ እጥረት ሊኖር ይችላል:: የዚህ የነፋንታ ደግሞ ምን ሆኖ ነው? አምቦ ውሃውስ ቢሆን፤ውስኪስ በኮካ ሆኖ የለ? ሰው የሚያወራው ስላለ ብሔራዊ ሀብት ሚኒስቴር ለእንዲህ አይነት አጋጣሚ ለምን መግለጫ አይሰጥም?

(አዲስ ዘመን መጋቢት 13 ቀን 1979 ዓ.ም)

*አንዲት ሴት ዕቃ ለመግዛት ከመደብራችን መጥታ ዕቃ ጠየቀች:: መልሱ የጅምላ ቤት ነው በማለት ከሥራ ጉአደኞቼ ጋር መልስ ሰጠናት:: እናንተ በዝባዦች አሁን መብታችን እኩል ነው በማለት ምኑን ልንገርህ ከሰው ልጅ አንደበት በማይወጣ ስድብ ተሳድባ ሔደች:: መብት የተሰጠው ለስድብ ያለመሆኑን እባክህን ንገርልኝ?

እድሪስ አህመድ

-እስዋን የሰው ልጅ ላለማድረግ ነው ከሰው ልጅ አንደበት የማይወጣ ስድብ ተሳደበች የምትለው? አንዳንድ መንደር የሚያስቸግሩ ሴቶች ከውጭም ያው ናቸውና መቻል ነው:: ንዴታም ደግሞ አለና ይሄንንም አትርሱ:: ቆርቁአዡም ተናዷል፤ተቆርቁአዡም ተናደዋል:: ይሄም ደግሞ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ስለሚቀር አሁን ዝም እያሉ ማሳለፍ ነው::

(አዲስ ዘመን መጋቢት 13 ቀን 1979 ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2016

Recommended For You