የሰሞኑ አነጋጋሪ ርዕሰ ጉዳይ ምን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ጉዳዩ ከመታወቅ ባለፈ ሁሉ የሚያወራው ሆኗል፡፡ አዎ! የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት እጅግ አስደንጋጭ ሆኖ አልፏል፡፡ መቼም ውድቀት ሲኖር ሁሉም ጆሮውን ሰጥቶ ያዳምጣል፡፡ ሁሉም ይተቻል፡፡ ሁሉም ስለውድቀቱ አብዝቶ ያወራል፡፡ ከሰሞኑ የሆነውም ይኸው ነው፡፡ አብዛኛው ሰው ሲያወራ የነበረው ስለተመዘገበው አስከፊ ውጤትና ስለወደቁ ተማሪዎች ብዛት እንጂ ስላለፉት ተማሪዎች አልነበረም፡፡
ምንጊዜም ቢሆን ፈተና ሁለት ተቃራኒ ውጤቶችን እንደሚያስተናግድ ይታወቃል። ይህን ደግሞ በትምህርት ዓለም ውስጥ ያለፈ ሁሉ አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ ጉዳዩም በዚህ መስመር ላለፉና ለብዙዎች አዲስ አይደለም፡፡ በትምህርት ዓለም መውደቅና ማለፍ የተለመዱ ጉዳዮች እንደሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም ታዲያ ለየት የሚያደርጋቸው ዐብይ ጉዳይ ግን አለ። ሁለቱን ለየት የሚያደርጋቸው በየትኛውም የፈተና ውጤት የአላፊው ቁጥር ሲበዛ የሚወድቀው ቁጥር አነስተኛና፣ ምናልባትም ከአጠቃላይ ተፈታኞች ቁጥር አንፃር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል እንኳን አለመሆኑ ነው። የዘንድሮው ግን በእጅጉ ይለያል።
የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና አስመልክቶ የትምህርት ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ በአጠቃላይ በ2015 ዓ.ም ከተፈተኑ ተማሪዎች ውስጥ 3 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ 50 በመቶ እና ከዛ በላይ ማስመዝገባቸውን አስታውቋል፡፡ ይህም ውጤት ከአምናው የተሻለ የፈተና ቁጥጥር ሥርዓት በሚገባ መዘርጋቱን ያመላክታል፡፡ በተፈጥሮ ሳይንስና በማህበራዊ ሳይንስ ለፈተና ከተቀመጡ በድምሩ 845 ሺህ 677 ተማሪዎች 50 ከመቶና ከዚያ በላይ ውጤት ያመጡት 31ሺህ 224 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ 160ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎችን በሬሜዲያል ፕሮግራም ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚቀበሉም ተጠቁሟል፡፡
በዚሁ መግለጫ መሠረት አምና 13 ሺህ 600 ተማሪዎች ፈተና አቋርጠው የውጡ ሲሆን ዘንድሮ ምንም ተማሪ አላቋርጠም። በአማካኝ 28 ነጥብ 65 በመቶ በአንድ ተማሪ፤ በተፈጥሮ ሳይንስ 29 ነጥብ 8 በመቶ፤ በማህበራዊ ሳይንስ 27 በመቶ፤ በግል ፈተና የወሰዱ ከ160 ሺህ በላይ ተፈታኞች 14 ሺህ፤ በኢትዮጵያ ከፍተኛው 649 በተፈጥሮ ሳይንስ (ሴት ተማሪ) ከክሩዝ ትምህርት ቤት፤ ከማህበራዊ ሳይንስ 533 ከደብረ ማርቆስ አዳሪ ትምህርት ቤት፤ ከ600 በላይ ያመጡ 205 ተማሪዎች ከተፈጥሮ ሳይንስ፤ ከማህበራዊ ሳይንስ 15 ተማሪዎች ከ500 በላይ ከ600፤ ከ50 ከመቶ በላይ ተማሪዎች ከ26 ከመቶ በታች አምጥተዋል፡፡
ምንም እንኳን የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ውጤት አስደንጋጭ ቢሆንም፣ በዚህ መካከል እንደ ወርቅ ተፈትነው ነጥረው በመውጣት ለሌሎች አርአያ መሆን የሚችሉ ኮከብ ተማሪዎች ተከስተዋል። እነዚህ ኮከቦች ከፈለቁባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው አንጋፋው የቀዳማዊ ምኒልክ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ይገኝበታል፡፡ ትምህርት ቤቱ እንደ ሌሎች አቻዎቹ ብዛት ያላቸው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን አስፈትኗል፡፡ የተጠበቀውን ያህል ባይሆንም የተወሰኑ ተማሪዎቹን ለውጤት አብቅቷል። ከዚህ ትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች ውስጥ ታዲያ አንዱ ተማሪ አበራ ሁሉፍ ነው፡፡
ተማሪ አበራ ሁሉፍ ተወልዶ ያደገው ትግራይ ክልል መቐሌ ከተማ ነው። አስፈላጊ ያልሆነውና የበርካታ ንፁሃንን ሕይወት የቀጠፈው ጦርነት መጥቶ ትምህርቱን እስካቋረጠበት ጊዜ ድረስ እዛው ነበር። እዛው ቆየ እንጂ አቋርጦም ወደየትም አልሄደም። ከሶስት ዓመት ቆይታ በኋላ ግን በቤተሰቦቹ አማካኝነት ያቋረጠውን ትምህርቱን ይቀጥል ዘንድ ወደ ሀገሪቱ መዲና አዲስ አበባ መጣ።
ተማሪ አበራ ሁሉፍ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ የትምህርት ቤቶች መከፈቻ ጊዜ ሳይሆን የመጀመሪያው መንፈቀ-ዓመት ተጠናቅቆ ተማሪዎች ሁለተኛውን መንፈቀ-ዓመት ለመጀመር በዝግጅት ላይ በነበሩበት ወቅት ነበር። የተማሪ አበራ ቤተሰቦች ትምህርቱን ከሁለተኛው ሴሚስተር እንዲቀጥልላቸው በማሰብ ትምህርት ቤት ማፈላለጉን ተያያዙት። ተሳካላቸውና ለአበራ በምኒልክ 2ኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤት ቦታ ተገኘለት። ከዛም ትምህርቱንም ቀጠለ።
የ12ኛ ክፍል ትምህርት ሄዶ ሄዶ ያው ማጠቃለያው በመላ ሀገሪቱ የሚሰጠው መልቀቂያ ፈተና ነውና ለፈተና ተቀመጠ። በሚገርም ሁኔታም፣ በመርፌ ቀዳዳ እንደ መሹለክ በሚቆጠረው የዘንድሮ ፈተና ውጤታማ ብቻ ሳይሆን በጥሩ ውጤት ማለፍ ቻለ፡፡
ተማሪ አበራ ‹‹የመቐሌ ልጅ ነኝ›› ይላል ንግግሩን ሲጀምር፡፡ ትምህርቴን ስከታተል የነበረው እዛው መቐሌ የሚገኝ፣ ‹‹ቀለሚ›› የሚባል ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር። ነገር ግን ጦርነቱ መጥቶ ከትምህርቴ ለየኝ፤ አቋረጥኩ። ለሶስት ዓመታትም በስጋትና አእምሮ መረበሽ ውስጥ ነው የቆየሁት። ከዛ ቤተሰቦቼ ይዘውኝ ወደ አዲስ አበባ መጡ። ቦታ ፈለጉና ትምህርት ቤት አስገቡኝ። ትምህርት ቤት የገባሁት ፈተናው አንድ ወር ሲቀረው ነበር፡፡ ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡ ፈተናው ሲደርስ ለፈተና ተቀመጥኩ። ያው አለፍኩ።
«ፈተናው ጥሩ ነው። በጣም ቀላል ነበር። ትንሽ ላጠና ተማሪ ያን ያህል ከባድ የሚባል አልበረም›› ሲል ይናገራል ተማሪ አበራ፡፡ ተማሪዎች በብዛት በፈተናው ሊወድቁ የቻሉት ያን ያህል ፈተናው ከባድ ሆኖ ተማሪው ሳይሆን ኩረጃን መጠበቁና አለማጥናቱ ነው ይላል፡፡ ተማሪው መኮራረጅን ባይጠብቅ፣ ቢያጠናና ቢዘጋጅ ኖሮ አብዛኛው ተፈታኝ ሊያልፍ ይችል እንደነበርም ያመለክታል፡፡
«እንደ ፈተናው ቅለት እኔ ራሴ 555 ማምጣቴ በጣም አናድዶኛል›› ሲል ተማሪ አበራ በቁጭት ይናገራል፡፡ ከዚህ በላይ ማምጣት ነበረብኝ። ግን ይሁን፤ በሁለትና ሶስት ወር ዝግጅት ስለሆነ ይህንን ውጤት ማምጣቴም ምንም አይደለም ሲል ይገልፃል፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በተለይ ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ኮምፒውተር ሳይንስ ማጥናት እንደሚፈልግ ይጠቁማል፡፡ ለወደፊቱ ተማሪዎች ጥሩ ውጤት እንዲያመጡ ከተፈለገ የመምህራን ድጋፍ በጣም አስፈላጊ መሆኑንም ይጠቅሳል፡፡ መምህራን ለተማሪዎቻቸው የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት እንዳለባቸውም ያመለክታል፡፡ በትርፍ ሰዓትም ጭምር ለተማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግና ይህ ከተደረገ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት የማያመጡበት ሰፊ እድል እንደሚኖር ይገልፃል፡፡
‹‹ቤተሰቦቼ ማለፌን ሲሰሙ ማመን ነው ያቃታቸው›› የሚለው ተማሪ አበራ፤ ከሶስት ዓመት በላይ ትምህርቴን አቋርጬ፣ ጦርነት በሚካሄድበት ከተማ ውስጥ ቆይቼ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሶስት በመቶ ብቻ ተማሪ ነው ያለፈው ሲባል እኔን ያልፋል ብለው አልጠበቁም ነበር›› ሲል ያስረዳል፡፡ ውጤቴን ሲሰሙ ከሚገባው በላይ ነው የተደሰቱት ይላል፡፡
ባለፈው ዓመት 100 በመቶ በማሳለፍ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ውጤትም በሀገር አቀፍ ደረጃ አንደኛ ወጥቶ የነበረውና ዘንድሮ ደግሞ 75 ተማሪዎችን አስፈትኖ 72ቱን ያሳለፈው ሌላኛው ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ኮከቦች መፍለቂያ ሆኗል፡፡
ወይዘሮ ዘላለም ሲሳይ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ርዕሰ መምህር ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት የካምፓሱ ተማሪዎች አይደለም በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ ናቸው። ዘንድሮ ሶስት ተማሪዎች ከ350 በታች በማምጣት በተለያዩ ምክንያቶች ማለፍ ያልቻሉ ቢሆኑም አምስት ተማሪዎች ከ600 በላይ ውጤት ማምጣት ችለዋል፡፡
ለአምስተኛ ጊዜ ያስፈተነው ይህ ተቋም በሚቀጥለው ዓመት ስድስተኛ ዙር የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን የሚያስፈትን ሲሆን፣ እነዚህ ተፈታኞች ሙሉ ለሙሉ መቶ ከመቶ የሚያልፉ ናቸው። ለዚህ መነሻ የሆነውም እስካሁን የተመዘገበው መልካም ውጤት ነው፡፡
ተማሪዎች ይህን ጥሩ ውጤት ማምጣት የቻሉት በክፍል ከ25 እስከ 30 ተማሪዎች ብቻ እንዲማሩ በመደረጉ፣ በዩኒቨርሲቲ መምህራን ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመማራቸው ፣ ወላጆች ከትምህርት ቤቱ ጋር በቅርበትና በመደጋገፍ በመሥራታቸው፤ ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚያዘጋጃቸው ጠንከር ያሉ ሞዴል ፈተናዎች መሰጠታቸውና ሙሉ ዝግጅት መኖሩ እንዲሁም የራሳቸው የተማሪዎች የእርስ በእርስ መደጋገፍ መኖሩ ነው፡፡
ርዕሰ መምህሯ እንደሚገልፁት እርሳቸው የሚመሩት ተቋም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በከተማዋ ዙሪያ የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው ከፍተኛ ውጤት ያመጡ፤ ለተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዓይነቶች ከፍተኛ ዝንባሌና የፈጠራ ተሰጥኦ ያላቸው፣ 10ኛ ክፍልን ካጠናቀቁ በኋላ በተፈጥሮ ሳይንስ መስክ ብቻ መቀጠል ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎችን ይቀበላል። በተግባር የተደገፈ ትምህርት በመስጠት የላቁ ተመራማሪዎችን ማፍራት ደግሞ ተቀዳሚው አላማ ነው፡፡ የወደፊት እቅዱም ከመዋእለ ሕፃናት (ኬጂ) ጀምሮ፣ ከሀገርም አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሞዴል ተማሪዎችን ማፍራት ላይ መሥራት ይሆናል፡፡
የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በሚመለከት የተቋሙ ተማሪዎች በማለፋቸው ደስ ሊያሰኝ ይችላል፡፡ እንደ ሀገር ግን ጉዳዩ ያስፈራል፣ ያሳፍራልም። ያለፉ ተማሪዎች ላይ የተቋሙ ዐሻራ እንዳለበት ሁሉ የወደቁ ተማሪዎች ላይም የተቋሙ ዐሻራ አለበት። ተማሪዎች በዚህ ደረጃ ወደቁ ማለት እንደ ሀገርም ውድቀትና ጉዳት ነው። ሄዶ ሄዶ በአንድ ወቅት ሀገር በሁሉም ዘርፍ ባለሙያዎችን ስትፈልግ ልታጣ ሁሉ ስለምትችል ጉዳቱ በዚህ ልክ ነው መታየት ያለበት። በዚህ ደረጃ፣ ትንሽ ቁጥር ያለውን ተማሪ ይዞ መሄዱም የትም ድረስ አያዋጣም። ይህ በጥልቅ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው።
በአሁኑ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል እየተጠና ያለ ጥናት አለ፡፡ እሱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። በማንኛውም ጉዳይ የትምህርት ባለ ድርሻ አካላትን የግድ ማሳተፍ ያስፈልጋል። መነጋገር ያስፈልጋል። መንግሥት የመምህራንን ኑሮም ማየት አለበት። መምህራን መኖር በሚችሉበት ደረጃ ሊኖሩ ይገባል። ዞሮ ዞሮ ተማሪ በአንድ ቀን ፈተና የመጨረሻ ማንነቱ አይለካም። ፈተና አንዱ የእውቀት መለኪያ እንጂ የሁሉም እውቀት መለኪያ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም አላለፉም በተባሉት በኩል ምንም የሚረብሽ ሁኔታ መኖር የለበትም።
የመማሪያ መጻሕፍት እጥረትን በተመለከተም “ለእኛ በፒዲኤፍ ደርሶን ለልጆቻችን አዳርሰናል። ይህ ለእኛ ልጆች ችግር ላይሆን ይችላል። እዛ፣ እሩቅ ላለው ግን እንደዚህ ቀላል ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ባለሀብቱንም፣ ባለ ድርሻ አካላትንም አስተባብሮ የመማሪያ መጻሕፍት ለተማሪዎች የሚደርሱበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል›› ሲሉም ነው ርዕሰ መመምህሯ ያመለከቱት፡፡
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም