በክልሉ አንድ ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፡- በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አንድ ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት እየተሠራ እንደሚገኝ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ።

የክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ሉአል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጀት እንደገለጹት፤ በ2016 የምርት ዘመን በበጋ መስኖ ስንዴ አንድ ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል ።

በአሁን ወቅት በዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ኃላፊው እስካሁን ድረስ 11 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል።

በዘር ከሚሸፈነው አንድ ሺህ ሄክታር መሬት ከ30 ሺህ በላይ ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን በመግለጽ፤ በአንድ ሄክታር መሬት ከ25 እስከ 30 ኩንታል ምርት ለመግኘት እቅድ ተይዟል ብለዋል።

አቶ ኡጁሉ እንደገለጹት፤ ባለፈው ዓመት የሙከራ ጊዜ በመሆኑ በሁለት የግብርና ሥነምሕዳር አከባቢዎች የበጋ መስኖ ስንዴ የማልማት ሥራ ተሠርቷል።

በዚህም ሙከራው የተደረገው ማጃንግ ዞን ወይና ደጋ አካባቢና በአኝዋክ ዞን ቆላማ አካባቢ የበጋ መስኖ ስንዴ እንደተዘራ አስረድተዋል።

በተሠራው ሥራ ወይና ደጋ አካባቢ በጣም ውጤታማ መሆን የተቻለ ሲሆን በቆላማ አካባቢ ለአካባቢው የሚሆን የስንዴ ዘር መጠቀም ባለመቻሉ ውጤታማ መሆን እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

በዘንድሮ በጀት ዓመት በወይና ደጋ አካባቢ የማስፋት ሥራ እየተሠራ ሲሆን፤ በቆላማ አካባቢ ውጤታማነትን ለማምጣት ከአካባቢው ሥነምሕዳር ጋር የሚሄድ የስንዴ ዝርያ የማጥናት ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

ኃላፊው እንደተናገሩት የዘንድሮ ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ በአመራሩ የተደገፈ ግብረ ኃይል የማቋቋም ሥራ የሚሠራ ሲሆን፤ ባለሙያውን በማደራጀት የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠት የግብርና ቢሮው እየሠራ እንደሆነ አስረድተዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ሥራ አዲስ እንደመሆኑ ለአርሶ አደሩ የምክር አገልግሎት የመስጠትና አርሶ አደሩን በማደራጀት በኩታ ገጠም እርሻ እንዲሠራ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አክለው ገልጸዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ተግባር የመደገፍ ሚናው የጎላ ነው ያሉት አቶ ኡጁሉ፤ ገበሬው ከዝናብ ጥገኝነት ተላቆ ዓመቱን ሙሉ እንዲያመርት እድል ፈጥሯል ብለዋል።

ከአንዳንድ አካባቢዎች የሥነ-ምሕዳር ሁኔታ አንጻር ሰብሎች ሲደርሱ በዝናብ የመጎዳት ሁኔታ ስለሚኖር ይህን ለመከላከልም ይረዳል ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

በመጨረሻም ኃላፊው የልማት ድርጅቶች በሚያስቀምጡት መንገድ የክልሉን የግብርና ሃብት በአመራሩ በመደገፍ ውጤታማ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You