መጋቢ አዕምሮ የኑሮ ውድነትን እንዴት መቋቋም ይቻላል?

በአሁኑ ጊዜ ኑሮ በሰዎች ላይ እያደረሰ ያለው ሁለንተናዊ ጫና ይህ ነው ተብሎ ሊገለፅ አይችልም:: የኑሮ ውድነቱ ጣራ ነክቷል:: በኑሮ ውድነት ያልተፈተነ የህብረተሰብ ክፍል የለም:: ከደሃ እስከ ሀብታም ድረስ በኑሮ ውድነት ተማሯል:: ዋጋ ያልጨመረ የምግብና የሸቀጣሸቀጥ እቃ የለም ለማለት አያስደፍርም:: ህብረተሰቡ ከነገ ዛሬ የኑሮ ውድነቱ ይቀንሳል ብሎ ተስፋ ቢያሳድርም እስካሁን ድረስ ጠብ ያለ ነገር የለም:: በዚህም የኑሮ ውድነቱ ይበልጥ እያሻቀበ መጥቷል:: በመንግሥትም በኩል የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ቢኖሩም የሚፈለገውን ውጤት እያመጡ አይደሉም::

ምንም እንኳን የኑሮ ወድነቱ ከአቅም በላይ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ወደራስ ተመልክቶ ለችግሩ መፍትሔ ማበጀት አንድ ነገር ነው:: ኑሮ እያደረሰ ያለውን ጫና አምኖና ተቀብሎ መደቆስ ህልውናን ማሳጠር ነው:: እናም ለኑሮ ውድነት እጅ ሳይሰጡ ለመኖር ትግል ማድረግ ይገባል:: ለመሆኑ ህብረተሰቡ ኑሮ እያደረሰበት ያለውን ጫና በራሱ መንገድ እንዴት ሊቋቋም ይችላል? ‹‹እነሆ መፍትሔዎቹ›› ይላሉ በዚህ ረገድ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ባለሞያዎች:: ከዛ በፊት ግን የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን ምንነትና መንስኤውን ማወቅ ያስፈልጋል::

የዋጋ ንረት በእንግሊዘኛው ‹‹ኢንፍሌሽን›› የሚባለው ነው:: አንዳንድ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ደግሞ የዋጋ ግሽበት ብለው ይጠሩታል:: ሌሎች ደግሞ የለም የዋጋ ግሽበት የሚለው ቃል ይበልጥ የሚወክለው የዋጋ መውረድን ወይም ‹‹ዲፍሌሽን›› ተብሎ የሚጠራውን ነው ሲሉ ይከራከራሉ:: ይህ እንዳለ ሆኖ ለመሆኑ የዋጋ ንረት ምንድን ነው? እንዴትስ ይከሰታል? ገንዘቡ ወረቀት ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለተመሳሳይ አገልግሎት በርካታ ገንዘብ ከኪስዎ አውጥተው ለረጅም ሰዓት ይቆጥራሉ? በአንበሳ ድፍረት ገበያ ወጥተው ዋጋ ሲጠራ ግን ነብር እንዳየ ሰው ይበረግጋሉ? ወይም ቁጣ ቁጣ ይልዎትና ተነጫንጨው ጥለው ይሄዳሉ? ለምሳሌ ነጋዴ በተጠራልዎ ዋጋ ተደናግጠውና ተናደው ለመግዛት ከወሰኑ በኋላ የመያዣ ፌስታል ሂሳብ ሲጠየቁ እንዲሁ ተመናጭቀው ትተው ይሄዳሉ? አዎ! ይሄን አያደርጉም ማለት አይቻልም::

በፊት ሳይጨነቁ ይገዙት የነበረ ምግብ ነክ ሸቀጥ ሁሉ ዛሬ አሻቅቧል:: ከቀይ ሽንኩርት እስከ ነጭ ሽንኩርት፣ ከቲማቲም እስከ ቃሪያ አልቀመስ ብሏል:: ነብሰ ጡር ባለቤትዎን ይዘው በጎዳና ሲራመዱ የበርገር ሽታ አውድዎት የባለቤትዎን አምሮት ለመቁረጥ በርገር ቤት ገብተው ቁጭ ሲሉ የሚቀርብልዎት የምግብ ዋጋ ዝርዝር ከተቀመጡበት መልሶ ያስነሳዎታል:: አምሮትዎን በሽታና በፎቶ ይቆርጡ ይመስል አሽትተውና ፎቶ ተነስተው ከበርገር ቤቱ ውልቅ ይላሉ::

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ አካል የሆነው የዓለም ሠራተኞች ድርጅት/ILO/ እንደሚለው ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዋጋ ንረት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ እንደጨመረ ያስቀምጣል:: ባለፈው መጋቢት ወር የዋጋ ንረቱ 3 ነጥብ 7 ከመቶ ብቻ እንደነበርና ነገር ግን በዚህ ዓመት በመጋቢት ወር ወደ 9 ነጥብ 2 ከመቶ ማሻቀቡን ተናግሯል:: ይህም ማለት የማንኛውም ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች እንዲሁም የአገልግሎቶች ዋጋ በአስደንጋጭ ሁኔታ ማሻቀቡን ይጠቁማል::

በመጀመሪያ ወደተነሳው ጥያቄ ሲመጣ የዋጋ ንረት ወይም ኢንፊሌሽን ለአንድ ሸቀጥ ወይም አገልግሎት የሚከፈለው ዋጋ በጊዜ ሂደት እየተወደደ መምጣት በሚል በቀላሉ ሊተረጎም ይችላል:: በኪስዎ የያዙት ተመሳሳይ ገንዘብ ትናንት ያገኙትን ተመሳሳይ ሸቀጥ ወይም አገልግሎት መግዛት ሳይችል ሲቀር የዋጋ ንረት ይፈጠራል:: ከዚሁ ጋር በተያያዘ የዋጋ ንረት ለምን ይከሰታል ብለው ይጠይቁ ይሆናል? ነገሩ ትንሽ እንቆቅልሽ ነው:: ሁለት ቀላል ምክንያቶችን ግን መጥቀስ ይቻላል::

አንዱ የፍላጎታችን መጨመር የሚፈጥረው የዋጋ ንረት ነው:: ይህም ለአንድ ሸቀጥ ወይም አገልግሎት በርካታ ሰዎች ከፍተኛ ፍላጎት ሲያሳዩ የዋጋ ንረት ይፈጠራል ማለት ነው:: ለምሳሌ ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው በሬዎች እየታደረዱ በጣም በርካታ ሰው ድንገት በቁርጥ ስጋ ፍቅር ቢወድቅ የዋጋ ንረት ይፈጠራል:: እንዲህ ዓይነቱ የዋጋ ንረት የሚፈጠረው ለብዙ ጊዜ ሲንኮታኮት የቆየ ምጣኔ ሃብት እያገገመ ሲመጣ ነው:: ሰዎች ኑሯቸው አስተማማኝ ሲሆንና ገቢያቸው ሲደረጅ በመንግሥት ሥርዓትና መዋቅር በገበያ መነቃቃት እምነት ሲኖራቸው ገንዘብ ከመቆጠብ ይልቅ ገንዘብ ለማጥፋት ይበረታታሉ:: ወደገበያ የሚወጣው ሰው ቁጥር ይበረክታል:: ምግብ ቤቶች በተመጋቢዎች ይጥለቀለቃሉ::

በዚህ በፍላጎት መናር የሚከሰተው የዋጋ ንረት ነጋዴዎች የፍላጎትን መጨመር በበቂ ሁኔታ ለማስተናገድ ሲሳናቸው ዋጋ ይጨምራሉ፤ የዋጋ ንረትም ይከሰታል:: የነዳጅ ዋጋ መጨመር የዋጋ ንረትን ማስከተል ረገድ ከሚጠቀሱ ዋነኛ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ነው:: ነጋዴዎች ዋጋ ቢጨምሩም ተገልጋይ ወይም ሸማች በቀላሉ ስማለይሸሽ አያሳስባቸውም:: ሸማች በፍፁም አልደነግጥ ሲል በተደጋጋሚ ዋጋ ይጨምራሉ:: ይህ ዓይነቱ የዋጋ ንረት በሸማቾች ምቾትና መደላደል የሚፈጠር ሲሆን በእንግሊዝኛው /Price infilation/ ተብሎ ይጠራል:: አዲስ ፍላጎት የፈጠረው አዲስ ዋጋ እንደማለት ነው::

ሁለተኛው የዋጋ ንረት የሚፈጠረው በብዙ ነገሮች ዋጋ መጨመር ምክንያት ነው:: ይህ በእንግሊዘኛ /Cost push infilation/ ተብሎ ይጠራል:: ይህ ዓይነቱ የዋጋ ንረት የሚከሰተው አንድን አገልግሎት ወይም ምርት ለማሟላት ግብዓቶች በየደረጃው ስለሚወደዱ ነው:: ይህም በብዙ ምክንያት ሊከሰት ይችላል:: ለምሳሌ አንዱና ዋነኛው የነዳጅ ዋጋ መጨመር ነው:: ነዳጅ ሲጨምር አብዛኛው አገልግሎትና ሸቀጥ አብሮ ይጨምራል:: በአጭሩ አንድን ምርት ወይም አገልግሎት አጠናቆ ወደገበያ ለማቅረብ በሂደቱ ላይ ሌሎች ግብዓቶች ዋጋ በመጨመራቸው ምክንያት ያንን የዋጋ ጭማሬ ተገልጋዩ ወይም ሸማቹ እንዲከፍለው ሲደረግ ማለት ነው::

ከላይ በተነሳው የቁርጥ ሥጋ ምሳሌ መሠረት በዚህ ሁኔታ የተፈጠረው የዋጋ ንረት የቁርጥ ሥጋ ተመጋቢ ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት ሳይሆን በሂደቱ ላይ የሚከሰት የዋጋ ጭማሪ ያመጣው ነው የሚሆነው:: በዚህ ሁኔታ ሥጋ ወዳዱ ማህበረሰብ ቁጥሩ አልጨመረም ቢባል ነገር ግን በሬውን ለመቀለብ የወጣው ወጪ፣ በሬውን ከክፍለ ሀገር ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት ለትራንስፖርት የተከፈለ ዋጋ፣ በሬውን ቄራ ለማሳረድ የተከፈለ የእርድ አገልግሎት ዋጋ፣ የቁርጥ ቤት አስተናጋጆች ደመወዝ መጨመር፣ የአዋዜ መወደድ፣ ስል ቢላዎችን ለመግዛት የወጣ ወጪና የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር የዋጋ ንረተን ያስከትላል::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከሰተ ባለው የገንዘብ ግሽበትና የዋጋ ንረት ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ ሰንሰለታማ ጣጣ ያመጣው ነው:: በተለይ ደግሞ የኮቪድ ወረርሽኝ ያቀዘቀዘው ምጣኔ ሀብት ለማንሰራራት እየዳኸ በነበረበት ጊዜ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከድጡ ወደማጡ ከትቶታል::

ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ደግሞ የዋጋ ንረት የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት አስደንጋጭ ከሚባሉት ውስጥ የሚጠቃለል ነው ለማለት ቢቻልም በዋጋ ንረቱ ከኢትዮጵያ የባሱ በርካታ ሀገራት አሉ:: በብዙ ሀገራት የዋጋ ንረቱ በሁለት አሃዝ የሚሰላ መሆኑ ጉድ እያስባለ ነው:: ለምሳሌ በቱርክ የዋጋ ንረቱ 70 ከመቶ ደርሷል:: በአርጀንቲና 51 በመቶ ተጠግቷል:: በሲሪላናካ 30 ከመቶ ሆኗል::

ዓለም ከሚገመተው በላይ በንግድ ሰንሰለት የተሳሰረ ነው:: ለምሳሌ የኮቪድ ወረርሽኝንና ምጣኔ ሀብትን ምን ሊያገናኛቸው ይችላል ተብሎ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል:: ሁሉ ነገር የተሳሰረ ነው የተባለውም ለዚህ ነው:: እንዴት? ለምሳሌ ኮቪድ የእንቅስቃሴ ገደብ አስከትሏል:: ላብ አደር ፋብሪካ አልሔደም:: ምርት አልተመረተም:: በዚህም ፋብሪካዎች ምርት ቀንሰዋል:: ሠራተኛው ሥራውን አጣ:: ሸማችም ምርት አልደርስ አለው:: በኮቪድ ምክንያት እዳቸውን በቱሪዝም ገቢ የሚከፍሉ ሀገራት ጭንቅ ውስጥ ገብተዋል:: አምራች ሀገራት በበቂ ሁኔታ ማምረት አቆሙ:: የዓለም የንግድ ሰንሰለት እጅግ ከሚታሰብው በላይ የተሳሰረ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው::

ስለዚህ እርስዎ ከዋጋ ንረት አዙሪት እንዴት ነው መውጣት የሚችሉት? ፤ የኑሮ ውድነቱን ተቋቁመውስ እንዴት ሊዘልቁ ይችላሉ? በየዘመኑ የዋጋ ንረት ይከሰታል:: የዘንድሮውስ የከፋ ነው ሲባል ሌላ የከፋ ይመጣል:: ነገሩ ከሚገመተው በላይ ውስብስብ በመሆኑ ሀገራትም ይህንን የሚቋቋሙበት ሁነኛ መላ የላቸውም:: ለዚህም ነው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ቀጥተኛ መልስ መስጠት የሚከብዳቸው:: ሆኖም ግን ከችግሩ መውጣት የሚያስችለው አንዱ መንገድ ምርትን መጨመር ነው:: እርግጥ ነው ደሃ ሀገራት መርፌም ጭምር ከውጭ ሀገራት ስለሚያስገቡ ከዚህ የዋጋ ንረት ለመውጣት ፍቃዳቸውን ማየታቸው አይቀሬ ነው::

እርስዎስ! ሀገራት የዋጋ ንረትን ለመቋቋም ምርታቸው በሁለንተናዊ መልኩ ማሳደግ እንዳለባቸው ሁሉ እርስዎም እንዲህ ከእለት እለት እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ከመደበኛ ሥራዎ በተጨማሪ ሁለትና ሶስት ሥራዎችን ጨምረው በመሥራት ገቢዎን ማሳደግ ይጠበቅብዎታል:: ገቢዎ አደገ ማለት ደግሞ የቤት ኪራይዎን ሳይሳቀቁ እንዲከፍሉና የእለት ጉርስዎን በበቂ ሁኔታ እንዲሸፍኑ ያስችልዎታል:: እንደውም ከወጪዎ ገንዘብ ተርፎ እንዲቆጥቡና ነገ ሌላ ፈተና ሲመጣ ገንዘብዎን አውጥተው ለመጠቀም ይረዳዎታል::

ትክክለኛ የማይክሮና ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተል የዋጋ ንረቱን ህመም ማስታገስ እንደሚቻል የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቹ ይጠቁማሉ:: በርግጥ የምጣኔ ሀብት ፅንሰ ሃሳቦች ሙልጭልጭ ናቸው:: ሽቅብ የተቆለለ መጽሐፍ ማለት ናቸው:: አንዱ ሲነካ ሌላው ሊፈርስ ይችላል:: ይሁንና እርስዎም ቢሆኑ የራስዎን የማይክሮና ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን መከተል የግድ ይልዎታል:: ለምሳሌ አላስፈላጊ ወጪዎችን መቀነስ፣ ገንዘብዎን ለሚፈለገው አላማ ብቻ ማዋልና መቆጠብ ያስፈልግዎታል:: በዚህ የኑሮው ውድነት በብርቱ እየተፈተኑ እንደሆነ ይታመናል:: ሆኖም ፈተናውን ሊያልፉ የሚችሉት እንዲሁ ቁጭ ብለው በመቆዘም አይደለም:: ይልቁንም ሁለት ሶስት ሥራ ሰርቶ ገቢ በመጨመርና የሚገኘውን ገቢ በአግባቡ በመጠቀም መሆኑን አምነው በዚህ መርህ መሠረት ወደ ተግባር ይግቡ::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You