በክልሉ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 23 ሺህ 500 ሔክታር በዘር ይሸፈናል

አዲስ አበባ፦ በ2016 ዓ.ም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 23 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በዘር እንደሚሸፈን የአፋር ክልል የእንስሳት፣ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ አሕመድ መሐመድ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በአፋር ክልል አጠቃላይ በምርት ዘመኑ 100 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ በስፋት እየተሰራ ይገኛል። ከዚህም ውስጥ በመስኖ ስንዴ 23 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዷል።

የአዋሽ ወንዝ ተፋሰስን ተከትሎ በዞን አንድና ዞን ሦስት ስር በሚገኙ ወረዳዎች ላይ የመስኖ ስንዴ ላይ ትኩረት በማድረግ አርብቶ አደሮች፣ ከፊል አርብቶ አደሮችና ማህበራት የመሬት ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

በበጋ መስኖ ስንዴ ከሚለማው መሬት ከ21 ሺህ ሄክታሩ በላይ የሚሆነው በባለሀብቶች፣ የተቀረው ደግሞ በከፊል አርብቶ አደሮችና በማኅበራት የሚለማ መሆኑን አቶ አህመድ ጠቁመዋል።

እንደ አቶ አህመድ ገለጻ፤ ባለፈው ዓመት በተከናወነው ሥራ የነበሩ ተግዳሮቶችንና ምቹ አጋጣሚዎችን በመለየት ወቅቱን በጠበቀ መልኩ የበጋ ስንዴ እርሻ ቀደም ብሎ ከሚከናወንባቸው ዞኖች በተጨማሪ ዞን አምስት ላይ የሚገኙ አዲስ አካባቢዎች ላይ ምርቱ ይለማል።

በግብርና ስራው ሜካናይዜሽንን በስፋት በመጠቀም ወደሥራ እንደሚገባ አመላክተው፤ በክልሉ በተቋቋመው የቴክኒክ ቡድን አማካኝነት በፕሮጀክቶችም ሆነ በሌሎች ድጋፎች የመጡ የእርሻ ትራክተሮች ያሉበትን ሁኔታ በማረጋገጥ ወደሥራ ለመግባት ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ከመስኖ ስንዴ ልማት ባለፈ በመኸር እርሻ ሥራ 30 ሺህ ሄክታር ለማልማት ታቅዶ ከ22 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል ብለዋል።

በክልሉ ዞን አንድና በዞን ሦስት በሚገኙ ወረዳዎች ማሽላ፣ ስንዴ፣ በቆሎ እና የመሳሰሉ ሰብሎችን ማልማት መቻሉን ዳይሬክተሩ አንስተዋል።

በተጨማሪም ማሾ፣ ሰሊጥ፣ በሎቄ፣ ጥጥ፣ ሽንብራ፣ጤፍና ገብስ በስፋት ለማልማት እቅድ ተይዟል ሲሉ አመላክተዋል።

በመኸር እርሻው የምርት አሰባሰብ ወቅት የምርት መባከን እንዳይፈጠር የቢሮው አመራሮችም ጭምር ያሉበት የቴክኒክ ቡድን ሙያዊ ድጋፍና የክትትል ሥራ በማከናወን ከአስተራረስ ጀምሮ እስከ ምርት አሰባሰብ ድረስ በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።

ባለፈው የምርት ዘመን ከክልሉ አቅም በላይ የሆኑ ተግዳሮቶች እንደነበሩ አንስተው፤ በተለይ የግሪሳ ወፍ በስንዴ ምርት ላይ ትልቅ ተግዳሮት እንደነበር አስታውሰዋል።

በቀጣይም የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብና በሰብል ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ተባዮችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋምት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You