የፈረንሳይ ለጋሲዮን እግር ኳስ ክለብ በተስፋ ጎዳና

ከተመሰረተ ገና አንድ ዓመቱ ነው፤ እንቅስቃሴውን ለተመለከተ ግን የብዙ ዘመን ልምድ ያለው ይመስላል። በ2014 ዓ.ም መጨረሻ ሕጋዊ ፈቃድ አግኝቶ በ2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አንደኛ ዲቪዚዮን እግር ኳስ ተሳታፊ በመሆን ወደ ከፍተኛ ዲቪዚዮን ማለፉን አረጋግጧል። ከነገ በስቲያም የአንደኛ ዲቪዚዮን ቻምፒዮን ለመሆን ለዋንጫ ይፋለማል። ይህ ክለብ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ይሰኛል። ከዚህ ቀደም አዱኛ፣ ኬላ ፍሬ፣ እንቡጥ አበባ፣ ባዮ ቪሌጅ፣ ይድነቃቸው ተሰማ፣ ኢፊኮ፣ ቻቺ፣ ነጎድጓድ እና ሌሎችም በዲቪዚዮን ደረጃ ይሳተፉ የነበሩ ጠንካራ ቡድኖች በነበሩበት የስፖርት ሰፈር የተመሰረተ ነው።

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የእነዚህ ክለቦች እንቅስቃሴ ተቀዛቅዞ ነበር። ይህን ለማስተካከልም ጥረት እየተደረገ መሆኑን የአዲሱ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ክለብ ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ከብካብ እንዲህ ሲሉ ይናገራል ‹‹ክለቡ ሕዝባዊ እንዲሆን ነው የምንፈልገው። አደረጃጀቱም ሆነ አሰራሩም የሕዝቡ እንደሆነ በሚያሳይ መንፈስ ነው››። የክለቡ ምክትል ፕሬዚዳንት አቤል ገብረኪዳን በበኩሉ፣ ክለቡ ሕዝባዊ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች ስለመኖራቸው ያስረዳል። በቡድኑ የጨዋታ ቀን የሚታደመው የተመልካች ብዛት በአንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር ላይ ከተለመደው በላይ መሆኑ አንዱ ማሳያ ሲሆን፤ በጨዋታዎቹም ከ1ሺ በላይ ማልያ ተሽጧል። በክለቡ የተመዘገቡ በርካታ ደጋፊዎች ያሉት ሲሆን በርካታ ተከታዮች ባለው የማሕበራዊ ገጹም ከደጋፊዎቹ ጋር ይገናኛል።

ክለቡ መሰረቱን ሕዝባዊ ማድረጉም ጠንካራ ወዳጆችን እንዲያፈራ አስችሎታል። ከእነዚህ መካከል አንዱ በኢትዮጵያ የሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ አምባሳደር የሆኑት ሬሚ ማርሾ በቅርቡ በቡድኑ ልምምድ ላይ ተገኝተው ማበረታቻ መስጠታቸው ይጠቀሳል። ቡድኑ ከወራት በፊት በተከበረው የፈረንሳይ ብሔራዊ በዓል ላይ ተጋብዞ የታደመ ሲሆን፤ ኤምባሲው በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ ይህን ከክለቡ ጋር ያለውን ግንኙነትም ዘግቧል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ፕሬዚዳንቱ አቶ ቴዎድሮስ ‹‹ከኤምባሲው ጋር ያለን ግንኙነት በጣም በጎ የሚባል ነው። አምባሳደር ሬሚ መልካም ሰው ናቸው፤ የክለባችን ደጋፊ እንደሆኑም ነግረውናል። ይሄም ለእኛ አስደሳች እድል ነው!›› በማለት ተናግሯል።

የክለቡና ኤምባሲው ግንኙነትን በተመለከተም ‹‹ግንኙነታችን ተቋማዊ እንዲሆን ነው ፍላጎታችን። የሚኖረን ትብብርም በእግር ኳሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በትምህርት እና ሌሎች የአካባቢውን ሕብረተሰብ በሚጠቅሙ ጉዳዮች ዙሪያ እንዲሆንም ተስማምተናል። አምባሳደር ሬሚ እና የኤምባሲው ባልደረቦችም ክለባችንን ለማገዝ ፈቃደኛ ናቸው። እኛም ጂምናዚየም እንዲገነቡልን እና ሜዳውን በማስተካከል እንዲያግዙን ጠይቀናቸዋል። በጎ ምላሽም አግኝተናል›› በማለት ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቤል ይናገራል። ክለቡ ከኤምባሲው በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ የካ ክፍለ ከተማ፣ አዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን እንዲሁም አካባቢውን ከሚያስተዳድሩት የወረዳ አመራሮች ጋርም ውጤታማ ግንኙነት እንዳለውም አክሏል።

ይህም ጥሩ ግንኙነት ክለቡ አሁን የሚጠቀምበት የጨፌ ዞናል ስቴድየም በብዙ ሚሊየን ብሮች እንዲገነባ አድርጓል። በዚህም ተጠቃሚ ሲሆን፤ 26 ክለቦች በተሳተፉበት የአዲስ አበባ አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር ከምርጦቹ ሁለት ቡድኖች አንዱ ሆኖ ወደ ከፍተኛ ዲቪዚዮን አልፏል። ይህ ስኬት የቡድኑ አንድነት ውጤት እንደሆነ የሚጠቁመው የክለቡ አምበል ቴዎድሮስ ዘውዱ ‹‹ሁላችንም ክለባችንን እንወዳለን። እያንዳንዱን ጨዋታ ለማሸነፍም የምንችለውን ሁሉ ጥረት አድርገናል። አንድነታችን ውጤታማ እንድንሆን አድርጎናል››ም ይላል። የቡድኑ ተጫዋቾች ከአካባቢው የተገኙ ሲሆኑ ከልጅነታቸው አንስቶ በተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተጫወቱ ያደጉ ናቸው።

በአሁኑ ወቅትም የራሱን ‹‹ይድነቃቸው›› የተሰኘ የታዳጊዎች የእግር ኳስ ፕሮጀክት ይዞ እየሰራ ይገኛል። ከክለቡ አመራሮች አንዱ የሆነው አቶ ሀብታሙ ጌታቸው ክለቡ ቀጣይ ጊዜን ታሳቢ በማድረግ ፕሮጀክቶች ላይ እየሰራ መሆኑን ይገልጻል። ‹‹ዛሬ ለእኛ የሚጫወቱት ልጆች በሙሉ በአንድ ወቅት የሆነ ሰው የለፋባቸው ናቸው። ስለዚህም ከዋናው ቡድን ባለፈ በታዳጊዎች ላይ እንሰራለን። በተያዘው ዓመት ከ17 ዓመት በታች የሚወዳደር ቡድን ለማቋቋምም ዝግጅት ጀምረናል። በቀጣይም በሌሎች ምድቦች ላይ እንሰራለን›› ይላል።

የክለቡ አመራሮች እንደሚናገሩት በአሁኑ ወቅት ከአምስት በላይ የታዳጊ ፕሮጀክቶች ያሉ ሲሆን፤ ይህም ክለቡ ለሚመኘው አካባቢያዊ የእግር ኳስ ንቅናቄ ትልቅ ተስፋ ነው። ‹‹እኛም ሆነ ሌሎች በእግር ኳሱ ዙሪያ በአካባቢያችን የሚሰሩ ሰዎች የምንደክመው ኳስ ተጫዋችን ብቻ ለማፍራት አይደለም። ጤናማ ትውልድ ለመፍጠርም ነው!›› ይላል ፕሬዚዳንቱ ቴዎድሮስ። ክለቡም ይህን ዓላማ ሊሳካ በሚችልበት ሁኔታ ማደራጀት እና አጋዥ አካላትን ለማፍራት እየሰራ ነው። ከአራት ዓመት በፊት የተጀመረውና ክለቡ ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ የሚያዘጋጀው የመላው ፈረንሳይ ለጋሲዮን የእግር ኳስ ውድድርም በቀጣይ ሳምንት ሊጀመር ቀጠሮ ተይዞለታል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You