አዲስ አበባ፡- የሥጋና ወተት ኤክስፖርት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የሁለት ነጥብ 10 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ቅናሽ ማሳየቱን የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበሌ ለማ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ባለፈው ዘጠኝ ወራት 72 ነጥብ 71 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል። ይህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 74 ነጥብ 81 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከአገር ውስጥ ላኪዎች 64 ነጥብ 80 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 42 ነጥብ 45 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር፤ እንዲሁም ከውጪ አገር ባለሀብቶች 77 ነጥብ 92 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 30 ነጥብ 26 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ከእቅዱ አንፃር የሁለቱም ባለሀብቶች አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ ቢሆንም፤ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተሻሉ ናቸው።
ከሥጋና እርድ ተረፈ ምርት የተገኘው ገቢ የአንበሳውን ድርሻ የያዘ ሲሆን በአንፃሩ የዓሣ፤ የሥጋ፣ የማር፣ የበግ፣ የፍየል እና የዳልጋ ከብት አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያትም በዘርፉ ጠንካራ ሥራዎች አለመሰራታቸውና የዳልጋ ከብት ተወዳዳሪነታቸን በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ነው።
እንደዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ ለዕቅዱ አለመሳካትም በዕቅድ ታሳቢ የተደረጉት የሥጋና እርድ ተረፈ ምርት ኤክስፖርት ቄራዎች አላና፣ አክሰከር፣ አቢሲንያ እና ዮንግታይ በተለያዩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮች የተነሳ በአማካይ የዕቅዳቸውን 29 በመቶ ብቻ ኤክስፖርት ማድረጋቸው ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ በጥራት እና በዋጋ ተወዳዳሪ ሆኖ ከመቅረብ ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ በመጣው ውድድር፤ እንዲሁም የአገር ውስጥ የማር ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ ከዚህ በፊት የተሻለ አፈፃፀም ከነበራቸው የማር እና ሰም አቀነባብሮ ላኪዎች ከቤዛ ማርና ሸካ ኖርዲክ ውጪ ሌሎች በእቅድ የተያዙ ማርና ሰም አቀነባብሮ ላኪዎች ምንም ምርት አለመላካቸው ሌላው ለዕቅዱ አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆን በምክንያትም ይጠቀሳሉ።
ምርታማነታቸውና የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ መሆን፤ ካለውም ምርት በበቂ መጠን አለመቅረብ፤ የግብዓት እጥረት፤ የመብራት መቆራረጥ፤ የድርጅቶች የአመራር ብቃት ውስንነት የሚሰጡት ድጋፎች እሴት የሚጨምሩ አለመሆናቸው በዕቅድ አፈፃፀም ላይ የራሳቸውን አሉታዊ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከሥጋና የሥጋ ተረፈ ምርት፣ ከማርና ሰም፣ ከዓሣ፣ ከወተትና የወተት ውጤቶች ኤክስፖርት 192 ነጥብ 72 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ግብ ጥሎ ነበር።
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2011
በአጎናፍር ገዛኸኝ