የውጭ ምንዛሬ ያስገኛሉ ተብለው ተስፋ ከተጣለባቸው የግብርና ዘርፎች መካከል የቁም እንስሳት አንዱ ነው። ይሁን እንጂ፤ በተደጋጋሚ ሕገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ ዘርፉን እየተፈታተነው ስለመሆኑ ይገለጻል። ሰሞኑንም ቢሆን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ዘርፉን ሕገ ወጥ የቁም እንስሳት ግብይት ፈተና እንደተጋረጠበት ያሳያል።
የግብርና ሚኒስቴር ከተለያዩ የግልና የሕዝብ ብዙኃን መገናኛ ለተውጣጡ ባለሙያዎች “የሚዲያ ባለሙያዎች ሚና በግብርና ልማት እንቅስቃሴ ውስጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ሰሞኑን ምክክር አድርጓል። በመድረኩ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ እንደሚሉት፤ የቁም እንስሳት ግብይት እየተከናወነ ቢሆንም ሕገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ ለዘርፉ ማደግ ፈተና ሆኖበታል።
ሕገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድን ለማ ስቆም እየተሰራ ቢሆንም ሊሻሻል አልቻለም የሚሉት ወይዘሮ አይናለም፤ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል ተብሎ ተስፋ ከተጣለበት አንዱ የግብርና ዘርፍ፤ እንደ ታሰበው መሆን አለመቻሉን ይጠቅሳሉ። በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር የሚወጡትን የቁም እንስሳት ማስቆም አለመቻሉንም ነው የሚያብራሩት፤ ዛሬም ሕገ ወጥ ንግድ በመኖሩ ዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት እያስገኘ አይደለም ይላሉ። እንዲህም ሆኖ ግን ዘንድሮ 30 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ግብይት መካሄዱን ይጠቅሳሉ።
በግብርና ግብአቶች ግብይትና በገጠር ፋይናንስ፤ በገበያ ጥናትና ማስፋፊያ፤ በግብርና ምርት ግብይት፤ እንዲሁም በግ ብርና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ሥራ ዎች ዙሪያ ትኩረት በመሰጠቱ የግብርና ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ግብአቶች በተፈለገው መጠንና ጊዜ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ውጤታማ የግብይት ሥርዓት ለመገ ንባት የሚያስችሉ አዳዲስ አሠራሮች እየ ተዘረጉ መሆናቸውን በማመልከትም፤ በወቅታዊ መረጃ ላይ የተመሰረተ ግብይት በማከናወን በዋጋና በጥራት ተወዳዳሪ ምርት ለማቅረብ፤ አምራቹን ከሸማቹ የሚያስተሳስር የገበያ ሥርዓት ለመፍጠር ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም
ይጠቅሳሉ። ማዳበሪያን በአገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆኑን በማመልከትም፤ ይህ እስኪተገበር ከውጭ አገር የሚደረገው ግብይት ዓለም አቀፍ ገበያን ያገናዘበና በሥርዓት የሚመራ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
ጠቀሜታቸው ባግባቡ የማይታወቁ እንደ ቀርከሀ ያሉ ምርቶች ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ መሆናቸውን የሚጠቁሙት ወይዘሮ አይናለም፤ ጠቀሜታቸው ባግባቡ የማይታወቁትን የግብርና ምርቶች የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚተገበርም ይናገ ራሉ።
አርሶ አደሩ ትክክለኛ የቴክኖሎጂ ምንጭ የሆነውን ለይቶ እንዲጠቀም፤ በቴክ ኖሎጂ የተገኙ ስኬቶችና መረጃ በማድረስ ሌሎች እንዲማሩበትና እንዲተገብሩት ይደረ ጋል ሲሉም ተናግረዋል። ብዙኃን መገናኛ የበኩሉን እንዲወጣም ያሳ ስባሉ።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲም፤ የዘርፉን ምሁራን የሚያቀርብና የሚያበረታታ አሠራር ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑንም ይጠቁማሉ። የአዋጅና የፖሊሲ ክለሳ መጀመሩንም ያመለክታሉ። በቆላ አካባቢዎች ጭምር የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ግብ ርናው የሚጠበቅበትን ያህል እንዲያድግ እና ሌሎቹን ዘርፎች እንዲደግፍ የሚደረግበት አሠራር እንደሚዘረጋም ይጠቁማሉ።
ግብርና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ፤ በምርምር የተደገፈና የተቀናጀ መሆን አለበት የሚሉት አቶ ሳኒ፤ ይህንን ባማከለ መንገድ ሚኒስቴሩ አርማውን ለመቀየር እንቅስቃሴ ላይ መሆኑንም ይጠቁማሉ። ለስንዴ ምርት ምቹ ሁኔታዎች በአገር ውስጥ ቢኖርም እ.ኤ.አ ከ1961 ጀምሮ እስካሁን ስንዴ ከውጭ አገር እየገባ ነው ብለዋል።
በአገር ውስጥ ላለው ነባራዊ ሁኔታ ተስማሚ፤ አካታች እና በሚያስገኘው ውጤት ላይ የተመሰረተ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ሲሉም ይጠቁማሉ። የግብርና ዕድገቱ ከፍላጎትና ከዘርፉ የማደግ ዕድል ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው ሲሉም ጠቅሰዋል። የግብርናው ዘርፍ የማደግ ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ የሚጠበቅበትን ያህል ማደግ እንዳለበትም ነው ያመለከቱት።
የግብርና ዘርፉ እንዲያድግ፤ የተለየ ጥረት ማድረግና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጠቀም፤ በገበያ የሚመራ ግብርና መፍጠርና አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም እንዲያመርቱና አመራረታቸውን እንዲያዘምኑ ማድረግ ይገባል ይላሉ።
በሰው ሀብት ልማቱ ረገድ የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚያስፈልግም ይጠቁማሉ። ለሰፋፊ እርሻ ልዩ ድጋፍ መስጠት፤ የመስኖ አጠቃቀምን ማሳደግና የሕግ ማዕቀፎችን በማስተካከል ለዘርፉ ዕድገት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ይሰራል ሲሉም አመልክተዋል።
የእንስሳት ሀብት ዘርፍ ልማት ዳይሬክተሩ አቶ ታሪኩ ተካ እንደሚሉትም፤ የአገር ውስጥ የወተት ፍጆታን አሟልቶ በዓመት እስከ 20 ሚሊዮን ሊትር ወተት አምርቶ የመላክ አቅም በአገር ውስጥ አለ። ለዚህም በቂ ባለሙያ፤ የተፈጥሮ ጸጋ ይገኛል። ወተት ወደ ውጭ በመላክ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት የድርሻውን እንዲወጣ መደረግ የሚችልበት ዕድል አለ።
ሆኖም ከዚህ በተቃራኒ ሆኗል የሚሉት አቶ ታሪኩ፤ በ2010 ዓ.ም ብቻ 10 ሚሊዮን ዶላር የወተት ምርት ከውጭ አገር ግዢ ተፈጽሞ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን ይናገራሉ። ከውጭ አገር የሚገባ የወተት ምርት በአገር ውስጥ ምርት በመተካት ማስተካከል ይገባል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2011
በዘላለም ግዛው