አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ለአገር አቀፍ ብሔራዊ ፈተና ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።
የትምህርት ቢሮው በከተማው ከሚገኙ ሁሉም የፈተና ባለድርሻዎች ጋር ትናንት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል የፈተና ንቅናቄ ማስፈፀሚያ ሰነድ ላይ ውይይት ባደረገበት ወቅት ለፈተናው የሚያስፈልገው ሥራ ሁሉ መጠናቀቁን አስታውቋል።
የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የማህበራዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ኢንጅነር እንዳወቅ አብጤ፤ ዝግጅቱ መልካም መሆኑን አንስተው ፈተናው እስከሚጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የንቅናቄውን ተሳታፊዎች ጠይቀዋል።
የትምህርት ቢሮው ኃላፊ አቶ ታቦር ገብረመድህን በበኩላቸው፤ የተደረገው የፈተና ዝግጅት በተቀመጠው መርሃ ግብር መሠረት ተግባራዊ እንዲሆን በፈተናው ላይ የሚሳተፉ ባለሙያዎች፤ ባለድርሻ አካላትና ኅብረተሰቡ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተናገረዋል።
በቢሮው የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ትግበራ ባለሙያ አቶ ፍቃደ ፋንታዬ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ፈተና ክፍል 61 ሺህ 80 የ10ኛ እና 32 ሺህ 760 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን፤ እንዲሁም 77 ሺህ 995 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ለፈተና ሙሉ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ የፈተናው ህትመት ዝግጅት በጥንቃቄ ተከናውኗል። በከተማ፣ በክፍለ ከተማ፣ በወረዳና በትምህርት ቤት ደረጃ ፈተናውን ለማስፈጸም ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል። የፈተናው ፈታኞችና ተቆጣጣሪዎች
መረጣም ተከናውኗል፤ የጋራ ግንዛቤም ተፈ ጥሯል። ፖሊስ፣ የመምህራን ማህበር እና የኅብረተሰብ ተወካዮችም ለፈተናው ዝግጅት እንዲያደርጉ ሥራ ተሰርቷል።
በአዲስ አበባ ከዚህ ከቀደም በተካሄዱት ፈተናዎች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በመ ጠቀም፤ በምስጢር ጎበዝ ተማሪዎችንና መምህራንን በማስገደድ ፈተና የመኮረጅ አጋጣሚዎች ነበሩ።
ከዚህ በተጨማሪ ፈታኞችና ተቆጣጣሪዎች በአቅም ማነስና ርካሽ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ኩረጃን ዝም ማለት፤ የግል ትምህርት ቤቶች ፈተናዎችን ተማሪዎቻቸው እንዲኮርጁ የመፈለግና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ኮራጆችን ዝም የማለት አዝማሚያዎች መታየታቸውን በማንሳት በዘንድሮው ዓመት ግን እነዚህን ክስተቶች ለመቆጣጠር በጥንቃቄ መሠራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ፈተናው ከሰኔ 3 እስከ 14 ቀን 2011 ዓ.ም ይካሄዳል። የአስረኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተና ከሰኔ 3 እስከ 5፤ የ12 ክፍል ተማሪዎች ከሰኔ 6 እስከ 11 እንዲሁም የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ከ12 እስከ 14 ይካሄዳል።
በሌላ በኩል ትምህርት ቢሮ፣ ከስድስት ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 850 ተማሪዎችን በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚያስፈትን ታውቋል። በአዲስ አበባ በኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት የሚሰጥባቸው 27 ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2011
በአጎናፍር ገዛኸኝ