አዲስ አበባ፡- ከ2011/2012 የመኸር እርሻ 406 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፣ በ2011/2012 የመኸር እርሻ 13 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
ከአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የማዳበሪያ ግዢ ተፈፅሞ ወደብ ላይ ደርሷል። ከዚህ ውስጥ ከ600 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ማዳበሪያ ወደ አርሶ አደሩ ተጓጉዟል። ከዚህ በተጨማሪም፤ በክልሎች ከ12 ሺህ በላይ የልማት ጣቢያ ሠራተኞች ስልጠና ወስደዋል። ከዘርፉ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች ጋርም ምክክር ተደርጓል።
እንደርሳቸው ገለፃ፤ ከተገዛው ማዳበሪያ ውስጥ ወደ አርሶ አደሩ የተጓጓዘው ግማሽ ያህሉ በመሆኑ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር፤ ከባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት፤ እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ግብአቶችን በማጓጓዝ ረገድ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው።
“አብዛኛው የበቆሎ ምርጥ ዘር የሚገኘው ከምዕራብ ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢዎች ነው። ይሁን እንጂ፤ ባለፉት ወራት በነዚህ አካባቢዎች በተከሰተው አለመረጋጋት ምክንያት ምርጥ ዘር በአግባቡና በሚፈለገው መጠን መሰብሰብ አልተቻለም።
በዚህ ምክንያት ክፍተት እንዳይፈጠር አርሶ አደሮች ሌሎች አማራጭና ተተኪ ምርጥ ዘሮችን እንዲጠቀሙ ምክረ ሃሳብ ተሰጥቷል” ብለዋል። በአስገዳጅነት መገዛት ያለባቸውን የምርጥ ዘሮች ግዢ ለመፈጸም አቅጣጫዎች መቀመጣቸውንም ኃላፊው ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል፤ በዘንድሮው የበልግ እርሻ እስካሁን ድረስ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር እንደተሸፈነና በዝናብ መቆራረጥ በመኖሩና በወቅቱ ባለመዝነቡ ምክንያት ለበልግ እርሻ የተያዘውን አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር የመሸፈን ጥቅል እቅድ እስከ ግንቦት 30 ድረስ ለማጠናቀቅ መታሰቡንም አቶ ዓለማየሁ ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2011
በአንተነህ ቸሬ