አዲስ አበባ፡- ለጤና ሙያተኞች በተሰጣ ቸው ላይ ሁለት እርከን ተጨምሮላቸው የተፈጠረው ልዩነት እንዲስተካከል መደረጉንና በሐምሌ ወር ሁለት ዓመት ለሚሞላቸው የጤና ሙያተኞችም በዕድገት ስም ሦስት ዕርከን እንዲሰጣቸው ውሳኔ ማግኘቱን ሲቪስ ሰርቪስ ኮሚሽን ገለጸ።
የጤና ሙያተኞች ቀደም ሲል በተሰ ጣቸው አንድ እርከን ደመወዝ ጭማሪ ሁለት እርከን እንዲጨመርላቸውና ሌሎች ክልሎች እንዳደረጉት የተፈጠረው ልዩነት እንዲስተካከል፤ በሐምሌ ወር ሁለት ዓመት ለሚሞላቸው የጤና ሙያተኞችም ሌላ ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልግ በዕድገት ስም ሦስት ዕርከን እንዲሰጣቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የውሳኔ ሃሳብ ቀርቦ መጽደቁን የሲቪስ ሰርቪስ ኮሚሽን ለዝግጅት ክፍሉ በላከው መግለጫ ገልጿል።
በኮሚሽኑ የሰው ሀብት አስተዳደር አማካሪ አቶ ይገዙ ጀማነህ፤ በ2009 ዓ.ም ጭማሪ ሲሰጥ እርከን ውስጥ የገቡ ባለሙያዎችና አጠቃላይ የመንግሥት ሠራተኞች በደንቡ መሠረት ከመነሻ በታች የሆኑትን ወደ መነሻው የማምጣት፤ መነሻውን ለደረሱበት ደግሞ አንድ ተጨማሪ እርከን እንዲያገኙ ተደርጎ እንደነበረ በማስታወስ፤ ለጤና ሙያተኞች አንድ እርከን ተሰጥቷቸው የነበረው ተቀይሮ ሁለት እርከን ተጨምሮላቸው የተፈጠረው ልዩነት እንዲስተካከል መደረጉን ጠቁመዋል።
በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ሁለት ዓመት ለሚሞላቸው የጤና ሙያተኞችም ደግሞ ሌላ ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልግ በግንቦት 8 ቀን 2011 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ወስኖ ባሳወቀው በዕድገት ስም መሠረት ሦስት ዕርከን ጭማሪ እንዲሰጣቸው መባሉንም ነው የገለጹት፤ “ጄኢጂ” ከተተገበረ ግን አሁን የወረደው መመሪያ ሊቀር እንደሚችልም ጠቁመዋል።
“ኬሪየር ስትራክቸሩ” ይቀጥላል ያሉት አማካሪው፤ ባለሙያዎቹ ሦስት ሦስት እርከኖች እያገኙ “ጄኢጂ”ው ከገንዘብ ጋር ተሳስሮ ተግባራዊ እስከሚሆን ይቀጥላሉ ብለዋል። የሚተገበረውም በዚህ ዓመት ይሁን በቀጣይ ጊዜውን በውል እንደማያውቁትም ተናግረዋል። የውጤት ምዘና ተግባራዊ እንደሚደረግ በመጠቆምም፤ ትግበራው የሚያስገኘው ውጤት ሊኖርም ላይኖርም ይችላል፤ እንደ ባለሙያው አፈጻጸም ይወሰናል ነው ያሉት፤
የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ዶክተር አየለ ተሾመ፤ የጤና ሙያተኞች አንዱ ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን በማንሳት፤ “ሙያው ቴክኒካል ነው፤ ሲከፈል የሚጨመር ሳይከፈል ደግሞ የሚቀነስ አይደለም። የሰሞኑ ሥራ ማቆምም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያደረሰው ተጽእኖ የለም” ብለዋል። ጥያቄው የቆየ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል። ጥያቄው መመለሱ አግባብነት እንዳለውም ተናግረዋል።
ትናንትናም የተወሰኑ ተመራቂ ተማሪዎች ሥራ እናቆማለን ብለው የቀሩ እንዳሉ የጠቀሱት ዶክተር አየለ፤ ቀድመው በደብዳቤ አሳውቀው ስለነበረ ያለውን የሰው ኃይል በመጠቀም ሥራው መሸፈኑን ተናግረዋል። በአገልግሎቱ ላይ የተፈጠረ ችግር ባይኖርም ባለሙያዎች ላይ ጫና ማሳደሩን ግን ጠቁመዋል።
አሁን የሚነሱ ጥያቄዎች አብዛኛዎቹ እርሳቸው ተማሪ በነበሩበት ጊዜም ይነሱ እንደነበሩ ጠቅሰው፤ ከደመወዝ ማስተካከያ፣ የጤና ትምህርት አሰጣጥ ሥርዓትና ምቾት፣ ጥቅማ ጥቅምና የጤና ደህንነት ችግሮች የዘርፉ ማነቆዎች እንደሆኑና ሊቀየሩ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። “በጥያቄዎቹ ልዩነት የለንም፤ ልዩነታችን የጤና ባለሙያዎች በጥያቄው አቀራረብ ላይ ነው። ባለሙያዎች ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ አገልግሎት ፈላጊዎችን እያገለገሉ ሊሆን ይገባል” ብለዋል።
በእኛ ዕድሜ ጥያቄ ስናቀርብ ተሰሚነት አልነበረንም ያሉት ዶክተር አየለ፤ አሁን ጥያቄው ምላሽ ማስገኘት መጀመሩን በበጎነት አንስተዋል። አብዛኛው ሐኪም ገቢው ዝቅተኛ ነው፣ የደህንነት ስጋቶችም አሉበት፤ መስተካከል ይገባዋል ብለዋል። የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻል እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን በመጠቆምም፤ በአገር አቀፍ ደረጃ በውጤት ላይ የተመሰረተ የአከፋፈል ሥርዓት መተግበር አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።
በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክተር ዶክተር ይርጉ ገብረ ሕይወት በበኩላቸው፤ በሆስፒታሉ ዋናውን አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች ሥራ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። እስከ ትናንት በነበረው ሂደት ግን ተለማማጅ ዶክተሮች ተግባር ላይ እንዳልተገኙ ጠቅሰዋል። “ተማሪ ሐኪሞች ናቸው፤ አስተዋጽኦ አላቸው፤ ያም ሆኖ ግን ሥራው ቀጥሏል” ብለዋል። በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተፈጠረ ምንም ተጽዕኖ አለመኖሩን ገልጸዋል።
ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የጤና ባለሙያ እንዳሉትም፤ ለሠራተኞች የጤና ደህንነት ክፍያ እንዲኖር፤ የሥራ ላይ ዋስትና ሊገባላቸው፤ የመኖሪያ ቤትና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ሊሰጧቸው እንደሚገባ አመልክተዋል። እንደርሳቸው አባባል፤ የሥራ ሰዓት በሕጉ መሠረት እንዲከበርላቸው፤ በእ ረፍት እንዲጣጣላቸው ወይም በክፍያ እንዲካካስላቸው ነው የሚፈልጉት፤ መድኃኒቶች እንዲሟሉ፤ የሕክምና መሣ ሪያዎች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ እና አስፈላጊ የሕክምና መሣሪያዎች እንዲሟሉ የቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ እንደሚገባም አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2011
በዘላለም ግዛው