አዲስ ዘመን ድሮ

በቀደሙት ዓመታት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሲወጡ የነበሩ የመረጃና የመዝናኛ ርዕሰ ጉዳዮች የቀድሞዋን ኢትዮጵያ በኋልዮሽ መነጽር አጉልተው የሚያሳዩን የማንነት ቅርሶች ናቸው። እነዚህ ዓለም አቀፋዊ፣አህጉራዊና በተለይ ደግሞ ሀገራዊ ትውስታዎች የትናንቷን ኢትዮጵያ እንድናውቃት ከማድረጋቸውም በላይ አውቀን ዛሬያችንን በትናንትና መሠረት እንድንገነባ በእጅጉ ወሳኝ ናቸው። በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ አምዳችንም “ታሪክ ዘ ኢትዮጵያዊት ሐማሴን ተድላ ፅረፍታ ለጽዮን” ስለ ሀገራችን የቀደመ ታሪክ የሚነግረንን ይህን ጽሁፍ ለአንባቢ በሚመች መልኩ በመቀንጨብ በሌላ በኩል ደግሞ ከእንስሳቱ ዓለም የአመጽና ወጣ ያሉ አስገራሚ ድርጊቶችን በማከል ቀርበዋል።

ታሪክ ዘ ኢትዮጵያዊት ሐማሴን ተድላ ፅረፍታ

ለጽዮን

የኢትዮጵያ መንግሥታት የትውልዱ ዘር ምንጭ መፍለቂያና የቀደመ ታሪክ መጠየቂያና የእምነት መጀመሪያ እንደሆነች እንኳንስ ደቂቀ ሴምና ደቂቀ ካም ደቂቀ ያፌት ቢሆኑ ቅሉ ይህን የታሪክ መሠረት ማናወጽ የተፈጥሮ ባሕርይና ልማድ ሀገርን መደምሰስ የአባትን እርግማን መልበስ የእግዚአብሄርን ፈቃድ መጣስ እንደሆነ መሳት የለባቸውም።

…..

የኩሽ ልጅ ሰብታህ በመርዌ ከተማ ከነገሠ ጀምሮ 1ኛ ፒኦር 15 ዓመት ነግሦ እስኪሞት ድረስ 22 ነገሥታት 560 ዘመን ሲነግሡ ኢትዮጵያዊት ሐማሴንን ቤተ መንግሥት አድርገው ከየመን መንግሥታት ጋር ሲዋጉ ይኖሩ ነበር።

የሰው ዘርም በአንድ ጊዜ መላ አልበቃም ነበርና የካም ዘሮች ጥቂት ጥቂት እያሉ እስከ የመንና እስከ ህንድ ጠረፍ ደረሱ። በሐማሴን ቤተ መንግሥት ሁነው በአክሱም አጠገብ ያለውን የሳባን ቤተ መንግሥት ሠርተዋል። ይህም ቢታወቅ የመርዌ አንጻር በሚሆን በሀገረ ናግራን ልዩ ልዩ የሆኑ የቤተ መንግሥት ፍርሽራሾች ግምቦች ይገኛሉ። መላዋ ኢትዮጵያዊት ሐማሴንም ለኢትዮጵያ ሁሉ ታሪክ ሁና ትገኛለች።

(አዲስ ዘመን መጋቢት 4 ቀን 1957ዓ.ም)

ዓመጸኛው ዝንጀሮ ተገደለ

ሁለት ቀን ሙሉ በመንደር ውስጥ እየተዘዋወረ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሰው ዝንጀሮ ተገደለ።

በልደታ ወረዳ መካኒሳ ቀበሌ ከመጣበት ያልታወቀ አንድ ገመር ዝንጀሮ መጋቢት 18 ቀንና መጋቢት 19 ቀን 7ሰዎችን ነክሶ ከማቁሰሉም በላይ፤በመንደሩ የሚገኙትን ውሾች በሙሉ እንዲባረሩ አድርጎአል።

በዚሁ ዝንጀሮ ከተነከሱት 7 ሰዎች መካከል 4ቱ በብርቱ ስለቆሰሉ ለሕክምና ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ከአሜሪካ ሉተራን ሚሲዮን ቄስ ዓለም ታደሰ በላይ ገልጠዋል። .

እራሳቸውን ለመከላከል ከሞከሩት መካከል የስካንስካ ጋራዥ ሠራተኞች ትናንት በ11 ሰዓት ገደማ ላይ በሦስት ጥይት ከመቱት በኋላ ዝንጀሮው የሞተ መሆኑን ከሠፈርተኛው ለመረዳት ተችሎአል።

በሠፈርተኛው ላይ ጉዳት ያደረሰው ዝንጀሮ እሬሳ አሁንም ከመካኒሳ በታች ከሚገኘው ወንዝ ዳር ተጥሎ ይገኛል።

(አዲስ ዘመን ጥቅምት 15 ቃን 1976ዓ.ም)

አህያም እንደ ጅብ

እጎረቤታችን ኬንያ ውስጥ ነው። ከላይ የተጠቀሰው ርእስ ግን የአንዲት የኪትዮ የቤት እመቤትን የሕይወት ዋጋ አውጥቶአል።

ነገሩ እንዲህ ነው ወ/ሮ ሞቢላ ንጃ ንጊ አህያቸውን ኪኦንግዊ የሚባለው ወንዝ ወደሚገኝበት ሚምባኒ ወደተባለ ስፍራ ውሃ በቆርቆሮ ለመቅዳት ጭነውት ይሄዳሉ።

ሞቢላም እወንዙ እንደደረሱ የመጀመሪያውን ቆርቆሮ ለመሙላት ጎንበስ ሲሉ አህያው ጠንካራ የሆነውን መንጋጭላውን በእግራቸው አካባቢ አስጠግቶ በሚሰቀጥጥ አኳኃን ወዲያውኑ ሸርክቶ ጣለውና አኝኮ ዋጠው። በዚህ ብቻ አላበቃም። ይህ ወደ አውሬነት የተለወጠው አህያ እመት ሞቢላ 2ኛውን አደጋ በእጃቸው ለመከላከል ሲሞክሩ እሱንም ቦጭቆ ውጦታል።

የዚህ አህያ ባለቤት የሆኑት የእመት ሞቢላ አማትም ከዚያን ጊዜ አንድ ምሽት በፊት አህያው ፍየላቸውን መዋጡን ቢናገሩም ያን ቀን ግን ብዙ ጄሪካን ውሃ ሲያመላልስ መዋሉን ጨምረው ተናግረዋል።

ይህ አህያ መሳሪያ በያዘ አንድ ሰው ራሱ ላይ ተመትቶ ቢሞትም መንደርተኞቹ ተጠራርተው በመምጣት ራሳቸውን የሳቱትን ወይዘሮ ሞቢላን ወደ ሆስፒታል በመውሰድ ላይ ሳሉ ወይዘሮዋ መንገድ ላይ ሞተዋል።

(አዲስ ዘመን ታህሳስ 20 ቀን 1976ዓ.ም)

ዝንጀሮ ሰው በላ

ጅማ፤ (ኢዜአ)- በከፋ ጠቅላይ ግዛት በሊሙ ኮሣ ወረዳ ግዛት በርቄ በተባለው ቀበሌ አንድ ዝንጀሮ የ2 ዓመት ዕድሜ ያለው ወንድ ልጅ መብላቱ ተነገረ። ዝንጀሮው ሕፃኑን ልጅ ከበላ በኋላ በተጨማሪ አንዲት የ3 ዓመት ዕድሜ ያላት ልጅ ለመብላት ሲሞክር ሰው ደርሶ አድኗታል። ሆኖም ልጅቷን ለመብላት መሬት ጥሎ በመቦጫጨቅ የመቁሰል አደጋ ያደረሰባት መሆኑ ከቀበሌው መልከኛ ተገልጧል ሲል የወረዳው ግዛት ጸሐፊ አቶ ለማ አዱኛ ገለጡ።

ዝንጀሮው አንዱን ልጅ በልቶ ሌላዋን ልጅ ያቆሰለው ልጆቹ በቤታቸው አቅራቢያ ሲጫወቱ አግኝቷቸው መሆኑን ዋና ጸሐፊው በተጨማሪ አረጋግጠዋል። ይኸው ዝንጀሮ ልጆቹን ከመብላቱ በፊት፤ ከ30 ያላነሱ በጐችና ፍየሎች በልቶ ወደ ጫካ እየተሸሸገ የኖረ መሆኑ ታውቋል።

(አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 1962 ዓ.ም)

የዓይን ጠብታ ወይንስ ቡና?

ስለ እራስ ወዳድ ነጋዴዎች ያልተባለና ያልተጻፈ ነገር የለም። ለሚሰጣቸው ገንዘብ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ብዙ ተመክሮአል። ይሁን እንጂ በግል ጥቅም ታውረው ነውሩን እንደጌጥ በማየት ከብዝበዛ ሥራቸው ያልታቀቡ ጥቂት አይደሉም።

ከጥቂት ዓመታት በፊት 2 እና 25 ሳንቲም የነበረው አንድ ፍንጃል ሲኒ ቡና ዛሬ 50 እና 55 ከዚያ በላይ አድርገውታል። ይግረማቸሁ ብለው ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አካባቢ ያሉት መደዳ ቡና ቤቶች የዓይን ጠብታ ይመስል ከፍንጃሉ ግማሽ የወረደ ከጉሮሮ የማይደርስ ቡና ጠብ እያደረጉ ማቅረብ ጀምረዋል። ድርጊቱ በተለይ የቡና ሱስ ያለብንን ሰዎች ቅሬታ አሳድሮብናልና ራሳቸው አገልግሎታቸውን ያስተካክሉ። አሻፈረን የሚሉ ከሆነ ጉዳዩ በቸልታ መታለፍ ስለሌለበት የሚመለከተው ያስብበት።

(አዲስ ዘመን የካቲት 16 ቀን 1976ዓ.ም)

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2016

Recommended For You