የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ አገራዊና ክልላዊ የፈተና ማስፈፀሚያ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ግንቦት 13 ቀን 2011 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል።
ዘንድሮ አዲስ አበባ 60,619 ተማሪዎች ለ10ኛ ክፍል እንዲሁም 31,833 ተማሪዎች ደግሞ ለ12ኛ ክፍል ለአገር አቀፍ ብሄራዊ ፈተና የተመዘገቡ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ባለሙያ አቶ ፍቃዱ ፋንታዬ ተናግረዋል።
አቶ ፍቃዱ አክለውም በ2011 ዓ ም በሚካሄደው ፈተና በአዲስ አበባ ከተማ ለ10ኛ ክፍል 79 እና ለ12ኛ ክፍል 37 የፈተና ጣቢያዎች እንደተዘጋጁ ተናግረዋል።
የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናን በተመለከተም አቶ ፍቃዱ እንዳሉት በከተማዋ 77,995 ተማሪዎች ለፈተና የተመዘገቡ ሲሆን እነዚህን ተፈታኞች ለማስተናገድ 152 የፈተና ጣቢያዎች፣ 650 ሱፐር ቫይዞሮች߹ 1ሺህ 950 ፈታኞች እና 10 የጉድኝት ማዕከል አስተባባሪዎችመዘጋጀታቸውንም ገልፀዋል።
በመድረኩ ላይ እንደተገለጸው በ2010 ዓ.ም የፈተና ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን በመመርመር በ2011 ዓ.ም እንዳይከሰቱ ፈተናውን በተረጋጋ እና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ለመምራት ዝግጅት መደረጉም ተገልጿል።
የዘንድሮው ክልላዊና ብሄራዊ ፈተናዎች ደህንነት ተጠብቆ ተማሪዎች በተረጋጋ ሁኔታ ፈተናቸውን እንዲፈተኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በሙሉ ሀላፊነት የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በ2011 የትምህርት ዘመን በአገር አቀፍ ደረጃ 1,277,573 የ10ኛ እንዲሁም 322,317 የኛ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ሲሆኑ ከዚህ ውስጥ 860,201 የ10ኛ እንዲሁም 251,091 የ12ኛ መደበኛ ተማሪዎች መሆናቸው ይታወቃል።
በማእረግ ገ/እግዚአብሔር