«የኢትዮጵያ ሕልውና እና ልዕልና ከቀይ ባህር ጋር የተሳሰረ ነው» ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ሕልውና እና ልዕልና ከቀይ ባህር ጋር የተሳሰረ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የውሃና የቀይ ባህርን ጉዳይ በተመለከተ ሰሞኑን ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ሕልውናዋና ልዕልናዋ ከቀይ ባህር ጋር የተሳሰረ ነው።

የኢትዮጵያ የዘመኑ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ሠላምና አንድነትን ማስፈን፣ ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመው፤ ጂኦፖለቲካውን በመረዳት ሁለንተናዊ ብልጽግናን፣ሠላምና አንድነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በውሃ ተከባ ነገር ግን ውሃ የሚጠማት ሀገር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቀይ ባህርና ዓባይ ኢትዮጵያን የሚበይኑ ከኢትዮጵያ የተቆራኙ ለኢትዮጵያ እድገትና ጥፋት መሠረት መሆናቸውን አመልክተዋል።

በቀይ ባህር ጉዳይ በዓባይ ግድብ ላይ እንዳለው ድርድር መደራደር እንደሚቻል ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በታሪክ፣ ጂኦግራፊን ጨምሮ በኢኮኖሚና በዘር ተገቢ ጥያቄ አላት የሚል ስምምነት የነበር በመሆኑ ስምምነቱን መፈተሽ ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል።

አንዳንዶች የቀይ ባህር ጉዳይ ከኤርትራ፣ ከጂቡቲ ያጋጫል የሚል ስጋት እንዳላቸው የገለጹት ዶክተር ዐቢይ፣ በቀይ ባህር ጉዳይ የማንወያይ ከሆነ በስንዴም፣ በአረንጓዴ ዐሻራም፣ በገቢው ጉዳይ መወያየት ትርጉም የለውም ብለዋል።

እንደ ሀገር የሚታሰበውን ሠላም፣ አንድነትና ብልጽግና በቀይ ባህር ምክንያት የሚታጣ ከሆነ ዋጋ እንደሌለው በመግለጽ፣ በ2030 ዓ.ም 150 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ በጂኦግራፊ ታሳሪ ሆኖ መኖር የማይችል በመሆኑ መወያየት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ ውሃን የማይወስድ ጎረቤት ሀገር አለመኖሩን ጠቅሰው፤ ኤርትራ፣ ተከዜን፣ ሱዳን ተከዜንና ዓባይን፣ ደቡብ ሱዳን ባሮን፣ ኬንያ ኦሞን ጨምሮ፣ሶማሊያ ዋቢሸበሌና ገናሌ ዳዋ እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።

አንድ ሀገር ለኢትዮጵያ አንድ ሊትር ውሃ የሚሰጥ ሀገር የለም። ሁሉም ተቀባይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይገባቸዋል በደንብ አብዝተን እንሰጣቸዋለን ግን የእናንተን እንካፈል የእኛን እንዳትጠይቁን ማለት ግን ትክክል አይደለም ብለዋል። አብሮ መኖርና ሠላም ከታሰበ ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ በመጋራት መኖር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ከአንዱ ወገን ብቻ የሚጠየቅ ከሆነ ፍትሐዊነት እንደሌለው ገልጸዋል።

ቀይ ባህር ከታሪክ አንጻር አብዛኛውን አካል የሚቆጣጠረው አክሱማይት ግዛት እንደነበር በመግለጽ፤ አሁን የሰው ጭንቅላት የፈጠረው ጉዳይ ሳይሆን በንጉሡ ዘመንም የነበረ ጉዳይ በመሆኑ ታሪካዊ እውነታዎች አሉት ብለዋል።

በሌላ በኩል የሕዝብ አሰፋፈር ሁኔታ የቀይ ባህር እውነታ መሆኑን በመገልጽ፤ በኤርትራ፣ በሶማሊያና ጂቡቲ የሚኖሩት ተጠቃሚ ሆነው በአንጻሩ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የአፋር፣ የሱማሌ ሕዝቦች ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

በዓለም ላይ 44 ሀገራት የባህር በር እንደሌላቸው የሚገልጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ይዞ የባህር በር የሌለው ከኢትዮጵያ ውጪ ማንም የለም ብለዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ የባህር በር ከሌላቸው 17 ሀገራት ሕዝቦች የሲሶው መኖሪያ ምድር መሆኗን በመግለጽ በምዕራብ አፍሪካ 21 ሀገራት የባሀር በር ያላቸው ሲሆን፤ በምሥራቅ አፍሪካ 7 ሀገራት ብቻ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በአካባቢው ያለው የባህር ሀብት ለሁሉ የሚበቃ ሆኖ ሳለ ጥቅም ላይ አለመዋሉን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያውያን ቁጥር እያደገ በመሆኑ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል። ጂቡቲ ላይ ቻይና፣ በርበራ ላይ ዩኤ፣ሞቃዲሾ ላይ ተርኪ ኢንቨስት በማድረግ ላይ መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በጋራ ለመኖር እኛም ኢንቨስት ማድረግ አለብን ብለዋል።

በጋራ ተጠቃሚነት እሳቤ ከዓባይ ግድብ፣ አየር መንገድ፣ ኢቲዮ-ቴሌኮም በአንዳቸው ላይ ድርሻ ወስደው ኢንቨስት ቢያደርጉ ይችላሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለኢትዮጵያ አሰብ፣ ዘዬና አዶሊስ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ያስፈልገናል የሚል መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ፣ የሶማሊያ፣ የጂቡቲና የኤርትራ መሪዎች ስለሚጸና ሠላም መወያየት እንዳለባቸው በመግለጽ፣ የቀይ ባህርን አጠቃቀም በኢንቨስትመንት፣ በድርሻና በሊዝ፣ የሚሏቸው ጉዳዮች ላይ መነጋገር ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት የመሆን ታሪክ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚም መሆኑን ጠቅሰው፤ የተማረ የሰው ኃይል፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ የሕዝብ ብዛት አላት። የሚቀራት ነገር አለ እርሱንም ሂደት ያመጣዋል ብለዋል። የወደብና የባህር በር አማራጮች ማየት ጠቃሚ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዘይላ ከሶማሌ ላንድ ፣ የጂቡቲ፣ በኤርትራ አዱሊስ፣ ምጽዋና አሰብን አማራጮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የባህር በሩ በግዢም፣ በሊዝ በሆነ በተለያየ መንገድ ስምምነት ከመጣ የሚፈለገው እርሱ መሆኑን በመግለጽ፣ በየሁለት ሦስት ዓመቱ ለወደብ የሚከፈለው ገንዘብን የዓባይን ግድብ ይሠራል ሲሉ ተናግረዋል። የባህር በርን ይገባኛል ጥያቄ ስላለን፣ መቶ ሚሊዮን ስለሆንን፣ ወታደር ስላለን፣ ዘለን የሰው ሀገር የምናንቅ መሆን የለበትም ያሉት ዶክተር ዐቢይ፣ የጋራ እድገት፣ ብልጽግና ሠላም በሚያስገኝ መልኩ ይከናወናል ብለዋል።

የባህር በርን በተመለከተ ያለው ምርጫ ያስቀመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ፌዴሬሽን ወይም ኮንፌዴሬሽን፣ ውህደት፣ የመሬት ልውውጥ፣ የትርክትና የታሪክ ዝግጅት፣ ጨምሮ በማኅበራዊና የሥነ ልቦና ዝግጅትና ዲፕሎማሲ ሥራ እንደሚያፈልግ አመልክተዋል።

አሁን አይቻልም ማለት ነገ አይቻልም ማለት ባለመሆኑ ተነጋግሮ ከተሳካ ይሳካል እንጂ ተዳፍኖ ይቅር የሚባል አለመሆኑን ጠቅሰው፣ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ እንጂ ቅብጠት አለመሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን በጋራ እንቁም፣ ሃሳባችን ግልጽ ያለ ይሁን፣ ኅብረታችን የማይናወጥ፣ የምንጣላበትና የማንጣላበትን የለየን እንሁን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለላቀ ቁም ነገር በጋራ የምንሠራና ለትውልድ የምናሻግር እንሁን ብለዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2016

Recommended For You