
በጡታቸው እና በደረታቸው መካከል አበጥ ያለ ነገር በእጃቸው ሲዳብሱ ህመም ተሰማቸው። ሳያመነቱ በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋም አምርተው ምርመራ አደረጉ። ከአንድም ሁለት የህክምና ባለሙያዎች ጋር ሄዱ። ነገር ግን ህመማቸው የጡት ካንሰር እንዳልሆነ ተነገራቸው። ግራ ቢገባቸው ምርመራ ከማድረግ ተቆጠቡ። ጥቂት ቆይተው ዳግም ሲመረመሩ ግን የጡት ካንሰር እንዳለባቸው በምርመራ ተረጋገጠ።
‹‹ያውም በፍጥነት የሚሠራጨው ካንሰር ነበር እኔን የያዘኝ›› ይላሉ ወይዘሮ ያይኔ አበባ ብርሃን በግዜው የነበረውን ነገር ሲያስታውሱ። ከምርመራው በኋላ ሃኪማቸው በአስራ አምስት ቀን ውስጥ ህክምና እንዲጀምሩ በነገሯቸው መሠረት ለሰባት ወራት ሲከታተሉ መቆየታቸውን ይናገራሉ። ይህንኑ በማድረጋቸውም ከካንሰር ነጻ መሆናቸውን ያስረዳሉ። ይህ የሆነው ታዲያ ከዛሬ ሃያ ሁለት አመት በፊት እንደነበርና ነገር ግን አሁን በካንሰር መታመማቸውን እንኳን እንደረሱት ይገልፃሉ።
ወይዘሮ ያይኔ አበባ ከ1995 ጀምሮ የኢትዮጵያ ካንሰር አሶሴሽን በመሥራችነት እና የቦርድ አባል በመሆን ከጡት ካንሰር መዳን እንደሚቻል ለብዙዎች ደርሰው አስተማሪ ወጣቶችን ለማፍራት በቅተዋል። እርሳቸው እንደሚሉት፣ በእነርሱ ጊዜ ስለ ጡት ካንሰር በቂ ግንዛቤ አልነበረም፤ ደፍሮም አይነገርም። የህክምና ባለሙያዎችም ቁጥራቸው ጥቂት የሚባል ነበር። ዛሬ ላይ ግን የካንሰር ህክምና የሚሠጡ የህክመና ባለሙያዎች ቁጥር ጨምሯል። ጤና ሚኒስቴርም ቢሆን አሁን ላይ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ትኩረት እየሰጠ መምጣቱንና የጡት ካንሰርን በሚመለከት ግንዛቤ ለመስጠት አመቺ ጊዜ አሁን መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል።
በጤና ሚኒስቴር ደረጃ የጡት ካንሰርን በተመለከተ በአግባቡና ሁሉንም ባማከለ መልኩ ግንዛቤ መስጠት ይገባል። በሌላ በኩል በፊልምና በሌሎች የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ውስጥ ‹‹ካንሰር ገዳይ ነው›› ወይም የመጥፎ ነገር ምሳሌ እንደሆነ የሚያመለክቱ ሥራዎች መቆም ይኖርባቸዋል። ከነዚህ በተጨማሪ ለህመሙ የሚሰጡ መድኃኒቶች ዋጋቸው በጣም ውድ መሆናቸው በዚህም ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል። በእርግጥ መንግሥት 50 በመቶ ዋጋውን ያስተካከለ ቢሆንም፤ አሁም አቅማቸው የማይችል ታካሚዎች በርካታ በመሆናቸው ይህን ያገናዘበ የዋጋ ማሻሻያ ማድረግ የግድ ይላል።
ዶክተር ማቴዎስ አሰፋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር እና የካንሰር ህክምና ስፔሻሊስት ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ካንሰር ከየትኛውም የሰውነት ክፍል ሊነሳ ይችላል። ጤናማ የሆኑ ህዋሶች ጉዳት ሲደርስባቸው ሰውነት ወደ ጤናማ ህዋስነት እንዲመለስ ያደርጋል። ነገር ግን ጉዳት የደረሰበትን ወደ ጤነኛ ህዋስነት ለመመለስ ሲያቅተው ወደ ካንሰር ህዋስነት ይቀየራል። ይህም አንድ የነበረው የካንሰር ህዋስ ከተፈጠረ በኋላ ጨምሮ እና ተባዝቶ የተለያዩ ስሜቶች እንዲፈጠር ያደርጋል።
የጡት ካንሰር ደግሞ በዋናነት የሚከሰተው የወተት መተላለፊያ ቱቦ ላይ ከሚገኙ ህዋሳት (ሴሎች) እና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ወተት ከሚያመነጩ ሴሎች ነው። ከአንድ ህዋስ ተነስቶ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣት በጣም ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚታወቀው በእብጠት መልክ ነው። በዚህም አንዳንድ ሰዎች የጡት ካንሰር የህመም ምልክት የሚያሳይ ይመስላቸዋል። ነገር ግን ይህም የተሳሳተ አመለካከት ነው።
በተለይም በወጣትነት ዕድሜ ጊዜ የሚከሰቱ እባጮች ይኖራሉ። ስለዚህም እባጮች ሁሉ የጡት ካንሰር ናቸው ማለት አይደለም። ዕድሜ እየጨመረ በመጣ ቁጥር የሚታዩ እባጮች ግን ካንሰር የመሆን እድላቸው ከፍተኛ ነው። ታዲያ እብጠቱ በየጊዜው መጠኑ እየጨመረ ከመጣ በፍጥነት ህክምና ካልተደረገ ወደ ብብት አካባቢ ወደሚገኙ ዕጢዎች፣ ሳምባ፣ ጉበት አጥንት፣ ጭንቅላት እና ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ሊሰራጭ ይችላል። ይህም እንደ ካንሰሩ ባህሪ የሚወሰን ሲሆን፤ አንዳንድ ጊዜ በጣም ፈጥኖ ሊሰራጭ እና ሊዘገይም ይችላል።
እንደ ዶክተር ማቴዎስ ገለጻ፤ የጡት ካንሰር አጋላጭ ከሚያደርጉት መካከል አንዱ ጾታ ነው። በተለይም ከ97 በመቶ በላይ የሚከሰተው ሴቶች ላይ ሲሆን፤ የወንዶች ታጋላጭነት በሁለት ወይም በሦስት በመቶ ብቻ ነው።ሌላው አጋላጭ ምክንያት ዕድሜ ነው። እድሜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር የጡት ካንሰር ተጋላጭነት እየጨመረ ይሄዳል። ይሄንንም በቁጥር ለማሳየት ያህል አንዲት ሴት በአማካይ ዕድሜዋ 80 ቢሆን ፤ 80 ዓመት ከሞላቸው ስምንት ሴቶች አንዷ ሴት በጡት ካንሰር ትያዛለች እንደማለት ነው። ይህም ለምን ሆነ? ከተባለ የጡት ካንሰር ዋነኛ ምክንያት ሴት ልጅ ከወር አበባ ጋር ተያይዞ የሚመረት ‹‹የኤስትሪጂንን›› የሚባል ሆርሞን በሴቶች ላይ በብዛት ያለ በመሆኑ ነው። በወንዶች ላይ ደግሞ በዝቅተኛ መጠን ያለ በመሆኑ በሴቶች ላይ የመከሰቱን ዕድል ያሰፋዋል።
በመሆኑም አንዲት ሴት ልጅ የወር አበባዋ ቀደም ብሎ ከመጣ እና ለመቆም ከ50 ዓመት በላይ ሲሆን፤ ለዚህ ሆርሞን ተጋላጭነቱ የረዥም ጊዜ ስለሚሆን የጡት ካንሰር ተጋላጭነቱ ትንሽ ይጨምራል። በሌላ በኩል ደግሞ አንዲት ሴት የወር አበባዋ በ15 እና በ16 ቀናት ውስጥ መጥቶ እና በ45 ቀኑ ሲቆም ለዚህ ሆርሞን ተጋላጭ የመሆን እድል ዝቅተኛ ነው። በተጨማሪም ሴቶች የመጀመሪያ ልጅ የሚወልዱበት ዕድሜ በጣም ዘግይቶ ከሆነ ለዚህ ሆርሞን ተጋላጭነታቸው የሚጨምር በመሆኑ ለጡት ካንሰር እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል።
የማያጠቡና አልኮል የሚጠጡ ሴቶችም የጡት ካንሰር ተጋላጭነታቸው ይጨመራል። ስለዚህ እነዚህ በአብዛኛው የጡት ካንሰር በሰውነት ውስጥ ካለ ቅመም ወይም ‹‹ኤስትሮጂን›› የሚባለው ቅመም በሰውነታቸው ውስጥ ለረዥም ጊዜ በመቆየቱ የሚፈጥር በመሆኑ ተጋላጭነታቸውን ይጨምረዋል። ሌላው ደግሞ በዘር የሚሄድ ተጋላጭነት ሲሆን፤ ይህም ሁለት ዓይነት መልክ አለው። አንደኛው የጡት ካንሰር ተጋላጭ የሚደርጉ የተወሰኑ ጂኖች ወይም ዘረመል ጋር የተያያዘ ሲሆን በእንግሊዝኛ መጠሪያ ስሙ /brca 1 እና brca 2/ተብሎ ይጠራል።
የነዚህ ጂኖች መዳከም ሲኖር አንዲት ሴት የጡት ካንሰር ተጋላጭነቷ ከፍተኛ ይሆናል። ወይም ተጋላጭነቷ እስከ 70 በመቶ ሊደርስ ይችላል። ከዚህ ውጪ ከሆነ ደግሞ ቤተሰብ ውስጥ የካንሰር ታማሚ ካለ ተጋላጭነቱ ይጨምራል። ይህም ማለት የመጀመሪያ ደረጃ ቤተሰብ እንደ እናት፣ እህት አክስት ያለ የቅርብ ዘመድ ሲኖር በዘር የመሄድ አዝማሚያ እንዳለው ያመላክታል።
ዶክተር ማቴዎስ እንደሚገልጹት፤ በወር አበባ ወቅት እንዲሁም የሆርሞን መጨመርና መቀንስን ተከትሎ ሴቶች ጡታቸውን ሲያማቸው የጡት ካንሰር ይመስላቸዋል። ነገር ግን ይህ ስህተት መሆኑን እና ከፍተኛ የግንዛቤ እጥረት እንዳለ ለማወቅ ያስችላል። ሌላው የተዛባ አመለካከት ደግሞ ሴቶች በጡት ካንሰር ከተያዙ በኋላ ‹‹ቀዶ ህክምና ልደረግ ነው፤ ጡቴ ሊቆረጥ ነው›› ብለው ማሰባቸው ነው። በዚሁ ፍራቻ የባህል ህክምና፣ የሃይማኖት እና ሌሎች የህክምና አማራጮች ሲወስዱ ይታያል። በዚህም ከዘመናዊው ህክምና የመዘግየት ሁኔታ ይፈጠራል።
አብዛኛዎቹ ሴቶች ካንሰር ታክሞ የሚድን ህመም እንደሆነም አይረዱም። ባደጉት ሀገራት ህክምናቸውን ተከታትለው የዳኑ ሰዎች ከጡት ካንሰር መዳን እንደሚቻል ወጥተው ያስተምራሉ። በእኛ ሀገር ደረጃ ግን የጡት ካንሰር ታማሚ የሆኑ ሴቶች ህመማቸውን አይናገሩም። እነዚህ ተደማምረው ወደ ህክምና በፍጥነት ያለመምጣቱ ነገር በስፋት ይታያል።
በኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜ በሚደረጉ ጥናቶች መሠረት ከሌሎች የካንሰር ህመሞች የጡት ካንሰር የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛል። በቁጥር ደረጃም አንድ ሦስተኛውን ይሸፍናል። በየዓመቱ ወደ 19ሺ የሚሆኑ ሴቶች በጡት ካንሰር ይያዛሉ። በአዲስ አበባ ውስጥ ወደ ስምንት ሺ ስድስት መቶ ሴቶች በዚሁ ጡት ካንሰር ይያዛሉ። ይህም ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። በዚህ ከቀጠለም ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ነው ዶክተር ማቴዎስ የሚገልፁት ።
እርሳቸው እንደሚያብራሩት ለጡት ካንሰር በዋናነት አጋላጭ ከተባሉት ምክንያቶች መካከል ዕድሜና ጾታ በመሆናቸው በመከላከል ብቻ ሊቀየር የሚችል ነገር አይኖርም። ስለዚህ ሴቶች ለጡት ካንሰር ሁሌም ተጋላጮች ናቸው። መፍትሄውም ቅድመ ምርመራ በማድረግ ካንሰሩ ደረጃው ከፍ ከማለቱ በፊት ቶሎ ህክምና አድርጎ ማዳን ይቻላል። ሴቶች 40 ዓመት ከሞላቸው የጡት ራጅ( ማሞግራፊ) ይህም በራጅ አይቶ አመላካች ነገር ካለ ወደ ህክምና ለማምራት የሚረዳ የምርመራ አይነት ነው።
ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በፊት ከሆነ ደግሞ የጡት ካንሰር መጠኑ ብዙ አይደለም።በተጨማሪም ማሞግራፊ እንደ ማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ፤ ካንሰርን የማሳየት አቅሙ ዝቅተኛ ስለሚሆን ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች በወር አንድ ጊዜ የወር አበባ መጥቶ ከሄደ በኋላ ሁለቱንም ጡቶቻቸውን በደንብ በመመልከት፣ በመዳበስ እና በሚዳብሱበት ጊዜ አጠራጣሪ ነገር ወይም እንደ ባቄላ እና መሰል ጠጣር ነገር ከታያቸው በአፋጣኝ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።
ከህክምና በፊት የጡት ካንሰር ያለበትን ደረጃ ማወቅ ያስፈልጋል። ደረጃውን ለማወቅም የሚደረጉ የተለያዩ ምርመራዎች አሉ። እነርሱም የራጅ፣የአልትራሳውንድ፣የሲቲስካን እና ሌሎች ምርመራዎች ናቸው።ከዚህ በተጨማሪም የጡቱን ካንሰር አይነቱን ከጡቱ ናሙና በመውሰድ እና ሊያስፈልጉ የሚችሉ የመድኃኒቶች አይነቶችን እንዲወስዱ ይደረጋል።
ዶክተር ማቴዎስ እንደሚያብራሩት፤ ካንሰሩ ከጡቱ ያላለፈ በሚሆንበት ጊዜ በአብዛኛው በቀዶ ህክምና ጡቱን ወይም እብጠቱን እንዲወገድ በማድረግ ቀጥሎም እንደ ደረጃው የኬሞ ቴራፒ፣ የጨረር፣በእንክብል መልክ የሚወሰዱ ተጨማሪ መድኃኒቶችን እንዲወስዱ ይደረጋል። ሌላው ህክምና ከጡት አልፎ ወደ ብብት ውስጥ የገባ ከሆነ ሁለት አማራጮች አሉት። አንደኛው ሁለቱንም ጡቶች ማስወገድ እና በመቀጠል የኬሞቴራፒ እንዲወስዱ እና ሌሎችን ህክምናዎች ይሰጣቸዋል።
ምንም እንኳን ጡቱ ላይ የተገኘው ካንሰር በቀዶ ህክምና ቢወገድም ሳይታዩ የሚቀሩ ሴሎች ሊኖሩ ስለሚችል በተቻለ መጠን በኬሞቴራፒ በማጥፋት እና በማዳከም ዳግም አገርሽቶ ወደ ተለያየ የሰውነት አካል ላይ እንዳይሠራጭ ማድረግ ያስፈልጋል። ሌላው ሰውነት ላይ የተሰራጨ ከሆነ የኬሞ ቴራፒ እና በእንክብል መልክ መድኃኒቶች እና እንደ ደረጃው አይነት የሆርሞን ህክምና እንዲወስዱ በማድረግ ይታከማሉ።
የጡት ካንሰርን መከላከል አይቻልም። ለዚህም ዋና አጋለጮች ጾታ እና ዕድሜ ናቸው። የጡት ካንሰር እንደ ማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ክትባት የለውም። ስለዚህ በዋናነት አጽንኦት ሊሰጠው እና በደንብ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ቅድመ ምርመራ ማድረግ ነው።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም