‹‹ተስፋአዲስ›› – የካንሰርሕሙማንሕፃናትየሕይወትተስፋ

በኢትዮጵያ ገና በለጋነታቸው የካንሰር ተጠቂ የሆኑ ሕፃናት ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል:: ኅብረተሰቡ ስለካንሰር ሕመም ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ፣ ሕክምናው እንደልብ አለመገኘቱ እንዲሁም በጥቂት ተቋማት ውስጥ ብቻ የሚሰጡት ሕክምናዎችም ውድ መሆናቸው የችግሩን ክብደት የበለጠ ፈታኝ አድርጎታል:: በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች ደግሞ በዚህ ችግር ምክንያት ለበለጠ አስከፊ መከራ ተዳርገዋል:: ጉዳዩ ያሳሰባቸው ግለሰቦችና ተቋማትም ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቀየር የተለያዩ ጥረቶችን አድርገዋል፤ እያደረጉም ናቸው::

ለካንሰር ታካሚ ሕፃናት የሚቀርበውን ሕክምና ጥራቱን በማሻሻል የሕፃናቱን ሕይወት በማዳን እና ወላጆች ለልጆቻቸው የተሻለ እንክብካቤ እንዲያደርጉ ማብቃት እንዲሁም የሕክምና ተቋማትን የሕፃናት ካንሰር ሕክምና ክፍል አቅም በመገንባት ሕሙማኑ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ የማስቻል ዓላማን ይዞ የተቋቋመው ‹‹ተስፋ አዲስ ፓረንትስ ቻይልድሁድ ካንሰር ድርጅት›› (Tesfa Addis Parents Childhood Cancer Organization) የችግሩን አስከፊነት ለመቀነስ ከተደረጉ የበጎ አድራጊ ዜጎች ጥረቶች መካከል ተጠቃሹ ነው::

የ‹‹ተስፋ አዲስ ፓረንትስ ቻይልድሁድ ካንሰር ድርጅት›› ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሳራ ኢብራሂም እንደሚናገሩት፣ ድርጅቱ የተመሠረተው በኅዳር 2005 ዓ.ም ነው:: የድርጅቱ መሥራቾች ደግሞ ልጆቻቸውን አሳክመው ያዳኑና ልጆቻቸው በሕክምና ላይ የነበሩ ወላጆች እና የሕክምና ባለሙያዎች ናቸው:: ስለካንሰር ታማሚዎች በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ ግንዛቤውን ከመቀየር ጀምሮ የካንሰር ታማሚዎች ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ ተግባር ስለነበር የ‹‹ተስፋ አዲስ›› ምሥረታ እውን ሆነ::

‹‹ድርጅቱ የተመሠረተው ልጆቻቸው በካንሰር ታመውባቸው በሕክምና የዳኑላቸው ወላጆች ትብብር ሲሆን፣ ወላጆቹም ሊተባበሩ የቻሉት ‹ልጆቻቸው ከዳኑ እኛ ደግሞ ለቀሩት የካንሰር ታካሚ ሕፃናት የበኩላችንን አስተዋጽዖ ማድረግ አለብን› ከሚል ቅን መንፈስ ተነሳስተው ነው›› በማለት ወይዘሮ ሳራ ስለድርጅቱ አመሠራረት ያስታውሳሉ::

ድርጅቱ የተቋቋመው የካንሰር ታማሚ ሕፃናት በሆስፒታል ቆይታቸው በቂ ሕክምናና እንክብካቤ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲፈጠር እና በቀጣይነት ሕክምናቸውን እንዲከታተሉ ጥረት ለማድረግ ታስቦ ነው:: በካንሰር የተያዙ ልጆች ተገቢውን ሕክምናና እንክብካቤ አግኝተው ከካንሰር ነፃ የሆነ ሕይወት እንዲመሩ የማድረግ ራዕይ ያለው ድርጅቱ፣ ተልዕኮው ወላጆችን ማዕከል ባደረገ እንቅስቃሴ ጥራቱን የተጠበቀ የሕክምና አገልግሎትና ክትትል በማድረግ የታካሚ ልጆች ከካንሰር ነፃ የመሆን እድልን መጨመር ነው::

‹‹ተስፋ አዲስ›› ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በጎንደርና በጅማ የታካሚ መርጃ (የማደሪያ) ማዕከላት አሉት:: ድርጅቱ የካንሰር ታማሚ ሕፃናትን የመርዳት ሥራውን የሚያከናውነው ከመንግሥት የጤና ተቋማት ጋር በመተባበር ሲሆን ተቋማቱ ጥቁር አንበሳ፣ ቅዱስ ጳውሎስ፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና ዓይደር ሆስፒታሎች ናቸው:: ድርጅቱ በዚህ ተግባሩ የካንሰር ታማሚዎቹ ሕክምና እንዲያገኙ ያደርጋል:: ከዚህ በተጨማሪም ተቋሞቹ ያሉባቸው የተለያዩ ክፍተቶች እንዲሟሉ እና ለታካሚዎቹም በቂ አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፍ ያደርጋል:: ለአብነት ያህል በቅርቡ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ፣ በእናቶችና የሕፃናት ሕክምና ማዕከል ውስጥ የሚገኘው የሕፃናት ካንሰር ሕክምና ክፍል ለሕክምና አስፈላጊ በሆኑ ግብዓቶች እንዲሟላና እንዲደራጅ አድርጓል:: ከዚህ ባሻገርም በክፍሉ ከተመደቡት የሆስፒታል ሕክምና ባለሙያዎች በተጨማሪ ድርጅቱ አንድ የሥነ ልቦና ባለሙያና አንድ መረጃ የሚያጠናቅር ሠራተኛ መድቧል::

የሕክምና አገልግሎቱን የሚያገኙት ልጆች ወደ ተቋሙ የሚመጡበት የራሱ የሆነ አሠራር አለው:: ድርጅቱ ዕገዛና ድጋፍ የሚሹ ሕፃናትን የሚያገኘው ድርጅቱ የድጋፍ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ሆስፒታሎች ውስጥ የመደባቸው የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ከሆስፒታሉ ሐኪሞች ጋር በመሆን አጣርተው በሚልኩት መረጃ መሠረት ነው:: ‹‹አዝላን›› ፕሮጀክትን (Aslan Project) ጨምሮ በርካታ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለ‹‹ተስፋ አዲስ›› የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ:: ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከ600 በላይ ለሆኑ ሕፃናትና ወላጆች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል::

ወይዘሮ ሳራ እንደሚያብራሩት፣ ድርጅቱ የካንሰር ሕሙማን ሕፃናት ሕክምና እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ ከሕክምናው ጋር ተያያዥ የሆኑ አገልግሎቶችንም ለታካሚዎቹ ያቀርባል:: እነዚህ አገልግሎቶችም የምግብ፣ የመጠለያ/ማደሪያ፣ የትራንስፖርት፣ የአልባሳት፣ የክህሎት ሥልጠና፣ የንጽሕና መጠበቂያ እና የሥነ ልቦና ድጋፎች ናቸው::

‹‹ድርጅቱ ለሕፃናቱና ለወላጆችና ማኅበራዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ድጋፎችን ያደርጋል:: ለታካሚዎችና ለወላጆች የምግብ አቅርቦት፣ ከክልሎች ለሚመጡና አቅም ለሌላቸው ታካሚዎችና ወላጆች የትራንስፖርት እና የማደሪያ አገልግሎት ይሰጣል፤ ለታካሚዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ይደረጋል፤ በተለያዩ ዘርፎች ለወላጆች የሚሰጣቸው ሥልጠናዎችም አሉት፤ ለታካሚዎችና ለወላጆች የምክር አገልግሎት ይሰጣል:: በተጨማሪም ድርጅቱ የሕፃናት ካንሰር ሕመም እንደሌሎቹ ሕመሞች ሊከሰት እንደሚችል፣ በጊዜው ከተደረሰበትና ከታከመ ግን የሚድን እንደሆነ ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ይሠራል›› ይላሉ::

የመጠለያ/ማደሪያ አገልግሎቱ ልጆቻቸውን ለማሳከም ወደ ማዕከላቱ የሚመጡ ወላጆች በቅርበት ሆነው ለልጆቻቸው ድጋፍ እንዲያደርጉ እድል ይሰጣቸዋል:: የመጠለያ አገልግሎቱ የምገባ፣ የጤና/ጽዳት፣ የትራንስፖርት (ወደ ሕክምና ተቋማት) እና የሕፃናት መዝናኛ አገልግሎቶችንም ያካተተ ነው:: በድርጅቱ የሚሰጠው ታካሚ ሕፃናትን ወደ ሕክምና ተቋማት የማድረስና ወደ ማዕከሉ የመመለስ አገልግሎት ሕፃናቱ ለአላስፈላጊ እንግልት እንዳይዳረጉ እንዲሁም ለኢንፌክሽን እንዳይጋለጡ ያደርጋቸዋል::

በሕፃናት ካንሰር ሕመም ምንነት፣ በሕክምና ዘዴዎቹ፣ በጤና አጠባበቅና በአመጋገብ ሥርዓት ላይ አተኩሮ የሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና የሥነ ልቦና ድጋፍና የታካሚ ሕፃናትን ሥነ ልቦና በመገንባት ለመዳን እድላቸው አወንታዊ አስተዋፅዖ ያበረክታል፤ የወላጆችን ግንዛቤ በመጨመር ለልጆቻቸው የሚያደርጉትን እንክብካቤና ድጋፍ በትኩረት እንዲያከናውኑ እና ኅብረተሰቡ ስለችግሩ ያለው አመለካከት እንዲቀየር ያግዛል::

‹‹የካንሰር ሕክምና ረጅም ጊዜ የሚፈጅ ነው:: ሕክምናው በቂ ጊዜ እንደሚፈልግ አስቀድሞ ወላጆችን ማስተማርና ማሳመን ያስፈልጋል:: ከዚህ በተጨማሪም ሕፃናቱ ለረጅም ጊዜ በሕክምና ላይ ሲቆዩ ጫና እንዳይፈጠርባቸው የሥነ ልቦና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል:: በሥነ ልቦና ዝግጁ ሆነው መታከም ስላለባቸው ድጋፍ የሚያደርጉ ባለሙያዎች አሉ:: ልጆቻቸው ታክመው የዳኑላቸው ወላጆችም ወደ ማዕከሉ እየመጡ “ያስተምራሉ፤ ልምዳቸውን ያካፍላሉ” በማለት ወይዘሮ ሳራ ድርጅቱ ለታካሚዎችና ወላጆች ስለሚያደርገው የሥነ ልቦና ድጋፍ ያስረዳሉ::

‹‹ተስፋ አዲስ›› በሚያከናውናቸው ተግባራት የካንሰር ታማሚዎች፣ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወላጆች ልጆቻቸው ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎች እየፈጠረ እንደሚገኝና የድርጅቱ የበጎ አድራጎት ተግባራት የብዙዎችን ሕይወት በበጎ መልኩ እንደቀየሩ ወይዘሮ ሳራ ይገልጻሉ::

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ድርጅቱ እስካሁን ድረስ ከሦስት ሺ በላይ ሕፃናትን ታድጓል:: ድርጅቱ በገንዘብ ምክንያት የሕክምና አገልግሎቱን ሳያገኙ ለሚሄዱ ሕሙማን በፍጥነት በመድረስ ሕክምና እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል:: የሕክምና አገልግሎቱንም ፈልገው የሚመጡ ሕሙማንን ወላጆቻቸው በፍጥነት ወደ ተቋሙ ካመጧቸው የመዳን ዕድላቸው ሰፊ ሲሆን፣ አንዳንድ ወላጆች ግን ስለበሽታው በቂ ግንዛቤ ስለሌላቸውና ዘግይተው በመምጣታቸው የተነሳ ልጆቻቸው ለከፋ ችግር ሲጋለጡ ይታያል:: እነዚህንም ችግሮች ለመፍታት ተቋሙ የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ሕሙማንን ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ እንዲያገግሙ እያደረገ ይገኛል:: በተለይም ደግሞ ከሩቅ ቦታ መጥተው ልጆቻቸውን ለሚያስታምሙ ወላጆች ተቋሙ ከሕክምና ጀምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል:: በሌላ በኩል ደግሞ ከሌሎች ተቋሞች ጋር ቅንጅት በመፍጠር ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ ነው:: ከጤና ሚኒስቴር፣ ከግል ተቋማትና ከኤምባሲዎች ጋር በመተባበር ታካሚዎች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ጥረት እያደረገ ነው:: መንግሥት ለድርጅቱ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝም ይገልጻሉ::

ወይዘሮ ሳራ ድርጅቱ በ11 ዓመታት የሥራ ጉዞው ስላጋጠሙት ችግሮች ሲያብራሩ፣ ‹‹ችግሩ ሰፊ ነው:: የሕክምናው ተደራሽነትም ገና ብዙ ይቀረዋል:: የመድኃኒትና ሌሎች ግብዓቶች ችግሮች አሉ:: መድኃኒትን በተመለከተ መንግሥት በጤና መድን በኩል የሚያቀርበው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አንዳንድ ጊዜ ከውጭ በሚገዛበት ጊዜ ዋጋው በጣም ውድ ይሆናል::››ይላሉ::

እሳቸው እንዳሉት፤ እስካሁን ሕክምናውን የሚሰጡት አምስት ሆስፒታሎች ብቻ ናቸው፤ ሕክምናውን የሚሰጡ ሐኪሞችም በጣም ጥቂት ናቸው:: የሕክምና አገልግሎቱ በሚሰጥበት ጊዜ የራዲዬሽን መትከያ መሣሪያ የሚገኘው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ላይ ብቻ ነው:: ለሕክምና የሚሆነው ማሽን ሲበላሽ ሕሙማኑ ችግር ላይ ይወድቃሉ:: በቅርቡ ይህ የሕክምና አገልግሎት በጅማ ሆስፒታል በመጀመሩ ችግሩ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ሊቀረፍ ችሏል:: ይሁን እንጂ ይህም በቂ አይደለም::

በግንዛቤ ረገድ ያለው ችግርም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤አብዛኛው ሰው ካንሰርን የማይድን ሕመም አድርጎ ይቆጥረዋል:: የካንሰር ሕሙማን ሕፃናት ተገቢውን ሕክምና በወቅቱ ማግኘት ከቻሉ የመዳን እድላቸው ከፍተኛ ነው:: ስለሆነም ‹‹ሐኪሞችን በብዛት ማሰልጠን ይገባል:: የሕክምና ቦታዎች መስፋፋት አለባቸው:: የመድኃኒት አቅርቦትንም መጨመር ያስፈልጋል:: ካንሰር በጊዜ ከተደረሰበት የመዳን ዕድሉ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ወላጆች ይህንን ተገንዝበውና ተስፋ ሳይቆርጡ ልጆቻቸውን ከማሳከም ወደ ኋላ ማለት የለባቸውም ›› በማለትም ይመክራሉ::

‹‹ግለሰቦችና ተቋማት በአጠቃላይ ኅብረተሰቡ ከግንዛቤ ለውጥ ጀምሮ ተጨማሪ ድጋፎችን ካደረገ ከዚህ የተሻለ ለውጥ ማስመዝገብ ይቻላል›› የሚሉት ወይዘሮ ሳራ፣ ‹‹ተስፋ አዲስ›› በቀጣይ ጊዜያት ሥራውን በስፋት በማከናወንና ብዙ የካንሰር ታማሚ ሕፃናትን በመታደግ ችግሩን ትርጉም ባለው መልኩ የመቀነስ እቅድ እንዳለው ገልፀዋል::

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 2/2016

Recommended For You