ዘነበች ደስታ፣ ቤቷ የገባችው ከወትሮው ዘግይታ ባይሆንም ቡናው ተቆልቶ የጠበቃት ግን ቀደም ብሎ ነው፡፡ ጓደኞቿ ሮማን ባልቻ እና ማርታ ታደሰ እንደሚመጡ ስለምታውቅ የጠበቀቻቸው የቡና ቁርስ በማዘገጃጀት ነበር፡፡ በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ተቀዳድመው የገቡት ጓደኞቿ ሮማን እና ማርታም እንደደረሱ ጓደኛቸውን ሰላም እያሏት ያቀኑት የጣት ውሃ ወደሚያገኙበት ክፍል ነበር፡፡ በቃ እንዲሁ ናቸው፤ ጠረጴዛው ላይ አንዳች የሚቀመስ ነገር ካዩ የማንንም ግብዣም ሆነ ፈቃድ አይጠብቁምም፤ አይጠይቁምም፡፡
ዛሬ ሦስቱም ጓደኛሞች ትኩረታቸውን አንድ ጉዳይ ላይ ለማድረግ የተመካከሩ ይመስል በአንድ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርገው ይጨዋወቱ ጀመር፡፡ ‹‹እኔ የምለው?›› አለች ማርታ ከቡና ቁርሱ እየጎረሰች። ‹‹ፕሮፌሰሩ ግን የሚሳካላቸው ይመስላችኋል?…እንዲህ ያልኳችሁ ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? አሁን እየመጣሁ ታክሲ ውስጥ ፕሮፌሰሩ…ማለቴ የትምህርት ሚኒስትሩ የሰጡት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ይፋ የተደረገው መግለጫ ሲነገር ነበር።
በ2015 ዓ.ም ለፈተና ከቀረቡ 845 ሺ ተማሪዎች መካከል የማለፊያ ውጤት ማምጣት የቻሉት 3 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ ናቸው የሚል ዜና ተደመጠ። የዜናው ዝርዝር ተነብቦ ሳይጠናቀቅ ሰው ከየጎኑ ካለው ሰው ጋር ያወራ ጀመር፤ በተለይ ደግሞ ጎልቶ ይሰማ የነበረው ‹አሁን ይህ ሰው ድከም ሲለው እንጂ በተማሪ ትጋት አጥጋቢ ውጤት ይመጣል ማለት ዘበት ነው› የሚል አስተያየት ከአንዱ ጥግ ሰማሁ፡፡ ‹‹የዚህ ሁሉ ተማሪ መውደቅ የተማሪዎቹ ጥፋት አይደለም፤ የትምህርት ሥርዓቱ ብልሽት ነው የሚል ሀሳብ ደግሞ ከሌላ ወግ ይሰማል፡፡›› ሁሉም ብቻ አንዱ አንዱን እየወቀሰ ጉዞው ቀጠለ፡፡
እኔም የተሳፋሪው አስተያየት እያስገረመኝ ከታክሲ ወረድኩ፡፡ እና ትምህርት ሚኒስቴር የጀመረው ሥራ መነጋገሪያ መሆኑ አንድ ጅምር ነው ብዬ አስባለሁ፤ ግን የሚኒስትሩ ጥረት ይሳካ ይሆን ወይ የሚል ስጋት አድሮብኛል›› አለች የተሳፋሪዎቹ አመለካከት ሙሉ ለሙሉ ተጽዕኖ እንደፈጠረባት በሚያስታውቅ ድምፀት፡፡
‹‹አንቺ ራስሽ የምትገርሚ ነሽ? ይህ ዜና አስደንግጦን ያለፈው አምና ነበር፡፡ ይኸው ዘንድሮም ተደገመ፡፡ በአምና እና በዘንድሮ ውጤት መካከልም ምንም አይነት ለውጥ የለም፡፡ የሆነው ሆኖ… የትምህርት ጥራት የትምህርት ሚኒስትሩ ጉዳይ ብቻ እኮ አይደለም፡፡›› አለች ዘነበች፡፡ ቀጥላም፤ ‹‹ያለፉ ተማሪዎች ማለቴ…ሦስት ነጥብ ሁለት በመቶ አገኙ የተባሉት ጠቅላላ ከቀረቡ 845 ሺ ተማሪዎች መካከል 27 ሺ 200 ምናምን ያህል ተማሪዎች ብቻ ናቸው፤ የማለፊያ ነጥብ ያመጡት ማለት ነው፡፡ ግን ደግሞ ይህ ውጤት ተማሪው ያመጣው ውጤት ነው፡፡
ፕሮፌሰሩ ደግሞ የዘቀጠውን የትምህርት ሥርዓት ለማስተካከል እና የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ ርዕይ ሰንቀው ስለትውልድ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ስለዚህ አሁን መወራት ያለበት ስለግለሰቡ ርዕይ መሳካት አለመሳካት ሳይሆን ስለሀገር ስኬትና ውድቀት ነው ብሎ ማሰቡ ተገቢ ይመስለኛል፡፡›› ስትል አከለች፡፡
ሁለቱ ጓደኞቿ እየተቀባበሉ ሲያወሩ ታዳምጥ የነበረችው ሮማን፤ ‹‹የትምህርት ጥራት ጉድለት ሲነሳ መንግሥት እና ተማሪው ላይ ብቻ ተጽዕኖ ሲያርፍ አስተውላለሁ፡፡ ተወቃሹ ግን መንግሥት እና ተማሪው ብቻ መሆን አለበት!? የለበትም፡፡›› አለች፡፡ ለትምህርት ጥራት መውደቅ ሁሉም የየራሱ ድርሻ አለው፡፡ መቼም…ሁሉም ስል…ያው…ይገባችኋል አይደል!? ለአጥሩ መጥበቅ አንዲት ምስማር ያላቀበለ ሁሉ ‹አጥሩ ጠንካራ ያልሆነው ስለምንድን ነው› ብሎ አካኪ ዘራፍ ሊል አይገባም፡፡…የአጥሩ መጥበቅ ሁሉንም ከክፉ አድራጊዎች የሚከላከለው እስከሆነ ድረስ ጠንካራ ሆኖ እንዲሠራ እና ከክፉ ነገር ሁሉ ማምለጥ እንዲያስችል የሁሉም ርብርብ የግድ የሚል ነው፤ ልክ እንደዚያው ሁሉ ለትምህርት ጥራት የሁሉም ባለድርሻ አካል ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው፡፡›› ስትል፤ ዘነበች ቀበል አድርጋ ‹‹እንዴ ሮሚ፣ መንግሥትማ አሳምሮ መወቀስ አለበት እንጂ…ማለቴ…ኢሕአዴግ፤ የትምህርት ጥራት በአፍጢሙ የተደፋው ባለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት ውስጥ አይደል እንዴ?
ትዝ አይላችሁም? ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ቀርቶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚሰየመው ርዕሰ መምህር ሳይቀር በመንግሥት የተሾመ መሆኑ? እንደዚያ ሆነ ማለት ደግሞ በወቅቱ የነበረው መንግሥት አድርግ ያለውን ሁሉ በታማኝነት የሚያደርግ ሆነ ማለት ነው፡፡ የግል ዩኒቨርስቲዎችም ቢሆኑ እውነት ተማሪዎቻቸውን እውቀት ሲመግቡ ነበር ማለት ይቻላል? ከጥቂቶች በስተቀር በፍጹም በእውቀት የታነጸ ትውልድ ሲቀርጹ ነበር ማለት አያስደፍርም፡፡›› አለች፡፡
‹‹ተይ እንጂ ዘኒ! ያለፈውን መንግሥት በዚህ ልክ ምንም እንዳልሠራ አድርገሽ አፈር ድሜ ማስጋጥ የለብሽም፡፡›› አለች ማርታ፤ ቀጥላም፤ ‹‹ቢያንስ ቢያንስ ትምህርትን ተደራሽ በማድረግ በኩል ሚናው የጎላ እንደነበር መቼም ላንቺ አልነግርሽም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገንባቱ በኩል የሚታማ አልነበረም፤ እድሜው ለትምህርት የደረሰ ሁሉ ወደትምህርት ቤት እንዲያቀናም ሲሠራ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎችን በየክልሉ በመክፈት የዩኒቨርሲቲዎችን ቁጥር በአጭር ጊዜ ከፍ… ማድረጉና ተማሪውም ርቆ ሳይሄድ በአቅራቢያው እንዲማር ማስቻሉ አይዘነጋም… አይደል?!…›› ስትል የድምፅዋን ቅላጼ ቀጠን እና ጎተት አድርጋ የልመና ያህል ለማሳመን ተጣጣረች፡፡
የቀድሞውን መንግሥት ዲስኩር በመስማቷ ፊቷ ቅጭም ያለው ሮማን፣ ‹‹እኔ ይህ አይነቱ አባባል አይገባኝም…›› ስትል ጓደኛዋ ማርታን ትኩር ብላ አየቻት፡፡ ‹‹ትምህርት ቤት በየደጃችን ስለተከፈተ ብቻ የትምህርት ጥራት ተረጋገጠ ማለት አያስችለንም፡፡ ደግሞም…›› እያለች ቀጠለች፤ በዚህ ጊዜ ማርታ ጣልቃ ገብታ፤ ‹‹ሮሚ…እኔ ያለፈው መንግሥት የትምህርት ጥራት አስጠብቋል የሚል ነገር አልወጣኝም…›› በማለት ለማስተባበል ሲቃጣት፤ ሮማን ግን የእርሷን ማስተባበያ አልሰማችም፡፡ የጀመረችውንም ወሬ አላቋረጠችም፤ ‹‹…የዩኒቨርስቲዎች መብዛትም እንደዛ አያረጋግጥም፡፡ በየትምህርት ተቋማቱ ምን ያህል የተሟላ የትምህርት ቁሳቁስ አለ? በምን ያህሉስ ነው ተማሪው እየተጠቀመበት ያለው? መምህሩስ በምን ያህል ልክ ነው ተማሪውን ለመቅረጽ እየጣረ ያለው? አየሽ…ችግሩ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡
አሁን አሁን ልብ ብላችሁ ከሆነ በየተቋማቱ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያለው ሰው ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ ይኸው ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እንዲበራከት ያደረገው የትምህርት ጥራት መጓደል ነው፡፡ መቼው እንደምታውቁት በአንድ ወቅት የተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ ይጣራ በተባለ ማግስት የብዙዎች ሠራተኞች የልብ ምት በብዙ ይደልቅ ነበር፡፡ ግን ደግሞ ይህ ዜና በተሰማ ጊዜ ከነበረው ድንጋጤ ጎን ለጎን የነበረው ነገር ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ መኖር አለመኖሩን ለማጣራት በሚደረግ እንቅስቃሴ ላይ የሚታይ መለገም ዓይን ያወጣ መሆኑ ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ የተጭበረበረ ሰነድ እንዳይመረመር ያለው መከላከል የሚያስደነግጥ ነው፡፡ አስቀድመው ቁጣ ቁጣ የሚላቸው ከፍተኛ አመራሮችም አሉ፡፡› አለች ማርታ፡፡
ማርታ ስለሐሰተኛ ሰነድ ስታወራ ከማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ያነበበችው ነገር ትዝ ያላት ዘነበች ደግሞ ‹‹የሚገርማችሁ ይህ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ መጋለጥ አለበት የሚል ዘመቻ ተጀምሮ በነበረበት ወቅት የሆነ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ አንድ ቀበሌ ያለ ትምህርት ቤት የመምህራንን የትምህርት ማስረጃ ያስመረምራል ሲባል የሰሙ የእዛ ትምህርት ቤት መምህራን መካከል ጥቂት የማይባሉ መምህራን የትምህርት ማስረጃቸው የተጭበረበረ ወይም ሐሰተኛ በመሆኑ ሀገር ጥለው የወጡት በጠፍ ጨረቃ ነው አሉ፡፡›› አለች፡፡
አክላም፤ ‹‹ተማሪው ግን ለምን አርፎ ትምህርቱን አይከታተልም?…አሁን ዘንድሮ ከተፈተኑት መካከል እንደ ሀገር ያመጡት ውጤት ከመቶ ሲሰላ ሦስት ነጥብ ሁለት ብቻ መሆኑ ጉድ ነው! ያስብላል፤ የሚያስገርመው እኮ ከተፈጥሮ ሳይንስ ከ600 ውጤት በላይ ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር 205፣ ከማኅበራዊ ሳይንስ ደግሞ ከ500 በላይ ውጤት ያመጡ 15 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸው የምር ተማሪዎቹ ግን ክፍል ውስጥ ነበሩ ወይስ አልነበሩም የሚያሰኝ ነው።›› አለች፡፡
‹‹እንደ እኔ…እንደ እኔ…ተማሪውን ብቻ ማብጠለጠሉ አግባብ ነው ብዬ አላስብም፡፡›› ስትል ሮማን የተማሪ ጠበቃ ሆና የመቆም ያህል መናገር ጀመረች፡፡ አክላም፤ ‹ተማሪ የብቃት ማረጋገጫ እንኳ በሌላቸው መምህራን ተምሮ የት ሊደርስ ይችላል ብለሽ ነው…!? ወላጅስ ቢሆን ልጁን ምን ያህል ሲከታተለውና ሲያግዘው ቆየ? የሚለው ጉዳይ መጤን ያለበት ነው፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ወላጅም ሆነ አሳዳጊ፣ ልጁ አሊያም የሚያሳድገው ልጅ የጠየቀውን ብቻ በማሟላት አስፈላጊውን ነገር ሁሉ አሟልቶለታል ብሎ መደምደም ከባድ ነው፡፡ ቢቻል የተማሪውን ውሎ መከታተል እንዲሁም ከትምህርት ቤት መልስም በማስጠናቱም ሆነ ሐሳቡን በመካፈል ረገድ ሊረዳው መሞከር ግድ ይለዋል ባይ ነኝ፡፡
ግልጹን እንነጋገር ከተባለ እኮ…ብዙዎቹ ወላጆች ልጆቻቸው የሚጠይቋቸውን ወይም ያስፈልጋቸዋል ብለው ያሰቡትን ከሙላታቸውም ሆነ ከጉድለታቸው ተጣጥረው መስጠታቸውን ካረጋገጡ ልጆቻቸው ምን አይነት ነገር ውስጥ እንዳሉ እንኳ የመከታተሉ ፍላጎት እምብዛም አይታይባቸውም፡፡ ከዚያ ይልቅ ወላጆች ራሳቸው ጊዜ እና ትኩረታቸውን የሚሰጡት ለማኅበራዊ ትስስር ገጽ ነው፡፡ በእነዚህ የማኀበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ተጥደው በሚሰሙት እንቶ ፈንቶ ወሬ በቁጭት ጥርሳቸውን ሲነክሱ እና ሲብሰለሰሉ ውለው ከማደር በዘለለ ለልጆቻቸው የሚገባቸውን ጊዜ የማይሰጡ ወላጆች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡›› ስትል እያባከኑ ስላለው ጊዜ እየተቆጨች ተናገረች፡፡
ማርታም ቀበል አድርጋ፤ ‹‹ሮምዬ በእርግጥ ልክ ነሽ፤ ለትምህርት ጥራት መጓደል ተወቃሽ ሊሆን የሚችለው አንድ አካል ብቻ መሆን የለበትም፤ ለትምህርት ጥራት ውድቀት ተጠያቂው ሁሉም ባለድርሻ አካል ነው፡፡ አንድ አይነድ እንደሚባለው የትምህርት ጥራት ጉዳይ ለአንድ ለተወሰነ አካል ብቻ ተትቶ መታለፍ የለበትም። የሁሉንም ትብብር የሚጠይቅ ነው፡፡ ዋና ተዋናይ ናቸው ተብለው ከሚጠሩት መካከል መንግሥት፣ ተማሪው፣ መምህሩ እና ማኅበረሰቡ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ስለዚህም ሁሉም የየድርሻውን ሚና በአግባቡ የሚጫወቱ ከሆነ ለውጥ ማምጣት ቀላል ይሆናል። ሕዝቡም አሁን ያለውን የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ብቻ በማየት ያልተገባ ሐሳብ መሰንዘር አለበት ብዬ አላምንም፡፡ በአንድ ጀምበር የሚመጣ የትምህርት ጥራት እንደማይኖር መጤን አለበት፡፡ የትምህርት ጥራትን እንደ ሀገር ለማምጣት ጊዜ ይወስዳል፤ የአምናውን ውጤት ከዘንድሮው ጋር በማነጻጸር ‹ለውጡ የታለ ታዲያ…?› ሊባል አይገባም፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ጥቂት ዓመታትን መታገስ ግድ ይላል፡›› ስትል ተናገረች፡፡
‹‹ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ነው፡፡›› ስትል ከመጀመሪያው መነሳት ችግሩን ከመሠረቱ መቅረፍ መሆኑን ለማስረዳት የሞከረችው ዘነበች፣ ‹‹የትምህርት አብዮት ማምጣት ከተፈለገ በሁሉም የሀገራችን ክፍል ቢቻል በየቦታው ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት መክፈት የግድ መሆን አለበት፡፡ ተማሪዎች ወደ አንደኛ ክፍል ከመምጣታቸው አስቀድመው ማንበብ ቢችሉ ተመራጭ ይሆናል›› ስትል ተናገረች፡፡ አያይዛም። ‹‹መሬት ላይ ያለውን እውነታ ስናይ ደግሞ መንግሥት ትምህርት በትውልድ ላይ መልካም የሆነ ለውጥ እንደሚያመጣ ስለሚያምን ዘርፉን በአግባቡ እየደገፈው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለትምህርት ከፍ ያለ ዓመታዊ በጀት ከሚመድቡ ሀገራት መካከልም እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፡›› አለች፡፡
የተንቀሳቃሽ ስልኳን ሰዓት ደጋግማ ማየት የጀመረችው ማርታ፣ ‹‹አንዱ በሌላው ሲስቅ ፀሐይ እንዳትጠልቅ ነው ስጋቴ›› አለችና። ‹‹የትምህርት ጥራት መጠበቅ ፋይዳው ለእከሌ እና ለእከሊት ነው የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ ጥቅሙ ለሁሉም ነው። እንደ ሕዝብም እንደ ሀገርም ያለው ጠቀሜታ ላቅ ያለ ነው፡፡ መማር መመራመር የአንድን አገር ችግር ለማስወገድ ሁነኛ መንገድ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ትምህርት የዘለቀው ሰው በሰለጠነ መንገድ ለመነጋገር የሚከብደው አይሆንም፡፡ ስለዚህ ለትምህርት ጥራት መጓደል መጠየቅ አለበት ከተባለ ሁሉም ነው። ትችቱ በአንድ ወገን ላይ ብቻ ያነጣጠረ መሆን የለበትም። ይልቁኑ መሆን ያለበት የዘርፉን ተግዳሮት በጋራ ለመፍታት መዘጋጀት ነው፡፡ በጋራ ለመፍታት መነሳሳት በራሱ ወደውጤት የሚያመራውን መንገድ መያዝ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ በእርግጥ በትምህርቱ ዘርፍ በአንድ ጀምበር የሚመጣ ለውጥ ላይኖር ይችላል፡፡ ምክንያቱም የሚገነባው ትውልድ ነው። የትውልዱን ፍሬ ለማየት ጥቂት ዓመታት የዘርፉን ተዋናይ ከመተቸት ይልቅ እየደገፉ መቆየት የግድ ነው፡፡›› አለችና የዛሬው የሮማን ለመሄድ አለመቸኮል አስገርሟት ‹‹ጓደኛዬ! ዛሬ ወደቤት የመሄድ እቅድ የለሽም እንዴ?!›› እያለች ለመሄድ ከተቀመጠችበት ብድግ ስትል፤ የግራ እጇን እንደጨበጠች ጉንጯን አስደግፋበት በጥሞና ስታዳምጣት የነበረችው ሮማን፣ ‹‹ወሬሽን ጨርሺ ብዬ በታገስኩሽ ነው አይደል?!…›› እያለች ተረጋግታ ከተቀመጠችበት ልክ እንደ ማርታ ሁሉ ብድግ አለች፡፡
የሰዓቱን መንጎድ ልብ ያላለችው ዘነበች ደግሞ ‹‹እንዲያው ግን የሀገራችን የዘመናዊ ትምህርት ታሪክ ጅማሬውን ያደረገው ከአንድ ምዕተ ዓመት ቀድሞ ቢሆንም በዘርፉ ግን እንደቀድሞ ጀማሪነታችን ተጠቃሚ ያለመሆናችን ነገር ይገርመኛል፡፡ ግን ደግሞ ለመልካም ውጤት መተባበር ዛሬም ቢሆን አይረፍድም›› ጓደኞቿን ልትሸኝ አብራቸው ወጣ አለች፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም