አፍሪካ እንደምን ሰነበተች? በቅኝ ግዛት የጠላት ወረራ ድንበሯ ተደፍሮ እጇ በሰንሰለት ሲጠፈር፤ እምቢ…አሻፈረኝ ስትል ነጻነቷን አውጃ ለተቀሩት ሁሉ የነጻነትን ፍኖት ያሳየችው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ባለውለታ ነች። በሌሎቹ የነጻነት ማግስትም አለሁላችሁ ስትል በሃሳብ ጫፍና ጫፍ የረገጡትን መሪዎች ሰብስባ ወደ አንድነት በማምጣት የተለያዩ ድርጅቶችን ከመመስረት ጀምሮ ታሪክን አኑራለች። በዛሬው ትውስታችን በስፋት የምንመለከታቸው ጉዳዮችም ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአንድነትና የነጻነት መሠረተ ድንጋይ የተጣለባቸውን ወሳኝ አህጉራዊ እትሞች ይሆናሉ። ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ የቆዩ ዘገባዎችንም ለትውስታ ያህል መርጠናል፡፡
ርእሰ አንቀጽ
አፍሪካ ሲነሣ
ከአፍሪካ መሪዎች ከፍተኛ ጉባኤ የተጠበቀው ውጤት ከፍተኛ ነበር። ያም ሆኖ ባለፉት ቀናት በአፍሪካ አዳራሽ ውስጥ የተፈጸመው ተግባር ከተአምር አቅራቢያ ሆኖ ተገምቷል። በአራቱ ቀን ጉባኤ አዲስ የአፍሪካ ታሪክ፤ አዲስ የዓለም ታሪክ ተጽፏል። ራሱ ታሪክ ነው።
ከአራት ቀን ውይይትና ክርክር በኋላ መሪዎች ለአፍሪካ ፍጹም አንድነት መሠረት የሆነውን “የአፍሪካና የማላጋሲ ሀገሮች ድርጅት” ቻርተር ተፈራርመዋል። በዚህም ቻርተር የሞኖሮቪያና የካዛብላንካ ብሎክ የሚባለው ነገር ተሰርዟል። አፍሪካ አንድ ብቻ ነው። ስለዚህም ወደፊት የአፍሪካ ዓላማና ምኞት ለዓለም የሚታወቀው በአንድነት ቻርተር፤ በአንድ ድምጽ ብቻ ነው። ኮሎኒያሊስቶችና ኢምፔራሊስቶች አንዱን ከሌላው የሚያጋጩበት ሰበብና ፍንጭ ከእንግዲህ አያገኙም። አፍሪካውያን ጠላቶቻቸውን ለመቋቋምም ሆነ ዕድላቸውን ለማቃናት በጠነከረ አንድነት ተነስተዋል። ይህ ታላቅ ነገር የሆነው በአራት ቀን ጉባኤ ነው። ተአምር ቢመስል አያስደንቅም። አዲሱ አፍሪካ በእርግጥም ተአምራታዊ ለውጥ የሚታይበት አህጉር ነው።
ከሰሞኑ ጉባኤ በተለይ ሁለት ስሜቶች ጎላ ብለው ተገልጠዋል። አንደኛው ብዙውን ጊዜ በከፍተኛ መሪዎች ዲፕሎማሲ ያልተለመደ ግልጽ አቀራረብ ነበር። በየሆዳቸው ብዙ ነገር ሲጉላላ ላይ ላዩን ብቻ “አሜን አሜን” ተባብለው ለመለያየት አልፈለጉም። ሐሳባቸውን ግልጥልጥ አድርገው ተወያዩ። የአፍሪካ ፕሮብሌም ፍርጥርጥ ብሎ ወጣ። አንዳንድ ጊዜ እውነቱ ሊመር ይችላል። ነገር ግን የፕሮብሌሙን መፍትሔ ሁሉ ለማግኘት የሚቻለው እውነቱ ሲወጣ መሆኑን በመገንዘብ የአፍሪካ መሪዎች በድብብቆሽ ጨዋታ እራሳቸውን ለማታለል አልፈለጉም። የጉባኤው አንዱ ታላቅ ውጤት ይህ ነበር።
……..
በመጨረሻው ቀን ስብሰባ በሦስት ሰዓት ገብተው ለምሳ በአዳራሹ ውስጥ ሳንድዊች ብቻ ተመግበው እስከ ሌሊቱ ስምንት ሰዓት ድረስ የሠሩት ስለዚሁ ነበር። ይህ ቁርጠኝነት ዋጋውን አስገኝቷል።
እያንዳንዱ አፍሪካዊ መሪ ይዞት ከመጣው የበጎ ፈቃድ የግልጽ አቀራረብ የቁርጠኝነት ስሜት ጋር ደግሞ የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት አስተዋይነትና ምክር የጉባኤውን ውጤት ሊያሳምረው የቻለው ታላቁ ቁም ነገር መሆኑን መሪዎች በንግግራቸው እየደጋገሙ ገልጸውታል።
(አዲስ ዘመን ግንቦት 19 ቀን 1955ዓ.ም)
በቅኝ ግዛት ላይ ዘመቻ ይደረጋል
ግንቦት 17 የአፍሪካ የነፃነት ቀን ይከበራል
“ጦርነት መነሣቱ ስለማይቀር” አፍሪካውያን የነፃነት ተዋጊዎችን የማሠልጠኑ ፕላን በምሥጢር እንደሚጠበቅ የዑጋንዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚልተን አቦቴ ገልጸዋል።
ሚልተን አቦቴ፣ በእንተቤ አኤሮፕላን ጣቢያ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ፖርቱጊዞች በአፍሪካውያን ላይ ለመተኮስ የሚሞክሩ ከሆነ፤ አፍሪካውያንም በፖርቹጊዞች ላይ መተኮስ ይኖርባቸዋል። የሚሊቴር ፕላናችን በምሥጢር መጠበቅ አለበት” ሲሉ ተናግረዋል። ሚስተር አቦቴ ይህንን የተናገሩት ከአዲስ አበባው ከፍተኛ ጉባኤ ሰንብተው ከሚስተር ኔሬሬ ጋር ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ነው።
ወደፊት በኮሎኒያሊዝም ላይ ጥብቅ ርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ከአዲስ አበባው ከፍተኛ ጉባኤ የወጣው ውሳኔ(ሪዞሊሽን) ያስጠነቅቃል።
…….
ለነፃነት የሚዋጉ አርበኞች ነፃ ወደወጡት ሀገሮች እየመጡ በልዩ ልዩ ሙያ እንዲሰልጥኑ የሚደረግ መሆኑን በውሳኔው አንቀጽ ፪ ላይ ተጠቅሷል።
(አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 1955ዓ.ም)
የአፍሪካ ዋና ጸሐፊ ኢትዮጵያ ትሾማለች
የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት መሪዎች በተፈራረሙት ቻርተር መሠረት የተቋቋመው “የአፍሪካ ሚኒስትሮች ምክር ቤት” ለመጀመሪያ ጊዜ በሰኔ አጋማሽ በሰኔጋል ከተማ በዳካር እንደሚሰበሰቡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ እሑድ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጉባኤ ገልጸዋል። በምክር ቤቱም ሠላሳ አባሎች ይኖሩበታል።
(አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 1955ዓ.ም)
የአፍሪካ ተክሎች
በአዲስ አበባው ጉባኤ ላይ ተሳታፊ የሆኑት 30 ነጻ የአፍሪካ መሪዎች ለመታሰቢያ በስማቸው አንዳንድ ጥድ ከአፍሪካ አዳራሽ ፊት ለፊት ከሚገኘው መናፈሻ ሥፍራ ላይ ተክለዋል፡፡
28ቱ መሪዎች ጥዱን የተከሉት ግንቦት 16 ቀን 55ዓ.ም ሲሆን፤ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትና የላይቤሪያው ፕሬዚዳንት ተብማን ግንቦት 17 ቀን 55ዓ.ም በተመደበላቸው ሥፍራ ተመሳሳይ ጥድ ተክለዋል፡፡ መሪዎቹ በተከሉቸው ጥዶች ግርጌ፤ ስማቸው የሀገራቸው ስም በዕብነ በረድ ተጽፎ ይገኛል፡፡
(አዲስ ዘመን ግንቦት 19 ቀን 1955ዓ.ም)
በ1976 ዓ.ም የመጀመሪያው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ይካሔዳል
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ብሔራዊ የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ ሥራ በ1976 ለማካሔድ የስታቲስቲክሰ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ትላንት አስታወቀ።
የቆጠራውም ሥራ ቅድመ ዝግጅት የሆነው የሕዝብ ቆጠራ ካርታ ሥራ በሚገባ በመፈጸምና ሥራውንም አመቺ ለማድረግ ሀገሪቱን በትናንሽ የቆጠራ ቦታና ከአምስት እስከ ስድስት የማይበልጡ የቆጠራ ቦታዎችን በያዙ የመቆጣጠሪያ ቦታ ካርታዎች መሸንሸን መሆን ገልጿል።
(አዲስ ዘመን ሰኔ 14 ቀን 1975ዓ.ም)
የዱር አራዊትን የገደሉ ሁለት ግለሰቦች ተቀጡ
በየረርና ከረዩ አውራጃ በቦስት ወረዳ በጉግሳና በደደቲ ቀበሌ በዶኒ አካባቢ ገበሬ ማኅበር ውስጥ የዱር አራዊትን የገደሉ ሁለት ግለሰቦች እያንዳንዳቸው ሁለት መቶ ሃምሳ ብር እንዲቀጡ የወረዳው ፍርድ ቤት ወሰነ።
መምሬ ሀብተ ሚካኤልና ቱፋ ገዛኸኝ ሀብተ ሚካኤል የተባሉ እነዚሁ ሁለት ግለሰቦች የተቀጡት ድኩላና አምባራይሌ አድነው በመግደል የዱር አራዊትን ጥበቃ አዋጅ በመተላለፋቸው መሆኑን የወረዳው ፍርድ ቤት ገልጿል።
(አዲስ ዘመን መስከረም 10 ቀን 1977ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2016