አዲስ አበባ፡- ዜጎች ለአዲስ አበባ ልማት የጀመሩትን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት በስቲያ ምሽት በታላቁ ቤተ መንግስት በተካሄደው የእራት ግብዣ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት፤ የሁሉም ተሳትፎ ከታከለበትና ዜጎች ባሉበት ጠንክረው መስራት ከቻሉ በአጭር ግዜ አዲስ አበባን ጤናማና ለኑሮ ተመራጭ ከተማ ማድረግ ይቻላል።
አዲስ አበባ የነበራትን ነፋሻ አየር፣ ጽዱነትና ለኑሮ ምቹነት ካጣች አመታትን አስቆጥራለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ከተማዋን ወደነበረ ጥሩ ገፅታዋ የመመለሻው ጊዜ ያለፈ ቢሆንም ፣አሁንም አልረፈደም››ሲሉ አስታውቀዋል፡፡የሚ ሰነዘሩ ትችትና ነቀፌታዎችን ወደጎን በመተው ለልማቷና ለጽዳቷ በተቻለ አቅም ሁሉ ተባብሮ መስራት ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያውያን የወል ካስማ- የታላቂቱ አፍሪካ ዋና ከተማ እና የብዙ ታሪካችን ማማ ለሆነችው ለአዲስ አበባ አደይ አበባዋንና ነፋሻ አየሯን የመመለስ ኃላፊነት ያለበት ደግሞ የአሁኑ ትውልድ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል። ለዚህ ደግሞ የተቻለውን ሁሉ በማድረግ ለመጪው ትውልድ የተሻለች አዲስ አበባን ገንብቶ አሻራ ለማስቀመጥ ወቅቱ አሁን መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ማብራሪያ፤ በዚህ ታሪካዊ የልማት ተሳትፎ ሁሉም የሚሰራው ስራና የሚያኖረው አሻራ ለመንግሥት ወይንም ለፓርቲና ለባስልጣን ሳይሆን ለሀገር ብቻ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። አዲስ አበባን የቀደሙት አባቶች አሁን ላለው ትውልድ እንዳወረሱት ሁሉ መጪው ትውልድም በወንዞቹ ዳርቻ እየተዝናና፣ በዛፎቹ ሥር እያወጋ፣ በቤተ መጻሕፍት ውስጥ እያነበበ እንዲኖር ማስቻል የዚህ ትውልድ ሃላፊነት ነው።
ከተማዋ የተጋረጠባትን የአረንጓዴ ልማት መመናመን በማስቆም ቀድሞ ወደ ነበረበት ለመመለስ፣ ብሎም በመጥፋት ላይ ያለውን የአካባቢ ሕይወትና ውበት፤ ከውድመት እና ከጥፋት እንዲያገመግም ለማስቻል የተባበረ ክንድ ማሳረፊያው ወቅት አሁን መሆኑን አመልክተዋል። ‹‹በተፈጥሮ ሚዛን ጥበቃ ውስጥ እኔ እንድኖር ሌሎችም መኖር ይኖርባቸዋል ብለን መነሣትም መስራትም ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ይሆናል›› ሲሉ ተናግረዋል።
በሸገር ፕሮጀክት ከተማችንን እንደስሟ የማስዋብ፣ የማሣመርና ከፍ የማድረግ እርምጃ መነሻ የመደመር ታላቅ ሐሳብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባም የአፍሪካ መዲና ብቻ ከመባል አልፋ የአፍሪካ ውብና ጽዱዋ ከተማ የምትባልበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ተናግረዋል። ከተማዋ በሀገሪቱ ላሉ ከተሞችም በአረንጓዴ ልማትና በነፋሻ አየሯና በንጹሕ የውሃ ምንጭ መፍለቂያነቷ ተምሳሌት እንድትሆን የተጀመረውን የልገሳና የድጋፍ እንቅስቃሴ ዜጎች አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ ማቅረባቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሰክሬታሪት ድረገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2011
የራስወርቅ ሙሉጌታ