ትኩረት – ለልጆች መጽሐፍ

 እንዴት ናችሁ ልጆች? መደበኛው የትምህርት መርሃ ግብር ሙሉ በሙሉ እንደጀመረ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ እናንተም በእቅዳችሁ መሠረት እያጠናችሁ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም ለእናንተ የሚጠቅማችሁን መጻሕፍት ባወጣችሁት እቅድ መሠረት በሚገባ እያነበባችሁ እንደሆነም እተማመናለሁ፡፡

ልጆች ፤ እናንተ መጻሕፍትን እንድታነቡ ‹ሕፃናት እና ታዳጊዎች›ን ያማከለ መጻሕፍት ከሚጽፉት መካከል ደራሲ የዝና ወርቁ አንዷ ናት፡፡ ልጆችዬ የዝናን ታውቋታላችሁ? እንግዲያውስ ለማታውቋት እናስተዋውቃችሁ አይደል? የዝና በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሴት ዘመናዊ አጭር የልብ ወለድ ደራሲ ናት፡፡ ‹‹መፍቻው እና ሌሎች አጫጭር ልብ ወለድ›› ለታዳጊዎች፤ ‹የአፍንጮ በር ወፎች› እና ‹ይቅርታ›› የተሰኙ የሕፃናት መጻሕፍትን እና ሌሎች ለንባብ አብቅታለች፡፡ “አበባ እና አበበ በሚል ርዕስ በተከታታይ በቴሌቭዥን ይተላለፉ ለነበሩ የሕፃናት ካርቱን ፊልሞች በግል እና በጋራ ስክሪፕቶችን አዘጋጅታለች፡፡ እንዲሁም ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ላሉት ተማሪዎች የሥነ ምግባር እና የሥነ ዜጋ መጻሕፍትን ለአንባብያን አብቅታለች፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ የሠራች ሲሆን ፤ በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን እየሠራች ትገኛለች። ደራሲዋ የልጆች መጻሕፍትን በተመለከተ በአንድ መድረክ ላይ ያቀረበችውን ጠቃሚ ሃሳብ ለእናንተ እና ለወላጆች (አሳዳጊዎች) ይጠቅማል ብለን በማሰብ ጽሑፉን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፡፡

በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የልጆች መጽሐፍ የተጻፈው ጥቅምት 1916 ዓ.ም ነበር፡፡ ርዕሱም ‹‹የፍቅር መላዕክት ለኢትዮጵያ ልጆች›› የሚል ነበር፡፡ ይህ መጽሐፍ በበቀለ ኃብተሚካኤል በአማርኛ ቋንቋ የታተመ ሲሆን፤ በውስጡ አንድነት ኃይል እንደሆነ፣ ስለጊዜ ጥቅም፣ አስቸጋሪ አጋጣሚዎች ወይም ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በኃይል እና በጉልበት ከመፍታት ይልቅ በብልሃት እና በጥበብ መፍታት እንደሚያስፈልግ የሚገልጽ ነው፡፡ እንዲሁም ዘመን ተሻጋሪ እና አሁን ላሉት ልጆች ጭምር ጠቃሚ መረጃዎችን የሚሰጥ እንደሆነ የዝና አስረድታለች።

‹‹ስኳር እና ወተት ለልጆች ማሳደጊያ›› የተሰኘው መጽሐፍ ሁለተኛው ለልጆች ተብሎ የተዘጋጀ መጽሐፍ ነበር፡፡ መጽሐፉ ከ‹የፍቅር መላዕክት ለኢትዮጵያ ልጆች›› መጽሐፍ ጋር ተመሳሳይ ዓላማ(ይዘት) ያለው ነው፡፡ በኅሩይ ወልደሥላሴ የተጻፈው ይህ መጽሐፍ፤ በ1922 ዓ.ም ነበር ለሕትመት የበቃው፡፡ በወቅቱ የሕትመት ሥራ እና የቴክኖሊጂ ውጤቶች እንደ አሁኑ ያልተስፋፋበት ይሁን እንጂ፤ አባቶቻችን ግን መጻሕፍትን በማሳተም ድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡ ደራሲዋ እንደምትናገረው፤ ሁለተኛው የልጆች መጽሐፍ ለንባብ ከበቃ በኋላ ወይም እስከ 1978 ድረስ አልፎ አልፎ የሚታተሙበት እና ጭራሽ ያልታተሙበት ወቅቶች ነበሩ፡፡ ይህም ለልጆች መጽሐፍ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ያሳያል፡፡

ከ1978 ዓ.ም በኋላ ግን በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት በኩል የሕፃናት መጽሐፍ በመጠኑም ቢሆን ትኩረት እያገኘ መጣ፡፡ ዛሬ ላይ ምንም እንኳን የልጆች መጻሕፍት ይኑሩ እንጂ፤ አንዳንዶቹ ለልጆች ጭራሽ የሚመጥኑ አይደሉም። ለዚህም ምክንያቶቹ በደራሲያን፣ በመንግሥት እና በወላጆች በኩል ትኩረት የተሰጠው ባለመሆኑ ነው፡፡ ‹‹በተለይም በመንግሥት በኩል ከቀለም ትምህርት ውጭ ለሕፃናት መጽሐፍ ትኩረት እየተሰጠው አይደለም። የቀለም ትምህርት ጠቃሚ ነው፡፡ ነገር ግን በትምህርት ቤት ውስጥ አንድ ሙያ ብቻ ይዘው እንዲወጡ የሚያደርግ ሲሆን፤ የልጆች መጻሕፍት ግን ሰብዓና (መልካም ሰው) እንዲሆኑ በመቅረጽ፣ ሀገራቸውን የሚወዱ፣ ወላጆቻቸውን የሚያከበሩ እና ኃላፊነት የሚሰማው ትውልድ እንዲሆኑ የሚያግዟቸው የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ናቸው፡፡›› በማለት ደራሲዋ ለልጆች መጽሐፍ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አስገንዝባለች፡፡

በእኛ ጊዜ ‹‹ምርጥ ምርጡን ለወላጆች›› ነበር ፤ አሁን ግን ‹‹ምርጥ ምርጡን ለልጆች›› ተብሎ ወላጆች ለልጆች የተለያዩ ነገሮችን ይገዛሉ፡፡ ነገር ግን አብዛኛው ወላጅ የልጆች መጽሐፍ ‹‹ውድ ነው፡፡›› በማለት እንደማይገዙ የሚገልጸው ደራሲ የዝና፤ ወላጆች መጻሕፍትን በመግዛት ልጆቻቸው ብሎም ራሳቸው በማንበብ ሊያበረታቷቸው ይገባል፡፡

በሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለማፍራት ልጆች በቀላሉ ሊረዷቸው የሚችሉ የሕፃናት መጽሐፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡ ‹‹በቤተሰብ ውስጥ የሚከወን ሥነ ቃል፣ ተረት እና ለልጆች ታሪክን መንገር የሚያስፈልግ ቢሆንም፤ አብዛኛው ወላጅ (አሳዳጊ) ለልጁ ‹‹ተረት ተረት›› የመንገር ችሎታም ሆነ ጊዜም የለውም፡፡›› በማለትም ደራሲዋ፤ ይህንን ኃላፊነት መወጣት የሚቻለው የሕፃናት መጻሕፍትን በማዘጋጀት መሆኑን ጠቁማለች፡፡

‹‹ሥነ ጽሑፍ የሰዎችን አእምሮ በማዝናናት እና በማስተማር መልካም አስተሳሰብ እንዲሰርጽ ለማገዝ ድርሻ አለው፡፡ በመሆኑም የልጆች መጽሐፍ ትኩረት የሚጠይቅ ሥራ ስለሆነ ወላጆች ትኩረት እንስጥ፡፡›› ስትል መልዕክት በማስተላለፍ ፤ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን እና እውቀታቸውን በመጠቀም የትውልድ ኃላፊነታቸውን ለሚወጡ ደራሲያን ምስጋና አቅርባለች፡፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን መስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You