የሰው ልጅ ሰው ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ሥራ አለ። መኖሩም ዓለማችን ዛሬ ያለችበት ደረጃና ሁኔታ ላይ እንድትገኝ አድርጓታል። ባጭሩ ዓለማችንን ለዚህ ለአሁን መልኳ ያበቃት ሥራ ሲሆን፤ በተለም ድርጊት ፈፃሚው ወጣቱ ሀይል ነው። በየትኛውም ዘመንና ትውልድ ይሁን መቼ የለውጥ ሀይሉ ወጣቱ ነውና ሥራ ሲነሳ ወጣቱን ማንሳት የግድ ነው። ስለ ሥራ ፈጠራ ሲነሳም እንደዛው።
በተለይ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ታዳጊ አገራት ፈጣን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት በመኖሩ የሥራ ፍላጎት ከፍተኛ ሲሆን የሥራ ፈጠራውም ከምን ግዜውም በላይ አጣዳፊና አስፈላጊ ነው። ይሁንና፣ ከሚገኘው የሥራ እድል ጀርባና ከተገኘው የሥራ እድል ተጠቃሚ ሰራተኛ አገር ምን ትጠቀማለች? የሚለው መሰረታዊ ጉዳይ ነው። በበርካታ ድርጅቶች ውስጥ በወጣቶችና የሥራ ሁኔታዎች ላይ ጥናት ያደረጉትና የስነ-ልቦና ምሁር የሆኑት አቶ ሳምሶን ይስሀቅ እንደሚሉት ሥራ “ለሰው ልጅ መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ሥራ መያዝም ሰንአዊ መብት ነው። “የሰው ልጅ ሥራ በመስራቱ ለራሱ ከሚያገኘው ጠቀሜታ በላይ ለማህበረሰቡና ለአገሩ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ይበልጣል።
ለምሳሌ፤ ሥራ የሌለው ሰው አእምሮው የሚያዘው ተገቢ ባልሆኑ ጉዳዮች ነው፤ ተገቢ ቢሆኑ እንኳን ጊዜያዊ እንጂ ወቅታዊ አይደሉም። ሥራ ከሌለው ጋር ሲነፃፀር ሥራ ያለው ለጭንቀት ተጋላጭነቱ አናሳ ነው። ፈረንጆቹ እንደሚሉት ‘ሥራ የፈታ አእምሮ የዲያቢሎስ መናኸሪያ ነው።’ በቀላሉ ለተለያዩ ሱሶች ይጋለጣል። ሥራ ያለው ሰው፣ ሁሉም ባይሆን፣ ግን ከእነዚህ የራቀ፣ ሓላፊነት የሚሰማው፣ ስለ ስራው የሚያስብ እና ለስራውም የሚጨነቅ፣ ነገን የሚያልም፣ አልባሌ ቦታ ለመዋል ጊዜ የሌለው ነው።
ይህ ደግሞ ለጊዜው ላይታወቀን ይችላል እንጂ በአብዛኛው ጥቅሙ ለሀገርና ለአጠቃላይ ማህበረሰቡ ነው።” በጉዳዩ ላይ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአንድ አገር ላይ ሥራ አጥ ዜጋ አለመኖሩና ሥራ ያለው ቁጥር መብዛቱ አገራዊ ጥቅሙና አኮኖሚያዊ ፋይዳው ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም። ማርክ ሪዲክስ የተባሉ ተመራማሪ “ዋና ዋና” በማለት ያቀረቧቸው ጥቅሞች ያሉ ሲሆን ከነዚህም መካከል ሰራተኛ የሆነ ዜጋ አንደኛ ሸማች ነው፣ ሁለተኛ አምራች ነው፣ ሦስተኛ ቀዳሚ የገንዘብ ልውውጥ አካል ነው፤ አራተኛ አከፋፋይና ተካፋይ ነው። እንደ ምሁሩ አገላለፅ እነዚህ ደግሞ “ለአንድ ኢኮኖሚ እድገት የጀርባ አጥንት” ናቸው።
እንደ ሪዲክስ ጥናት የስራና ሰራተኛ ጥምረት ከስብጥር የዕድገት ምንጮችም አንዱና ዋነኛው ነው። አዳዲስ ሰዎችን ወደ ስራው ዓለም ማስገባት አዳዲስ ክህሎት፣ እውቀት፣ ልምድ፣ አሰራር ወዘተ ለማግኘት ሰፊ እድልን ለተቋማት ይከፍታል የሚሉን ደግሞ ሚራንዳ ብሩኪንስ ናቸው። እነዚህ የሌሉት ሰራተኛ ወደ ድርጅት ከተቀላቀለ ደግሞ ውጤቱ የዚህ ተቃራኒ እንደሚሆንም ይኸው ጥናት ያስረዳል። በቅርቡ የቻይናን “ቀበቶ እና መንገድ/Belt & Road” ስትራቴጂ የገመገሙ አንጋፋ ጋዜጠኛ እና ማህበራዊ ሀያሲ ሀርሌይ ቬግ ሥራ ያላቸውንና የሌላቸውን በንፅፅር ባዩበት ጥናታቸው ውስጥ “ጠቃሚ ነጥቦች” በማለት ካሰፈሯቸው መካከል የሥራ እድል ያገኙ ሰዎች የሥራ እድል ካላገኙት በተሻለ አገርን እየጠቀሙ መሆኑ፤ ሥራ ያላቸው ሰዎች የተለያዩ ወጪዎችን በማውጣት ኢኮኖሚው እንዲስፈነጠር ማድረጋቸው፤ ኢኮኖሚው እንዲያድግና ሌሎች አዳዲስ የስራ እድሎች እንዲፈጠሩ ማድረጋቸው እንዲሁም ለመሰረተልማት መፋጠን ከፍተኛ ሚና ያላቸው መሆናቸው ዋና ዋና ነጥቦች ናቸው።
ለፖለቲካ መረጋጋትም ሆነ ለኢኮኖሚ እድገት ያለውን ቁልፍና የማይተካ ሚና የሚነግሩን ደግሞ የሥራ ፈጠራ ባለሙያና ሥራ ፈጣሪው ምራገሽ ከጅሪዋል (Indian Institute of Management ምሁር) ናቸው። እንደ ምራገሽ አስተያየት ሥራ ያለው፣ በትክክልም ስራውን ሰርቶና ውጤታማ ሆኖ የሚውል ሰው በብዙ መልኩ አትራፊ ነው፤ የሞራል ልእልናው ሲበዛ ከፍተኛ፣ በራሱ የሚተማመን፣ የተረጋጋ፣ ፍላጎቱ እየጨመረ ስለሚሄድም ጥሩ ሸማች ነው። ይህ ደግሞ ለኢኮኖሚው መነቃቃት ከፍተኛ እገዛን ያደርጋል። በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ሀብቱን በማዋል በኩል ጥሩ ኢንቨስተር ነው። ፍላጎቱ ሁሉ በመበጥበጥና ሁከት በመፍጠር ሌሎችን ለመረበሽ ሳይሆን ለማስደሰት ይጥራል። ለህይወቱ ትርጉም ይሰጣል፤ ለመኖሩም ምክንያታዊ ነው።
የራሱን ህይወት መኖር ላይ ያተኩራል። አቶ ሳምሶን ይስሀቅም ከዚሁ ባልተለየ ሁኔታ “ሥራ ያለው ሰው ቤተሰቡንም የሚመራ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ለአገርም ለማህበረሰብም የሚያስገኘው ፋይዳ ቀላል” እንዳልሆነ ይናገራሉ። “ሰዎች ሥራ አጥ በሚሆኑበት ጊዜ ሁከትና አለመረጋጋትን ይፈጥራሉ የሚለው የምራገሽ ጥናት ሥራ አጥ መሆን ሰዎችን ለማንኛውም እኩይ ተግባር ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋል። ከዚህ መረዳት እንደ ሚቻለው ሥራ መፍጠር፤ ዜጎችን የተፈጠረው የሥራ እድል ተጠቃሚ ማድረግና ሰዎች ሰርተው መግባት መቻላቸው ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባለፈ ፖለቲካዊ ፋይዳም ያለው መሆኑን ነው።
ለዚህም ነው ምሁሩ “መንግስታት አጓጉል ነገር ላይ ገንዘባቸውን ከማፍሰስ ይልቅ ለወጣቶች የሥራ እድል በሚፈጥር መልኩ ማዋል” እንደሚገባቸው አበክረው የሚመክሩት። አቶ ሳሙኤል ይስሀቅም ይህንኑ ሀሳብ በመደገፍ “ለእኩይ ተግባራት የተጋለጠ ነው። ጥፋት ይቀናዋል። ድንጋይ ለመወርወር፣ ንብረት ለማውደም፣ ሁከት ለመፍጠር፣ በሌሎች አላማ ለመነዳት ወዘተ ሲበዛ ቅርብ ነው።” ሲሉ የገለፁት። አያይዘውም “ይነስም ይብዛ ሥራ ያለው ሰው ለፖለቲካው ስጋት መሆኑ ቀርቶ እንደውም አጋዥ ነው የሚሆነው።
ምክንያቱም በየመንግሥት ተቋማቱ ሲሰራ፣ መንግሥትን ሲያገለግል ነው የሚውለው። ለህብረተሰቡም ቢሆን ይህ ሰው አዎንታዊ አስተዋፅኦ ያደርጋል እንጂ ጎጂ ሊሆን አይችልም። ለዚህም ነው መንግሥታት ሥራ መፍጠሩ ላይ ሊተጉ የሚገባው።” የሺካጎ ዩኒቨርሲቲው ኢኮኖሚስት ራንዳል በርንስ በበኩላቸው ሥራን መፍጠር አጠቃላይ አገራዊ ምርት እንዲጨምር ያደርጋል ይላሉ። እንደ በርንስ አባባል ወጣቶች በሥራ በመጠመዳቸው ብቻ ከሁከትና ረብሻ ይርቃሉ። ይህ ደግሞ የአገር ሀብትና ንብረት እንዳይወድም፤ የሰው ልጅ ህይወት እንዳይጠፋ ያደርጋል። ይህም ለአንድ አገር አጠቃላይ ምርት እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉ ምንም ጥርጥር የለውም።
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2011
ግርማ መንግሥቴ