አንዳንድ የኪነ ጥበብ ዘርፎች ወደ ሀገራችን ብቅ ብቅ ማለት ሲጀምሩ ሕዝቡም ማልዶ በመነሳት ‹ይሄ ደግሞ የምን ጉድ ነው› ሲል አይኑን በጥያቄ ማሸቱ አልቀረም ነበር። በግራ መጋባትና በጥርጣሬም በአይነ ቁራኛ ሲመለከታቸው ኖሯል። የቆየ ባህልና ሥርዓቱም አዳዲስ ነገሮችን በአሜንታ የመቀበል ፍላጎቱን ከልቡ ውስጥ በሩን በመዝጋት ክርችም አድርጎ ቆልፎበት ነበር። እንደ ባዕድና ዘመን አመጣሽ ይታይ ስለነበረም ፍጥጫው ትውልዱን ነጻ የማውጣትም ጭምር ነበር። ንጉሱ አጼ ምሊኒክ ስልክን ወደ ሀገራችን አስገብተው በቀጭኑ ሽቦ ለመጀመሪያ ጊዜ `ሃሎው` ሲሉ ሕዝቡም፤ ንጉሱ የሰይጣንን ነገር ወደ ሀገራችን አስገቡ እያለ በጊዜው ሲያማቸው ነበር። ታዲያ የኋላ ኋላ ጥቅሙን ሲረዳ `አበስኩ ገበርኩ! ለካ እንዲህ ኖሯል እንዴ? በማለት የሀሜት አፉን አብሶ በምስጋና መመለሱ አልቀረም። በኪነ ጥበቡም ቢሆን የነበሩት አብዛኛዎቹ ከዚሁ ተመሳሳይ ናቸው። ሲመጡ አዲስ እየሆኑብንና ጠረናቸው እየከረፋን አፍንጫችንን እንይዝባቸዋልን። የኛን ባህልና ወግ የሚያጠፋ እየመሰለን ከአዝመራው መሃል እንደበቀለ አረም ነቅለን ለመጣል ብዙ እንታገላለን። መጨረሻውም ሊሆን የሚችለው ወይ ሰልችቶን እንተወዋለን አሊያም ወደን በፍቅር እንቀበለዋለን።
ለኢትዮጵያዊማ ስለ ጥበብና ኪነ ጥበብ እንዴት ይነገረዋል? ቀድሞውንስ የእርሱ የራሱ አይደሉምን? ሁሉም የኪነ ጥበብ ዘርፍ አሜንታዊ ገጽታ አልነበራቸውም እንዳንል የድንጋይ ላይ ሥዕሎችን፣ የብራና ላይ ጽሁፎችን ለዓለም ያስተማረው ማን ሆነና…ቅኔ ማህሌቱን በአዕዋፋት ዝማሬ ያስደመጠውስ? ብቻ ግን የጉምጉምታ ናዳ እየወረደባቸው የኛው ሆነው ወደፊትም ወደኋላም ሳይሉ፤ በተዘጋ ቤት እንዲኖሩ የፈረድንባቸው የኪነ ጥበብ ልጆችም አሉ። ለምሳሌ ያህል ለዛሬው ልናነሳቸው ከመረጥናቸው ሙዚቃ በቤት ስሙ ደግሞ አዝማሪነት አንደኛው ሲሆን ሌላኛውና ሁለተኛው ደግሞ መነሻውን ከወደ ባህር ማዶ አድርጎ ከቴክኖሎጂው ማሳ ስለበቀለው የፊልሙ ኢንዱስትሪ ይሆናል። ሁለቱ የኪነ ጥበብ ዘርፎች በሀገራችን ከመነሻቸው አንስቶ በአሜንታና በጉምጉምታ ታጥረው ሲኮረኮሙ የኖሩ ናቸው። ከውልደታቸው አንጻር ለእድገታቸው መቀጨጭ መንስኤውም ይሄው ኩርኩም ነው ሲሉ አንዳንዶች ይቺን ሀሳብ ጣል ያደርጋሉ። ከባህልና ማሕበረሰብ እስከ ኪነ ጥበብ፣ ከአዝማሪነት እስከ ሙዚቀኝነት፣ ከሰይጣን ቤት እስከ ፊልም ኢንዱስትሪው በአሜንታ ወይንስ በጉምጉምታ?
የሀገራችን የሙዚቃ ታሪክ ከ4ኛው ክፍለ ዘመን ይጀምራል፡፡ መነሻው ከወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን፤ ታላቁ የሙዚቃ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ደግሞ ዛሬ የምንመለከተውን የባሕላዊ ሙዚቃ መሠረት የጣለ የመጀመሪያው ባለቅኔ ነው፡፡ ከዚያም ሙዚቃ የሚባለው ጽንሰ ሀሳብ በብዙዎች እየታወቀና ውስጥ ውስጡን እየሰረጸ የባሕላዊ ሙዚቃና ድምጻውያን ተወለዱ። እንደዛሬው ቴክኖሎጂው ባለመኖሩ ሙዚቃዎቹ በቴፕ አሊያም በካሴት ክር የሚቀዱ ሳይሆኑ እንደ አዝማሪያኑ ሁሉ ሥራዎቹ የሚቀርቡት ፊት ለፊት ወይንም ገጽ ለገጽ ነበር። የባሕል ድምጻውያኑ የራሳቸው የሆነ ፈተና ቢኖርባቸውም እንደ አዝማሪያኑ ጉምጉምታው አልበረከተባቸውም። በባሕላዊ የሙዚቃ ታሪክ ሁለተኛው ወሳኝ በር የተከፈተው በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ሲሆን በዚህች በር የገባው የመጀመሪያው ሙዚቀኛ ደግሞ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ነበር። ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በሀገረ ጀርመን ሳለ አንድ የጀርመን የሙዚቃ ካምፓኒ ሙዚቃዎቹን በሸክላ ሊቀርጽለት እንደሚፈልግ ነገረው። እሱም በሀሳቡ በመስማማት ዘለሰኛን ጨምሮ 17 ያህል ልዩ ልዩ ይዘት ያላቸው ሥራዎቹ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሸክላ ታተሙ።
ከአራተኛው ክፍለ ዘመን በፊትም ሆነ በኋላ በሙዚቃ ሐረግ በቅሎ ዛሬም በ21ኛውም ክፍለ ዘመን ያለ አንድ ግዙፍ የሙዚቃ ግንድ አለ። ይሄውም አዝማሪነት ነው። ባሕላዊውም ሆነ ዘመናዊው ሙዚቃ የበቀለው ከዚሁ ከአዝማሪያኑ ግንድ ላይ ነው። ዘመናዊውን የሙዚቃ ዓለም በማስተዋወቅ ነጮቹ ቢቀድሙም በሙዚቃ ዓለም በመኖር ግን አዝማሪዎቻችንን የሚቀድም አልነበረም። ጥበብም እንደ አምላክ የተናቁትንና ትንንሾቹን መረጠች። ካልጠፋ መንደር ሁሉ በአዝማሪዎቹ መንደር ማደርን ሽታ በችግር እራሷን ለቅርቃር አሳልፋ ሰጠች። በሀገራችን፤ የሙዚቃ ጥበብ በአዝማሪያኑ ልብ አድራ በሯን ዘግታ ያለቀሰችበት ዘመነ ሰቆቃ የታሪክ ምዕራፍ እንደነበራት ግልጽ ነው። ያውም አዝማሪነት እስከ ውግዘት የሚል ባለ ብዙ ገጽ ምዕራፍ። የሙዚቃው ናርዶስ የሆነው የመንፈሳዊው ዝማሬ ከወደ ቤተ ክርስቲያን እንደ እጣን ከርቤው የሚያውድ መዓዛ ነበረው። በሌላኛው ወገን ያለው የአዝማሪያኑ ሙዚቃ ግን ቃናው የሚከረፋ ጣዕሙም መራራ ነበር። የሙዚቃ ጥበብና የአዝማሪው ሙዚቃ እንደ ጉድፍና እንደ አጸያፊ ነገር እየታየ ሲወርድ ሲዋረድ መጥቶ ጅራቱ የተቆረጠበት ዘመንም እሩቅ አይደለም። ከወዲህኛው አለፍ ብሎ የነበረው ዘመን ሁለቱንም በቀኝና በግራ ይዞ መልካቸውን ያሳየናል።
በአዝማሪያኑ ዘመነ ሰቆቃ፤ የአባት ለልጅ ትልቁ ምርቃት “ዘማሪ እንጂ አዝማሪ ከመሆን ይጠብቅህ” ነው። አዝማሪ መሆን ጦሱ ለራስ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰብና ለዘመድ አዝማዱም ነው። የእከሌ ልጅ አዝማሪ ሆኖ ዘራችንን አሰደበ ተብሎ ለተግሳጽና ለምክር የሚሰበሰበውን የዘመድ አዝማድ ጉባኤ መመልከት አዝማሪነት ባፍንጫዬ አስብሎ የሚያስበረግግ ቢሆንም፤ አዝማሪና አዝማሪነት ግን ፈጽሞ አልሞቱም። በጊዜው የነበረው አዝማሪነት ከአሁኑ ባህላዊ ሙዚቃ ጋር የበለጠ ቁርኝት ቢኖራቸውም የባህላዊም ሆነ የዘመናዊ ሙዚቃ ውልደታቸው ከዚሁ ከአዝማሪዎቹ መንደር ነው። በዚህኛው ዘመን ሙዚቀኛ መሆን አንገት የሚያስደፋ ሳይሆን ደረት የሚያስነፋ ነው። ለመናገርም የሚያሸማቅቅ ሳይሆን ምነው በጠየቁኝና ቶሎ በነገርኳቸው የሚያስብል ነው። ሙዚቃ በዚያኛው ዘመን ግን፤ በሕግ ያልተደነገገ አንቀጽ አልባ የወንጀለኛ መቅጫ ነበር። ፍርዱም ማሕበረሰባዊና ቤተሰባዊ የሆነ ጥምር የጋራ ውግዘት ነው። አዝማሪነት የተወገዘ በመሆኑ ወደዚህ የሚገባ ሁሉም የተወገዘና የተገለለ ይሆናል። አንዳንዴም አለፍ ብሎ የቅጣት እርከኑ ከፍ ሲል ከቤተሰቡ የልጅነት መዝገብ ላይ የሚያሰርዝ ፍርድን ያስከትላል። ለአንድ አባት ትልቁ ሞት ማለት ልጅህ አዝማሪ ሆነ ወይንም ሆነች ሲባል መስማት ነው። ለእናትም ቢሆን ከዚህ የከፋ ሕመም የለም። “በተከበርኩበት ሀገር አዋረድከኝ…ዘጠኝ ወር በሆዴ ተሸክሜ በእነዚህ ሁለት ጡቶቼ እንዳላሳደኩሽ ዛሬ አንገቴን አስደፋሽኝ…እንደ እከሌ ልጅ ቤልጅግና ምንሽሩን ታጥቀህ…እንደ እከሌ ልጅ የቀለም ቀንድ ሆነህ ስሜን ታስጠራለህ ስል እንዲያው ያንተ መጨረሻ አዝማሪነት ይሁን! ከእንግዲህ ወዲያ አንተም ልጄ እኔም አባትህ አይደለሁም” የተባሉስ ስንቶቹ ናቸው…ዛሬም በሙዚቀኞቹ ዘመን ጥንት የነበረው የጉምጉምታ ወላፈን በረድ፤ ቀዝቀዝ አለ እንጂ ፈጽሞ ግን አልተዳፈነም። ከዚህ ረገድ ሁለት ጽንፍ የያዙ ሙግቶች አሉ። አንደኛው ሙዚቀኞችን በመቃወም ሙዚቃ አይጠቅምም፤ አያስፈልግም በማለት በአራት ነጥብ የሚዘጉ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ሙዚቃ ሕይወት ነው በማለት አስፈላጊነቱን ብቻ ሳይሆን ሀያልነቱንም የሚናገሩ ናቸው። ዛሬ ላይ ሆነው የቀደመውን ጊዜ በመደግፍ ሙዚቃን በሚቃወሙም ሆነ የቀደመውን እየነቀፉ ስለ ታላቅነቱ በሚገልጹት በሁለቱም ሰዎች ዘንድ የራሳቸው የሆነ እውነት አለ። እውነቱም የሚገኘው እራሳቸው ጋር ብቻ ነው።
ጊዜው ገሰገሰ ዘመንም ዘምኖ ቴክኖሎጂን አፈራ። የቴክኖሎጂውን ጽዋ ከቀመሱ የኪነ ጥበብ ልጆች መካከል አንደኛውና ዋነኛው የፊልሙ ኢንዱስትሪ ነው። የፊልሙ አንዱስትሪ ያለቴክኖሎጂ የማይታሰብ ነበር። ውልደቱ ደግሞ ከቴክኖሎጂውም አስቀድሞ የነበረው የቲያትሩ ዓለም ነው። ከ1988 ዓ.ም በፊት በሀገራችን ስለ ፊልም ምንነትም ሆነ ፊልም የሚለውን ነገር ጨርሶ ማንም አያውቀውም ነበር። በ1988 ዓ.ም እስቴቨን የተባለ አንድ የውጭ ዜጋ ወደ አጼ ምኒልክ ጠጋ በማለት ስለነገሩ ምንነት ያጫውታቸዋል። ሁሉንም ቴክኖሎጂ ቀምሶ የማጣጣም ፍላጎታቸው ከፍተኛ የነበረው ንጉሱም እንዲህ ከሆነስ እስቲ እኛም እንየው በማለት ቴክኖሎጂውን ይዞ እንዲመጣ ነገሩት። ግለሰቡም በ1989 ዓ.ም `ቤንሀር` የተሰኘውን ስለክርስቶስ ገድል የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ለማሳየት የሚረዳውን አንጸባራቂ ቴክኖሎጂ ይዞ ከተፍ አለ። በዚያው ዓመት ሚያዚያ 1 ቀን አጼ ምኒልክን ጨምሮ የቤተ መንግሥቱ ሹማምንትና ቀሳውስት ተሰባስበው ‹አጃኢብ ነው› ሲሉ ፊልሙን ተመለከቱት። ከአንድ ዓመት በኋላም 1890 ዓ.ም አንድ ሲኒማ ቤት ተከፈተ። በጊዜው ወሬው እየተናፈሰ ሕዝቡም ይህን ጉድ ለመመልከት ወደ ሲኒማ ቤቱ ይጎርፍ ጀመረ። መጀመሪያ ላይ ነገሩን በአሜንታ ቢቀበለውም ብዙም ሳይቆይ ግን የሚያየው ነገር ምትሀታዊና የማይጨበጥ እየሆነበት ሲመጣ ጊዜ አዝማሚያው አላምር አለው። ወደኋላ በማፈግፈግ ጉምጉምታውንም ጀመረ። ቤቱንም “የሰይጣን ቤት“ ሲል ጠራው። ሰውም ከመዝናናት ወደ ፍርሃት ስለገባ ተመልካች ጠፍቶ ቤቱ ተዘጋ። የፊልም ቤቱ ባለቤትም ዕቃውን ለኢጣሊያን ሚኒስቴር ተወካይ ሽጦ ወደ ሀገሩ ገባ።
ከአስፈሪ ጉምጉምታ የተነሳ ሕዝቡ ይህ የፊልም ነገር እንዲያው ምንም አልዋጥልህ ቢለውም፤ ገመዱ ግን ሙሉ ለሙሉ አልተቆረጠም ነበር። ከሲኒማ ቤቱ ደጅ እንደምንም እየተፍገመገመ መጥቶ በሀገራችን የሚሰሩ ፊልሞች ወዳበቡበት 1990ዎቹ መጀመሪያ ደረሰ። ጥቂት አሜንታ ብዙ ጉምጉምታ፤ አሁንም ከፊልሙ አብዮት ጋር ተያይዞ ተነሳ። ከቴሌቪዥን የመስኮት ስርጭት አልፈው በዲስክና በሲዲ ወደየቤቱ መግባት ሲጀምሩ ደግሞ ውስብስብነቱ እየጨመረ በወጣቱና በአዛውንቱ፣ በታችኛውና በላይኛው ክፍል የአመለካከት ልዩነትን ፈጠረ። የታችኛው ክፍል በተለይ ደግሞ የወጣቱ ክፍል ወደዚህ እየተሳበ መሄዱን በጨመረ ቁጥር የላይኛው ክፍል ደግሞ አንድ እግሩን በእጁ እየጎተተ ለማስጣል ቢሞክርም የማይቻለው ነበር። እንደዛሬው ቤተሰብ ተሰባስቦ ሲኒማ ሲመለከት ማየት ከተአምር የማይተናነስ ምትሀት ነበር። ገንዘብ እያስከፈሉ ፊልሞችን ያሳዩ የነበሩ ፊልም ቤቶች በማሕበረሰቡ ዘንድ ያላቸው ምስል ልክ እንደያኔው የሰይጣን ቤት ነበር ። ሲኒማ ቤት ሳይሆን የብልሽት ክትባት የሚሰጥበት የመጥፊያ ካምፕ ተደርገው ነበር የሚቆጠሩት። በርግጥም በከፊል መሆናቸው አልቀረም ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የወላጆቹን ከቤት አለመኖር እየጠበቀ ለሁለትና ለሶስት ሰዓታት ፊልሙን ተከራይቶ የሚያየውም ልጅ አንድ አይኑን ከቴሌቪዥን መስኮት፤ አንድ አይኑን ከቤቱ በር ተክሎ ነበር የሚመለከተው። ነገሩ የአይጥና የድመት ጨዋታ ነበር የሚመስለው። ፊልም ማየት የዱርዬነት፤ አለማየትም የጨዋነት መለኪያ ተደርጎ መቆጠሩም አልቀረም። ወላጅ የልጁ አመል አስቸጋሪ የሆነበት እንደሆን “ይሄው ይሄን ፊልም የሚሉት ጂኒ ማየት ከጀመረ ወዲህ ጸባዩ ሁሉ ብልሽትሽት አለ” ሲል አመለሸጋው ልጅም ቁጭ ብሎ ፊልሙን ሲኮመኩም ድንገት የደረሰበት ጎረቤት “አሄ…ትልቁ ዳቦ ሊጥ“ በማለት ተርቶ ይሄዳል።
በእነዚህ ሁሉ ነገሮች ውስጥ የማሕበረሰቡ በአሜንታ የመቀበል ፍላጎቱ ምንም እንኳን ዝቅተኛ ቢሆንም፤ ለመውቀስ የሚያስደፍር አንዳችም ምክንያት ግን የለም። ማሕበረሰባችን በሀይማኖቱ ታፍሮ በባህሉ ተከብሮ የሚኖር ሕዝብ በመሆኑ የሚሆነው ሁሉ ትውልዱ ከዚህ ማንነት እንዳያፈተልክ በመስጋት እንጂ በኋላ ቀርነት ተሸብቦ አይደለም። ነገር ግን በስጋት የበቀለውን ጉምጉምታ በእውቀት ላይ በቆመ አሜንታ መቀየር ይቻላል። አውቆ በመናገር ጠርጥሮ በመብላት ላይ የተመሠረተ የኪነ ጥበብ ዓለም የግድ ነው። በሙዚቃውም ሆነ በፊልሙ፤ በአሜንታና በጉምጉምታ እንደ አፋር ስምጥ ሸለቆ ለሁለት የተከፈለውን የሀገራችንን የኪነ ጥበብ ምድር አንዳች ስበትን ፈጥረን ወደ አንድ ማምጣት የምንችለው፤ የማሕበረሰባችንን የልብ ትርታ በመጨመር ሳይሆን በማድመጥ ነው።
መርፌን ካወቅህበት የወጋህን እሾህ ትነቅልበታለህ፤ ካላወክበት ግን የባሰውን እራስህን ወግተህ ታደማበታለህ። ኪነ ጥበብም ካወቅንበት መዳኛ ካላወቅንበት መጥፊያችን ለመሆን የሚያግደው አንዳችም ነገር የለም። ለአሜንታችንም ሆነ ለጉምጉምታችን በእውቀት ላይ የተመሠረተ ምክንያታዊነት ያስፈልገናል። ጉዳዩ ያለው ከአያያዛችን ላይ እንጂ የትኛውንም የኪነ ጥበብ ዘርፍ ከመቀበልና ካለመቀበል ጋር መሆን የለበትም። የተጠቀሙበት ሀገርና ባህላቸውን አሳድገዋል። አንዳንዶች ደግሞ `ከበሮ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናግር` አይነት ሆኖባቸው፤ማንነታቸውን ያጡበት እንደሆነም አይተንበታል። ቀድሞውኑ የኛ የሆኑትን ነገሮች ወስደው ለወዙ ከቅባቱ ደፋፍተው የራሳቸው እንደሆነ ነገር በኩራት ለኛው መልሰው ሲሰጡን፤ የፈረንጅ እያልን የተቀበልነው ስንቱን ነው? የኛ ለኛ የሆነውን ማየት ተስኖን በማይገባን ነገር የሚገባንን አጥተናል። ባህልና ኪነ ጥበብ ወደ አንዲት ሀገር የሕልውና ባህር በእኩል የሚፈሱ ገባር ወንዞች ናቸው። የአንዱ መድረቅ ሌላውን ያደርቃል፤ የአንደኛው መደፍረስም ሌላኛውን ያደፈርሳል። ባህልን ገሎ ኪነ ጥበብን ለማዳን፤ አሊያም ኪነ ጥበብን ገድሎ ባህልን ለማዳን መሞከር ዶሮዋን አርዶ እንቁላልዋን እንደመጠበቅ ነውና አንዱ ያለ አንዱ የማይገኝ መሆኑን መረዳት የመክፈቻው ቁልፍ ነው።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም