ሳንዋራ ቤጉም ማሌዥያ ደርሳ የማታውቀውን ሰው ለማግባት በአጋቾቿ ተገድዳ ለሁለት ሳምንት በተራራዎችና በወንዞች መካከል በመኪናና በጀልባ ተጉዛለች። የተጓዘችበት መንገድ አቀማመጥ አባጣ ጎርባጣ በመሆኑ ለእሷ አዲስ ነበር። ጉዞዋን የጀመረችው ባንግላዴሽ ከሚገኘው የሮሂንግያን ስደተኞች ካምፕ ሲሆን በወቅቱ የ23 ዓመት ወጣት ነበረች። በአሁን ወቅት የሮሂንግያን ሴቶች የማያውቁትን ሰው ለማግባት እየተጠለፉ የመሄድ ሁኔታ ተበራክቷል።
በባንግላዴሽ ኮክስ ባዛር የኩትፓሎግ ሰፈራ ቦታ እንደሚያሳየው እአአ 2017 በካምፑ ውስጥ ያለው የሴቶች ቁጥር እያደገ መጥቷል። በተለይ የማይንማር መንግሥት በአናሳ ሙስሊሞች ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ወደ ስደተኛ ጣቢያው የሚመጡት ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። በጣም በሰዎች የተጨናነቀው ካምፕ ውስጥ ለሴቶች ጥበቃ የማድረግ አቅም የለውም። አብዛኛዎቹ ሴቶች በቀርከሃና በላስቲክ በተሰራ ቤት ውስጥ ኑሯቸውን እየገፉ ይገኛሉ። እንደ ሮሂንግያን አክትቪስትና የመብት ተከራካሪዎች አባባል በአሁን ወቅት ብዛት ያላቸው ሴቶች ሮሂንግያ ወንድ ለማግባት ማሌዥያ ደርሰዋል።
በአንዴ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች በህገወጥ መንገድ ይጓጓዛሉ። ‹‹ ቅድሚያ በእግር እንጓዛለን፣ አንዳንድ መንገዶችን በመኪና እንቋርጣለን። የተወሰነ ካምፕ ውስጥ ካረፍን በኋላ ወደ ህንድ ድንበር በማቅናት ማሌዥያ እንገባለን። በወቅቱ ሶስት ተጠላፊዎች ነበርን።›› በማለት ቤጉም ትናገራለች። ‹‹ጠላፊዎቹን ስለማላወቃቸው እደፈራለሁ የሚል ስጋት ነበረኝ። ምክንያቱም ቀደም ብሎ ስለተደፈሩ ሴቶች ሰምቼ ስለነበር ነው። ለዚህም ስጋት ውስጥ ነበርኩ።›› ብላለች። የጋብቻ ሁኔታውና ጉዞው የሚመቻቸው በሮሂንግያ ወንድ ነው።
ወንድ ሮሂንግያውያን በህገወጥ መንገድ ወደ ማሌዥያ የገቡ ቢሆንም የማሌዥያን ሴቶች ማግባት አይፈልጉም። ወንዶቹ ለማግባት ቢፈልጉም ከማስረጃ ውጭ ወደ ማይንማር ወይም ወደ ስደተኞች ካምፕ መመለስ አይችሉም። በዚህም ጓደኞቻቸውን ወይም ዘመዶቻቸው በመጠየቅ ሴቷ ብዙም ተሳታፊ በማትሆንበት ሁኔታ እንዲያጋቧቸው ያደርጋሉ። አብዛኛዎቹ በባንግላዴሽ ስደተኞች ካምፕ የሚገኙ ሮሂንግያን ተመሳሳይ የሆነ ሁኔታ ውስጥ አልፈዋል። አብዛኛዎቹ ሴቶች በዘመዶቻቸው ወይም በሚያገቡት ሰው ቤተሰብ ተጠልፈውይወሰዳሉ።
ወደ ማሌዥያ የሚደረገው ጉዞ አድካሚና ወራት የሚፈጅ ነው። አንዳንድ ተጠልፈው የተወሰዱ ሴቶች ቤተሰቦቻቸው በማይንማር የሚገኙ ሲሆን ጠላፊዎቹ ቤተሰቦቻቸውን ወደ ባንግላዴሽ እንዲሄዱ በማስደረግ እና ደግመው ወደ ማይንማር እንመልሳቸዋለን በማለት ያስፈራሯቸዋል። በቅርቡ ማሌዥያ የህፃናት ጋብቻ የከለከለች ሲሆን ምክንያት የሆናት 11 ሊያገቡ ከነበሩ ህፃናትና ከዘመዶቻቸው ጋር በተደረገው ቃለ መጠይቅ ነበር።
በማሌዥያ በፀደቀው ህግ ላይ ተሳታፊ የነበረው ጆን ኩዊንሊ እንደሚለው፤ በቅርቡ በመሬት ምክንያት በማይንማርና በባንግላዴሽ፣ በህንድና በማይንማር በሚገኘው ሲን ከተማ እንዲሁም በማዳላይ እና ያንጎ ከተሞች ግጭቶች ተከስተዋል። በማይንማርና በታይላድ ድንበር የተነሳው ቀስ ብሎ ወደ ማሌዥያ ተሸጋግሯል። በባንግላዴሽ ኮክስ ባዛር ስደተኞች ካምፕ የሚገኙ ሮሂንግያን ያላቸው ምርጫ አነስተኛ ነው።
ምንም አይነት ስራ መስራት እና መደበኛ ትምህርት ማግኘት አይችሉም። የሮሂንግያን ስደተኞች ካሉበት ቦታ በግዴታ ሊለቁም ይችላሉ። ይህ ሁኔታ ሮሂንግያውያን ወዳልፈለጉበት አቅጣጫ የሚመራቸው ሲሆን ሴቶቹ በጋብቻ ወደ ማሌዥያ በብዛት እንዲገቡ ማድረጉን ጆን ኩዊንሊ ይናገራል። እስከ እአአ 2015 ድረስ ህገወጥ የሰው አዛዋዋሪዎች ሮሂንግያውንን በደቡብ ታይላድ በኩል ወደ ማሌዥያ አጓጉዘዋል። አብዛኛው ተጓዥ በማሌዥያ ነፃነት እንደሚኖረውና ማንኛውንም ስራ ከባንግላዴሽና ከማይንማር በተሻለ እድል አገኛለሁ የሚል ተስፋ አለው። ነገር ግን በታይላንድ የ139 ሰዎች መቃብር በህገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች ካምፕ በመገኘቱ ምክንያት ህገወጥ ዝውውሩ መቀዛቀዝ አሳይቶ ነበር። እአአ 2017 በባንግላዴሽ ህገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች በጀልባ ሰው ይዘው ሲጓዙ በአገሪቱ ድንበር ጥበቃዎች ከለላ ተሰጥቷቸዋል። በዚህም ባለፉት ዓመታት ሮሂንግያኖች በህገወጥ መንገድ በብዛት ተጓጉዘዋል።
አብዛኛዎቹ ጉዞዎች በእግር የተደረጉ ናቸው። በታይላንድ የሮሂንግያን አክቲቪስት ለአልጀዚራ እንደተናገረው፤ ወደ ማሌዥያ በህገወጥ መንገድ የገቡ ሮሂንግያን ቁጥር በውል አይታወቅም። ነገር ግን አሁንም ብዙ ሴቶች በህገወጥ መንገድ እየገቡ ይገኛሉ። አክቲቪስቱ እንደሚለው፤ አንድ ወጣት ሴት ከህፃን ልጇ ጋር በማሌዥያ ውስጥ የታሰረች ሲሆን የአገሪቱ ባለስልጣናት ወጣቷና ህፃኗ ደህንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መግለጫሰጥተዋል።
ሀሚዳ የ30 ዓመት ወጣት ስትሆን በማይንማር አቅራቢያ በባንግላዴሽ ስደተኞች ካምፕ ውስጥ ትኖራለች። እሷ እንደምትለው፤ በማሌዥያ የሚኖረው ወንድ ልጇ ማግባት ስለሚፈልግ የ15 ዓመት ሴት ከማይንማር ወደ ባንግላዴሽ አስመጥታለች። ልጅቷ ወደ ማሌዥያ ከመሄዷ በፊት ከእሷ ጋር ትቆያለች። ‹‹ልጅቷ መንገዱ ርቀት በጣም ፈርታለች ነገር ግን ምንም ማድረግ አይቻልም። ምክንያቱም አንዴ የተዘጋጀ ነገር በመሆኑ›› በማለት ሀሚዳ ትናገራለች። እንደ ሀሚዳ ገለፃ፤ ከባንግላዴሽ ህንድ ድንበር ለመድረስ ረጅም የእግር ጉዞ ይደረጋል። ጉዞው ረጅም ቀናትን የሚፈጅ ሲሆን ታይላንድ ከተደረሰ በኋላ በአውቶቡስ ወይም በመኪና ማሌዥያ ድረሰ ይኬዳል።
አጠቃላይ ጉዞው ሶስት ወራት የሚፈጅ ሲሆን ልጅቷ በመንገዱ ርቀት ልትከሳ ትችላለች። የሀሚዳ ወንድ ልጅ ለረጅም ዓመታት በማሌዥያ የኖረ ሲሆን ጋብቻውን በጓደኞቹ በኩል እንዲካሄድ አድርጓል። የቤጉም የጋብቻ ሁኔታ ተሰናድቶ የነበረው በወንድሟ በዛኪር ሁሴን ነው። ወንድሟ በማሌዥያ የሚኖር ሲሆን የ17 ዓመት ሚስት አግብቷል። ልጅቷን በህገወጥ መንገድ ከስደተኞች ካምፕ አስመጥቶ ነው። ቤጉም በተመሳሳይ ከባሏ ጋር በኳላላምፑር እየኖሩ ይገኛሉ።
ዛኪር እንደሚለው፤ የሮሂንግያ ወንድ በማሌዥያ ለማግባት ቢፈልግ ምንም አማራጭ የሌለው የመኖሪያ ፈቃድ ስለሌለውና በዝቅተኛ ደመወዝ ፋብሪካዎች ውስጥ ስለሚሰራ ነው። ‹‹ጠላፊዎቹ በሚያደርጉት ነገር ፍራቻ ቢያድርብንም ሁሉንም ነገር ለፈጣሪ እንሰጣለን። ጠላፊ መቅጠር አንፈልግም ግን አማራጭ የለንም።›› በማለት ዛኪር ይናገራል። ቻኩፋ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሮሂንጋ ሴቶችን በካምፕ አካባቢ አደራጅቷል። አደረጃጀቱ በበጎ ፈቃደኝነት ሴቶች በኢኮኖሚ ጫና ለፍላጎት እንዳይዳሩና ተጠልፈው እንዳይወሰዱ ለመከላከል የተቋቋመ ነው።
‹‹አብዛኛው በአካባቢው የሕፃናት ጋብቻ ተስፋፍቷል። ምክንቱም በየወሩ የሚደረገው የግንዛቤ ስራ በቂ ባለመሆኑና የገቢ ምንጭ ባለመኖሩ ነው።›› በማለት ቻኩፋ ይገልፃል። በአካባቢው የምግብ ማግኘት ሁኔታው አነስተኛ መሆኑ በየወሩ በሚደረግ ሪፖርት እንደ ተግዳሮት ይጠቀሳል። በካምፕ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች መንግሥታዊ ላልሆኑ ለጋሽ ድርጅቶች ምግብ እንዲሟላላቸው በተደጋጋሚ ጠይቀዋል። ስደተኞቹ ተመሳሳይ የሆነ የምግብ ተመኖች በመኖራቸው ቅሬታ አቅርበዋል። አንዳንዴ ምግቡ የአሸዋና ሌሎች ደቃቅ ነገሮች እንደሚይዝ ይናገራሉ።
ቻኩፋ እንደሚለው፤ ይህ ሁኔታ በካምፕ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን እያስጨነቃቸው በመሆኑ ሴት ልጆቻቸውን በመዳር የተመጋቢ ቁጥር እየቀነሱ ይገኛሉ። ያለእድሜ ጋብቻ እንዲቆም ከብዙ ቤተሰቦች ጋር ውይይት ተደርጓል። ልጆቻቸውን ካልዳሩ የሚፈልጉትን ነገር ለማሟላት አስፈላጊው እርዳታ እንደሚደረግላቸው አንዳንዴ ቃል ይገባላቸዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የእድሎች አለመመቻቸትና ጥብቅ ቁጥጥር አለመኖር ብዙ ሴቶች ቤታቸው ተቆልፎባቸው ይገኛል። ቤተሰቦቻቸው እንደሚሉት በስደተኞች ካምፕ የሰው ጭንቅንቅ ውስጥ ትኩረት ላለመሳብ ነው። ካሊህዳ በካምፕ ውስጥ የምትኖር ስትሆን የ14 ዓመት ልጇን ማሌዥያ ለሚገኝ ሰው እንድትድር ጥያቄ ቀርቦላታል።
ነገር ግን ልጅትዋን ለመላክ አቅም ስለሌላቸው ጥያቄውን ውድቅ አድርገዋል። በዚህ በተዘጋጀ የጋብቻ ስነስርዓት የጥሎሽ ገንዘብ የሚከፍሉት የሴቷ ቤተሰቦች ናቸው። በተጨማሪም ለህገወጥ አዘዋዋሪዎቹም ግማሹን ገንዘብ የሚሸፍኑት እነሱ ናቸው። ካልሂዳ እንደምትለው፤ ልጇ በአካባቢው ካለ ሰው ጋር ብትጋባ ደስተኛ ቢያደርጋትም ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ የመክፈል ግዴታ አለባት። በካምፕ አካባቢ ምንም አይነት ትምህርት አይሰጥም። በዚህም ልጇ በቤት ውስጥ ሙሉ ጊዜዋን ታሳልፋለች። ካህሊዳ ይህ ሁኔታ ደህንነቷን ያስጠብቅላታል ብላ ታምናለች።
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2011
መርድ ክፍሉ