የሀገር ፍቅር በጥላሁን ገሰሰ አንደበት

ተፈጥሮ ሳትሰስት ያለልክ በለገሰችው ድምፁ የተቹትን ሁሉ ሳይቀር በዙሪያው አሰባስቦ በሃሴት ያስጨፈረ የመድረክ ላይ ንጉስ እንደነበር ይነገርለታል። የሃገሪቱን ዘመናዊ ሙዚቃ በምርኮው ውስጥ ያዋለ ጀግናም እንደሆነ ምስክርነታቸውን ይሰጡለታል። ከሁሉም በላይ ግን ሀገር ወዳድነቱን በእንባ ጭምር የሚገልጽ መሆኑ ከሁሉም ሙዚቀኞች ለየት ያደርገዋል የሚባልለት ነው፡፡ የዛሬው የባለውለታዎቻችን አምድ እንግዳ ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ፡፡ እናም ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያገኘናቸውን መጣጥፎች በማጠናቀር ውለታነቱ እንዴት ነበር ስንል ልናወጋችሁ ወደናል። መልካም ንባብ ፡፡

ውልደትና እድገት

1933 ዓ.ም ዕለተ መስቀል ለአቶ ገሰሰ ቤተሰብ አውደ ዓመት ብቻ አልነበረም፡፡ ለጎጇቸው ሌላ የምስራች የተገኘበት ልዩ ቀን ነው፡፡ እማወራዋ ጌጤ ጉርሙ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ የተገላገሉበት ልዩ ዕለት። መላው ቤተሰብ በዓሉን ድርብ አድርጎ ያሳለፈበት የስጦታ ጊዜ። በዚህ ቀን የተገኘው ፍሬ ለመላው ቤተሰብ የአዲሱ ዓመት ታላቅ በረከትም ነበር፡፡ በትዳር ለተጣመሩት ጥንዶች የዓይን ማረፊያ የሆነው ብላቴና የተገኘበት፡፡ ይህ ልጅ ደግሞ ጥላሁን ነው፡፡

ጥላሁን ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ‹‹ጠመንጃ ያዥ›› በተባለ አካባቢ ሲሆን፤ እንደ እኩዮቹ ሆኖ አድጎበታል፡፡ ለሚያዩት ሁሉ ልጅነቱ የሚያጓጓ፣ መልኩ የሚያምር ፣ ቁመናው የሚማርክ ነበርም። ሆኖም በአዲስ አበባም ሆነ በሰፈሩ በአብሮነት እምብዛም አልዘለቀም፡፡ 14ኛ ዓመቱን ባከበረ ማግስት ከተማውን ለቆ ጉዞውን ወደ ወሊሶ አደረገ፡፡ ወሊሶ አያቱ ይኖራሉ፡፡ እናም እዚያ ለማደግ ነው ወደዚያ የተጓዘው፡፡

ትምህርትና የሙዚቃ ጥሪ

ጥላሁንና ትምህርት የተገናኙት አዲስ አበባ በነበረበት ወቅት ሲሆን፤ የትምህርት ሀሁውን የጀመረውም በአካባቢው ከሚገኝ የራስ ጎበና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ በዚያ ፊደል እንዲቆጥር ተመዘገበ፡፡ ብዙም በቦታው ላይ ባለመቆየቱ የተነሳ ቀጣዩን ትምህርት የተማረው ወሊሶ ላይ ነው። በእርግጥ የእሱ ፍላጎት ከቀለሙ ጋር የሚገናኝ አልነበረም። ውስጡ ያደረው የሙዚቃ ፍቅር ይታገለዋል፣ ያሸንፈው ይዟል፡፡ ይህን ያስተዋሉት አያት ሁኔታውን አልወደዱም፡፡ ምክንያቱም የእርሳቸው ፍላጎት በትምህርቱ ብቻ ላይ እንዲያተኩር ነው፡፡

የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ ሱዳናዊው ሼድድ ግን ጥላሁንን በተለየ መልኩ አይተውታል፡፡ ፍላጎቱን አብዝተው ያከብሩለታል፡፡ ስለዚህም ፍላጎቱን እንዲሞላ ትኩረት ቸሩት፡፡ ችሎታውን መዝነውም ወደ ሱዳን ሄዶ ሙዚቃ እንዲያጠና ምክር ለገሱት። እርሱም ምክራቸውን ሰማና የተባለውን ባያደርግም ከራሱ ስሜት ጋር ሲታገል ቆየ፡፡ አንድ ቀን ግን ምክሩን እውን የሚያደርግበት እድል ገጠመው። ይህም የሀገር ፍቅር ቴአትር ባለሙያ የነበሩ ባለሙያዎች በትምህርት ቤታቸው የሙዚቃ ትዕይንት ለማሳየት የተገኙበት ነው፡፡ ከመጪዎቹ መካከል ደግሞ አቶ ኢዮኤል ዮሐንስ አንዱ ናቸው። እናም ጥላሁንም ቀረብ ብሎ ያለውን ችሎታና ፍላጎቱን አስረዳቸው፡፡ እዮኤል ጆሮ ሰጥተው አደመጡት፡፡ ፍላጎቱ ካለውም አዲስ አበባ መምጣት እንደሚችል ጠቆሙት፡፡ እንግዶቹ ከወሊሶ ከተሸኙ በኋላ ጥላሁን እንቅልፍ ይሉት አጣ። ትምህርቱን መማር፣ መከታተል ተሳነው፡፡

አንድ ማለዳ የጥላሁን ልብ ቆርጦ ተነሳ፡፡ ማንም ሳያየው ከቤት ጠፍቶ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀመረ። ሁኔታውን ያወቁት አያት ለዘመድ ነግረው ሰላይ ላኩበት፡፡ 15 ኪሎ ሜትር በእግሩ የተጓዘው ጥላሁን ቱሉ ቦሎ ሲደርስ አዳሩ ከአክስቱ ቤት ሆነ። ማግስቱን ጉዞ ከመቀጠሉ በፊት ግን ተይዞ ወደ ወሊሶ ተመለሰ፡፡

በአስገዳጅነት ተመልሶ ወሊሶ የገባው ጥላሁን በሆነበት ሁሉ አዘነ፡፡ እልህና ቁጭት ያዘው፡፡ በውስጡ ያደረውን የሙዚቃ ፍቅር ያደናቀፉበትን በሙሉ በክፉ ዓይን አያቸው፡፡ በቤቱ ከአንድ ቀን በላይ አልቆየም፡፡ በጭነት መኪና ተሳፍሮ ዳግም ጉዞ ጀመረ፡፡ አዲስ አበባ ያደረሰው እግሩ ከሀገር ፍቅር ቴአትር አገናኘው። የጥላሁን ምኞት ዕውን ሆነ፡፡ የውስጡ ፍላጎትና የሙዚቃው ፍቅር ገጠሙለት፡፡ የትናንትናው የወሊሶ ጉብል አዲስ አበባ ላይ ታዋቂ ለመሆን አልዘገየም። እንዳሻው የሚታዘዝለት ድንቅ ጉሮሮው የሰጡትን ግጥምና ዜማ እያንቆረቆረ በርካቶችን ይማርክ ያዘ። የዘመኑ ተወዳጅ ድምጻዊ በመሆን ቀዳሚም ሆነ፡፡

ጥቂት ጊዜያትን በሀገር ፍቅር የቆየው ጥላሁን ለሌላ ዕድል ታጨ፡፡ ወደ ክቡር ዘበኛ ተዛውሮ ከአንጋፋና ታዋቂ የሙዚቃ ሰዎች ጎን ተሰለፈ፡፡ የላቀ ዝነኝነቱን ተከትሎ ግን ፈተና አላጣውም፡፡ በታህሳሰ ግርግር ዘፍኖታል የተባለ ዜማ ትርጉም ተሰጥቶት ለእስር ዳረገው፡፡ ይህም ቢሆን መዝፈኑን አቁሞ አያውቅም። ይበልጡን ከእስር ከተፈታ በኋላ ጠነከረ። በዚህም ብዙዎች እርሱ ያልነካው የሕይወት ጫፍ፣ ያላነሰው የዓለም እውነታ የለም። ክፋትና ደግነት፣ ሀዘን ደስታ፣ ሕይወትና ሞት የለም ይሉታል፡፡

የጥላሁን ሙዚቃና የሀገር ፍቅር

ጥላሁን ከሙያ አቻዎቹ የሚለየው በዘመናት ሂደት በተቻለው ሁሉ በሙዚቃ ሥራው ውስጥ ራሱን ከፍ እያደረገ መሄዱ ነው ይላሉ፡፡ ከአሁን በኋላ በቃው በሚባልበት ጊዜ በድንገት የሚያስደምም ሥራ ይዞ ብቅ ይላል፡፡ ‹‹ጥላሁን በላብ እየተጠመቀ መድረክ ላይ ወጥቶ ሲዘፍን በአካባቢው መድፍ እንኳ ቢተኮስ አይሰማም›› ሲሉ አስተያየታቸውን የሚሰጡም አሉ፡፡ ማለትም መመሰጥ ከምንም በላይ ይችላል። መመሰጥን ከሃገር ፍቅር አንፃር፤ ማስተማርን ከጀግንነት አኳያ እንዴት ሲያዋህደው እንደነበረ ጥቂቶቹን ግጥሞቹን በማንሳት እናውጋ፡፡

አጥንቴም ይከስከስ ደሜም ይፍሰስላት፣

አገሬን በጭራሽ አይደፍራትም ጠላት፡፡ የሚለው አንዱ ሲሆን፤ በ1967 ዓ.ም ኢትዮጵያ ባገጠማት ድርቅና ርሀብ የከፋ ችግር ላይ በወደቀችበት ዘመን ላይ ሆኖ መላው ዓለም ኢትዮጵያን ርዕስ አድርጎ ስለከፋው ርሀቧ፣ በየዕለቱ እንደ ቅጠል ስለሚረግፈው ምስኪን ህዝቧ በእጅጉ ሲያወራ ጥላሁን ግን የሙያ አጋሮቹን ሰብስቦ ከመደገፉ ባለፈ በእጁ የገባውን ግጥም ከዜማ አዋህዶ ለሁሉም ‹‹ይድረስልኝ›› ሲል በታላቅ ሀዘንና ለቅሶ

ዋይ !ዋይ ሲሉ፣

የርሀብን ጉንፋን ሲስሉ፡፡

እያዘንኩ በዓይኔ አይቼ፣

ምን ላድርግ አለፍኳቸው ትቼ፡፡

ወይ እማማ ወይ አባባ፣

ብለው ሲሉ ሆዴ ባባ፡፡

አስጨነቀኝ ጭንቀታቸው፣

ምንስ ሆኜ ምን ላርጋቸው፡፡

ሳያቸው አይኔ አፍጥጦ፣

ተለየኝ ልቤ ደንግጦ፣

ተብረከረከ ጉልበቴ፣

ምን ላድርግ ዋ! ድህነቴ‹‹

በርሀብ ስቃይ ቸነፈር፣

ግማሹ ጎኔ ሲቸገር፡፡

ክው ብሎ ደርቆ አፋቸው፣

የእግዜር ውሀ ሲጠማቸው እያለ አንጎራጎረ። በዚህ ሙዚቃው ደግሞ ከሀገር አልፎ ባህር ማዶ ተሻገረ። ወገኖቹን ከችግር ታደገ፡፡ ምክንያቱም በእርሱ ጥበብ ለእርዳታ እጁን ብዙ ሰው ዘረጋ። ወገን ለወገኑ እንዲደርስ፣ አስከፊው የርሀብ ጊዜ እንዲታወስ አደረገ። ይህ አይረሴ ዜማ ዛሬ ድረስ ለመላው ኢትዮያውያን የክፉ ቀን ማስታወሻ እንደሆነ ዓመታትን ተሻግሯል።

ጥላሁን በዜማው ባለስልጣንን የሚቃወምና ድልንና ለውጥን ለሀገር የሚያሳይም ነው፡፡ በየትኛው ሙዚቃው ከተባለ ለአብነት ‹‹በአልማዝን ዓይቼ›› በዚህ ሙዚቃው በዘመነ ደርግ የነበረውን የስልጣን ሹምሽር በደንብ ተችቶታል፡፡ አድማጩን አንቅቶ የለውጥ አምጪ አድርጎበታል፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ ሶስቱን አልማዞች ከወቅቱ ሶስት የደርግ ባስልጣናት ጋር አመሳስሎ የራሱን ትርጓሜ ይሰጥ ነበርና ታሪክ እንደሚነግረን ደግሞ እነዚህ ሶስት ሰዎች የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክ የመቀየር ገጽታን ተላብሰው ነበር፡፡ እንዲህ መሆኑ ደግሞ ምርጫው ወደ ሌላ እንዲያደለና በመጨረሻ ጥሩወርቅ ከተባለችው ላይ እንዲያርፍ መገደዱን ጭምር ይነግረናል፡፡ ስለዚህም ጥላሁን የሀገር ለውጡ ላይ ሳይቀር ተሳትፎ ነበረው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ሌላው ጥላሁንን ለየት የሚያደርገው በትግል ሜዳም አዋጊ ጀግና መሆኑ ነው፡፡ በተገኘባቸው የጦር አውድማዎች ጀግናን ማወደስ፣ ወታደሩን ማጀገን ያውቅበታል፡፡ በጦርነት መሀል ተገኝቶ ወደ ፊት በሉለት ይለይለትን አዚሟል፡፡ የጀግና ሰው ክብሩ ዳር ድንበሩ ሲል አነቃቅቷል፤ ዘማች ነኝን ዘፍኗል። ከሁሉም ግን የውትድርና ሕይወትን መሰረት አድርጎ ለጀግኖች ኢትዮጵያውያንና ቤተሰቦቻቸው መታሰቢያነት ያንጎራጎረው ይህ ዜማ ፍጹም አይረሴነትን እንደያዘ እስከዛሬ ቀጥሏል፡፡

ለአገሬ ስታገል ለድንበሯ

ከአገሬ ስታገል ለድንበሯ፣

ተኝቻለሁ እኔ ከአፈሯ፡፡

ስለድል ታሪኬን ስታወሱ፣

ቤተሰቦቼን ግን እንዳትረሱ፡፡

እንዳይራቡብኝ አስታውሱልኝ፣

እንዳይራቆቱ አልብሱልኝ፡፡

እንዳይቸገሩብኝ ልጆቼ፣

አደራ ብያለሁ ወገኖቼ፡፡

ጥላሁን ገሰሰና የሀገር ፍቅር ፈጽሞ አይነጣጠሉም። ስለሀገሩ ካሉት ደግሞ የዕንባው ነገር ይለያል፡፡ አገሩን እያነሳ አልቅሶ ታዳሚውን ጭምር ያስለቀሰባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው። ከጥላሁን የዕንባ ዜማዎች መካከል ስለነጻነት ያዜመው ስንኝ እንዲህ ይታወሳል፡፡

እንኳንስ ደስታዬን -የሰውነቴን ሰው፣

እንኳን ነጻነቴን- ጸጋ ክብሬን ትቼው፡፡

በእናት ሀገር ምድር – በሚያውቀኝ፣

በማውቀው ፣

ስቃይ መከራየን ካንቺው ዘንድ ያድርገው፡፡

ጥላሁን ገሰሰ በአማርኛ ከተጫወታቸው እጅግ በርካታ ዜማዎች በተጨማሪ በኦሮምኛና ሱዳንኛ ዘፈኖቹ ጭምር ይታወቃል፡፡ ሁሉም በሚባል መልኩም ዜማዎቹ ተወዳጅና ተደማጭ እንደሆኑም ምስክር የሚሆነው ዓመታትን መሻገራቸው ነው። ከዚህ አንጻርም የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉስ ተብሎ ይጠራል፡፡

ጥላሁን በሕይወት ዘመኑ በርካታ ውጣውረዶችን አልፏል፡፡ በ1985 ዓ.ም በአንገቱ ላይ የደረሰበትን ጉዳት ጨምሮ በስኳር ህመሙ መነሻ ባጋጠመው ሕመም አንድ እግሩን አስከመቆረጥ ደርሷል። እንዲያም ሆኖ ከመድረክ የመለየት ፍላጎት አልነበረውም፡፡ ሁሌም ቢሆን ሙያውን ማሳየት፣ ለአድናቂዎቹም ፍቅሩን መግለጽ ይሻል፡፡

የጥላሁን ሽልማቶች

ዕድሜውን ሙሉ ለሀገሩ ባበረከተው የኪነጥበብ ስራዎች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት አግኝቷል፡፡ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የኪነጥበብና የብዙኃን መገናኛ ሽልማት ድርጅት የሙሉ ዘመን ተሸላሚ ለመሆን ችሏል፡፡

ጭለማው ፋሲካ

ጥላሁን ለግማሽ ምዕተ ዓመት በሙዚቃው ማማ ንጉስ ስለነበረው ክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሰሰ ብዙ ማለት ይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን መጨረስ አይቻልም፡፡ ገና በአፍላ የሙዚቃ ዘመኑ በሲራክ ታደሰ የተደረሰውን ‹ትንፋሼን› ስንሰማ ከሕይዎትም በላይ ሞትን ያልዘነጋ ንጉስ መሆኑን እንረዳለን። በሕይወት ካለፈ በኋላ በሀገር እንዲታወስና በሙያው እንዳይረሳ ያዜመ ብርቅዬ ዘፋኝ መሆኑንም እናረጋግጣለን፡፡ እስኪ ‹‹በትንፋሼን›› ምን አለ ካላችሁ በቃላት አዳምጡት፡፡

ትንፋሼ ተቀርፆ ይቀመጥ ማልቀሻ፣

ይህ ነው የሞትኩለት የእኔ ማስታወሻ፡፡

ውበቷን ሳሞግስ -የለምለም ሀገሬን፣

ማንም አይዘነጋው በጩኸት መኖሬን፡፡

ዜማ እንጉርጉሮዬን የግሌን ቅላጼ፣

ተቀርፆ ይቀመጥ ታሪኬ ነው ድምጼ፡፡

ድምጻዊ ዘፋኝ ነኝ አንጎራጉራለሁ፣

ይኸው ነው ታሪኬ ሌላ ምን አውቃለሁ፡፡

ዕለተ ፋሲካ ለሁሉም ሰው ፍስሀ ሲሆን ለጥላሁን ቤተሰብ ግን ጨለማ ነበር፡፡ ሆኖም በማይረሱት ሙዚቃዎቹ ዘወትር ስለሚታሰብ ሀዘናቸውን ከሌሎች ጋር ተጋርተው ዕለቱን በደስታ እንዲያሳልፉ ይሆናሉ። እርሱ ሲታሰብም ከለቅሶ ይልቅ ሀሴትን ያደርጋሉ። ምክንያቱም እርሱ ከሚወዳት አገሩ፣ ከሚያከብረው መድረክና በፍቅር ከተንበረከከለት ሙያው በድንገት የተለየው ሚያዚያ 11 ቀን 2001 ዓ.ም በዕለተ ፋሲካ ሌሊት ቢለያቸውም ልደቱ በዕለተ መስቀል ተከብሮ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ጎልቶ ይታያልና እርሱ አልሞተምን በየዓመቱ ያስባሉ። ልክ ነው ንጉስ በሀገሩ ሁሌ መከበሩ አይቀርምና አይሞትም፤ ሕያውነቱን በሥራዎቹ ይገልጣል፡፡

ፅጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን መስከረም 23/2016

Recommended For You