የኃይል አቅርቦት ማርሽ ቀያሪዎቹ የዓባይ ግድብ ተጨማሪ አምስት ተርባይኖች

2016፤ የዓባይ ግድብ ግንባታ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱ የተረጋገጠበት ዓመት ነው። ከብዙ ጫና በኋላ የግድቡ አራተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት የተጠናቀቀበት ከመሆኑም ባሻገር ተጨማሪ አምስት ተርባይኖች የሚገጠሙበት አመትም በመሆኑ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው። ለመሆኑ ግድቡ አሁን የደረሰበት ደረጃና ዘንድሮ የሚተከሉት አምስት ተርባይኖች በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ እድገት አንጻር ምን ትርጉም ይኖራቸዋል?

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪና የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ ከዚህ ቀደም በዓባይ ግድብ ላይ ሁለት ተርባይኖች ተተክለው ኃይል ማመንጨት በመጀመራቸው በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ስርጭት ውስጥ ተጨማሪ ብርሃን እንዲሁም አዲስ የሥራና ዕድገት መሠረት መፈጠሩን ያወሳሉ። አራተኛውን ሙሌት ተከትሎ ደግሞ በጀመርነው አመት በጋ ላይ እየተገጠሙ የሚገኙት አምስት ተርባይኖች ተጠናቀው ተጨማሪ ኃይል ያስገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ዶ/ር ያዕቆብ፣ የሚገኘው ተጨማሪ ኃይል በከተሞች እና በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች የብርሃን ስርጭትን ከፍ ያደርጋሉ። በኤሌክትሪክ ኃይል አማካኝነት የሚሠሩ በርካታ የሆኑ የኢንዱስትሪና አግሮ ኢንዱስትሪ ሥራዎች እንዲስፋፉ በማድረግም ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ድህነትን ለመቀንስ ያግዛል ብለው እንደሚያምኑ ይገልጻሉ።

ከአምስቱ ተርባይኖች የሚመነጨው ኃይል ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት በሽያጭ የምታቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ከፍ እንዲል በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን እንደሚያሳድግም ዶክተር ያዕቆብ ያስረዳሉ፣ «ለጎረቤት ሀገሮች ጅቡቲና ሱዳን የኃይል ሽያጭ እየተካሄደ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ግድቡ ኃይል የማመንጨት አቅሙ እየጨመረ ሲሄድ ለጅቡቲና ሱዳን ተጨማሪ ኃይል ማቅረብ እንችላለን። በተጨማሪም ወደ ኬንያም የኃይል ተሸካሚ መስመር ዝርጋታው በመጠናቀቁ ወደፊት በርካታ ኃይል ለመግዛት ውለታ አላቸው። ከኬንያ ባለፈ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳንን የመሰሉ ሀገራትም ለኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ጥያቄ ማቅረባቸው የታወቀ ነው። ስለዚህ ባጠቃላይ ከግድቡ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል የሀገሪቱን ኢኮኖሚና የሥራ እንቅስቃሴ ከፍ የማድረጉን ያህል ለጎረቤት ሀገሮች እየተሸጠ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ አንድ መንገድ የመሆኑ ዕድል ከፍ እያለ ይመጣል» ብለዋል።

አያይዘውም ኢትዮጵያ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ስታመነጭ ውሃ የሚቀበሉትም ሆኑ ሌሎች ጎረቤት ሀገሮች ከኢትዮጵያ ኃይል የመግዛት ዕድላቸው ከፍ እንደሚል መዘንጋት እንደሌለበት በመግለጽ፣ ትስስሩ በኢኮኖሚ መያያዝን ከፍ ስለሚያደርግ ፖለቲካዊ ትብብር እና መቀራረብ እንዲኖር እንዲሁም ሠላምና የጋራ ብልጽግናም ለወደፊት ተስፋ ያለው ነገር እንዲሆን እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሀብት ተመራማሪውና በዓባይ ግድብ ጉዳይ ላይ አስተያየት በመስጠት የሚታወቁት ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ በበኩላቸው አምስት ተርባይን ማለት ከግድቡ አጠቃላይ ኃይል የማመንጨት አቅም አንድ ሦስተኛ ያህል መሆኑን በመግለጽ፣ ኢትዮጵያ ላላት የኤሌክትክ ኃይል አቅርቦት ትልቅ ጭማሪ ነው ይላሉ። በሥርዓት ለአገልግሎት ከቀረበ ብዙ የኃይል እጥረት የገጠማቸው ማምረቻ ድርጅቶች ተጨማሪ ኃይል እንዲያገኙ ያደርጋል። በኅብረተሰቡም ደረጃ በየቤቱ የሚደርሰው የኃይል መጠን የተሻለ ይሆናል ብለዋል።

ዶ/ር ያዕቆብም የአምስቱ ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት መጀመር በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት የተለየ እንድምታ አይኖረውም ይላሉ። ኢትዮጵያ ገና ግድቡ ሲጀመር ጀምሮ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ የመገደብ መብት እንዳላት አሳውቃለች። ፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀም መኖር አለበት የሚል አቋም ይዛ በጥናቱ፣ በዲዛይኑ እና አሠራሩ ውሃ ተቀባይ ሀገሮች የከፋ ጉዳት ላይ እንዳይወድቁ በከፍተኛ ጥንቃቄ መነሳቷ ይታወቃል። ስለዚህ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ የምትደራደረው የውሃ መብቷን ለማስከበር ሳይሆን የውሃ ሀብቷን በሉዓላዊነቷ ላይ ተመስርታ የማልማት መብቷ የተረጋገጠ መሆኑን በሚገባ ለማሳየትና የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው በምክክር እንዲሠሩ ለማስቻል ነው ብለዋል።

በአንጻሩ ከኢትዮጵያ ውሃ የሚቀበሉ ሀገሮች በተለይም ግብጽ ኢትዮጵያ የውሃ ልማቷን እነሱን እያስፈቀደች እንድትሠራ ይፈልጋሉ ሲሉም ይወቅሳሉ።

አክለውም «ይሄ እንደማይሆን ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እየተነገራቸው ነው። ከዚህ ቀደምም ሆነ ሁልጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ ሃሳብ የውሃ ልማትን እነሱን አስፈቅዶ የመሥራት አይደለም። ኢትዮጵያ ለትብብር ዝግጁ እንደነበረች ባለፉት በርካታ አስርት አመታት የተገለጸ ነገር ነው። በዓባይ ግድብም የተገለጸውና በተግባርም እየዋለ ያለው መርህ ይሄ ነው» በማለት በዚህ መሠረት እስካሁን ያለው ሥራ በሚገባ እየተሰራና የኢትዮጵያ ሀሳብ በግልጽ ለግብጽና ሱዳን እየተነገረ መሆኑን ያስረዳሉ። ወደፊት ድርድሩ የሚቀጥለው ግብጾች አስገድደን እናስፈርም በሚሉት አቅጣጫ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ውሃዋን ስታለማ ግብጽና ሱዳን በከፋ ሁኔታ እንደማይጎዱ ማረጋገጫ በመስጠት የጋራ ልማት እንዲቀጥል በሚያስችል መልኩ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑም ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ግድቧን እንዳትሞላ የሚከለክላት ምንም ዓይነት ሕግም ሆነ የሞራል ገደብ አይኖርም የሚሉት ፕሮፌሰር አድማሱ፤ አምስቱ ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ሲጀምሩ ከታችኛው ሀገራት በኩል ጩኸት ሊበረክት እንደሚችል በመግለጽ፣ ጩኸቱን እና ፍሬ ነገሩን መለየት ያስፈልጋል በማለት ያሳስባሉ።

ፕሮፌሰር አድማሱ እንደሚናገሩት፣ የኃይል ፍላጎታችን እያደገ ሲሄድና የገቢ ምንጭም እናድርገው ስንል የዓባይ ግድብን ጨምሮ ያሉን ኃይል ማመንጫዎች ላይበቁ ይችላሉ። አሁን እያገባደድን የምንገኘውን ግድብ መያዣ አድርገው የማዋከብና የማደናገር ተግባር ላይ የሚሰማሩት የወደፊት ዕጣፈንታችን ከሆነው ሀብት የመጠቀም መብታችንን የሚገደብ ስምምነት ውስጥ እንድንገባ በመፈለግ ነው። ይህን ልናደርግ አንችልም፤ ኢትዮጵያም የምትጠነቀቀው ለዚሁ ነው። የዓባይ ግድብን የውሃ ሙሌት ምክንያት በማድረግ ወደፊት በሚገነቡ ሌሎች ግድቦች ላይ ውሳኔ ማሳለፍ ጥንቃቄ ማድረግ እንዲሁም በቂ ውይይት ይፈልጋል።

ይህ ግድብ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው የመጨረሻ ግድቧ እንዳልሆነ ሊታወቅ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ፕሮፌሰሩ፣ «የዓባይ ግድብ የመጨረሻዋ ነው ብሎ የሚያስብ ካለ ይሄ ምክንያታዊ አስተሳሰብ አይደለም። በኢትዮጵያ በኩል እጃችን ላይ ያለው አጀንዳ ግድቡን መሙላትና ጥቅም ላይ ማዋል ነው። በዚህ ሂደትም ኢትዮጵያ የምታባክነው ውሃ እና እነሱ የሚጎዱበት ሂደት የለም» ብለዋል።

በዓባይ ወንዝ ተጠቃሚ መሆንን በተናጠል ከመወጠን በመውጣት በጋራ እያሰብን የጋራ ፕሮጀክቶችን ጭምር አብረን መሥራት ብንለማመድ፣ ከውሃው ውጪ በባህልና ኢኮኖሚም የሚወራረስ ነገር ስላለን ብዙ ተጠቃሚ እንሆናለን ሲሉ ይመክራሉ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በቅርቡ እንደገለጹት፣ ዘንድሮ ወደ ሥራ ከሚገቡት አምስቱ ተርባይኖች የሚገኘው የኃይል መጠን ግልገል ጊቤ ሦስት ከሚያመነጨው የሚበልጥ እና የበለስ፣ የግልገል ጊቤ አንድና ሁለት እንዲሁም የተከዜ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከሚሰጧቸው አማካይ አንድ ሺህ 180 ሜጋ ዋት ተመጣጣኝ ወይም የሚበልጥ ይሆናል። ይህም ግድቡ ሳይጠናቀቅ በኢትዮጵያ ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ እንዲሆን ያደርገዋል። በግድቡ የሚገጠሙት ተርባይኖች እያንዳንዳቸው በአማካይ ከ375 በላይ ሜጋ ዋት ኃይልን ያመነጫሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን መስከረም 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You