አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፉ አመራር እውቀት ማነስ ለሳይበር ደህንነት ስጋት መሆናቸውን አንድ ጥናት አመለከተ። በሲፒዩ ኮሌጅ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምህር የሆኑትና “የሳይበር ደህንነት አተገባበርና ተግዳሮቶች” በሚል ጥናት ያደረጉት አቶ ቴዎድሮስ ጌታነህ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደተናገሩት፤ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞች እና በዘርፉ ያለው የአመራር እውቀት ማነስ በአገሪቱ ውስጥ ለሚታየው የሳይበር ደህንነት ስጋት ዋነኛ መነሻዎች ናቸው። በተጨማሪም ማህበራዊ ትስስር አጠቃቀም፣ የሳይበር ደህንነት አጠባበቅ ሙያዊ ብቃት አለመኖር፣ የህግ ማዕቀፎች አለመዘጋጀት እና የአክቲቪስት እንቅስቃሴዎችም ለችግሩ መባባስ በዋናነት ይጠቀሳሉ።
በድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ሰራኞች ማህበራዊ ትስስር አጠቃቀም ችግር ስላለበት ለሀገርና ለተደራጁ የሳይበር ወንጀለኞች ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው የሚናገሩት አቶ ቴዎድሮስ አክቲቪስቶች ድርጅት ውስጥ ከሚሰራ ሰው ጋር ግላዊ ግንኙነት በመፍጠርና ሠራተኛው ቀስበቀስ መረጃዎችን እንዲያቀብል የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የሳይበር ጥቃት እንደሚፈጽሙ ተናግረዋል። እንደ አቶ ቴዎድሮስ አባባል፤ የማህበራዊ ትስስሮችን አጠቃቀም በአግባቡ መስራት ካተቻለ በቀጣይ ከፍተኛ ችግሮች ይፈጠራሉ። በሌላ በኩል የውስጥ ሰራተኞች ማህበራዊ ትስስሮችን ለግል ጥቅማቸው የማዋል ነገር እንዳለ ጥናቱ አመላክቷል። የውስጥ ተጠቃሚዎች ትልቁ የሳይበር አደጋ ናቸው።
ድርጅቶች ለሰራተኞቻቸው የደህንነት አደጋዎች ከምን ይመነጫሉ ለሚለው ስልጠና መሰጠት እንደሚገባም አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል። ጥናቱ በኢትዮ ቴሌኮም፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይልና በኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ ያተኮረ መሆኑን የገለፁት አቶ ቴዎድሮስ፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ደህንነት መረብ ኤጀንሲ (ኢንሳ) የመንግሥት ተቋም የሳይበር ደህንነት ሥራው በመመሪያው መሰረት እንዲተገብር አቅጣጫ ቢያስቀምጥም ተግባር ላይ አለመዋሉን አመልክተዋል።
እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለፃ፤ የሳይበር ደህንነት ከመንግሥት ተቋማት አንፃር ሲታይ ተቋማቱ የተለያዩ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው። በተለይ የማህበራዊ ሚዲያና የውስጥ ለውስጥ ኔትወርክ ግንኙነቶች በይበልጥ ተግባር ላይ አውለዋል። ጥናቱ በተደረገባቸው ተቋማት በድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ሠራኞች ማህበራዊ ትስስር አጠቃቀም ችግር፣ የሳይበር ደህንነት አጠባበቅ ሙያዊ ብቃት አለመኖር፣ የህግ ማዕቀፎች አለመዘጋጀት እንዲሁም የአስተዳዳሪዎች እውቀት ማነስ ተስተውሏል።
የሳይበር ደህንነት ስታንዳርድ መመሪያ መዘጋጀቱ ጥሩ ቢሆንም ወደ መሬት የወረደ ባለመሆኑ ችግሮችን መፍታት አለመቻሉን በመጥቀስ፤ በድርጅቶች ለሳይበር ደህንነት በቂ በጀት በመመደብና በሳይበር ደህንነት የአመራር ብቃት ያለው ሰው በማስቀመጥ ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል አብራርተዋል። እአአ 2017 ዓለም አቀፍ የሳይበር አጠባበቅና መረጃ ደህንነት ቢሮ ባወጣው ደረጃ መሰረት ኢትዮጵያ በሳይበር ደህንነት ዘርፉ ትልቅ ድክመት አለባት። በዚህም በሳይበር ደህንነት 97ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ መረጃው አመልክቷል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2011
መርድ ክፍሉ